የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የ2012 የምርጫ ማስፈጸሚያ የጊዜ ሰሌዳን ለውይይት ይፋ አድርጓል፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የመጀመሪያ ዙር ውይይት አድርገውበታል። በዚሁ ውይይታቸውም ዘርዝረው ባቀረቧቸው ምክንያቶች የተነሳ የጊዜ ሰሌዳውን የደገፉም የተቃወሙም ፓርቲዎች መኖራቸው ግልጽ ሆኗል።
አቶ በቀለ ገርባ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ቦርዱ ይፋ ካደረገው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ በአንዳንዶቹ ሀሳቦች አይስማሙም።
“የምርጫው ጊዜ ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ይሆናል” የሚለው የጊዜ ሰሌዳ በአቶ በቀለና ፓርቲያቸው ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ምክንያቶቻቸውም ዘርዘር ያሉ ናቸው። በዋናነትም አቶ በቀለ የሚያነሱት፤ ወቅቱ ክረምቱ ጠንከር የሚልበት በመሆኑ ወንዞች የሚሞሉበትና ለመንቀሳቀስ የሚያስቸግር ይሆናል የሚለውን ነው።
መደበኛ ተማሪዎች በእረፍት ላይ የሚሆኑበት፣ በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድምጽ ለመስጠት መመዝገብ የሚችሉት በየትምህርት ተቋማቸው ሆኖ ሳለ፤ በድምጽ መስጫው ወቅት በትምህርት ቤት ውስጥ አለመሆናቸው ድምጽ የማይሰጡበት እክል ይፈጠራል የሚልም ስጋት አላቸው።
በተጨማሪም፤ የትምህርት ተቋማቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የክረምት ትምህርት ተከታታዮቻቸውን የሚያስተምሩበትና መምህራንም በተመሳሳይ ስልጠና የሚወስዱበት ጊዜ በመሆኑ የተጠቀሰው ጊዜ ተመራጭ አይደለም ባይ ናቸው።
አቶ በቀለ ምርጫው በተባለው ቀን ይካሄድ ቢባል እንኳን ያሸነፈው ፓርቲ የስልጣን ርክክብ ለማድረግም በቂ ጊዜ ይኖረዋል የሚል እምነት የላቸውም። ምክንያቱም የስልጣን ማስረከቢያ ወቅት ተብሎ በህገመንግሥቱ ላይ ከተቀመጠው ጋር ይጋጫል ብለው ያምናሉና ነው።
የታዛቢዎች ስም ዝርዝር የማስረከቢያ ጊዜም ከአንድ ቀን በላይ መሆኑ ሌላው ስጋታቸው ነው፤ የአቶ በቀለ። ከዚህ ቀደም በተካሄደው ምርጫ ፓርቲያቸው ስም ዝርዝራቸው ቀድሞ በመላኩ ታዛቢዎቹን በገንዘብ የመደለል፣ አንዳንዶችንም በማስፈራራት፣ በመደብደብና የተለያዩ ተጽዕኖዎችን በማድረስ በብዙ ቦታዎች የፓርቲው ታዛቢዎች እንዳይገኙ መደረጉን ያስታውሳሉ። ያለፈ ታሪክ እንዳይደገም ምርጫው ከመካሄዱ 24 ሰአት በፊት ቢከናወን ስጋቱን ይቀንሳል የሚል አማራጭም አላቸው።
አቶ በቀለ ድምጽ የሚሰጥበትና የምረጡኝ ዘመቻ የሚከናወንበት ጊዜ መራራቁም ችግር አለው ይላሉ። ፓርቲያቸውም ይህንንና መሰል ክፍተት ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ጉዳዮች በመለየት የጊዜ ሰሌዳው ከመጽደቁ በፊት በተወካዩ አማካኝነት ለቦርዱ ለማሳየት እየሞከረ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ አቶ በቀለ ማብራሪያም፤ ክፍተቶቹ ከተስተካከሉ ፓርቲያቸው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳውን አክብሮ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ነው። በድርድር፣ በውይይትና በክርክር ላይ የተመሰረቱ ሂደቶች ሁሉ በፓርቲያቸው ዘንድ ተቀባይነት አለው። ሁሉም የሚደሰትበት ባይሆንም አብዛኛው የሚስማማበት ቅድመ ምርጫ ዝግጅትና ተአማኒ ምርጫ እንዲካሄድም የፓርቲያቸው ፍላጎት ነው።
ከአቶ በቀለ በተቃራኒው ፓርቲያቸው የምርጫውን የጊዜ ሰሌዳ በፀጋ መቀበሉን የሚናገሩት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ናቸው። ፓርቲያቸው ለውይይት ይፋ ከሆነው የጊዜ ሰሌዳ ጋር የሚጣጣም እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል ይላሉ።
እንደ አቶ በቀለ ያሉ የፓርቲ አመራሮች የሚያነሷቸው “ምርጫው በክረምት መካሄዱ ምቹ አይሆንም” የሚሉት ስጋቶችን በተመለከተም አቶ ናትናኤል፤ “ችግሩ ለኢዜማ ብቻ እንዳልሆነ በመገንዘብ የጋራ ነው ብሎ ተቀብሎታል” የሚል አቋም አላቸው።
ምርጫው ፍትሀዊ፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ለሁሉም እኩል በወጣ ህግ፣ መመሪያና ደንብ እንዲሁም ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም በፈረሙት የቃልኪዳን ሰነድ መገዛት የግድ ነው የሚሉት አቶ ናትናኤል፤ ፓርቲያቸው ለዚህ ዝግጁ መሆኑንና ለአባላቱና ለደጋፊዎቹም ይህንኑ እያስገነዘበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ዶክተር የሺጥላ ወንድሜነህ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የተረጋጋ የፖለቲካ ሽግግር እንዲኖርና ህዝቡም በመረጠው እንዲተዳደር ከተፈለገ የሰከነ አካሄድ ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ሁሉንም ያማከለ ሊሆን ይገባል ባይ ናቸው። ፓርቲዎች እያነሷቸው ያሉ የክረምት ወቅት ስጋቶች አሳማኝ በመሆናቸው፤ በድህረ ምርጫው ላይ “እንዲህ ብለን ነበር” የሚሉ መከራከሪያዎች እንዳያስነሱ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ነው የሚሉት።
ዶክተር የሺጥላ፤ ምርጫው የማይቀር ከሆነ ነሐሴ ወር መጨረሻ ወይንም በጳጉሜን ቢካሄድ የሚል አማራጭ አላቸው። ይህ ካልሆነም ይላሉ መምህሩ፤ የሁሉም ወገን ድምጽ የተሰማበትና የአብዛኛው ባለድርሻ አካላት ይሁንታን ካገኘ ምርጫውን ማራዘም ይበጃል የሚል ምክረ ሀሳብም ይሰጣሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 14/2012
ለምለም መንግሥቱ
Веном 3: Последний танец (фильм 2024) смотреть Онлайн Бесплатно в Хорошем Качестве 1080 HD на Русском Языке веном 3 часть смотреть онлайн Веном 3: дата выхода фильма когда выйдет в России