ከፊት ለፊታችን በርካታ ተሽከርካሪዎች ዝግ ብለው ይሄዳሉ፤ ይመጣሉ፤ የመንገድ ግንባታ ተሽከር ካሪዎች፣ከባድ መኪናዎች፣ አውቶቡሶች፣ አውቶሞቢሎች በየዓይነቱ መንገዱን ሞልተውታል፡፡ ተሽከርካሪዎቹ በዝግታ ቢንቀሳቀሱም የሚቀሰቅሱት አቧራ እና ከተሽከርካሪዎቹ የሚያወጠው ጭስ እንድ ላይ ሆኖ አካባቢውን የሚቃጠል አስመስሎታል።
በአዲስ መልክ እየተገነባ በመሆኑ ለተሽከርካሪዎች፣ለእግረኞች ፣ለአሽከርካረዎች ይጎረብጣል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች የተቀበሩ ትላልቅ ቱቦዎች ፣በአንዳንዶቹ አካባቢዎች ደግሞ የቱቦዎቹ መስኮቶች ከፍ ብለው ይታያሉ፡፡ መንገዱ በጣም ሰፊና ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲወል ተደርጎ እየተገነባ ይመስላል፡፡ የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ግንባታ፡፡
እንዲያም ሆኖ መንገዱ አላረፈምም፡፡ አንደኛው የመንገዱ አካል ሲገነባ ሌላው ለተሽከርካሪዎች ክፍት ይደረጋል። ለተሽከርካሪዎች ብዙም የማይመች ቢሆንም አማራጭ ከማጣት የተነሳ አሽከርካሪዎች ይጠቀሙበታል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ይህ ከቃሊቲ አደባባይ ቱሉ ዲምቱ ድረስ የሚሠራው መንገድ አምስት ዋና ዋና ተሻጋሪ ድልድዮችን ያካትታል፡፡ የመንገዱ ርዝመት 11ኪ.ሜ ስፋቱ ደግሞ 50ሜትር ይሆናል፡፡
የግንባታው አፈፃፀም ባለፈው በጀት ዓመት 18 ነጥብ 75 በመቶ የደረሰ ሲሆን። የቱሉ ዲምቱ ቂሊንጦ አደባባይ መንገድ እና የቃሊቲ ቀለበት ቱሉ ዲምቱ መንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ 4ነጥብ 7ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞላቸዋል፡፡ በዓይነታቸው ልዩ የሆኑት እነዚህ የመንገድ መሠረተ ልማት ዝርጋታዎች አጠቃላይ 21ኪ.ሜ የሚጠጋ ርዝመት እና 50ሜትር ስፋት ይኖራቸዋል፡፡
በቃሊቲ የመንገድ ትራንስፖርት ማሠልጠኛ አካባቢ በመኪና ጥበቃ ሥራ ላይ የተሰማሩት ወጣት መስፍን ተስፋዬ እና ወጣት እስጢፋኖስ ድንቁ መንገዱ ከሚያስተናግደው ተሽከርካሪና ከሚመላለስበት እግረኛ አንፃር በፍጥነት ሊሠራ ይገባው ነበር ይላሉ።
የመንገዱ ግንባታ አለመፋጠን አሽከርካሪዎችን ብቻ አይደለም እየጎዳ ያለው፡፡ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ታራሚ ቤተሰቦቻቸውን የሚጠይቁ ወገኖችንም ለችግር እየዳረገ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በክረምት ጭቃው፣ በበጋ አቧራው ፈታኝ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ አቧራው ለጤና ጠንቅ እየሆነ መምጣቱን በመጥቀስ በፍጥነት እንዲገነባ ይጠይቃሉ፡፡
የመንገድ ግንባታውን ለመፋጠን የሚያስችል እንቅስቃሴ በአካባቢው እንደማይታይ ተናግረው፣ ዘወትር ውሃ በቦቴ አመጥቶ ከማርከፍከፍ ባለፈ ምንም ዓይነት ሥራ አይታይም ይላሉ።
የትራፊክ ፍሰቱን በማስተናበር ሥራ ላይ ያገኘናቸውና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ቡድን መሪ ዋና ሳጅን ገብረጻህማ ተሰማ መንገዱ የትራፊክ ፍሰት የሚባዛበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ግንባታው እጅግ አዝጋሚ ነው ይላሉ።
‹‹መንገዱ በአዲስ መልክ እየተገነባ መሆኑን እናውቃለን፤ ሆኖም በሚፈለገው ፍጥነት እየተሠራ አይደለም›› የሚሉት ዋና ሳጅን ገብረጻህማ፣ ለነዋሪዎች፣ ለነጋዴዎች፣ የተለያዩ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ወደ አዲስ አበባ ለሚመጡትም ሆነ ከአዲስ አበባ ወደ ምሥራቁና ደቡቡ ክፍል ለሚጓዙ እንዲሁም ለትራፊክ ፖሊስ አባላት ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን ይጠቁማሉ፡፡ በመንገዱ ዳርና ዳር የተቀበሩት የፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎች በአግባቡ ባለመደፈናቸው በተለይ በምሽት አደጋ እያስከተሉ መሆናቸወንም ይገልጻሉ፡፡
አሽከርካሪው አቶ የሱፍ ሐጂ ከቃሊቲ ባቡር ጣቢያ ጀምሮ እስከ ቱሉ ዲምቱ ባለው መንገድ እየተመላለሱ የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በመንገዱ ግንባታ መጓተት ምክንያት ይህን የሥራ ቦታቸውን መቀየራቸውን ይናገራሉ።
የሥራ ቦታቸውን ቢቀይሩም የመኖሪያ ቤታቸው በአካባቢው በመሆኑ አቶ የሱፍን ችግሩ አልተለያቸውም፡፡ በተለይም በአካባቢው የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሙ፤ በመንገዱ አባጣ ጎርባጣ መሆንና የተቆፋፈሩት ዳርቻዎቹ ባለመደፈናቸው ሁሌም እንደሚቸገሩ ይጠቁማሉ፡፡
አምቡላንስና የእሳት አደጋ መኪናዎች በቶሎ ደርሰው የአካባቢውን ነዋሪዎች ከአደጋ ለመታደግ የሚችሉበት አማራጭም የጠበበ መሆኑንም ነው የተናገሩት። በመንገዱ ምቹ አለመሆን የተነሳ በተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ ለከፍተኛ የጥገና ወጪ የሚዳረጉ መኖራቸውንም አቶ የሱፍ ይገልጻሉ።
ወይዘሮ ሱመያ ጀማል እና ዘነበች በቀለ በአካባቢው ቤት ተከራይተው ይኖራሉ፡፡ መንገዱ መኪኖች በብዛት የሚመላለሱበት እና ዕረፍት የሌለው መሆኑን ተናግረው፣ ከመንገዱ የሚነሳው አቧራ እንኳን መንገደኛን ቤቱ የተቀመጠውንም ማስቸገሩን ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ የተነሳም የልጆቻቸው ጤንነት አደጋ ላይ እየወደቀ መምጣቱን ይጠቁማሉ።
በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር መረጃ እንዲሰጡን በስልክ በተደጋጋሚ፣ በአካልም በቢሯቸው ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ስብሰባ ላይ ናቸው በሚል አልተሳካም።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2011
በኃይለማርያም ወንድሙ