አዲስ አበባ፡- በጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ድጋፍ በውሃው ዘርፍ ለሚሠሩ ሱዳናውያንና ኢትዮጵያውያን የሥራ ኃላፊዎች የሚሰጠው ዓለም አቀፍ ስልጠና የሃገራቱን የውሃ ቴክኖሎጂ ትምህርትና ስልጠና ግንኙነት እንደሚያጠናክር የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ስልጠናው በኢንስቲትዩቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ትናንት በተጀመረበት ወቅት የኢንስቲትዩቱ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ጉደታ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ስልጠናው ሲሰጥ የዘንድሮው ለሦስተኛ ጊዜ ነው። ይህም ኢንስቲትዩቱ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን መስጠት መቻሉን ያረጋግጣል፤ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለውን የውሃ ቴክኖሎጂ ትምህርትና ስልጠና ግንኙነት ያጠናክራል።
በውሃው ዘርፍ ያሉ ኢትዮጵያውያን ኃላፊዎችና ባለሞያዎችን አቅም ስልጠናው እንደሚገነባ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ሱዳናውያንም የውሃ አገልግሎትን በብቃት መስጠት እንዲችሉ አቅማቸውን ለመገንባት እንደሚረዳ ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ስልጠናዎች በጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮና በውሃ ጄኔሬተር ጥገና ዙሪያ ጠቃሚ ግብአት መገኘቱንም ዳይሬክተሩ አስታውሰው፤ በቀጣይም ኢንስቲትዩቱ በአስራ አምስት የስልጠና መርሐግብሮች በሀገር ውስጥ፣በምሥራቅ አፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አጃናው ፈንታው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ስልጠናው በኮርፖሬት ማኔጅመንት፣ በህዝብ ግንኙነትና በካይዘን ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በጃፓናውያን ባለሞያዎች የሚሰጥ ሲሆን፣አርባ ሱዳናውያንና ኢትዮጵያውያን ይሳተፉበታል። በዚህም በተለይ ኢትዮጵያውያን ሰልጣኞች ከስልጠናው ጠቃሚ ግብአት የሚያገኙበት ይሆናል።
በጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የሱዳን ፕሮጀክት የህዝብ ግንኙነት ሚስ ዩሪ ሳቶ በኮርፖሬት ማኔጅመንት ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ሰልጣኞች ከውሃ ጋር በተያያዘ ውጤታማ የቢዝነስ ፕላን ማዘጋጀት እንደሚችሉ ትምህርት የሚቀስሙበት መሆኑን ገልጸዋል።
በስልጠናው ከደምበኞች ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር የፐብሊክ ስትራቴጂዎችን እንዴት መጠቀም እና የውሃ ዘርፉን አገልግሎት እንዴት ማሻሻል እንደሚቻል ሰልጣኞች ትምህርት የሚያገኙበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2012
አስናቀ ፀጋዬ