አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ ከክፍያ መንገዶችና ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች ከ192 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ። በክፍያ መንገዶች ላይ የሚደርሰው የትራፊክ የሞት አደጋ 50 በመቶ መቀነሱም ተጠቁሟል።
በኢንተርፕራይዙ የኮሙዩኒኬሽንና ማርኬቲንግ ቡድን መሪ ወይዘሮ ዘሀራ ሙሀመድ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ኢንተርፕራይዙ በተያዘው በጀት ዓመት ገቢውን ለማሳደግ አስር ስትራቴጂካዊ ግቦችን እንዲሁም ዘጠኝ የማስፈጸሚያ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ወደ ተግባር በመግባቱ፤ በስድስት ወራት ውስጥ ከክፍያ መንገዶችና ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች ከ192 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል።
ቡድን መሪዋ እንዳብራሩት፤ በተያዘው በጀት ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ – አዳማ እና በድሬዳዋ – ደወሌ የክፍያ መንገዶች በድምሩ አራት ሚሊዮን 532 ሺ 197 የትራፊክ ፍሰት የተስተናገደ ሲሆን፤ በዚህም ከክፍያ መንገድ አገልግሎት 181 ሚሊዮን 728 ሺ 254 ብር ተሰብስቧል።
በተጨማሪም ከልዩ ልዩ ገቢዎች (ከማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይ፣ ከተሽከርካሪ ማንሺያና መጎተቻ ወ.ዘ.ተ….) 10 ሚሊዮን 284 ሺ 984 ብር በመሰብሰብ በአጠቃላይ በ 2012 በጀት አመት የመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት 192 ሚሊዮን 13ሺ 238 ብር መሰብሰብ መቻሉን ወይዘሮ ዘሃራ ተናግረዋል።
ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት ግንዛቤ በመፍጠር፤ በመንገዱ ክልል ውስጥ የ24 ሰዓት የመንገድ ላይ ቅኝታዊ ቁጥጥር በማድረግ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ
ወቅት ጋር ሲነጻጸር በትራፊክ አደጋ የሚደርስ የሞት አደጋ 50 በመቶ መቀነስ መቻሉን ወይዘሮ ዘሃራ ጠቁመው፤ በዚህም አምና በተመሳሳይ ወቅት በአዲስ አበባ – አዳማ የክፍያ መንገድ 12 የሞት የትራፊክ አደጋ ያጋጠመ ሲሆን፤ ዘንድሮ ወደ ስድስት ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል።
የጥገና አቅምን በማሳደግ በሁለቱም አቅጣጫ ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ መስመሮችን ቀለም በመቀባት እንዲሁም በአገልግሎት እድሜ ማብቃት እና በአደጋ ምክንያት በመንገድ ንብረቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በመጠገን የመንገዱ ምቾት እና ደህንነት እንዳይጓደል የማድረግ ስራ መሰራቱን የሚናገሩት ቡድን መሪዋ፤ ኢንተርፕራይዙ በቴክኖሎጂ በመደገፍ የአገልግሎት አሰጣጡን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
በዚህም የስራ ቦታን ምቹ የማድረግ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ሰራተኞች በተሻለ የስራ አካባቢ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ተደርጓል። የመረጃ ቋት አቅም ማሳደግ፣ የመረጃ አስተዳደር ስርዓት ትግበራ፣ የመንገድ ላይ መብራት ማስፋፊያ ዝርጋታ ፕሮጀክቶች መከናወኑንም ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገር ኢንተርፕራይዙ በአዲስ አበባ – አዳማ እና ድሬዳዋ – ደወሌ የክፍያ መንገዶችን ያልተቋረጠ የ24 ሰዓት የክፍያ መንገድ አገልግሎት በየቀኑ መስጠቱ፤ በኢንተርፕራይዙ የመንገድ አካፋይ ላይ የሚገኙ ንብረቶችን በወቅቱ መጠገኑ፤ 27ሺ ችግኞችን በመትከል እና 85 በመቶ በላይ የሚሆኑትን በማጽደቅ በመሳሰሉት ፕሮጀክቶች ላይ ኢንተርፕራይዙ ጠንካራ አፈጻጸም ያስመዘገበ ሲሆን፤ በድሬዳዋ – ደወሌ የክፍያ መንገድ ላይ ያለው የክብደት ቁጥጥር አስተማማኝ ባለመሆኑ፤ ከክብደት በላይ ጭነው የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች በመንገዱ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ቡድን መሪዋ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 14/2012
ሰሎሞን በየነ