አካባቢው ለመልሶ ልማት ተፈልጎ ነዋሪዎቹ በአስቸኳይ እንዲነሱ ቢደረግም ፣ቦታው አሁንም ልማቱ አልተካሄደበትም። ከሜክሲኮ ወደ ቄራ በሚወስደው መንገድ ከገነት ሆቴል ወረድ ብሎ በስተግራ በኩል የሚገኘው ይህ ሰፊ ቦታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በርካታ ገልባጭ መኪኖች ይገቡ ይወጡበታል።
ከተሽከርካሪዎቹ ግማሾቹ የድንጋይ ቋጥኝ ይዘው ይገባሉ፤ የተቀሩት ደግሞ ለግንባታ የተፈለጠ ድንጋይ ጭነው ይወጣሉ። የሚፈለጠው ድንጋይ ሜክሲኮ አካባቢ ከሚካሄዱ ግዙፍ ግንባታዎች የሚወጣ ሲሆን፣ በአካባቢው ግዙፍ የድንጋይ ቋጥኝ ክምር ጭምር ተፈጥሯል። ጠጋ ብሎ ለተመለከተ ደግሞ እዚህም እዚያም የተጠረበ ድንጋይ በመደብ በመደብ ተከምሮ ይመለከታል። ቦታው ካባ ተደርጓል ማለት ነው፤ በመሀል አዲስ አበባ ቡልጋሪያ አካባቢ።
ወጣቶችም በሥራ ተጠምደው ይታያሉ። በማህበር ተደራጀተው እንደሚሠሩ ይገልጻሉ፤ አንዳንዶቹ የሚወጣ የሚገባውን መኪና ስር ዓት ያስይዛሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ድንጋይ ይጠርባሉ፤ ሌሎች ድንጋይ ይጭናሉ።
ወጣት መንግሥቱ በቀለ በከተማ አስተዳደሩ ጊዜያዊ ውሳኔ መሰረት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ አስራ አንድ ፅሕፈት ቤት በትስስር ባመቻቸው የሥራ ዕድል በቦታው ላይ የመሥራት ዕድል እንደገጠማቸው ይናገራል።
ወጣቱ እንደሚለው፤ማህበራቸው 101 ወጣቶችን በአባልነት ይዟል፤ ማህበሩ ድንጋይ በማስፈለጥ የሚያስጭን ሲሆን፣ ወጣቶቹ አንድ የግንባታ ድንጋይ በሰባት ብር በመሸጥ በቀን እያንዳንዳቸው አስከ 150 ብር ያገኛሉ።
ሜክስኮ አካባቢ መንግሥት ሕንፃዎችን ለማስገንባት ቁፋሮ ከሚያካሄድባቸው ቦታዎች
ላይ በማስጫን በአንድ የኮንስትራክሽን ድርጅት አማካኝነት በቦታው እንደሚራገፍ የሚናገረው ወጣት መንግሥቱ፣ድንጋዩን በጉልበት ሠራተኞች በማስፈለጥ ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርቡ ያስረዳል። የአካባቢው ወጣቶችም መኪናዎችን ሲገቡና ሲወጡ ክፍያ በመጠየቅ ገቢ እንደሚያገኙ ይገልጻል።
አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ለሕንፃ ግንባታ ተቋራጮች የግምብ ድንጋይ ያቀርባሉ። ድንጋዩን ከቃሊቲና ከሌሎች አካባቢዎች በማስጫን ለተቋራጮቹ ሲያቀርቡ ለድንጋይ ግዢና ለማስጫኛ ከፍተኛ ወጪ እንደሚያወጡ ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳም የሚገባቸውን ትርፍ እንደማያገኙ ያስረዳሉ።
ወጣቶች ድንጋይ አስፈልጠው ለተጠቃሚዎች ማቀርብ መጀመራቸውን በመስማታቸው ወደዚሁ አካባቢ እንደመጡና በተመጣጣኝ ዋጋ ድንጋይ ገዝተው በማስጫን ለተቋራጮች እንደሚያቀርቡም ይገልፃሉ። ድንጋዩን በተለይ መሀል አዲስ አበባ በማግኘታቸውም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደልብ ለተቋራጮች በማቅረብ የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ይናገራሉ።
በጭነት አገልግሎት ሰጪነት የተሰማራው ወጣት ዘሚካኤል ተስፋ ገብርኤል ሰፈራ ከሚባል አካባቢ ድንጋይ በመጫን ለተጠቃሚዎች ያቀርብ ነበር። ከቦታ ርቀት አኳያ ድንጋይ ጭኖ ቶሎ ማድረስ የማይቻል በመሆኑ ሳቢያ ደምበኞቹ ቅር ይሰኙበት እንደነበር አስታውሶ፣ ገቢው ዝቅተኛ እንደነበር ያብራራል።
በአሁኑ ወቅት ቤት ሠሪዎችና ተቋራጭ ደምበኞቹ ሲያዙት ወደዚሁ ስፍራ በመምጣት ድንጋይ በመግዛት የተሻለ ገቢ ማግኘት እንደቻለ ይናገራል። ድንጋዩ መሃል ከተማና በሚኖርበት አካባቢ መገኘቱ ይበልጥ ተጠቃሚ አድርጎታል። እንደ ቦታው ርቀት በአንድ ጭነት ከአንድ ሺ አስከ አንድሺ ሦስት መቶ ብር እንደሚያገኝም ይገልጻል።
ወጣቶቹ የወረዳው መሬት ልማት ማኔጅመንት ፅህፈት ቤት የፈጠረው የሥራ ዕድል ትስስር መንግሥት ግንባታ ለማከናወን ባሰባቸው ሌሎች ቦታዎች ላይም ቁፋሮ ሲካሄድ የሚገኘውን ድንጋይ የየአካባቢው ወጣቶች እንዲጠቀሙበት እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
በቂርቆስ ክፍለከተማ የወረዳ አስራ አንድ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈይሰል ተስፋዬ እንደሚሉት፤ወረዳው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሕንፃ ከሚያስገነባበት ስፍራና ከደብረወርቅ ሕንፃ ጀርባ ለግንባታ ቁፋሮ ከሚያካሂደው የኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር በመነጋገር ከስፍራው የሚወጣውን ድንጋይ ንዑስ ተቋራጩ በሜትር ኪዩብ እየከፈለ በጊዜያዊነት በተሰጠው ቦታ ላይ በአነስተኛ ኪራይ እንዲያራገፍ ተደርጓል።
በወረዳው ሥራ ዕድል ፈጠራ መሰረት በጊዜያዊነትና በረጅም ወራት የአካባቢው ወጣቶች ድንጋይ አስፈልጠው በመጫን እንዲጠቀሙ ለማድረግ ድንጋዩን ቆፍሮ ከሚያወጣው የኮንስትራ ክሽን ድርጅት፣ ድንጋዩን በዚሁ ቦታ ላይ ከሚያ ራግፈውና ከሚያሠራው ንዑስ ተቋራጭና ከወጣቶቹ ጋር የማስተሳሰር ሥራ መሠራቱን ይገልጻሉ። በትስስሩም ድንጋዩ በተራገፈባቸው ሁለት ቦታዎች ላይ አንድ መቶ አንድ የሚሆኑ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው እየሠሩ መሆናቸውን ያብራራሉ።
በትስስር የሥራ ዕድል የመፍጠሩ ተግባር በወረዳው የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ፅህፈት ቤት በኩል በበጎ እንደሚታይ ኃላፊው ገልጸው፤ የግል ባለሀብቶች መሬት ተረክበው ወደ ግንባታ ከመግባታቸው በፊት በጊዜያዊነት ቦታቸው ላይ ወጣቶች ተደራጅተው እንዲህ ዓይነቱን ሥራ በማከናወን ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ይጠቁማሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2012
አስናቀ ፀጋዬ