
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ለቅኝ ገዥዎች አልበገር ባይነቷን ያሳየችበት፣ በዚህ በመላው ዓለም የገነነችበትና የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝብ ድል ነው። ኢትዮጵያም ይህን የዓድዋ ገድል በየዓመቱ የካቲት 23 ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች በሀገር ደረጃ ታከብራለች።
ታሪኩ የተፈጸመባቸው እነዛ የክፉ ቀን መከታ ተራሮች ግን አንድም የተለየ ማስታወሻ አልተደረገላቸውም። ወደ ተራሮቹ የሚያቀና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊም ይሁን የውጪ ሀገር ጎብኚ በተራራዎቹ ላይ ሲደርስ ሊመለከት የሚችለው እነዚያኑ ተፈጥሮ አሰናስላ ያስቀመጠቻቸውን ግዙፍ ተራሮች ብቻ ነው።
በተለያዩ ቦታዎች በጦርነቱ የተገደሉ የጣሊያን ወታደሮችና ባለስልጣናት ማስታወሻ ተቀምጦላቸው ማየት እንኳን ኢትዮጵያውያንን የሌላ ሀገር ጎብኚዎችንም የሚያስደምምና ለምን ያሰኛል ሲሉ የሚመለከታቸው አካላት ይናገራሉ።
የዓድዋ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬ ወይኒ ፍስሃ የዓድዋ ድል በዓልን ማክበር ሀገርን ለማስተዋወቅ፣ በቱሪዝም መስክም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እና የገቢ ምንጭ ለመፍጠር እንደሚያስችል ይገልጻሉ። በዚህ በኩል አስካሁን በየትኛውም የአስተዳዳር ዘመን በክልሉም ሆነ በፌዴራል መንግሥት በኩል የተሰራ እንደሌለም ይጠቁማሉ።
ከፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የምስረታ ሀሳብ ጀምሮ በአካባቢው በርካታ የመሰረት ድንጋዮች ተቀምጠዋል የሚሉት ወይዘሮ ፍሬህይወት፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ስፍራውን የተመለከቱ የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናትም
የመሰረት ድንጋይ ሳያስቀምጡ ሄደው እንደማያውቁም ያስታውሳሉ። ይህ ሁሉ ቢደረግም ሁሉም የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው ሀሳቦች ወደተግባር ሲለ ወጡ አይተን አናውቅም ይላሉ። ስለዓድዋ ድል ዓመት ሲመጣ በሚዲያ ከማስነገር የዘለለ የድሉን ያህል የተሰራ እንደሌለ ጠቅሰው፣ ይህ ጉዳይ ትኩረት እንደሚፈልግም ይናገራሉ።
የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የማርኬቲንግ ባለሙያ አቶ ነቢያት ታከለ የዓድዋውን ጦርነት ሲመሩ ከነበሩት የጣሊያን ከፍተኛ መኮንኖች መካከል ሜጀር ጄነራል ዳቦርሜዳ በሞተበት ቦታ ላይ ሀውልት መሰራቱን ጠቅሰው፣ በሁለተኛው ወራራ ወቅትም ለሞቱት የጣሊያን ወታደሮች የጣሊያን መንግሥት በመቀሌ እንዳየሱስና በአዲግራት ጎላቀናት ቀበሌ መቃብር አሰርቶ የሚታወቁትን በስም ሌሎቹንም ሲቪልና ወታደር እያለ በክብር አጽማቸው እንዲያርፍ አድርጎ እያስጠበቀ መሆኑን ያብራራሉ።
በርካታ ጣልያናውያንም የአያቶቻቸው አጽም ያረፈበትን ለማየት ወደ አካባቢው እንደሚመጡም ይጠቅሳሉ። በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ በኩል ህዘብ ሊጎበኘው በሚችል ደረጃ የተሰራ ሥራ እንደሌለም ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳም ማግኘት የሚቻለው ታሪካዊም ሆነ የገንዘብ ጥቅም እየተገኘ አለመሆኑን ያብራራሉ።
የዓድዋ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የመስህብ ባለሙያ አቶ ሀይለአብ ታረቀኝ በበኩላቸው የዓድዋ ጦርነት የተፈጸመባቸውን ቦታዎችና ታሪክ በሙሉ በተለይም ዋናዎቹ ጦርነቶች የተካሄዱባቸውን ሦስት ቦታዎች ምንድብድብ፤ ማርያም ሸዊቶና ራዕዮን ለቱሪዝም መስህብነት መጠቀም ይቻላል ይላሉ። የጣሊያን ሰራዊት የመጨረሻውን ሽንፈት ተቀብሎ ወደ ኤርትራ እስከ ተገደደበት ጊዜ ድረስ በርካታ ታሪኮች መፈጸማቸውንም ያመለክታሉ።
መረጃ በማቀበሉ ረገድ እነ ባሻ አውአሎም ከአሉላ ጋር የሰሩት ስራ አንድ የሚያስደንቅ ታሪክ ነው ያሉት አቶ ሀይለአብ፣ ዛሬ በየቦታው ተበታትነው የምናገኛቸው የመሳሪያና የቁሳቁስ ምርኮዎች የተሰበሰቡት ከእነዚሁ ቦታዎች ላይ መሆኑን ይገልጸሉ።በወቅቱ የኢትዮጵያውያን የምርኮኛ አያያዝ እንዲሁም የወገንንም የጠላትንም አስክሬን በክብር ያሳርፉ የነበረበት ሁኔታ ሰብአዊ ርህራሄ ብሄራዊ መግባባትና የሀገር ክብር የነገሰበት ነበር ይላሉ። ይህም አንድ ትልቅ ታሪክ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
ታሪካዊ ቅርሶቹን አሰባስቦ ታረኩን ሰንዶ እነዚህ ኩነቶች የተፈጸሙባቸው ቦታዎች ላይ ቢያንስ አንዳንድ የቱሪስት መዳረሻ በማዘጋጀት ቋሚ የቱሪስት መስህብ በመፍጠር ሀገርንም የአካባቢውንም ነዋሪ በገንዘብ መጥቀም ትውልዱም ታሪኩን እንዲያውቅና የሀገር ፍቅር እንዲገባው ማድረግ እንደሚቻል ያስገነዝባሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ