• የ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የመንግሥት የሕንፃ ግንባታ ፕሮጀክቶች ተጓተዋል
የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙና ወደ አስራ አራት በሚጠጉ የመንግሥት የሕንፃ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ባካሄደው የቁጥጥር ሥራ የማስተካከያ እርምት እርምጃዎች በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።
የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነትና የኮሚኒኬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ ሲሳይ ደርቤ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት ፕሮጀክቶቹ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ከተያዘላቸው ጊዜ በአማካኝ አራት ዓመታት ያህል ተጓተዋል። አማካኝ አፈፃፀማቸውም ከ45 በመቶ የዘለለ አይደለም።የግንባታ ፕሮጀክቶቹ ከአንድ ቢሊዮን ሦስት መቶ ሃያ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ የተበጀተላቸው ሲሆን ለግንባታዎቹም እስካሁን ወደ ግማሽ ቢሊዮን የሚጠጋ ብር ክፍያ ተካሂዶባቸዋል።
ተቋሙ የቁጥጥር ስራውን ካከናወነባቸው ፕሮጀክ ቶች መካከል በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ የስታዲየም፣ የአስተዳደር ህንፃ፣ የመማሪያና የመምህራን መኖሪያ ግንባታ ፕሮጀክቶች የሚገኙባቸው ሲሆን የቤተ- መንግሥት አስተዳደር የሚያስገነባው የመቀሌ ቤተ- መንግሥት የእንግዳ ማረፊያ ኮምፕሌክስ፣ የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ቢሾፍቱ ቅርንጫፍ ማስፋፊያ ፕሮጀክት፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤት የሆስፒታልና የአባ ሳሙኤል ማረሚያ ቤት የመሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች የቁጥጥር ስራው ከተከናወነባቸው ፕሮጀክቶች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ኃላፊው አስረድተዋል።
ከፍተኛ የሀገር ሀብት የፈሰሰባቸው ፕሮጀክቶቹ ለመጓተታቸው ዋነኛ መንስዔዎች መካከል የዲዛይን ስራዎች፣ የኮንትራት አስተዳደርና የክትትል ስራዎች ፣ የጨረታ ሂደቶች ላይ የታዩ የሙያ ስነምግባር ግድፈቶች፣ የግል ጥቅም ላይ ማተኮር፣ የመረጃ ክፍተቶች እንዲሁም የአቅም ውስንነቶች ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ያመለከቱት ኃላፊው የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ቁጥጥር ያከሄደባቸውን የፕሮጀክቶች ሪፖርት፣ እንዲሁም በአፋጣኝ መወሰድ ባለባቸው የማስተካከያ ርምጃዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ የውሳኔ አቅጣጫዎችን ማሳለፉንም ጠቁመዋል።
ይህንኑ ተከትሎም የተወሰዱ የእርምት እርምጃዎችን በመከታተል ተፈፃሚ እንዲሆኑ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑንም አብራርተዋል።በዚሁ መሰረ ትም መጠናቀቅ ከነበረባቸው ጊዜ ለአራት ዓመታት የዘገዩት የፌዴራል ማረሚያ ቤት ፕሮጀክቶች በተወሰደው እርማት፣ እንዲሁም ድጋፍና ክትትል መሰረት ሥራው ተጀምሯል።
በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ሥራው እስካሁን ያልተጀመረ አንድ የግንባታ ፕሮጀክትን አስመልክቶ ቀደም ሲል ጨረታውን የወሰደው ተቋራጭ ላይ ጉዳዩ በሕግ አግባብ እንዲታይ፤ ፕሮጀክቱ ተጫርቶ ለሌላ አሸናፊ ተቋራጭ እንዲሰጥ አቅጣጫ መቀመጡም ታውቋል።
በሌላም በኩል የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ቢሾፍቱ ቅርንጫፍ የሚያካሂደው እና ከ 4 ዓመታት በላይ የተጓተተው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ቀጣይ ዕጣፋንታውን ለመወሰንና የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ይረዳ ዘንድ በገለልተኛ ወገን የጥራት ፍተሻ እየተካሄደበት እንደሚገኝና ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በፕሮጀክቶቹ አጠቃላይ ገፅታ፣ በተፈፀሙ ብልሹ አሰራሮች እና ክፍተቶች፣ እንዲሁም መወሰድ ባለባቸው ርምጃዎች ላይ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሪፖርት ማድረጉን አቶ ሲሳይ ገልጸዋል።
የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1097/ 2011 በአንቀፅ 32 ንዑስ አንቀፅ 18 የተቋቋመ መንግሥታዊ ተቋም ሲሆን፤ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 439 / 2011 መሰረት ተቋሙ በአገሪቱ የሚከናወኑ ግንባታዎችን የመቆጣጠር ስልጣን እንደተሰጠው ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2012
እስማኤል አረቦ