አዲስ አበባ፤- በኢትዮጵያ በቀጣዩ ምርጫ ታዛቢ ለማሰማራት ጉብኝት እያደረገ ያለው የአውሮፓ ህብረት የልዑካን ቡድን ኢትዮጵያ ለምርጫው ያደረገችው ማሻሻያና ዝግጅት መልካም መሆኑን አስታወቀ።
የልዑካን ቡድኑ ትናንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝቶ ስለምርጫውና ስለተደረጉ የህግ ማሻሻያዎችና ዝግጅት በምክትል አፈጉባዔ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለና በውጭ ግንኙነትና በሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ዳባና በቋሚ ኮሚቴው አባላት ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል። የልዑካን ቡድኑ የተደረገው የህግ ማሻሻያና እየተደረገ ያለው ዝግጅት መልካም መሆኑ ገልጸዋል።
ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ፤ በሰጡት ማብራሪያ፣ የምርጫ ቦርድ፣ የሲቪል ማህበረሰብ፣ የጸረ ሽብር እና ሌሎች አፋኝ የነበሩ ህጎች ተሻሽለዋል። ምርጫ ቦርድም እንደገና በገለልተኛ ሊቀመንበር፣ ምክትልና ሌሎች አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲደራጅ ተደርጓል። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የእንባ ጠባቂና ሌሎች የዲሞክራሲ ተቋማት በገለልተኛነት እንዲደራጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አዋጆቹን ማውጣትና ተቋማቱን ማደራጀት ብቻ ሳይሆንም በአዋጆቹ ማውጣት ሂደት የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማትና ህዝብ ተሳትፎ አድርገዋል። የምርጫ ህግን ከአስፈፃሚው ገለልተኛ በሆነ መንገድ ለማውጣት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሳይወያይበት በቀጥታ ለምክር ቤቱ በመምራት ምክር ቤቱ ከፍተኛ ክርክር በማድረግ አጽድቋል።
የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር አስተያየት እንዲሰጡባቸው ተደርገው ተሾመዋል። የምርጫ ቦርድ በጀትም በቀጥታ ለምክር ቤቱ ቀርቦ አምስት ሳንቲም ሳይቀነስ ጸድቋል። በአጠቃላይ የዴሞክራሲ ተቋማትና ኃላፊዎች በገለልተኛነት ተደራጅተዋል ብለዋል።
ምክትል አፈጉባዔዋ፤ በአገሪቱ የጠበበው የፖለቲካ ምህዳር ሰፍቷል። በሀሳብ ጫፍና ጫፍ የያዙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መወያያት ጀምረዋል። በርካታ መገናኛ ብዙሃንም የተለያዩ ሀሳቦች እያንሸራሸሩ ዜጎች በነጻነት ሀሳባቸውን እየተወያዩ ነው።
በአንዳንድ ቦታዎች የሚታዩ የሰላም ችግሮች አልፎ አልፎ ቢታዩም ሁሉም በተፈጠረው ምህዳር ምርጫ ለማካሄድ ፍላጎት አለው። ሰላማዊ ምርጫም እንደሚካሄድ ተስፋ አለኝ። በዚህም የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች አካላት በመገኘት ታሪካዊን ምርጫ እንዲታዘብ እንጋብዛለን ብለዋል።
በአገሪቱ ጠንካራና ገለልተኛ ቦርድ መቋቋምን ያነሱት አቶ ተስፋዬ፤ የምርጫ ህጉም ቢሆን ከአባላት ፊርማ ቁጥር ውጭ በሌሎች ጉዳዮች ላይ በሁሉም ፓርቲዎች በሚባል ደረጃ የተደገፈ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በጊዜ ሰሌዳው ላይ ከጸጥታና ከሌሎች ችግሮች አንፃር “ይራዘም አይራዘም” የሚል ክርክር ቢኖርም የአገሪቱ ህገ መንግስት ስለማይፈቅድ ምርጫውን ለማካሄድ መወሰኑንም አንስተዋል። በተዋረድ ያሉ ህጎችም የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፋ መሆኑም ገልጸዋል።
በአንዳንድ አካባቢ በተለይም በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል አልፎ አልፎ ካለው የጸጥታ ችግር ውጭ ምርጫ ለማካሄድ ጸጥታ አለ። በምዕራብ ያለውን መንግስት እርምጃ እየወሰደ ነው። ለምርጫው የመከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የደህንነትና የክልል የጸጥታ መዋቅር ምርጫውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑም ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።
የልዑካን ቡድኑ በተሰጠው ማብራሪያ መልካም መሆኑን ገልጾ በቀጣይ በሚደረገው ምርጫ የአውሮፓ ህብረት ተሳታፊ በቀጣይ እንደሚወስንና የሚሳተፍ ከሆነ ዝግጅት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በአውሮፓ ህብረት በአፍሪካ የምስራቅ አፍሪካ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ዲስክ ኦፊስ ሚስተር ሎክ ዲፋይ፤ በቀጣይ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ምርጫ ለመታዘብ የሚመለከታቸው ተቋማትና ግለሰቦች ጋር ውይይት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። እስካሁን ባለው ሁኔታ መልካም ነገሮች መኖራቸውን አንስተው ከአነጋገሯቸው አካላት መካከልም፣ የጸጥታ፣ ስለምርጫው ግንዛቤ መፍጠርና የጥላቻ ንግግር ስጋታቸው መሆኑን እንደተገለጸላቸው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 13/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ