. የግድቡ ግንባታ 71 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡
ጉባ:- የለውጡ አመራር በጀግንነት ያሳለፈው ቆራጥ ውሳኔ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ከውድቀት ማዳን እንደቻለ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግድቡ ግንባታ ሂደት ያለበትን ደረጃ ትናንት ጉባ ተገኝተው በተመለከቱበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ከዚህ በፊት በነበረ የአመራር ክፍተትና የቅንጅታዊ አሰራር ጉድለት ምክንያት ፕሮጀክቱ በከፍተኛ ሁኔታ አክሳሪ እንዲሆን ተደርጎ መመራቱን ገልፀው፤ በለውጡ አመራር በጀግንነት የተላለፈ ውሳኔ ግን የህዳሴ ግድቡን አድኗል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ተነስቶ ሆለታ የሚደርሰውና ከሁለት አመት በፊት ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀውን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ጥራት ችግር ብዙ መቶ ኪሎ ሜትር የሚረዝም መንገድ ገንብቶ አንድም መኪና ማስተናገድ ካለመቻል ጋር አወዳድረውታል።
በህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት መዘግየት ምክንያት ኢትዮጵያ በየአመቱ 1 ቢሊዮን ዶላር እያጣች መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የተፈጠረውን ችግር በመቅረፍ የኢትዮጵያውያንን ተስፋ እውን ለማድረግ የለውጡ አመራር በቆራጥነት እርምጃዎችን ወስዷል፤ ለውጥም ተመዝግቧል ብለዋል።
የግድቡን የኤሌክትሮ መካኒካል ስራ ሲያከናውን የነበረውና ለፕሮጀክቱ መዘግየት ዋነኛ ምክንያት የነበረው ሜቴክ ጋር ውሉን በማቋረጥ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ማኔጅመንትና ቦርድን በመቀየር፣ ኮንትራቶችን ለአዳዲስ ኩባንያዎች በመስጠትና ሌሎችም ጠንካራ ውሳኔዎች ግድቡን ከነበረበት ስጋት በማላቀቅ ማዳን እንደተቻለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ትልቅ ፀጋ የሆነው ፕሮጀክት ቀድሞ ሲሰራበት በነበረው የጥራት ሁኔታ ቢቀጥልና የቴክኒክ ችግር አጋጥሞ ቢሆን ኖሮ አመኔታን የሚያሳጣና የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትም ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገቡ ያደርግ እንደነበር ተገልጿል። ትውልድ የተጀመረን ፕሮጀክት የማስቀጠል ብቻም ሳይሆን ስህተትን የማረምና የማስተካከል አቅም እንዳለው ማሳያ የሆነው የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በሀገር ግንባታ ስራ የትውልድ ቅብብሎሽ ያለውን ትልቅ ፋይዳ ማወቅ የተቻለበት እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።
የመደመር ፍልስፍና የታየበት አንደኛው ስራ የሆነው የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የነበሩበትን እጥረቶች በመቅረፍ፣ የነበረውን ጥራት እንዳለ በመጠበቅ እና ለትውልድ ይተርፍ ዘንድ መፍጠን ያለበትን ስራ መሰራቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከግንባታው ተቋራጭና አማካሪ ኩባንያዎች ጋር በነበራቸው ውይይት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ቅንጅታዊ አሰራርን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ መክረው፤ ይህም የአንዱ መዘግየት ሌላውን እንዳይጎትተው ያስችላል ብለዋል።
የግድቡ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት የግድቡ ብረታብረት፣ ኤሌክትሮ መካኒካልና ሲቪል ስራ በተቀናጀ ሁኔታ በከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ እንዳለ ገልፀው፤ አጠቃላይ አፈፃፀሙ 71 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል። እንደስራ አስኪያጁ ገለፃ በ2013 ዓ.ም መጨረሻ ሁለት ተርቫይኖችን የሀይል ማመንጨት ስራ ለማስጀመር ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን ይህንን ለማሳካት የሚያስችሉ የብረታ ብረት ገጠማ ስራዎች የተጀመሩ ሲሆን የጀነሬተርና ተርባይን ገጠማ ስራም በእቅዱ መሰረት ይከናወናል።
በግድቡ ጥራትና ልኬት ላይ ምንም ድርድር የለንም ያሉት ኢንጂነር ክፍሌ፤ ከዚህ በፊት የነበረውን የብረታብረት ጥራት ችግር ለመቅረፍ በግድቡ የሚተከል እያንዳንዱ ብረት በአልትራሳውንድና ኤክስሬይ ፍተሻ እየተደረገበት እንደሆነ ተናግረዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ተቋራጮችና አማካሪ መሀንዲሶች በዚህ ስራ እየተሳተፉ መሆኑ በዚህ ረገድ ለተሰጠው ትኩረት ማሳያ ነውም ብለዋል። የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ባለቤት ፔድሮ ሳሊኒ የሁለቱ ሀይል ማመንጫ ተርቫይኖችን በ2013 ዓ.ም ስራ ለማስጀመር እና ግድቡን በ2015 ለማጠናቀቅ ካምፓኒያቸው ከሌሎች ካምፓኒዎች ጋር በመናበብ እየሰራ መሆኑን ተናግረው፤ የኢትዮጵያውያን ነዳጅ የሆነውን የአባይ ውሃ በመገደብ ሀይል ለማቅረብ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል። በግድቡ ግንባታ ለወጣት ኢትዮጵያውያን ኢንጂነሮች የእውቀት ሽግግር እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ሚስተር ፔድሮ፤ ይህም ሌሎች ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለመገንባት ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 24/2012
ድልነሳ ምንውየለት
ፎቶ፡- ዳኜ አበራ