አዲስ አበባ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ላለፉት ስምንት ወራት በደብዳቤ፣ በስልክና በአካል በመገኘት መረጃ ቢጠይቀም ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ የዕንባ ጠባቂ ተቋም መረጃውን በግድ እንዲያሰጠው ይግባኝ ጠየቀ።
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስር የሚታተመውና በአገሪቱ አንጋፋ የሆነው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ለዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ያስገባው ይግባኝ እንደሚያመለክተው፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፉት ስምንት ወራት በቃል፣ በደብዳቤና በአካል ጭምር በመሄድ ስለተቋሙ እንቅስቃሴ፣ በተቋሙ አለ ስለሚባለው የግልጽነትና የአሠራር ችግር፣ የብድር አሰጣጥና አመላለስ፣ የብድር ብልሽትና መንስዔ፣ በተቋሙ ስለተከሰቱ የብድር ብልሽቶችና ተጠያቂነት፣ የቀጣይ ማሻሻያና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ለባንኩ ፕሬዚዳንት ጨምሮ በየደረጃው ላሉ ኃላፊዎች ማብራሪያ እንዲሰጡትና ተቋሙ ላይ ያሉ አሠራሮችና የባንኩ አካሄድ ለባንኩ ባለቤት ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም የተለያዩ ሰበቦችን በመደርደር መረጃውን ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ይግባኝ መጻፉን ያመለክታል።
ይግባኙ እንደሚያመለክተው፤ በስልክ በተደጋጋሚ የባንኩ የኮሚኒኬሽን ኃላፊዎች መረጃ እንዲሰጡ ከመጠየቅ በተጨማሪ በደብዳቤ ሰኔ 5 ቀን 2011 በደብዳቤ ቁጥር TL1/2/3023፣ በጥቅምት 12 ቀን 2012 በደብዳቤ ቁጥር TL1/2/1867 እንዲሁም በታኅሣሥ 1 ቀን 2012 በደብዳቤ ቁጥር T41/2/2713 የባንኩ ፕሬዚዳንትና ኃላፊዎች ለጋዜጣው ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠየቁን ያመለክታል።
ከዚህም በተጨማሪ ሁለት የአዲስ ዘመን ጋዜጠኞች እንዲሁም የአገር ውስጥ ቋንቋዎች ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት በአካል በመገኘት ጭምር የተቋሙን የኮሙኒኬሽን ኃላፊዎች ለጋዜጣው መረጃ እንዲሰጡ መጠየቃቸውን ያመለክታል።
‹‹ደብዳቤዎች የባንኩ ፕሬዚዳንት ወደሚመለ ከታቸው የሥራ ክፍሎች ይመራሉ። የሥራ ክፍሎቹ ደግሞ በአጠቃላይ የመገናኛ ብዙሃንን ጠርተን በኃላፊዎች መረጃ እንሰጣለን፣ ሌላ ጊዜ ቦርዱ እንዳትሰጡ ብሎናል፤ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ምክንያቶችን በመደርደር ጋዜጣው መረጃውን ለማግኘት ያደረገው ጥረትና ማግባባት ፍሬ ሊያፈራ አልቻለም›› ሲል ይግባኙ ያብራራል።
በመገናኛ ብዙሃኑና በመረጃ ነፃነት አዋጁ አንድ ተቋም መረጃ ለመስጠት የሚፈጅበት ጊዜ
ቢታወቅም ባንኩ ጋዜጣው በህግ ከተሰጠው መረጃ የማግኛ ጊዜ እያራዘመና ምክንያት እየደረደረ መረጃዎችን ሊሰጥ አልቻልም። መረጃ ይሰጠናል በሚልም በትዕግስት ስምንት ወራትን ቢጠብቅም ባንኩ መረጃውን ሊሰጥ አለመቻሉን ይግባኙ ያመለክታል። ይህ የመረጃ ክልክላ በኃላፊነት እንደሚንቀሳቀስ አንድ የመገናኛ ብዙሃን ዝም ብሎ ማለፍ ኃላፊነት አለመወጣት እንደሆነም ጠቁሟል።
ጋዜጣው በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 590/2000/ ለህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል በአንቀጽ 31/4/ የመረጃ ጥያቄያቸው በተቋማት ኃላፊዎች ውድቅ የተደረገባቸው አካላት ለዕንባ ጠባቂ ጥያቄ ይግባኝ ማለት ይችላሉ።
በአንቀጽ 33/1/3/ ዋና ዕንባ ጠባቂው የቀረበላቸውን ይግባኝ በመመርመር መረጃ የከለከለው ተቋም መረጃውን እንዲሰጠና እርምጃ እንዲወስድ እንደሚደነግግ አመላክቷል። በዚህ መሰረትም ዋና ዕንባ ጠባቂ ይግባኙን በመርመር ከባንኩ መረጃውን ለጋዜጣው እንዲያሰጠው በመጠየቅ ከዚህ ቀደም ለባንኩ የተጻፉትን ደብዳቤዎች አያይዞ አቅርቧል።
ጋዜጣው የዕንባ ጠባቂ ተቋም ከባንኩ እንዲያሳጠው የሚፈልገው ዋና ዋና መረጃዎች፤ ባንኩ የገጠመው የ40 በመቶ የብድር ብልሽት ምክንያት፣ ብልሽት ያጋጠማቸው ድርጅቶች ዝርዝር፣ ችግሩን በፈጠሩ አካላት ላይ የተወሰደ ዕርምጃ፣ ባንኩ የሰጠው ብድር በክልሎች ያለው ድርሻ፣ ባንኩ ከውጭ አገራት የተበደረው አጠቃላይ ዕዳና የብድር አመላለሱ፣ የሊዝ ፋይናንስ አሰጣጡ፣ ብድር ሲሰጥ ከሙስናና ከአድሏዊነት የጸደ መሆኑን የሚያረጋግጥበት ስርዓት፣ በውሸት የሥራ እቅድ ብድር የሚወስዱ አካላት ላይ ያለው ክትትል እና ዕዳ የተሰረዘላቸው ድርጅቶች ማብራሪያ የተመለከቱ ናቸው።
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ