አዲስ አበባ:- ከታህሳስ ሃያ አንድ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በቻይና ውሃን (Wuhan) ክልል የተከሰተው የኖቭል ኮሮና ቫይረስ (corona virus) በሽታ ወደ አገራችን እንዳይዛመት እየተሠራ መሆኑ ተነገረ።
የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በትላንትናው እለት በኢንስቲትዩቱ አዳራሽ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለፀው ይህ አዲስ የተከሰተ ቫይረስ እስከ ትናንትናው እለት ድረስ በጠቅላላ 581 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው በዓለም ጤና ድርጅት በኩል ሪፖርት የተደረገ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 571ዱ ቻይናውያን፤ አስሩ ደግሞ የተለያዩ አገራት ዜጎች መሆናቸውን አመልክቷል።
በቫይረሱ ከተጠቁት 571 ቻይናዊያን መካከል 17ቱ ህይወታቸው ማለፉን ያመለከተው የኢንስቲትዩቱ መግለጫ ቫይረሱ ወደ ተለያዩ ሀገራት ማለትም አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ታይላንድ፣ ኮሪያ ሪፐብሊክ እና ሲንጋፖር በተጓቾች አማካኝነት መሰራጨቱንም አስታውቋል።
ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ እንዳሉት ይህ አይነቱ ክስተት ወደ እኛም አገር እንዳይገባ አስፈላጊው ሁሉ እየተደረገ ሲሆን፤ በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበርካታ አገራት በረራ የሚያደርግ በመሆኑ እና በተለይም ወደ ቻይና የተለያዩ ግዛቶች በሳምንት ሰላሳ አምስት በረራዎችን ከማድረጉ አኳያ ጉዳዩ ልዩ ትኩረትንና ጥንቃቄን ይፈልጋል።
ዶክተሩ እንደገለፁት በማንኛውም የአየር መንገድ በኩል ለሚሄዱ መንገደኞች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ስለ በሽታው መረጃ መስጠትና ወደ ሀገራችን ለሚመጡት ደግሞ በበሽታው ተይዘው ሊሆኑ ስለሚችሉ በዓለም የጤና ድርጅት ምክረ ሀሳብ መሰረት ለሁሉም መንገደኞች የሰውነት ሙቀት ልየታ ስራ (Screening) በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እየተካሄደ ይገኛል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተለያዩ የዝግጅት ሥራዎችን የጀመረ ሲሆን ለክልሎች እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትም አስፈላጊ የዝግጅት ሥራዎችን እንዲያከናውኑ መልዕክት ተላልፏል።
“አልዘገየም ወይ?” ተብለው ለተጠየቁትም “ከዓለም ጤና ድርጅት በምናገኘው መረጃ፣ ከሌሎች ዓለም አቀፍና አፍሪካዊ የጤና ድርጅቶች ጋር መረጃ በመለዋወጥና በመናበብ ነው የምንሰራው። አሁን የጀመርነውም ከእነዚሁ አካላት ጋር በምናደርገው ግንኙነትና በምናገኘው መረጃ መሰረት ስለሆነ አልዘገየንም።” በማለት ዶክተር ኤባ መልሰዋል።
በሽታው በአገራቸው መገኘቱን ሪፖርት ወደ አደረጉ ሀገራት የሚጓዙ መንገደኞች ሊያደርጓቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎችን በተመለከተም የትኩሳትና ሳል ምልክት ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር ንክኪ አለማድረግ፣ እጅን በሳሙናና ውሃ መታጠብ፤ በተለይም ከታመሙ ሰዎች ወይም ከአካባቢያቸው ጋር ንክኪ ከመፍጠር መቆጠብ እንደሚገባ ተገልጸዋል።
ያልበሰሉ የእንስሳት ተዋፅኦ የሆኑ ምግቦችን ከመመገብ መቆጠብ፣ በህይወት ካሉም ሆነ ከሞቱ የቤት እንስሳት ጋር ንክኪ አለማድረግ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት፣ ጤና ሚኒስቴር፣ ህክምና ተቋማት፣ ከጉዞ ማህበራት ፤ከአየር መንገድ፣ ከመዳረሻ ቦታዎች ወይም ከሌሎች የመረጃ ምንጮች ስለ በሽታው በቂ መረጃ ማግኘትና ራስን ከበሽታው መከላከል ይገባል ሲሉም ዶ/ር ኤባ አሳስበዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሳሰቡት ከሆነ ማንኛውም በበሽታው ተይዣለሁ ብሎ የጠረጠረ፤ ወይም ከበሽታው ጋር የተያያዙ ምልክቶች ማለትም የመተንፈሻ አካል ህመም፣ ትኩሳትና እንደ ሳል ያሉ የህመም ምልክቶች ከተከሰቱ ወይንም የበሽታው ስሜት ከመፈጠሩ ከ14 ቀናት በፊት በሽታውን ሪፖርት ወዳደረጉ አገራት ሄደው ከነበረ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ጣቢያ በመሄድ መመርመር ይገባል።
ማንኛውም ሰው ህመሙ አለብኝ ብሎ ከጠረጠረ፣ ሌላው ሰው አለበት ብሎም ካሰበ፣ ከበሽታው ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮች ካጋጠሙት ወይም ስለ በሽታው መረጃ ማግኘት ከፈለገ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በመደበኛ መስመር 0112765340 መደወል፤ ወይም በኢሜል አድራሻ – phemdatacenter@gmail.com ወይም ephieoc@ gmail.com መላክ የሚቻል መሆኑን እና ጳውሎስ እና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎችም ይህንኑ እንዲያስተናግዱ የተመደቡ መሆኑንም በመግለጫው ላይ ተነግሯል።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2012
ግርማ መንግሥቴ