አዲስ አበባ፡- ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ 210 ሺ የመስኖ ውኃ መሳቢያ ፓምፖች እና ሞተሮች ውስጥ 20 በመቶ የማይሰሩ መሆናቸው በጥናት መረጋገጡን የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ገለጸ። የፍተሻ ማዕከልም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅት ተገንብቷል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በልሁ የአነስተኛ የውኃ መሳቢያ ፓምፖችና ሞተሮች መፈተሻ ማዕከልን አጋር ድርጅቶች በተገኙበት በመስሪያ ቤታቸው አዳራሽ ትናንት ባስመረቁበት ወቅት እንደገለጹት፣ ለአርሶ እና ከፊል አርብቶ አደሮች የሚቀርቡት የመስኖ ውኃ መሳቢያ ሞተሮችና ፓምፖች ጥራታቸውን የጠበቁ አይደሉም። በዚህ የተነሳም የመስኖ ተጠቃሚዎች ለጥገና እና ለአላስፈላጊ ወጪ መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ጥናቶችን ጠቅሰው እንዳሉት፣ ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡት 210 ሺ የመስኖ ውኃ መሳቢያ ሞተሮችና ፓምፖች ውስጥ 42 ሺ የማይሰሩና የተበላሹ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም ችግሮቹን በዘላቂነት በመፍታት ጥራታቸውን የጠበቁ የመስኖ ፓምፖችንና ሞተሮችን ማቅረብ የሚያስችል ብሔራዊ የፍተሻ ማዕከል ከግብርና ሚኒስቴር፣ከንግድ ሚኒስቴር እና የመስኖ ስራዎችን ከሚደግፉ የካናዳና የኔዘር ላንድ መንግሥታት ጋር በመተባበር በ19 ሚሊዮን 134 ሺ 244 ብር በሆነ ወጪ መገንባት መቻሉን አብራርተዋል።
የውኃ ፓምፕና ሞተር ፍተሻ የጥራት ስታንዳርድ አስገዳጅ በመሆኑ በአስመጭዎች አማካኝነት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት ጥራታቸውን የጠበቁ መሆናቸውን እንዲረጋገጥ የሚያደርግ ነው። በመሆኑም የአርሶ አደሮች የመስኖ ሥራ የተሳለጠና ምርታማነቱ እንዲጨምር እንደሚያደርግ ተናግረዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
የመስራት አቅማቸውን፣ጥራታቸውን፣ የናፍታ ፍጆታቸውን እና በአጠቃላይ ለመስኖ ስራው ብቁ ስለመሆናቸው ማዕከሉ እንደሚያረጋግጥም አክለው ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ካባ ኡርጌሳ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የአርሶ አደሮች አሰራር እንዲዘምን፣ ምርታማነቱ እንዲጨምር እና ከዝናብ ጠባቂነት እንዲላቀቅ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በመሆኑም በአገሪቱ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑት አርሶ አደሮች አነስተኛ የመስኖ ሥራን ተግባራዊ ያደርጋሉ።
ከዚህ ውስጥ 400 ሺህ የሚሆኑት አነስተኛ የውኃ ፓምፖችና ሞተሮች ተጠቃሚዎች እንደሆኑም ተናግረዋል። እነዚህ አርሶ አደሮች በሚገጥሟቸው መሰናክሎች ተስፋ እንዳይቆርጡ ችግሮቻቸውን መቅረፍና አምራችነታቸው እንዲጎለብት ማድረግ አስፈላጊ ነው። በመሆኑም የመፈተሻ ማዕከሉ መገንባት በዘርፉ የማይተካ ሚና የሚጫወት ከመሆኑም በተጨማሪ የአገሪቱ አርሶ አደሮች ጥራታቸው በተጠበቁ የመስኖ መሳሪያዎች በዘላቂነት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
እ.ኤ.አ ከ2004 እስከ 210 ባሉት ዓመታት 482 ሺ ፓምፖች ወደ አገር ውስ ጥ መግባታቸውም ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2012
ሙሐመድ ሁሴን