አዲስ አበባ፡- የኢንተርኔት ማቆም፣ መረጃን አጣርቶ ማውጣትና መዝጋት በተመለከተ በአገር ደረጃ የወጣ ህግ ባለመኖሩ ተገቢው መረጃ ለተገቢው አካል እንዳይደርስ ሆኗል። በዚህም ይህንን ለማረም በኮምፒውተር ወንጀሎች አዋጅ ለማካተት ረቂቅ እየተዘጋጀ መሆኑን የብሔራዊ ህግና ፍትህ አማካሪ ምክርቤት አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህርና በጠቅላይ አቃቤ ህግ የተቋቋመው የህግና ፍትህ አማካሪ ምክርቤት አባል ረዳት ፕሮፌሰር መሰንበት አሰፋ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ መንግስት ኢንተርኔትን በማቆም፣ በመዝጋትና መረጃ አጣርቶ በማውጣቱ ዙሪያ ሊከተላቸው የሚገቡ ህጎች በአገር ደረጃ አልተቀመጡም። በዚህም በተለያየ መንገድ እነዚህ ክዋኔዎች ተግባራዊ እየሆኑ መጥተዋል። ይህ ደግሞ ተጠቃሚዎችንም ሆነ ህዝቡን መረጃ በትክክል እንዳያገኝ አድርጎታል።
በሚዲያ የመረጃ ነጻነትና በኮምፒውተር ወንጀሎች ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ አሁን ባለው ደረጃ ምክር ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ህግ ለማውጣት እየሰራ እንደሆነ የሚገልጹት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ የህጉ መውጣት በህግ አግባብ የተቃኘ መረጃ ለህዝብ እንዲደርስ እድል ይሰጣል ብለዋል። የኢንተርኔት አጠቃቀም ሁኔታውም ሥርዓት እንዲኖረው ያደርጋል። ከዚያ ባሻገር መንግስት ምን ምን አስገዳጅ ሁኔታ ሲገጥመው ኢንተርኔትን ማቆም፣ መዝጋትና ትክክለኛ መረጃ አውጥቶ
ማሰራጨት እንዳለበትም ያመላክታል። ከዚያ ውጪ ከተሰራ ደግሞ ተጠያቂነት እንዲኖርበት ያደርጋል። በተመሳሳይ ተጠቃሚ አካላትም የህግ አግባብን ተከትለው አቤቱታቸውን እንዲያቀርቡ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት የመገናኛ ብዙሃን ህግ መምህርና በኔቶርክ ፎር ዲጅታል ራይት አባል ዮሐንስ እንየው በበኩላቸው፤ አገሪቱ በተለያየ መልኩ በቴክኖሎጂ እያደገች ከመምጣቷ ጋር ተያይዞ ብዙ ወንጀሎች ይፈጸማሉ። በዚህም ይህ ህግ አለመኖሩ ወንጀሉ እንዲበራከት ያደርጋልና ህጉ እንዲወጣ መታሰቡ የመረጃ ትክክለኛነትን ከማረጋገጥ አኳያ የማይተካ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
በኮምፒውተር ወንጀሎች አዋጅ ውስጥ ተካቶ ተጠያቂነት እንዲኖር መደረጉ ግን አጠያያቂ እንደሆነ የሚጠቅሱት መምህር ዮሐንስ፤ ኢንተርኔት ከለውጥ በፊትም ሆነ በኋላ እየተዘጋ ነው። አሁንም ዝግ የሆነባቸው ቦታዎች አሉ። ስለሆነም ለምን ተዘጋ የሚለውን በደንብ ግልጽ ማድረግና ከኮምፒውተር ወንጀል አዋጁ ጋር ማገናኘት ያስፈልጋል ብለዋል። ተፈጻሚነቱንም ማፋጠን እንደሚገባ አሳስበዋል። ምክንያታቸውም በቅርብ በወጣው የኢትዮ ቴሌኮም መረጃ 22 ነጥብ 74 ሚሊዮን ህዝብ ኢንተርኔት ይጠቀማል።
በዚህ አዋጅ ውስጥ የሚካተቱ የኢንተርኔት አገልግሎቶች ጥርት ባለ መልኩ መጻፍና መተግበር እንዳለባቸው የሚናገሩት መምህር ዮሐንስ፤ ሁኔታው በፍጥነት ተጠናቆ በህግና መመሪያ ታስሮ ወደ ትግበራ መግባት እንዳለበት አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 24/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው