አዲስ አበባ፡- በክልሉ ጊዜውን ያልጠበቀ ዝናብና የበረሃ አንበጣ ችግር ቢፈጥሩም 182 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉን የኦሮሚያ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የኦሮሚያ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ ትናንት የክልሉን ምርት አሰባሰብ በማስመልክት መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደገለፁት፤ በተያዘው የምርት ዓመት 186 ሚሊየን ምርት ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ የበልግን ወቅት ሳይጨምር 182 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተገኝቷል፡፡ ምርቱ ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 15 ሚሊየን ኩንታል ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ምርት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ከመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ጀምሮ ምርት መሰብሰብ ላይ ተሳትፎ ሲያደርጉ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ዳባ፤ የበረሃ አንበጣ ለመከላከል የኬሚካል ርጭት በመደረጉ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ሥር መዋሉን፤ የበረሃ አንበጣ አሁን በተለያዩ ኣካባቢዎች የመከሰት ዕድል ስላለ በዘላቂነት ለመፍታት መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
አቶ ዳባ በክልሉ የተፋሰስ ሥራ ለማከናወን ሁለት ሚሊየን ሄክታር መሬት የተዘጋጀ ሲሆን፤ የውሃ እቀባ፣ የአፈር ለምነት ለመጠበቅ እንዲሁም ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፤ በተጨማሪም በክረምት ወራት የተተከሉ ችግኞችን ህብረተሰቡ በበጎ ፈቃደኝነት እንዲንከባከብ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ አቶ ዳባ ገለፃ፤ አርሶ አደሩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የግብርና ሥራውን እንዲያከናውን በብድር መልክ አራት ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ተዘጋጅቷል:: በሰብሎች ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ተባዮችን ለመቆጣጠር ለአርሶአደሩ ኬሚካሎች እንዲሰራጩ ተደርጓል፡፡ በቀጣይ በመስኖ ሥራዎች ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ይሠራል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 4/2012
መርድ ክፍሉ