• በአንዳንድ የእምነት ተቋማት እስከ 90 ሺህ ብር ይጠየቃል
አዲስ አበባ፤- በእምነት ተቋማት ለዘላቂ ማረፊያ የተጋነነ ክፍያ ማስከፈል ተገቢ አለመሆኑ ተገለጸ። በአንዳንድ የእምነት ተቋማት ለመቃብር ስፍራ እስከ 90 ሺህ ብር እንደሚጠየቅም ተጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጪ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ዶክተር አቡነአረጋዊ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት አንድ ሰው የመኖር መብት እንዳለውና ተፈጥሯዊ የመሞት ግዴታ እንዳለበት ሁሉ በዘላቂ ማረፊያም የማረፍ /የመቀበር/ መብት አለው።
በዚህ በኩል ቤተክርስቲያን የዘላቂ ማረፊያን ኃላፊነት ወስዳ አገልግሎት እየሰጠች መሆኑ ይታወቃል ያሉት ሊቀጳጳሱ ይህም ሆኖ ለዚህ አገልግሎት የሚከፈለው ክፍያ ግን የህዝብን ኑሮ ያገናዘበ መሆን ይጠበቅበታል ብለዋል።
ሊቀጳጳስ ብጹዕ ዶክተር አቡነአረጋዊ እንደገለፁት፣ በከተማዋ ብዙ መክፈል የማይችሉ አቅመ ደካሞች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በመንፈሳዊ ርህራሄም ጭምር ማስተናገድ ተገቢ ነው። እያንዳንዱ አድባራትና ገዳማት የየራሳቸው አስተዳደርና ስርዓት ያላቸውና የዘላቂ ማረፊያዎችንም በተመለከተ እንደይዞታቸው የራሳቸው ተመን የሚያወጡ ቢሆንም የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ያላገናዘበ ክፍያ ማስከፈል ግን ተገቢ አይደለም።
በመሆኑም ለቀብር ማስፈጸሚያውና ለካህናት አገልግሎት የሚወጣውን ብቻ ታሳቢ አድርገው ሚዛናዊ የሆነ ዋጋ ማስከፈል እንጂ እንደ ንግድ የገቢ ማስገኛ አድርገው መስራት እንደሌለባቸው ዶክተር አቡነአረጋዊ ገልጸዋል፡፡
የዚህ አይነት ተግባርም ከመንፈሳዊ ተቋማት የሚጠበቅ ባለመሆኑ የዘላቂ ማረፊያን የሚያስተዳድሩ አካላትም ለሁሉም በየደረጃው የማስተናገድም ኃላፊነት እንደሚጠበቅባቸው መገንዘብም አለባቸው ብለዋል።
በተጨማሪም አጠቃላይ ዘላቂ ማረፊያዎችን በተመለከተ ወቅታዊ ሁኔታውን ባገናዘበና የወደፊቱንም የህዝብ ብዛት ከግምት ባስገባ መልኩ ጥናት ማከናወን ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር አቡነአረጋዊ፤ በአሁኑ ወቅት ያሉት ዘላቂ ማረፊያዎች ከአያያዛቸው ጀምሮ ችግር ያለባቸው በመሆኑ ፕላን የሌላላቸው፤ መሬትን በአግባቡ የማይጠቀሙ፤ የቆሻሻ ማጠራቀሚም ሆነው ይታያሉ ብለዋል።
በመሆኑም በሌላው አለም እንደምናየውና እንደ ምሳሌም በቀጨኔ መድኃኒአለም እንደተጀመረው ስርዓት ባለው መልኩ መስራትና እንደ ፉካ ያሉ ሌሎች አማራጮችንም ማማተር ይጠበቃል ሲሉ ጠቁመዋል።
ትልልቅ ሀውልቶችን ከማስቀመጥ ይልቅም የመቃብር ቦታዎችን ለአረንጓዴ መናፈሻነት በማዘጋጀት ለንባብና ለጸጥታ ግዜ ቦታውን ለመጠቀም አሰራር መዘርጋት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በተፋሰስና አረንጓዴ አካባቢዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ የተቀናጀ የዘላቂ ማረፊያ ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አጃኢብ ኩምሳ በበኩላቸው በእምነት ተቋማት እስከ ዘጠና ሺህ የሚደርስ ክፍያ እንደሚጠየቅ በመግለጽ ተገቢ አለመሆኑንና ነዋሪውን ለምሬት እየዳረገ መሆኑንም ይናገራሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ በከተማዋ በመንግሥትና በሀይማኖት ተቋማት የሚተዳደሩ ሁለት አይነት የዘላቂ ማረፊያዎች አሉ። በመንግሥት ስር ያሉት ወጥ የዋጋ ተመን የወጣላቸው ቢሆንም በሀይማኖት ተቋማት ስር ያሉት ግን ክፍያውን የሚተምኑት ራሳቸው በመሆናቸው በአንዳንድ ቦታዎች እጅግ የተጋነነ ዋጋ ስለሚጠይቁ ህብረተሰቡ እየተማረረ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት በመንግሥት በኩል ከቂርቆስና ልደታ ውጪ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለሁሉም እምነት ተከታይ የሚያገለግሉ አስራ አምስት ዘላቂ ማረፊያዎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በነዚህ ማረፊያዎች የመሬት አቅርቦት በነጻ ቢሆንም ኮሚሽኑ ባስቀመጠው መሰረት ለመደበኛ (ቤተሰብ ላላቸው) ለቀብር አገልግሎት (ለቁፋሮ፤ አሸዋ፤ ሲሚንቶና ድንጋይ) ዝቅተኛው 370 ከፍተኛው ደግሞ 2 ሺ 125 እንዲከፍሉ ይደረጋል ብለዋል።
ለባይተዋር (ቤተሰብ ለሌለው) ደግሞ ሙሉ ወጪው በመንግሥት ተሸፍኖ ቀብር እንደሚፈጸም ጠቁመዋል። ከዚህ ውጪ በሀይማኖት ተቋማት ስር ሰማኒያ የሚደርሱ ዘላቂ ማረፊያዎች ቢኖሩም የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን ተናግረዋል።
በአንድ በኩል ለዘላቂ ማረፊያ የተሰጡ ቦታዎች ለህንጻ ግንባታና ሌሎች የንግድ አገልግሎቶች እየዋሉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለመቃብር አገልግሎት የሚሰጡትም ቢሆኑ የተጋነነ ዋጋ እየተጠራባቸው ተገልጋዮች ለኮንዶሚንየም ያስቀመጡትን ብር እስከመክፈል የደረሱበት አጋጣሚ መኖሩን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ አንዳንዶችም አስክሬን አስጭነው ከአዲስ አበባ ውጪ ሄደው ለመቅበር ተገደዋል። ኤጀንሲው እነዚህንም የመቆጣጠር ኃላፊነት ቢኖርበትም ይህን አድርጉ ለማለት የሚያስችል የህግ መሰረት አልተቀመጠለትም። በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ኤጀንሲው የማልማቱንና የማስተዳደሩን ኃላፊነት እየሰራ ሲሆን ከባይተዋር ጋር በተያያዘ ደግሞ የሚሰራው የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ነው።
በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍ የዘላቂ ማረፊያዎችን በወጥነት ሙሉ ለሙሉ የሚያስተዳድርና ከእምነት ተቋማትም ጋር አብሮ የሚሰራና የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ አንድ ተቋም ማቋቋም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ጥር 15/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ