• ገንዘቡን ለማስመለስ የሚያስችል ውሳኔ መተላለፉንና ክስ እንደሚመሰረትም ተጠቆመ
አዲስ አበባ፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ኮሚቴ አቋቁሞ አላግባብ የተከፈለ ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ለማስመለስ ቢሰራም ማስመለስ አለመቻሉን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ገለጸ። ገንዘቡን ለማስመለስ የሚያስችል ውሳኔ መተላለፉንና ክስ እንደሚመሰረትም ተጠቆመ።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የውጭና ዓለም አቀፍ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አወቀ ጤናው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ዋና ኦዲተር ከ2002 እስከ 2009 ዓ.ም ባደረገው ኦዲት አላግባብ ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ተከፍሏል። ድርጊቱ የተፈጸመው በሁሉም 190 የፌዴራል ተቋማት ሲሆን በተለይም ከፍተኛ ክፍያ የፈጸሙ 35 ተቋማት ናቸው።
ዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝቱን በየጊዜው ማስተ ካከያ እንዲያደርጉ ለምክር ቤቱ ቢያሳውቅም በምክር ቤቱ መደበኛ አሰራር ሳይስተካከል በየዓመቱ ሲንከባለል መጥቷል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በ2011 ዓ.ም በምክር ቤቱ ዋና አፈጉባዔው አቶ ታገሰ ጫፎ፣ አማካኝነት ከምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ከሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎችና የሚመለከታቸውን አካላት ያቀፈ ልዩ ኮሚቴ በማቋቋም ተቋማቱን በመደገፍ አላግባብ የተከፈለውን ገንዘብ በስድስት ወራት ለማስመለስ ጥረት ቢደረግም 27 ተቋማት የሚያስመልሱበትን የጊዜ መርሃ ግብር ከማቅረብና እጅግ በጣም ጥቂት ገንዘብ ከማስመለስ ያለፈ ገንዘቡን እስካሁን ማስመለስ አለመቻሉን ገልጸዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ልዩ ኮሚቴው ድጋፍ በማድረግ ለአሰራር እንቅፋት የሆኑ ህጎችን ከማውጣት ያለፈ አላግባብ የተከፈለውን ገንዘብ ለማስመለስ በሚፈለገው ደረጃ ውጤት አላመጣም። ኮሚቴው የደረሰበትን የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አቅርቦ አላግባብ የህዝብ ገንዘብን የከፈሉ ኃላፊዎች፣ ሰራተኞችና ተባባሪዎቻቸው በጠቅላይ አቃቤ ህግ እንዲጠየቁ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ውሳኔ አሳልፏል ።
ዋና ኦዲተር የኦዲት ሪፖርቱን በወቅቱ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ ማቅረቡን ያስታወሱት አቶ አወቀ፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ መስርቶ ገንዘቡ አለመመለሱንም አንስተዋል። ዋና ኦዲተር ከኃላፊነቱ በላይ በመለጠጥ ግፊት ቢያደርግም ገንዘቡ አልተመለሰም። ተጠያቂነትም አልተረጋገጠም። አላግባብ የተከፈለው ገንዘብ ካለመመለሱም በላይ አሁንም በተቋማት ተመሳሳይ ችግሮች እየተከሰቱ ነው። በመሆኑም ተጠያቂነት መረጋገጥ እንዳለበት ተናግረዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበኩሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ እንዲያስመልስ ውሳኔ አሳልፌያለሁ ሲል የገለጸ ሲሆን፤ ጠቅላይ አቃቤ ህግም አላግባብ የከፈሉ አስራ አራት ተቋማት ኃላፊዎች፣ ሰራተኞችና ተባባሪዎቻቸው ላይ በቅርብ ቀን ክስ እንደሚመሰርት አስታውቋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክዋኔ ኦዲት ዘርፍ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢና የወቅቱ የልዩ ኮሚቴው ሰብሳቢ የነበሩት ወይዘሮ ወይንሸት ገለሶ፤ ልዩ ኮሚቴው አላግባብ የተከፈለውን ገንዘብ ለተቋማት ድጋፍ በማድረግ ገንዘቡን እንዲመልሱና ለአሰራር አስቸጋሪ የሆኑ ህጎችን ለማሻሻል ተቋቁሟል። ልዩ ኮሚቴው የሚመለከታቸውን ተቋማት በማቀናጀት ለአሰራርና ለሀብት ብክነት ምክንያት የሆኑ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን ማሻሻሉንም ተናግረዋል።
ድጋፍ በማድረግ አላግባብ የተከፈለውን ገንዘብ ለማስመለስ ጥረት ተደርጓል። ሆኖም ያልተመለሰ ገንዘብ በመኖሩ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ በመመስረት ገንዘቡን እንዲያስመልስ፤ ዋና ኦዲተርም የኦዲት ሪፖርት በማቅረብ እንዲያግዝ ምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳብ አሳልፏል። አቃቤ ህግ የከሰሳቸውና ለመክሰስም በሂደት ላይ እንዳለና ምክር ቤቱም ክትትል እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱሉ፤ የዋና ኦዲተር ያለአግባብ የተከፈለ ገንዘብ መመለስ ያለባቸው ተቋማት የኦዲት ሪፖርት ደርሷል። ከተሰጡት ተቋማት መካከል የ14 ተቋማት አላግባብ ክፍያ የፈጸሙ ኃላፊዎች፣ ሰራተኞችና ተባባሪዎቻቸውን ክስ ለመመስረት ዝግጅት አጠናቀናል። የክስ መዝገብም ከፍተናል በቅርብ ጊዜ ውስጥም ክስ መስርተን ተጠያቂ እናደርጋለን ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ችግሩ በአስተዳደራዊ እርምጃ ሊስተካከሉ የሚችሉ እርምጃ እንዲወሰድና ማስተካከያ እንዲያደርጉ ለተቋማቱ አስተያየት ሰጥተናል ያሉት አቶ ዝናቡ፤ በቀጣይም ክትትልና ምርምራ በማድረግ በሌሎች ተቋማት ላይም እርምጃ እንወስዳለን፤የህዝብን ሀብት የመዘበሩ አካላት ቅጣታቸውን እንዲያገኙና የመዘበሩትም ገንዘብ እንዲመልሱ እናደርጋለን ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 24/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ