አዲስ አበባ፡- የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እንዲቻል ለእቀባ እርሻ መስፋፋት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ የእቀባ እርሻ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አሰራሮችን አቀናጅቶ የያዘ በመሆኑ አርሶ አደሩ ከተለመደው አስተራረስ ዘዴ በመውጣት ምርቱን እንዲያሳድግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡ የእቀባ እርሻን ለማስፋፋት የሚያስችል የፖሊሲ ማዕቀፍና የአሰራር መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡ የምርምር ማዕከላትና ተመራማሪዎችም ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመቀመር ጭምር በስራው ላይ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ለረጅም ዓመታት ሲተገበር የቆየው መሬትን ደጋግሞ የማረስ አሰራር የአፈር መሸርሸርን በማባባስ የመሬት መራቆትን ማስከተሉን አቶ አለማየሁ ጠቅሰው፣ ከዚህ አሰራር በመውጣት መሬትን ደጋግሞ ባለማረስ፣ አፈርን በሰብል ተረፈ ምርቶች በመሸፈንና አፈራርቆ መዝራትን ማዳበር እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡ የእቀባ እርሻ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ በአፈር መሸርሸርና በመሬት መራቆት ምክንያት አፈሩ ወደ አሲዳማነት እየተቀየረ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን በማመልከት፣ የእቀባ እርሻ ለችግሩ መፍትሄ እንደሚሆንም አስገንዝበዋል፡፡
‹‹95 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ የእርሻ ሥራ በአነስተኛ የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የሚከናወን ነው›› ያሉት አቶ ዓለማየሁ፣ የእቀባ እርሻ ዘዴን በእነዚህ የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ በመተግበር ውጤታማ ለመሆን ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በደቡብ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የእቀባ እርሻ የተተገበረባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ከአካባቢዎቹ የተገኙትን መልካም ተሞክሮዎች ወደሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ለማስፋት እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡
የእቀባ እርሻ መሬትን ደጋግሞ ማረስን በመቀነስ፣ በማሣ ላይ የሰብል ቅሪቶችን በማስቀረትና ሰብሎችን በፈረቃና በስብጥር በመዝራት የማረስ ዘዴ ሲሆን አፈርን፣ ውሃን፣ ሌሎች ማዕድናት በመቆጠብ ምርትና ምርታማነትን እስከ 40 በመቶ በዘላቂነት ለማሳደግ ያስችላል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2011
በአንተነህ ቸሬ