የጥምቀት በዓልን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓ.ም በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባሕር የተጠመቀበትን ዕለት የሚያስታውስ፤ ኤጲፋንያ በመባልም የሚታወቅ በዓል ነው። በዓሉን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፫ ቁ ፲፫-፲፯ ውስጥ መገለፁም እንዲሁ የሚታወቅ ነው።
በአገራችን ገዝፈው ከሚጠበቁትና ከሚከበሩት ክብረ በዓላት መካከል አንዱ ጥምቀት ነው። ይህ በየዓመቱ ጥር 11 የሚከበረው አውዳመት መሠረቱና ምክንያቱ ከላይ የተገለፀው ሲሆን በዓሉን ከሌሎች በተለይ እንዲታይ የሚያደርጉት በርካታ ተጓዳኝ ጉዳዮችም አሉ።
ከ2ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ መከበር የጀመረው ይህ ታላቅ በዓል በይዘቱም ሆነ በክዋኔው አንድም የመበረዝም ሆነ መከለስ እክል ሳያጋጥመው፤ ያለ ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊም ሆነ ታሪካዊ ዝንፈት እዚህ የደረሰ ሲሆን ይህም ረቡዕ ታኅሣሥ 1/2012 ዓ.ም በዩኔስኮ የማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ አስችሎታል።
በአገራችን፣ ጥር 10 ቀን፣ በከተራ፣ በገጠር ወራጅ ውሃ የሚከተርበት፣ ታቦታት ከየአቢያተ ክርስቲያናቱ በዓሉ ወደሚከበርበት ቦታ በምዕመናን ታጅበው በዘፈንና በሆታ የሚሄዱ ሲሆን የአዲስ አበባው ጃን ሜዳ እና የጎንደሩ የአከባበር ሥነ ሥርዓት ከሌሎች ላቅ ብለው የሚታዩ በዓላት ናቸው። ከዚህም ባሻገር በኦሮሚያ ክልል በጎባ ከተማ በዓሉ በድምቀት እንደሚከበር መረጃዎች ያሳያሉ። በዓሉ ባለው ሰፊ ተቀባይነትና እውቅና ምክንያት በዩኔስኮ ከመመዝገቡ አስቀድሞ የአፍሪካ በዓል ተደርጎ ይወሰድ የነበረ መሆኑ፤ “African Epiphany/የአፍሪካ ኤጲፋኒያ” በሚል የሚታወቅ መሆኑ በተለያዩ ጥናቶች ላይ ተገልጿል።
«ከፈረሱ አፍ» እንደሚባለው የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለመመዝገቡ ምክንያቶቹን ለማወቅ ወደ አዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ብቅ ብለን በቢሮው በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የቋሚ፣ ተንቀሳቃሽ እና የኢንታንጀብል ቅርስ ምዝገባና ቁጥጥር ቡድን ከፍተኛ ባለሙያ መምህር መክብብ ገብረማርያምን አግኝተናቸው እንደነገሩን የጥምቀት በዓል ከጥንት ጀምሮ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና ወንድማማችነት ተምሳሌት በመሆን እዚህ የደረሰ በዓል ነው። በዓሉ ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ እሴቱ ባሻገር ከእኛም አልፎ ጠቅላላ አፍሪካውያንን የመንፈስ ኩራት የሚያጎናፅፍ፤ የአገራችንን መልካም ገፅታ የሚገነባ፣ ቱባ ባህላችንን ለመላው ዓለም የሚያስተዋውቅ፣ ኢትዮጵያውያንን በአንድ የሚያስተሳስር ገመድ ወዘተ መሆኑ በዩኔስኮ ለመመዝገቡ ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች ናቸው።
መምህር መክብብ እንደነገሩን በዓሉ እነዚያን ሁሉ ክፍለ ዘመናት አልፎ ከነሙሉ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘቱ እዚህ የደረሰው በቀላሉ አይደለም። እዚህ እኛ ትውልድ ላይ ሊደርስ የቻለው የእናት አባቶቻችን ደምና አጥንት ተከፍሎበት ነው። «ስለዚህ» ይላሉ መምህር መክብብ «መጪው ትውልድ ሊንከባከበው፣ ሊያከብረው፣ ሊያስከብረውና እንዳይኑ ብሌን ሊጠብቀው ይገባል። ለዚህ ደግሞ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧልና ጥበቃውም ሆነ እንክብካቤው የጋራ ስለሆነ ችግር የለውም። ያም ሆኖ ግን ባለቤቶቹ እኛው ነን።»
ኢትዮጵያ ለዓለም ሕዝብ፣ ልማት እድገት፣ ሥልጣኔና ታሪክ ያበረከተችው ይህ የጥምቀት በዓል በዘርፉ ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት አንዱ ነው። ክብረ በዓሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ እሴት እንደሆነም ተደጋግሞ ይነገራል፤ በንግሱ ሥርዓት ላይም ያለው እውነታ የሚያሳየው ይሄንኑ ነው።
ምንም እንኳን የጥምቀት በዓል መነሻውና መሠረቱ ሃይማኖታዊ ቢሆንም ከዚህ ባልተነናነሰ ደረጃ ባህላዊና ማህበራዊ ገፅታዎችንና ክንውኖችንም በተጓዳኝ ያስተናግዳል። ከእነዚህም መካከል አንዱ የመተጫጫ አውድን የሚፈጥርና በዚያው ልክም ወጣት ሴቶች ከዕድሜ አቻዎቻቸው ወንዶች ጋር በአይን የሚጣጣሉበት፣ በእስክስታ የሚፎካከሩበት፣ በዳንስ የሚውረገረጉበት፣ ትከሻ ለትከሻ የሚጎሻሸሙበትና ከዚያም፤ ሄዶ ሄዶ ለጎጆ የሚበቁበት ዕድል የሚፈጠርበት ልዩ ዕለት መሆኑና ይህም እንደ ነውር ሳይሆን ምንም ዓይነት ከልካይ የሌለበትና የማህበረሰቡን «ፍቃድ» ያገኘ፤ እንዲያውም የሚጠበቅ መሆኑ ነው።
«ሎሚ ጣሉባት በደረቷ፣
የጌታ ልጅ ናት መሰረቷ»
«ሎሚ ውርወራ» አንዱ የበዓሉ አከባበር አካል የሆነበትና ደረት ላይ አነጣጥሮ «መጣል» በጀግንነት የሚያስወድስበት ዕለት ቢኖር ይሄው የጥምቀት በዓል ሲሆን፤ በተለይ በገጠሩ የአገራችን አካባቢዎች በበዓሉ ላይ በተጠነሰሰ የአይን ፍቅር ዘግየት ብሎና የልጅነትን አካባቢ አጥንቶ ሽማግሌ መላክ የተለመደ ሲሆን የብዙዎችም ትዳር ይህንኑ ሂደት ያለፈ ስለመሆኑ በወግ መሀል ሲነገር ይሰማል።
ከዚሁ ከሎሚ ውርወራ ጋር በተያያዘ የአዲስ አድማሱ ደረጀ «ከአሲድ፣ ከዱላ፣ ከጥፊ፣ ከቢላ፣ የተረፈ ገላ … በሎሚ ታክሞ፣ ጃንሜዳ ተበላ፤ …» የሚል የዮሐንስ ግጥም መኖሩን በአንድ ወቅት ፅፎት አንብበናል። (የግጥሙን ስላቅም ልብ ይሏል።)
ዮሐንስ (የምስኪኑን ተሜ ድምፅ ሆኖ) «ጥምቀትና ሎሚ» በሚል ርእስ «በስሟ ለማርያም ከደጅሽ ታድሜ፤ ቁራሽ ልማጸንሽ፣ ከበራፍሽ ቆሜ፤ ካየሁሽ ጀምሮ፣… ፍቅርሽ ሰቅዞኛል፣ ልብሽ ልቤ ገብቶ፤ ሐሳቤ ካንቺው ነው፣ ከደብሩ ሸፍቶ፤ ፍቀጅ እመቤቴ!… ሎሚ መግዣ የለኝ፣ ውርወራ አላውቅ ከቶ፣ ጥምቀት ብዬ፣ ልንካሽ በስክሪፕቶ …» ሲል መግጠሙንም ይሄው የደረጀ ጽሑፍ ይነግረናል።
ከሎሚ ውርወራና ፍቅር ምስረታ ጋር በተያያዘ ብዙ የተባለ፤ የተነገረ አለ። የጭራ ቀረሽ:-
«ሎሚ ብወረውር ደረቱን መታሁት፣
ምነው ኩላሊቱን ልቡን ባገኘሁት።»
የሚለው ዜማ የዚሁ በጥምቀት ወንዶች ለሴቶች ከሚወረውሩት «ሎሚ ውርወራ» ተግባር ተወስዶ በግልባጩ እንዲውል የተደረገ ግጥም ነው። አላማው አንድ ነውና የተደረገው ውሰት ምንም የሚጎረብጥ ነገር አይታይበትም።
በዓሉ በርካታ ክውን ጥበባትን የሚያስተናግድ ሲሆን በአርሞኒካ ከሚደንሰው አነስተኛ ቡድን ጀምሮ አስፋልቱን ከዳር እስከዳር፤ ሰፊ ርዝመትን በመሸፈን እስከሚደረገው ባህላዊ ጭፈራ ድረስ የሚስተዋሉበት ሲሆን፤ በተለይ በበዓሉ ላይ የተገኘው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የየራሱን አካባቢ ባህል – አለባበስ፣ ዜማና ጭፈራ – በማከናወን ለበዓሉ የሚሰጠው ድምቀት እንኳን ለሌላው ለራሳችንም ያጓጓል። ልዩነት ምን ያህል ውበት (ከወሬ ባለፈ) መሆኑን ለመረዳትም የሚሰጠው ዕድል ሰፊ ነው።
የጥምቀት በዓልን ለየት የሚያደርጉት እነዚህ ብቻም አይደሉም፤ በዓሉ እንደሌሎች ፋሲካና ገናን የመሳሰሉ አቻዎቹ ብዙም ወደ ምግብና መጠጥ ያደላ አለመሆኑም ከሌሎች ለየት የሚያደርገው ገፅታው ነው። እረዱልኝ አይልም፣ ዶሮና እንቁላል ኖረ አልኖረ ጉዳዩ አይደለም። በዓሉን ለማክበር የወጡ ታዳሚዎች በየመንገዱ በሚሰጥ ንፁህ ውሃ (ካጋጠመም ጠላ) እና የድፎ ዳቦ ቁርጥ ውሎ መግባት ከፋሲካው ሽንጥና ብርንዶ በላይ ሲረኩበት ማየት የበዓሉን ሌላኛውን ገፅታ ፍንትው አድርጎ ያሳያልና ዓለም በበዓሉ ቢደመም አይገርምም።
ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ ጎብኚዎች፣ የምርምር ሰዎች፣ ተጋባዥ እንግዶች፣ ዲፕሎማቶች፣ ጋዜጠኞች ወዘተ ሌላው ለበዓሉ ድምቀት ምክንያቶች ሲሆኑ ለእነሱም እዚህ መገኘት ምክንያቱ የበዓሉ ድምቀት መሆኑን በአድናቆት ሲገለፅ መስማት የተለመደ ነው። ዘንድሮም ይሄው ድምቀት ከእስከዛሬው በበለጠ ደምቆ ይውላል የሚለው በበርካቶች እየተጠበቀ ያለ ጉዳይ ነው። በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር «በዓሉን ለማክበር ከውጪ በርካታ እንግዶች ከውጪ እየመጡና ሆቴሎችን ቀድመው በመያዛቸው በአዲስ አበባ የመስተንግዶ እጥረት እንዳይኖር ከወዲሁ እየሰራሁ ነው» ማለቱን ተከትሎ የበዓሉን በድምቀት መከበር ከወዲሁ እያመላከተው ይገኛልና የተለመደው ኢትዮጵያዊ ጨዋነትም በዚያው ልክ ከፍ እንደሚል እየተነገረ ይገኛል። ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ!
መልካም በዓል።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 8/2012
ግርማ መንግሥቴ