የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዋልታዬ ሲባል የቆየው አረንጋዴ ወርቋ ቡና የፈለገችውንና የሚገባትን ያህል መጠቀም እንዳልቻለች ይታወቃል። የቡና የውጭ ንግድም የሚፈለገውን ያህል መራመድ እንደተሳነው መረጃዎች ያመላክታሉ። ለዚህም በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ እንደሚቻል የዘርፉ ባሙያዎች ያስረዳሉ።
የቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቅናሽ ማሳየቱ፣ ጥራትን አስጠብቆና እሴት ጨምሮ የመላክ ውስንነት፣የቡና ምርት በሚጓጓዝበት ወቅት የሚያጋጥመው የተደራጀ ስርቆትና ዝርፊያ፣ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቡና ከውጭ ይልቅ አገር ውስጥ የተሻለ ዋጋ ማግኘቱ፣ የቡናው የውጭ ንግድ የሚፈለገውን ያህል መራማድ እንዳይቻል አድርጎታል ሲሉ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ያብራራሉ።
አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን የገበያ መረጃና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ኸይሩ ኑሩ ይህን ይጋሩና የአገሪቱ ቡና ዋጋ እያንሰራራ መምጣቱን ይጠቅሳሉ። በተለይ በዚህ አመት ገበያው በመድራቱ አርሶ አደሩን ለምርቱ ዋጋ ማግኘት ስለመጀመሩ ያብራራሉ።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ዓለምአቀፉ ዋጋው በመውረዱ የኢትዮጵያ ቡና ዋጋም መቀነስ ግድ ብሎት እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ በዚህ ዓመት ባለፉት ሁለት ወራት ግን ዋጋው በእጅጉ መሻሻል አሳይታል ይላሉ።
እንደ የአካባቢው ቢለያይም እሸት ቡና ከ15 እስከ 25 በመቶ፣በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሆነው የይርጋ ጨፌና የሃረር ቡናም እስከ 30 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል›› ብለዋል። ዘንድሮ ላኪዎችም በቀጥታ ትስስር አስተማማኝ ስርዓት መተግበሩን ሲያረጋጋጡ ከገዥዎቻቸው ጋር ውል እየገቡ በተሻለ ዋጋ ከአርሶ አደሩ መግዛት ስለመጀመራቸውም ይገልጻሉ።
የቡና ዋጋ መጨመር ፋይዳው ሁለንተናዊ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኸይሩ፣ በተለይ ‹‹አርሶ አደሩ ቡናው ዋጋ ካወጣለት ቡናን እየነቀለ ሌሎች ሰብሎችን እንዳያማትር ከማድረግ በላይ አገሪቱ ከውጭ ምንዛሬ የምታገኘውን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ትልቅ አቅም የሚፈጥርና እንደ ስኬት ሊወሰድ የሚችል ስለ መሆኑም ያብራራሉ።
የቡና ዋጋ ጭማሪው ለአርሶ አደሩ መልካም አጋጣሚ መሆኑን በመጥቀስ የቡናው የውጭ ንግድ ዘንድሮም የሚፈለገውን ያህል መራማድ እንዳይቻል ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት ያሳደረባቸው ባለሙያዎችን ፈጥሯል። የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ፣ የቡናው በተለይ የአገር ውስጥ የቡና ዋጋ መጨመር እንደሚያስደስት ሁሉ ከፍተኛ ስጋትን የሚደቅን ስለመሆኑ ያሰምሩበታል።
‹‹አርሶ አደሩ የተሻለ ዋጋ በማግኘት መጠቀሙ ያስደስታል፤ ከአርሶ አደሩ የሚገዛበት ዋጋም ሆነ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሚደረገው ግብይት የቡና ዋጋ መጨመሩ እንደ ባለሙያ ለእኔ በጣም ያስፈራኛል›› ሲሉ አስገንዝበው፣ የአገር ውስጥ የቡና ዋጋ ከፍ አለ ብሎ መፈንደቅም አግባብ አለመሆኑን ነው የሚያብራሩት።
እንደ አቶ ግዛት ገለፃ፣በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጡ የቡና ዋጋ ከዓለም አቀፉ ዋጋ ይበልጣል። አርሶ አደሩ ጋር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋጋ በራሱ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። ሀገሪቱ ለውጭ የምትሸጥበት ዋጋና ከምርት ገበያው የሚገዛበት ዋጋ ከመቀራረብ ይልቅ እየተራራቀ መጥቷል።
ይህ ዓይነት ኡደት አግባብ አለመሆኑን የሚያስገነዝቡት አቶ ግዛት፣ ውጤቱም በተለይ ከአርሶ አደሩም ሆነ ከምርት ገበያው የሚገዛው አካል የሚሸጥበት እንዲቸገር እና በጣም በከባዱ የሚከስሩ አቅራቢዎች እንዳይፈጥር ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸው ይናገራሉ።
ቡና ገዝተው ለሚያቀርቡ አካላት ብድር የሚያቀርበው ባንክ ተመላሽ በማግኘት ረገድ እንዲቸገር እንደሚያደርግ ጠቅሰው፣ ‹‹አርሶ አደሩ በቀጣይ ተመሳሳይ ዋጋ በመጠበቅ አልሸጥም ቢል የታጠበ ቡና ገበያ ውስጥ ላይገኝ ይችላልም። ሲሉ ያብራራሉ።
‹‹ይህ በተለይ በውጭ ምንዛሬ ግኝቱ ላይ ከባድ ጫና ይፈጥራል። እስከአሁን ባይታይም በተለይ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የከፋ ችግር እንዳይመጣና መሸጥ በማንችልበት ደረጃ ላይ እንዳንደርስ ያሰጋኛል›› ይላሉ።
የደቡብ ክልል ቡና እና ሻይ ባለስልጣን የቡና ጥራት ቁጥጥር ባለሙያ አቶ አብረሃም አስታጥቄ ግን በዚህ ረገድ የሚነሱ ስጋቶች ብዙም ሚዛን እንደማይደፉ ያስረዳሉ። የአገር ውስጥ ዋጋ ሲጨምር የቡናው ገበያ ተዋናዮች ከውጭ ይልቅ አገር ውስጥ ማማተራቸው እውን ስለመሆኑ ይስማማሉ።
ይህም በተለይ 2009 እና 2010 ይስተዋል እንደነበር የሚጠቁሙት አቶ አብረሃም፣ በቀደሙት ዓመታት ወደ ውጭ አገር መላክ ከሚኖርበት ቡና እስከ 47 በመቶው አገር ውስጥ እንደሚቀር መረጃዎች ማመላከታቸውንም ያስታውሳሉ። ይሁንና በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፉ ደረጃም የቡና ዋጋው መሻሻል በማሳየቱ መሰል ተግባራት ይከሰታሉ የሚል እምነት የለኝም ይላሉ።
‹‹የአገር ውስጥ ቡና ፍላጎቱ መናር የሚጠላ ባይሆንም ለውጭ ገበያው የሚቀርብን ቡና አገር ውስጥ ማስቀረት የማይበረታታ ነው›› የሚሉት አቶ አብረሃም፣ በተለይ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ባለበት በዚህ ወቅት ተግባሩ ፈፅሞ ተቀባይነት እንደሌለው ያመለክታሉ። ይህን ችግር ለማስወገድም የውጭ ገበያው እንዲቀጥል ለማድረግ ጥራት ያለው ቡና ማዘጋጀትና በቋሚነት ማቅረብ፣ተደራድሮ የመሸጥ አቅምን ማዳበር እንደሚገባ ነው ያስገዘቡት።
አቶ ግዛት የአገር ውስጥ ገበያው እንዲረጋጋ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን አለባቸው ይላሉ። ዋጋ ጨመረ ብሎ መፈንደቅ እንደማይገባም በመጥቀስ፣ ‹‹ዋጋም ለምን ይወጣል፣ ከእክስፖርቱ ዋጋ ለምን በለጠ፣ በሚለው ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበን መምከር መወያየትና መፍትሔ ማፈላለግ ይኖርብናል›› ይላሉ። መንግሥትም መሰል ‹‹ሰው ሠራሽ›› የሚያብጡ ገበያዎችን በተለያዩ ማበረታቻዎችና ሌሎችም ዘዴዎች ፈር ማስያዝ አለበት ነው ያሉት።
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2012
ታምራት ተስፋዬ