አዲስ አበባ፡- ካናዳ ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንትና የንግድ ማስፋፋትና ጥበቃ ስምምነት እንዲፈረም መጠየቋ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ ላለፉት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮ-ካናዳ የቢዝነስ ፎረም ትናንት ከተጠናቀቀ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤በሁለቱ አገራት መካከል የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንትና የንግድ ማስፋፋትና ጥበቃ ስምምነት እንዲኖር የካናዳ የንግድ ሚኒስቴር ጠይቋል።
በኢትዮጵያ በኩልም በሁለቱ አገራት መካከል ድርድር ከተደረገ በኋላ ስምምነት ማድረግና መፈራረም እንደሚቻል ማረጋገጫ መሰጠቱንም ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
በካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ተመርቶ ለመጣው የካናዳ የንግድ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ቅድሚያ ሰጥታ ትኩረት በምታደርግባቸው የግብርና ማቀነባበሪያ፣ የኃይል፣ ማዕድን፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ቱሪዝም፣ ማኒፋክቸሪንግና ሌሎች ዘርፎች ላይ ባለሀብቶች እንዲሰማሩ ሰፊ ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ኮሚሽነሩ ተናግረው፣ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን ለማገዝ ዝግጁነትና ፍላጎት እንዳላት ለልዑካን ቡድኑ መብራራቱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ምቹ የንግድ ከባቢ እየፈጠረች መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፣ የካናዳ ባለሀብቶች ይህን ዕድል በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ ሁለቱንም አገራት ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሠሩ ገለጻ መደረጉንም ተናግረዋል።
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትርና ከፍተኛ ባለስልጣ ናት ከንግድ ልዑካን ቡድናቸው ጋር ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንትና በሌሎች ዘርፎች በጋራ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው እንደሚያመለክት ገልጸው፣ የተደረጉት ውይይቶች ወደ ሥራ እንደሚቀየሩ እምነታቸውን አስታውቀዋል።
እንደ ኮሚሽነር አበበ ገለጻ፤በኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የሚያስችል ቀላል፣ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሠራርና እየተዘረጋ ነው። ከተለያዩ ተቋማትና ከክልል መንግሥታት ጋር በመሆን በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል። ኢንቨስተሮች ወደ ሥራ ሲገቡ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ተከታተሎ የሚያስተካከል ተግባርም እየተከናወነ ነው።
በቢዝነስ ፎረሙ ላይ የተሳተፉ በካናዳ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ውይይቱ በሁለቱ አገራት መካከል ንግድንና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ያስችላል ብለዋል። ውይይቱም ካናዳውያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ የንግድ አቅም እንዲረዱ አድርጓቸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ