አዲስ አበባ :- ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር በትብብር እየሠራች መሆኑን አስታወቀች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት ከ33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች መሪዎችን ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሰላምና ጸጥታ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር ደግሞ የውይይታቸው ዋና ትኩረት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከደቡብ ሱዳን፣ ከጅቡቲ፣ ከአልጄሪያ፣ ከሞሮኮ፣ ከሱዳንና ከጋና መሪዎች ጋር መወያየታቸውን የኢዜአ ዘገባ አመልክቷል፡፡
የውይይታቸው ትኩረትም በአገሮቹና በቀጣናው ያለው ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስሮች መሆናቸው ታውቋል። ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኬር ማያርዴት ጋር በተለይ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ላይ በትኩረት የተወያዩ ሲሆን ኢትዮጵያ በርካታ የአገሪቱን ስደተኞች ተቀብላ ከማስተናገድ ባለፈ ለአገሪቷ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኑን አስታውቀዋል።
በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ቋሚ መንግሥት መመስረት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አገሪቷ በመቶ ቀናት ቋሚ መንግሥት እንድትመሰርት ውሳኔ ማሳለፉን አስታውሰዋል። ይሁንና የኢጋድ ውሳኔ ተግባራዊ ሳይሆን የተሰጠው ቀነ ገደብ እየተገባደደ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቋሚ መንግሥት ምስረታው እውን እንዲሆን ተገቢውን ድጋፍ እንደምታደርግ ያስታወቁ ሲሆን ደቡብ ሱዳንም በዚህ ለመተባበር ፍቃደኝነቷን አሳይታለች።
ከጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ጋር በወደብና በባቡር አገልግሎት ማሻሻልና የሁለቱን አገሮች ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። ከአልጄሪያው ፕሬዚዳንት አብዱል መጂድ ተቦን ጋር በነበራቸው ውይይትም የኢትዮ-ኤርትራን ግጭት ለመፍታት የአልጀርስ ስምምነት የነበረው ሚና ከፍተኛ እንደ ነበር አንስተዋል።
ሁለቱ አገሮች አብዛኛው ህዝባቸው ወጣት እንደ መሆኑ የወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንዳለባቸው የተስማሙ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማብራሪያ መስጠታቸው ታውቋል።
ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ አምዶክ ጋር በነበራቸው ውይይትም አገሮቹ ታሪካዊ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር በተለይ የሰላምና ጸጥታ እንዲሁም የኢኮኖሚ ትስስር ላይ ትኩረት ሰጥተው ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2012