አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በምርምር የሚያወጣቸውን ከአካባቢ ስነ ምህዳርና አየር ንብረት ጋር ተስማሚ የሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶና አርብቶ አደሮች የማስተዋወቅና የማስፋፋት ሥራውን እንዲያጠናክር ተጠየቀ።
ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተወጣጡና የተቋሙን የምርምር ውጤቶች በመጠ ቀም ውጤታማ የሆኑ ተጠቃሚዎችን፣ የልማትና የኤክስቴንሽን ባለሙያዎችንና ተመራማሪዎችን ያሳተፈ የአርሶ አደሮች ኮንፍረንስ ትናንት በተቋሙ አዳራሽ አካሂዷል፡
በመድረኩ መክፈቻ ላይ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ እንደገለፁት፣ ኢንስቲትዩቱ በምርምር የሚያወጣቸውን ከአካ ባቢ ስነ ምህዳር እንዲሁም አየር ንብረት ጋር ተስማሚ የሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ የግብርናው ዘርፍ ዘላቂ እድገት እንዲያስመዘግብ ብሎም የአርሶ፣ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ኑሮ የተሻለ ለማድረግ ከፍተኛ አስተ ዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ተቋሙ የተለያዩ ችግር ፈች ምርምሮችን የማፍለቅ፣ በምርምር የተገኙትን የማባዛትና የተባዛውንም ወደ ተጠቃሚው የማድረስ ዋነኛ ኃላፊነት እንዳለበት የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣‹ ‹እስከአሁን ባለው ሂደት በጥናት የተገኙ የግብርና ምርምር ውጤቶችን በሚፈለገው መጠን አርሶ እና አርብቶ አደሩ ዘንድ አልደረሱም›› ብለዋል።
ምርምሮች የማፍለቅ፣የተገኙትን የማባዛትና የተባዛውንም ወደ ተጠቃሚው የማድረስ ተግባ ራትን አቀናጅቶ መጓዝ እስካልተቻለ የግብርናውን ዘርፍም ሆነ ተዋናዮችን ማሳደግ ብሎም ሁለንተናዊ አገራዊ ለውጥ ማምጣት አዳጋች እንደሚሆንም ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።
ተቋሙ ይህን ችግር ለማስወገድ በአሁኑ ወቅት ልዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ይህን ጥረት ዳር ለማድረስና ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን የሚመ ለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ኤክስቴንሽን የሙያ ማህበር ፕሬዚዳንት፣ ዶክተር ጭመዶ አንጫላ በበኩላቸው፣ ኢንስቲትዩቱ በምርምር የሚያወጣቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለግብርናው ዘርፍ ሁለተናዊ እድገት ወሳኝ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ስለመሆናቸው አብራርተዋል።
የምርምር ውጤቶችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ አሁንም ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ያመላከቱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ኢንስቲትዩቱ ባፈለቃቸው ቴክኖሎጂዎች ምን ያህሉ ተጠቃሚ ሆነዋል ከተባለ ግን ከ15 እስከ 30 በመቶ አይዘልም›› ብለዋል። የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገም ምርምሮች ለአርሶና አርብቶ አደሮች የማስተዋወቅና የማስፋፋት ሥራ መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።
ከመድረኩ ታዳሚዎች መካከል አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው አርሶ አደር አሰለፈች ተሊላ እና ግርማ አበቦ፣ ተቋሙ በሚያፈልቃቸው የቴክኖሊጂ ውጤቶችና ከማሳ ዝግጅት እስከ ስብሰባ በሚደረግላቸው የባለሙያ እገዛ ተጠቃሚ በመሆን ምርትና ምርታማነታቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ተናግረዋል።
እንደ እነርሱ ሁሉ ሌሎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ኢንስቲትዩቱ በምርምር የሚያወጣቸውን ከአካባቢ፣ ስነ ምህዳር እንዲሁም አየር ንብረት ጋር ተስማሚ የሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅና የማስፋፋት ሥራውን ማጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2012
ታምራት ተስፋዬ