አዲስ አበባ፡- የአፍሪካን ፈጣን ለውጥ እና ዕድገት ለማረጋገጥ ለአህጉሪቱ ወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ በትኩረት መረባረብ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳስበዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች፣ትላልቅ የዓለም አቀፍ ኩባንያ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ባሉበት በሲውዘርላንድ ዳቮስ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ የዕድገት ፕላትፎርም የምክክር መድረክ ላይ እንደተናገሩት፣ ለአህጉሪቱ ፈጣን ዕድገት በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች በየዓመቱ የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው መንግሥት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣እየተከናወኑ ያሉ መልካም ተሞክሮዎችንም ለተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።
በቀጣይ የአፍሪካ የዕድገት ፕላትፎርም ከተቀመጠለት የጊዜ ወሰን አኳያ ሃገራት ስኬታማ ልምዶችን እና ውጤታማ ተሞክሮዎችን የሚጋሩበት መድረክ ሊፈጠር እንደሚገባም አስታውቀዋል።
የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም የአፍሪካ ምዕራፍ እ.ኤ.አ በመጪው መስከረም 2020 አዲስ አበባ እንደሚካሄድ የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለተሻለ ልምድ ልውውጥ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በአፍሪካ ዕድገት ማዕቀፍ ውስጥ እ.ኤ.አ 2025 ዓ.ም በዋናነት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያጎለብት ፕላትፎርም መቋቋሙ መጠቆሙን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የፌስቡክ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አዲስዘመን ጥር 14/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር