የመጀመርያውን የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር “ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ በአምላክሽ ኃይል በንጉሥሽ” የሚለውን የደረሱት ቀኝጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፤ ስለአገር ፍቅርና ጀግንነት የሚያወሱ በርካታ ድራማዎች፣ ግጥሞችና መዝሙሮችን የደረሱ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል “አፋጀሽኝ”፣ “እለቄጥሩ” ወይም “ጎበዝ አየን” ይገኙበታል።
በተወለዱ በ14 ዓመታቸው የቀኝ ጌትነትን ማዕረግ ያገኙት እኒህ ሊቅና የሀገር ባለውለታ በድል ማግስት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ከ1935 ዓ/ም እስከ ሕልፈታቸው ድረስ አገልግለዋል።
ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ የኪነጥበብ ሰው ብቻም ሳይሆኑ መምህር፣ አርበኛ እና ዲፕሎማትም ሆነው ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ያገለገሉ ሲሆን ሀምሌ 1 ቀን 1939 ዓ.ም በተወለዱ በ52 ዓመታቸው ማረፋቸውን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
ስርዓተ ቀብራቸው በቀድሞው ባለወልድ በአሁኑ መንበረ ፀባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል የተፈፀመ ሲሆን ቤተክርስቲያኗ በ2001 ዓ.ም ‘‘የቀብር ቦታዎችን ለልማት ለማዋል ስለተፈለገ የቤተሰቦቻችሁን አፅም በማንሳት ተባበሩን’’ ብላ ባወጣችው ማስታወቂያ መሰረት የቤተሰቦቻቸውን አፅም ለማስወጣት በቦታው የተገኙና የቀኝ ጌታውን ታሪክ የሚያውቁ አቶ ጀማነህ ወርቁ፣ ዶክተር ፍስሀ ገ/አብ እና አቶ ጌታቸው ግዛው የተባሉ ግለሰቦች ያገባኛል የሚል የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ቤተሰብም ሆነ ዘመድ ባለመገኘቱ በዚሁ ዓመት ግንቦት ወር በራሳቸው ተነሳሽነት አፅሙን አስወጥተው ለቤተክርስቲያኗ በአደራ መልክ እንዳስረከቡ ይታወቃል።
ይህ ከሆነ ከስምንት ዓመታት በኋላ ደግሞ በጨለማ ክፍል ውስጥ በትንሽ ሳጥን የተቀመጠውን የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴን አፅም ወደ ትውልድ ስፍራቸው ደብረ ኤልያስ በመውሰድ በክብር ለማሳረፍ ብሎም በከተማዋ መታሰቢያ ሀውልት ለመገንባት እና በስማቸው ሙዚየም ለማሠራት በወረዳው አስተባባሪነት በአዲስ አበባና በደብረ ኤልያስ ከተማ ኮሚቴ ተቋቁሞ በተሠራ ሥራ አፅማቸው ህይወታቸው ባለፈ በ70ኛ ዓመቱ ሀምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም በደብረ ገነት ነብዩ ቅዱስ ኤልያስ ቤተክርስቲያን በክብር አርፏል።
የባለቅኔው ማስታወሻ በተገባው ቃል መሰረት ሳይሠራ ሁለት ዓመታት አልፈው ሦስተኛው ዓመት ላይ መደረሱ ነዋሪዎችን ቅር አሰኝቷል፤ ቅሬታቸውንም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልጸዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የደብረ ኤልያስ ወረዳ ነዋሪዎች ሥራውን ለማከናወን የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አፅማቸው ባረፈበት ዕለት ተዘጋጅቶ እንደነበርና በዕለቱ የተወሰነ ገንዘብ እንደተሰበሰበ፣ የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦችም ለዚሁ ፕሮጀክት የሚውል ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ለመስጠት ቃል እንደገቡ አስታውሰዋል።
አፅሙ ካረፈ ማግስት ጀምሮ ግን ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለመኖሩና ቃል የተገባው ገንዘብ ሳይሰበሰብ ጉዳዩ ተረስቶ መቅረቱ ‹‹እኒህን ታላቅ ሰው እንደመርሳት ሆኖብናል፤ ስለጉዳዩ በተለያየ አጋጣሚ የወረዳውን አመራሮች ብንጠይቅም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም›› ሲሉ ነዋሪዎቹ ጨምረው ይገልፃሉ።
ነዋሪዎቹ አፅሙን በክብር ካሳረፈው ኮሚቴ ውስጥ የተወሰኑ ግለሰቦች ተቀይረው አዲስ ኮሚቴ ተቋቁሞ የነበረ ቢሆንም ወረዳው የማስተባበር ሥራውን እንዲያስቀጥል ተጠይቆ አዎንታዊ ምላሽ በጊዜው ማግኘት እንዳልተቻለ መረጃ እንዳላቸው ገልጸል።
እኛም በቦታው ተገኝተን ባደረግነው ምልከታ ለሀውልት ማሠሪያ እና ለሙዚየም ግንባታ የተቀመጡ የመሰረተ ድንጋዮች ላይ ምንም ግንባታ አለመጀመሩን አይተናል።
ዝግጅት ክፍላችን ቅሬታውን ይዞ የደብረ ኤልያስ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑትን አቶ አያሌው በየነን አነጋግሯል። አቶ አያሌው በጊዜው በአሁኑ ኃላፊነታቸው ላይ እንዳልነበሩ ገልጸው ጉዳዩን ግን እንደሚያውቁት ተናግረዋል።
ዋና አስተዳዳሪው በምላሻቸው በነዋሪዎች የተነሳው ቅሬታ ትክክል መሆኑንና ቃል የተገባው ግንባታ አለመከናወኑን ገልጸው ወደ ተግባራዊ እንቅስቅሴ ያልተገባበት ዋነኛው ምክንያት አዲስ አበባ በነበረው ኮሚቴ ውስጥ አለመግባባት በመፈጠሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ የኮሚቴ አባላት መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ አዲስ ኮሚቴ በማዋቀር የእውቅና ደብዳቤ ተልኮ ወረዳው ምላሽ ባለመስጠቱ ወደ ሥራ መግባት አለመቻሉን ያውቃሉ ወይ? ተብለው ለተጠየቁት አቶ አያሌው ሲመልሱ ስለዚህ ጉዳይ እንደማያውቁ ነገር ግን አሁን ይህንን መነሻ በማድረግ የማጣራት ሥራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
በወቅቱ የተሰበሰበው ገንዘብ አፅሙን በክብር ለማሳረፍ በነበረው ሂደት ለወጣ ወጪ አገልግሎት ላይ እንደዋለ የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው ከዚህ ውጪ የባከነ ወይም የተመዘበረ ገንዘብ አለመኖሩን አረጋግጠዋል።
ቃል የተገባውን ገንዘብ በተመለከተ ግን ዋና አስተዳዳሪው ማን ምን ያህል ቃል እንደገባ የተደራጀ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረው እንደመንግሥት ሥራዎችን ለመሥራት በማሰብ በዚህ ዓመት ለሀውልቱ ግንባታ የዲዛይን ማሠሪያ የሚውል 120 ሺህ ብር መመደቡን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተገብቶ የተጀመረ ሥራ አለመኖሩን አቶ አያሌው ተናግረው በቀጣይ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት አሁን የተጀመረው የቤተክርስቲያን ማደስ ሥራ በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተከናወነ ስለሆነ ህብረተሰቡ ለተጨማሪ ወጪ እንዳይዳረግ በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
የሀውልት፣ ሙዚየምና ቅኔ ማዕከል ግንባታ ሥራው በተጨባጭ መቼ እንደሚጀመር አቶ አያሌው ቁርጥ ያለ ምላሽ አልሰጡም።
በኢትዮጵያ የኪነጥበብ ታሪክ ውስጥ ትልቁን አሻራ ማኖር ከቻሉ እውቅ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ የነበሩት ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ ትውልድ እና ዕድገታቸው በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ከተማ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 23/2012
ድልነሳ ምንውየለት