የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ እነሆ 9ኛ አመቱን ሊደፍን ጥቂት ቀናት ይቀራሉ። በነዚህ አመታትም በመሃል ባጋጠሙ ችግሮች ከተፈጠረው መጓተት ውጭ ግድቡ ለአፍታም ሳይቆም በሞቀ ህዝባዊ ድጋፍ ታጅቦ ቀጥሏል። እነሆ በአሁኑ ወቅትም ሃይል ማመንጨት የሚችልበት የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ እየደረሰ ይገኛል። በተለይ የግድቡ ሁለቱ ምዕራፎች በቅርቡ ሃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።
አባይ ለመላ ኢትዮጵያውያን የዘመናት የቁጭት መንስኤ ሆኖ ኖሯል:: አባይን በተመለከተ ለአመታት ሲሰሙ የነበሩ የቁዘማና የቁጭት ስነቃሎቻችንም የሚያሳዩት ይህንኑ የህዝቦች የቁጭት ስሜት ነው። አባይ ማደሪያ የለው፤ ግንድ ይዞ ይዞራል፤ የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው፤ ወዘተ።
እነሆ ይህ የቁጭት ምዕራፍ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ከተዘጋ በኋላ ግን መላው ኢትዮጵያዊ የታላቁ ህዳሴ ግድብ እውን ሆኖ የሚያይበትን ቀን እየናፈቀ ይገኛል። በግድቡ ግንባታ እውን መሆንም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በላቡ፣ በገንዘቡና በሃሳብ ጭምር ሲሳተፍ ቆይቷል።
በግንባታው ሂደት ላይ ከ15ሺህ በላይ ሰራተኞች መሳተፋቸው አንድ ማሳያ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ከሁለት ሺህ የሚበልጡ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ወጣቶች ተደራጅተው በደን ምንጣሮ ስራ ላይ ለመሰማራት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። ከዚህም ጎን ለጎን መላው ህብረተሰብ እስካለፈው አመት ድረስ ከ12 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ ለግድቡ ስኬታማነት የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል::
በሌላ በኩል ግድቡ ሲጠናቀቅ ለመላው ኢትዮጵያውያን ከሚኖረው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ይታመናል። በተለይ የተፋሰሱ አገራት አመቱን ሙሉ የተመጠነ ውሃ እንዲያገኙ በማድረግና ደለልን በመከላከል የሚያደርገው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም። ከዚህም ባሻገር ለአካባቢ ጥበቃ ስራ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። የጎረቤት አገራትም ከሚመነጨው ሃይል ተጠቃሚ ሊሆኑ ይሆናሉ።
ኢትዮጵያ እነዚህን የግድቡን ጠቀሜታዎች በመገንዘብም የተፋሰሱ አገራት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጭምር ስታሳስብ ቆይታለች። በዚህም መሰረት ሱዳን ይህንኑ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ በመረዳት ሃሳቡን በተደጋጋሚ ስትደግፍ ቆይታለች። በአንጻሩ ግብፅ ስራውን ለማደናቀፍ ተደጋጋሚ ጥረቶችን ስታደርግ መቆየቷ ለማንም ግልጽ ነው።
ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ የተካሄደውና ያለስምምነት የተጠናቀቀው የሶስትዮሽ ስብሰባም የዚሁ አካል ነበር። በዚህ የሶስትዮሽ ስብሰባ ግብጽ በውሃ አለቃቁ ላይ ያስቀመጠችው ከ14 እስከ 21 ዓመት የሚል ቀልድ አዘል ምክረ ሃሳብም የግድቡን ፍሬ ለሚጠብቁ ኢትዮጵያውያን ፈጽሞ የሚዋጥ አይደለም። ይልቁንም መላውን ኢትዮጵያዊ የሚያስከፋና የሁለቱን አገራት ወዳጅነት የሚያሻክር ነው።
ነገር ግን ይህንን ያለስምምነት የተጠናቀቀ ውይይት ተከትሎ ሶስቱ አገራት ወደአሜሪካ በማቅናት ባደረጉት ውይይት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። ይህ ደግሞ ሰላምን ብቸኛ አማራጭ አድርጋ እየተጋች ላለችው ኢትዮጵያ ትልቅ ዲፕሎማሲዊ ድል ነው። የግድቡን ፍሬ ለሚጠብቁ መላው ኢትዮጵያውያንም ትልቅ የምስራች ነው።
በርግጥ ኢትዮጵያ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታም ሆነ ለሌሎች የውስጥ የልማት ስራዎቿ የማንንም ይሁንታ አትሻም። ነገር ግን እንደማንኛውም አገር ለምታከናውናቸው የልማት ስራዎቿም ሆነ ለሌሎች የዲፕሎማሲ ስራዎቿ በትብብር የመስራት መርህን ትከተላለች። ከጎረቤትም ሆነ ከተፋሰሱ አገራት ጋር የምታደርጋቸው ስምምነቶች ሁሉ ሰላማዊና የሁሉንም ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እንዲሆኑም ትሻለች። ይህ ደግሞ ከማንም የሚሰጣት የቤት ስራ ሳይሆን ቀድማም የምትከተለው አቅጣጫ ነው። አሁን የጀመረችው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆንም በዚሁ አቅጣጫ የሚታይ ነው።
አሁን የተደረሰው ስምምነት ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ስታራምደው የነበረውን የጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚያበረታታና የሁሉንም ጥቅም የሚያስጠብቅ በመሆኑ ለግንባታው መፋጠን ያለው ፋይዳ የላቀ ነው። በመሆኑም ቀጣዩ የቤት ስራ ግድቡን ማጠናቀቅ ብቻ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ የመላው ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ወሳኝ ነው። በመሆኑም ትላንት እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን በሚል መርህ የተጀመረውና እስካሁን ደምቆ የቀጠለው ህዝባዊ ድጋፍ ዛሬም ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!
አዲስ ዘመን ጥር 8/2012