በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ብርቅነሽ ገመቹ በሰው ቤት ልብስ በማጠብ በሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ሶስት ልጆችን ያለ አባት ያሳድጋሉ። በዚሁ መልኩ በሚያገኙት ገቢ ልጆችን ያስተምራሉ፤ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውንም በዚሁ ሁኔታ በሚያገኙዋት ጥቂት ገንዘብ ያሟላሉ። ከሶስቱ ልጆች አንዱ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፣ ሁለቱ የ10ኛና የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው።
ልጆቻቸውን ያለ አባት ማሳደግ፣ ማስተማርና መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት እጅግ ከባድ እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ ብርቅነሽ፤ አብዛኛውን ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት ለሚሄዱ ልጆቻቸው ቁርስ አዘጋጅተው ምሳ መቋጠር ቢችሉም፤ አንዳንድ ጊዜ ከአቅማቸው በላይ ስለሚሆንባቸው ለአንዱ ወይም ለሁለቱ ቋጥረው ለሌሎቹ ምሳ ሳይቋጥሩላቸው ትምህርት ቤት ውለው ለመመለስ፤ ቁርስ ሳይበሉ ትምህርት ሄደው ምሳም ሳይበሉ እስከ 10 ሰዓት ለመቆየት ይገደዱ ነበር።
ወይዘሮ ብርቅነሽ እንደሚሉት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ልጃቸው ከቅርብ ወራት ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንግስት ትምህርት ቤቶች የጀመረው የምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል።
ይህም ጫና እንደቀ ነሰላቸው ይናገራሉ። ለሶስት ልጆች ይቋጥሩ የነበረውን አነስተኛ ምሳ ለሁለቱ ልጆች በመቋጠር ሁለቱ ልጆቹ በቂ ምግብ እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።
ከምገባ በተጨማሪ መንግስት የደንብ ልብስ ለተማሪዎች ማቅረቡ ብዙ ጫና እንደቀነሰላቸው ይናገራሉ። ለዩኒፎርም ያወጡት የነበረውን ብር ለሌሎች ነገሮች ለማዋል እንደቻሉም ያብራራሉ።
የከተማ አስተዳደሩ ለ300 ሺህ ተማሪዎች የምገባ እና ለ600 ሺህ ያህሉ ተማሪዎች ደግሞ ዩኒፎርም እና የመማሪያ ቁሳቁስ ማቅረቡ እንዲሁም የከተማ ነዋሪዎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸው ሌሎች ፕሮጀክቶች እንደ ወይዘሮ ብርቅነሽ ገመቹ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎችን አስደስቷል።
በአዲስ አበባ በልደታ ክፍለ ከተማ ጎላ ሚካኤል አካባቢ ነዋሪ መምህር ተፈራ ማሞ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ገደማ ከክልል መጥተው በጥቁር አንበሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደ አዲስ መምህር ሲቀጠሩ ያጋጠማቸውን ነገር እንዲህ ያስታውሳሉ፤ “እያስተማርኩ ተማሪዎች እያስፈቀዱ ተራ በተራ ወደ ውጭ ይወጣሉ።
ምን ሆናችሁ ነው ብዬ ስጠይቃቸው ሊነግሩኝ ፈቃደኛ አልነበሩም። የተማሪዎቹ ሁኔታ ግራ ቢገባኝ ወደ ውጭ የሚወጡ ተማሪዎችን ተከትዬ ወደዬት እንደሚሄዱ ማየት ጀመርኩ።
አንዱን ተማሪ ተከታትዬ ስሄድ እየሮጠ ሄዶ ከቧንቧ ውሃ ሲጠጣ አየሁትና ለምን በእረፍት ሰዓት አትጠጣም ብዬ ጠየቅኩት። ቁርሱን ሳይበላ ስለሚመጣ ጨጓራውን ሲያቃጥለው ለማስታገስ ውሃ ለመጠጣት እንደወጣ ነገረኝ” ይላሉ።
አንዳንድ ተማሪዎችን ቀርበው የማናገር ልምድ እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ተፈራ፤ ምሳና ቁርስ ሳይበሉ ውለው ራት ብቻ በልተው ትምህርት ቤት እንደሚመጡ የነገሯቸው ተማሪዎች እንደነበሩም ያስታውሳሉ። በዚህም ምክንያት በርካቶች በትምህርት ገበታ ላይ ሆነው ራሳቸውን ስተው ሲወድቁ እንደነበር ያነሳሉ።
አንዱ ተማሪ ምግብ ቋጥሮ ሲመጣ ሌሎቹ ቋጥረው ስለማይመጡ ስነልቦናዊ ጫናውም እጅግ ከፍተኛ እንደነበር የሚያነሱት አቶ ተፈራ፤ በነበረው ችግር ምክንያት መጠን ማቋረጥና መድገም እጅግ ከፍተኛ እንደነበር ያስታውሳሉ።
እንደ አቶ ተፈራ ማብራሪያ፤ የከተማ አስተዳደሩ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ያደረገው የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም የመመገብ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች በሙሉ የሚመገቡበት ሁኔታ በመፈጠሩ በምግብ እጥረት ተማሪዎች ላይ ይደርስ የነበረውን ጉዳት፣ የስነ ልቦና ጫና እንዲሁም የወላጆችን ጭንቀት አስቀርቷል። በዚህም ምክንያት በትምህርት ቤቶች ይታይ የነበረው የማርፈድ፣ የማቋረጥና የመድገም ምጣኔ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ ዘጠኝ ነዋሪው ወጣት አወቀ ተስፋ እንደሚለው፤ የከተማ አስተዳደሩ የጀመራቸው አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች የተለየ ትርጉም ያላቸው ናቸው።
የትምህርት ቤት ምገባና፣ የተማሪዎች የደንብ ልብስ ማቅረብ፣ የዳቦ ፋብሪካ ግንባታ፣ ለዘመናት ሳይታደሱ የቆዩ ትምህርት ቤቶችን የማደስ፣ ሳይጠናቀቁ የቆዩ የወጣቶች ማዕከላትን በማጠናቀቅ ወደ ስራ ለማስገባት መንግስት እያደረገ ያለው ጥረት ለከተማዋ ነዋሪዎች ትልቅ ጠቃሜታ ያላቸው ናቸው።
በተለይም ተገንብተው ሳይጠናቀቁ ግማሽ ደርሰው የቆሙ የወጣት ማዕከላትን አጠናቆ ወደ ስራ በማስገባት እና አዳዲስ የወጣት ማዕከላትን በመገንባት ረገድ አስተዳደሩ እየወሰደ ያለው እርምጃ የሚደነቅ ነው። ለአብነት ያህል አራት ኪሎ አካባቢ ለብዙ ዘመን የወጣት ማዕከል አልባ ሆኖ ቆይቷል።
በተያዘው ዓመት የከተማ አስተዳደሩ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባባር አካባቢውን የወጣት ማዕከል ባለቤት ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ነው። የወጣት ማዕከሉ ለወጣቶች ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው። የማዕከላቱ መጠናቀቅ መልካም ሰብዕና ያለው ወጣት ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት እገዛ እንደሚኖረው ጠቁሟል።
አቶ አወቀ አክሎም እንደገለጸው፤ ለ100 ዓመታት ገደማ ሳይታደሱ ፈራርሰውና ተጎሳቁለው የነበሩ ትምህርት ቤቶች ጭምር ታድሰዋል። ትምህርት ቤቶችን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የማድረግ ስራም እንዲሁ ይበል የሚያሰኝ ነው።
የከተማ አስተዳደሩ የጀመራቸው ፕሮጀክቶች በከተማዋ ነዋሪዎች መካከል የነበረው የኑሮ ልዩነት ለማጥበብ፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ለማስፈን እንዲሁም የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ወጣት አወቀ አብራርቷል።
በከተማዋ በተለምዶ ፈረንሳይ ለጋ ሲዮን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ህይወት ደረጀ በበኩላቸው እንደሚሉት የከተማ አስተዳደሩ ያተኮረ ባቸው ዘርፎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎችን በተጨባጭ ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ እና የሚችል በመሆኑ ሊበረታታና ሊደገፍ የሚገባ ነው። በተለይም በመገንባት ላይ ያለው የዳቦ ፋብሪካ መገንባት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ ያለውን የዳቦ ዋጋ በማረጋጋት የኑሮ ውድነትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳላቸው አብራርተዋል።
አንዳንድ ፕሮጀክቶች ፍትሃዊ ተጠቃ ሚነትን ከማረጋገጥ ባሻገር የስራ እድልም በመፍጠር የስራ አጥነትን የመቀነስ አቅም ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ ወይዘሮ ህይወት ማብራሪያ እነዚህ ፕሮጀክቶች የብዙሃኖችን ተጠቃሚነት ማዕ ከል ያደረጉ ናቸው። ለጥቂቶች ብልጽ ግናን ለብዙሃኑ ጉስቁልናን የሚያመጡ አይደሉም። ሁሉም አብሮ እንዲያድግ የሚያደርጉ ናቸው።
ወደ ስራ የገቡት ቀጣይነት እንዲኖራቸው፣ ያልተጠናቀቁትም ተጠናቀው ወደ ስራ እንዲገቡ ባለሃብቱ እና መላው ህብረተሰብ እንደራሱ ፕሮጀክት ሊመለከታቸው ይገባል። ለመንግስት ብቻ ከመተው ይልቅ ሁሉም ባለው አቅም ሊደግፍ ይገባል። ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ እውቀት ያለውም በእውቀቱ እየደገፈ ቀጣይነታቸውን ሊያረጋግጥ ይገባል።
ፕሮጀክቶቹን በጥርጣሬ ከማየትና የተለ ያዩ ትርጉም ከመስጠት ይልቅ መንግስት ፕሮጀክቶቹን በሚያስፈጽምበት ወቅት የሚስተዋሉ ድክመቶች እንዲታረሙ አቅ ጣጫ በማመላከት፤ መልካም ጅማሮዎች እንዲቀጥሉ በማድረግ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲሉም ያሳስባሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 14/2012
መላኩ ኤሮሴ