- 15 ተቋማት በሂሳብ ጉድለት ሊከሰሱ ነው
አዲስ አበባ፡- ባለፈው በጀት ዓመት የክትትል ኦዲት ተደርጎባቸው የሂሳብ ጉድለት የታየባቸው ክፍለከተሞችና ሴክተር መስሪያ ቤቶች 101 ሚሊዮን 103 ሺ ብር ተመላሽ ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር አስታወቀ። ሌሎች 15 ተቋማትም በተደጋጋሚ የሂሳብ ጉድለታቸውን እንዲያስተካክሉ ቢነገራቸውም ምላሽ መስጠት ባለመቻላቸው በአቃቢ ህግ እንዲከሰሱ ውሳኔ መተላለፉን አመለከተ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር ወይዘሮ ፀጌወይን ካሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ ባለፈው በጀት ዓመት በተደረገው የክትትል ኦዲት በአስሩም ክፍለከተሞች ስር ያሉ የመሬት ባንክ ማስተላለፍ ፅህፈት ቤት ከሊዝ ቅድመ ክፍያና ዓመታዊ ክፍያ ጋር በተያያዘ የሂሳብ ጉድለት ታይቶባቸዋል። ከነበረባቸው 261 ሚሊዮን ብር ጉድለት ውስጥ ከ101 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሚሊዮን በላይ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ተመላሽ አድርገዋል።
በዚህም መሰረት ከተሰብሳቢ ሂሳብ፥ ያለአግባብ የተከፈለ ደመወዝ፥ አበልና የትርፍ ሰዓት ክፍያ፥ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ፥ ከግዥ አዋጅ መመሪያ ውጪ የተፈፀመ ክፍያ፥ በብልጫ የተከፈለ በድምሩ 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ተመላሽ መደረጉን ጠቁመዋል። በተመሳሳይ ሰባት ክፍለ ከተሞችና ሁለት ሴክተር መስሪያ ቤቶች ደግሞ በውል መሰረት ያልተጠናቀቁ ግንባታዎች ያልተሰበሰበ ቅድመ ክፍያ ካልፈፀሙት 79 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ውስጥ 42 ነጥብ 9 ሚሊዮን ያህሉን ተመላሽ ማድረግ መቻሉን ዋና ኦዲተሯ አስገንዝብዋል።
እንዲሁም በወቅቱ በተደረገው የክትትል ኦዲት አምስት ክፍለከተሞች በበጀት ዓመቱ 86 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር አለመሰብሰባቸው መረጋገጡን፤ ይሁንና ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 23 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ተመላሽ ማድርግ መቻላቸውን ወይዘሮ ፅጌወይን አመልክተዋል።
በአጠቃላይ ጉድለት ታይቶባቸው ከነበሩት ተቋማት ከሐምሌ ወር ወዲህ ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ ተመላሽ መደረጉን አስረድተዋል።
በሌላ በኩልም ሐምሌ 2011 ዓ.ም ለአስተዳደሩ ምክር ቤት ከቀረበው የኦዲት ዘገባ በተሰጠ የኦዲት አስተያየት መሰረት በሁለት ወራት ውስጥ ምላሽ እንዲሰጡ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም እስከአሁን ዕርምጃ ባለመውሰዳቸው ምክንያት 15 ተቋማት በዐቃቢ ህግ እንዲከሰሱ ውሳኔ መተላለፉን ዋና ኦዲተሯ አመልክተዋል።
«እስከአሁን ዕርምጃ ያልወሰዱ 15 ተቋማት ግኝት ለፌዴራል ሙስና ወንጀል ምርመራ ዳይሬክተር ፤ለአስተዳደሩ አቃቢ ህግ ቢሮና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ዲቪዚዮን በህግ እንዲታይ ተልኳል» ብለዋል።
በህግ እንዲጠየቁ ውሳኔ ከተላለፈባቸው ተቋማት ውስጥ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፥ መንገዶች ባለስልጣን፥ ዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል፥ አነስተኛ እና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት፥ ጥሩነሽ ቤጂንግ አጠቃላይ ሆስፒታል፥ ትራንስፖርት ባለስልጣን፥ የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ማዕከል፥ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የሚገኙበት መሆኑን ወይዘሮ ፅጌወይን አብራርተዋል።
ተቋሙ በተያዘው በጀት ዓመትም የኦዲት ትኩረቱን ከፍተኛ በጀት የተመደበላቸው ተቋማት ላይ በማድረግ እና የክዋኔ ኦዲት ሽፋኑን ለመጨመር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ዋና ኦዲተሯ አስገንዝበዋል። በተጨማሪም የተቋማቸውን የኦዲት ሥራ የሚጠይቀውን ሙያዊ ነፃነት ጠብቆ ለመሥራት እና ያለበትን የባለሙያ ፍልሰት ለመግታት ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ እና ደንብ አዘጋጅቶ በአስተዳደሩ ካቢኔ እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል፡
የአዲስ አበባ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት መረጃ እንደሚያሳየው፤ በ2011 በጀት ዓመት በዋና ኦዲተሩ ግኝት መሰረት ጉድለት የታየባቸውን 59 ተቋማት በጠቅላይ ዐቃቢ ህግ እንዲጠየቁ የተደረጉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 39ኙ እስከአሁን ምላሽ ያልሰጡና ጉዳያቸው አሁንም በህግ ሂደት ላይ የሚገኝ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 23/2012
ማህሌት አብዱል