አዲስ አበባ:- የአርሶ አደር የመሬት ካሳ ክፍያን አስመልክቶ አዲስ አዋጅ ቢወጣም ማስፈፀሚያ መመሪያና ደንብ ለክልሎች ባለመውረዱ ላለፉት ስድስት ወራት ለኢንቨስትመንት የሚውል መሬት ለባለሀብቱ ማስተላለፍ እንዳልቻለ የደብረብርሀን ከንቲባ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የደብረብርሃን ከተማ ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ የአርሶአደሮችን የመሬት ካሳ አስመልክቶ በፌዴራል ደረጃ አዲስ አዋጅ ወጥቷል። ይሁን እንጂ አዋጁ ደንብና መመሪያ ወጥቶለት ወደ ስራ ባለመግባቱ አርሶ አደሩን ካሳ ከፍሎ ማስነሳት እና መሬት ለባለሀብቱ ማስተላለፍ አልተቻለም።
በአሁኑ ወቅት ወደ ደብረብርሃን ከተማ እየመጣ የሚገኘውንና በርካታ ቁጥር ያለው የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብት ለማስተናገድ ትልቅ እንቅፋት የሆነው ይህ በፌዴራል ደረጃ መመሪያና ደንብ ያልወረደለት አዲስ አዋጅ ተግባራዊ ባለመሆኑ ነው ያሉት ከንቲባው፤ ጉዳዩ በደብረብርሃን ከተማ የሚሰጠውን ቀልጣፋ አገልግሎት ከማደናቀፉም በላይ በአገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል ብለዋል።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ያየህ አዲስ በበኩላቸው፤ ችግሩ እንደሀገር ኢንቨስትመንቱን እየጎዳ መሆኑን በመግለፅ፤ የፌዴራል መንግስት ማስፈፀሚያ ደንቡን አውጥቶ ማስተላለፍ ይጠበቅበታል። ይህ ማስፈፀሚያ ደንብና መመሪያ ተግባራዊ ባለመሆኑ ከስድስት ወር በላይ የገጠር መሬት ለባለሀብቱ ማስተላለፍ አለመቻሉን ጨምረው ገልፀዋል።
አርሶ አደሩ በአዋጅ የተፈቀደለትን የካሳ ክፍያ ባለመሰጠቱ አልተነሳም። በመሆኑም፤ ኢንቨስትመንቱ በስፋት እየጠየቀ የሚገኘውን የገጠር መሬት ካለፈው ሰኔ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ማስተላለፍ አልተቻለም። ይህ ደግሞ በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃም ኢንቨስትመንቱ እንዲቀዛቀዝ እያደረገው እንደሚገኝ አስታውሰው፤ የፌዴራል መንግስት አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 25/2012
ፍሬህይወት አወቀ