– በታማሚዎች ላይ የሚደርሰው መድሎና መገለል አሁንም አልቀረም
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ በየዓመቱ በስጋ ደዌ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከ30 ሺህ ወደ አራት ሺህ ዝቅ ማለቱን የስጋ ደዌ ብሄራዊ ማህበር አስታወቀ። በስጋ ደዌ ታማሚዎች የሚደርሰው መድሎና መገለል አሁንም እንዳልቀር የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
የኢትዮጵያ ስጋ ደዌ ተጠያቂዎች ብሄራዊ ማህበር ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ታደሰ 21ኛውን የዓለም የስጋ ደዌ ቀንን በማስመልከት ትላንት በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በፊት በዓመት በአማካይ ከ25 ሺህ እስከ 30ሺህ ሰዎች በስጋ ደዌ በሽታ ይጠቃሉ። በየጊዜው ቁጥሩ እየቀነሰ መጥቶ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ሦስት ሺህ 700 እስከ አራት ሺህ ድረስ ዝቅ ብሏል።
በስጋ ደዌ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም አዳዲስ ሰዎች በበሽታው እንዳይያዙ ብዙ ሥራ ይጠይቃል ያሉት አቶ ተስፋዬ ከስጋ ደዌ ነጻ የሆነ ማህበረሰብ ለመፍጠር በህብረተሰቡ ዘንድ በሽታው በህክምና ሊድን የሚችል መሆኑን በማስገንዘብ ረገድ በትጋት ልንሠራ ይገባል ብለዋል።
በሽታው ከሚያደርሰው ጉዳት ባሻገር ህብረተሰቡ በታማሚዎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖና የስነ ልቦና ጫና ከባድ መሆኑን የገለጹት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው፤ በሽታው ከእግዚአብሄር ቁጣ የመጣና ታክሞ የማይድን ሳይሆን በቀላሉ የሚድን መሆኑ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም አሁንም ሙሉ ለሙሉ አልቀረም ብለዋል።
መንግሥት ለስጋ ደዌ ተጠቂ አካል ጉዳተኞች መብትና ጥቅም መከበር ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ስራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ አመልክተው በተለይ በተሳሳተ አመለካከት ሳቢያ በተጠቂዎች ላይ የሚደርሰውን አድሎና መገለል ለማስቀረት በተከታታይ በህብረተሰቡ ዘንድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በስጋ ደዌ የተጠቁ ወገኖችም በአዲስ አበባ ከተማ ዘነበ ወርቅ፣ሻሸመኔ ደግሞ ኩየራ ተብሎ በሚጠሩ ሰፈሮች ተለይተው ይኖሩ እንደነበር የመገለልና የአድሎ ማሳያዎች እንደሆኑ ተገልጿል።
የዓለም ስጋ ደዌ ቀን በኢትዮጵያ ለ21ኛ ጊዜ በብሄራዊ ደረጃ “በዕውቀትና በፍቅር ላይ የተመሰረተ ሁለንተናዊ አገልግሎት በመስጠት ከስጋ ደዌ ነጻ የሆነ ማህበረሰብ እንፍጠር” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች በመጪዎቹ ቅዳሜና እሁድ እንደሚከበር ታውቋል።
አዲስ ዘመን ጥር 15/2012
ጌትነት ምህረቴ