የዛሬ እንግዳችን የተወለዱት በቀድሞ አሰብ አውራጃ በ1960 ዓ.ም ነው።የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሰብና በአዲስ አበባ ተከታትለዋል።በትምህርታቸውም በመቀጠል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቋንቋና በታሪክ ተቀብለዋል።የሁለተኛ ዲግሪያቸውንም በኢዱኬሽናል ሪሰርች ኤንድ ዴቨሎፕመንት በ2004 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል።ከዚሁ ዩኒቨርሲቲም በመካከለኛው ምስራቅ የጂኦፖለቲክስ ጥናት በ2009 በተጨማሪነት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
እንግዳችን በፖለቲካውም ዘርፍ የቆየ ልምድ አላቸው።በ1983 ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ህብረትን ከመሰረቱ ጥቂት ፖለቲከኞች አንዱ ናቸው።የአማራጭ ሃይሎች የተባለውንም ፓርቲ ከፖለቲካ አጋሮቻቸው ጋር በ1987 መስርተዋል።የመኢአድ፤የብርሃን ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፤የአንድነት ፓርቲዎች መስራችና አመራርም በመሆን አገልግለዋል።
ከ2007 ዓ.ም ጀምሮም የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀ መንበር በመሆን እስካሁን ድረስ ፓርቲውን በመምራት ላይ ይገኛሉ።እንዲሁም በቅርቡ በመቀሌ የተቋቋመው የፌደራሊስት ኃይሎች ፎረም ምክትል ሊቀ መንበር ሆነው አገልግለዋል።እኛም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የዛሬ እንግዳችን አድርገን አቶ ትዕግስቱ አወልን ይዘን ቀርበናል።መልካም ንባብ
አዲስ ዘመን፤- በነበሩበት ፓርቲ ለረጅም ጊዜ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ እናውቅዎታለን።ወደ ፌደራሊስት ኃይሎች እንዲቀላቀሉ ያደረገዎት ምክንያት ምንድን ነው? አቶ ትዕግስቱ አወል ፤-እንደሚታወቀው በተለይ ከ2010 አጋማሽ ጀምሮ በአገራችን ለውጥ በሚል ገዢው ፓርቲ ራሱን ተሃድሶ አደረግኩ በሚል በለውጥ ስም አዲስ አመራር መምረጡ ግልፅ ነው።ይህን ተከትሎ ከሪፎርም ጋር በተያያዘ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነበር።በአንድ በኩል ይህ እየሆነ እያለ በሌላ በኩል ደግሞ ገዢው ፓርቲ ውስጥ የተፈጠሩ የpower politics የምንለው ነገር በለውጥ እንቅስቃሴው ውስጥ የራሱ የሆኑ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ነበሩት።
በዚህ ረገድ በተለይ 2011 ክረምት አካባቢ አንደኛው የገዢ ፓርቲ አባል ድርጅት ህወሓት በጠራው ስብሰባ (እንደማንኛውም አገራችን አካል ነው) ድርጅቴን ወክዬ ሄጃለሁ።እኔም ብቻ ሳልሆን ሌሎችም አመራሮችም ጭምር ነው የሄዱት።በዚያ ጊዜ ሕብረ ፌደራሊዝምና ሕገ መንግሥቱን ማዳን የሚል ገዢ ሃሳብ ነበረ።የምሁራን አስተያየቶች ነበሩ፤ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል።
በዚህ ጊዜ ከሃያ በላይ የሚሆኑ ፓርቲዎች ተካፍለዋል ልክ እንደእኛ።በስብሰባው መቋጫ ላይ ይህን ነገር ለማስቀጠል ሌላ ፎረም ሌላ መድረክ የሚያዘጋጅ ቡድን እንዲቋቋም ከነበሩት ፓርቲዎች፣ ተወካዮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን ተውጣጥቶ አንድ ግብረ ኃይል ተቋቋመ።ያ ግብረ ኃይል ሁለተኛውን ሕዝባዊ መድረክ (አሁን በቅርቡ የተካሄደውን) በጥሩ ሁኔታ አዘጋጀ።ካዘጋጀ በኋላ እዚያም ላይ ካለፈው ቁጥር በተሻለ ወደ 50 የሚደርሱ ጥሪ ተደርጎላቸው ተገኝተዋል የሚል መረጃ ነው ያለው።በዚያ ውስጥም ፎረም መመስረት አለበት የሚል ሃሳብ ቀርቦ በፎረሙ ምስረታ ላይ የተገኘን በሙሉ ፎረሙን ለመመስረት አቋም ተያዘ።ይህ ፎረም ደግሞ የሽግግር ፎረም የሚል ስያሜ ተሰጠው።ፎረሙም የፌደራሊስት ሀይሎች ፎረም ተብሎ ነው የተመሰረተው።ስለዚህም በእኔ በኩል እንደማንኛውም ፓርቲ በጥሪ ነው መቀሌ የተገኘሁት።
አዲስ ዘመን ፦አንድ ፖለቲከኛ የሆነ ቦታ ከመሳተፉ ወይም ከመቀላቀሉ በፊት ቅድመ ትንታኔ ያስቀምጣል።በእነዚህ በእነዚህ ምክንያቶች በቦታው ላይ ብሳተፍ ለአገርም ፤እንደ ፓርቲም ትልቅ ስራ እሰራለሁ ብሎ ነው የሚገባው ።ስለዚህ መቀሌ ሄደው ለመሳተፍ ውሳኔ ላይ የደረሱት እንዴት ነው?
አቶ ትዕግስቱ ፦ የድርጅቴን ፕሮግራም ነው መተንተን የምችለው ድርጅቴ ፌደራል ነው፤ ፕሬዚደንሻል ነው። ፌደራል ሲባል ደግሞ ልዩነት የለንም፤ ነገር ግን በአከላለል በኩል እኛ ጂኦግራፊካሊ ነው የምንከተለው ሌላው ደግሞ የማንነት ወይም የብሔር አከላለል ሊከተል ይችላል።ይህ ግን ገና ያልለየለትና ትክክለኛው ፌደራሊዝምም ስላልተተገበረ የትኛው ይሻላል የሚለው አልታወቀም።የሄድነው በጥሪ ነው፤ በጥሪ ስንሄድ ደግሞ አላማው አሁን የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ የማዳን ጉዳይ ነው የሚል ነበር በእኛ በኩል የነበረው ግንዛቤ።ሆኖም ግን እንደጠበቅነው አልሆነም።
አዲስ ዘመን ፦ ችግሩ ምን ነበር?
አቶ ትዕግስቱ ፦ ችግሩማ በገዥው ፓርቲ መካከል የተፈጠረው ልዩነት ራሱ አሉታዊ ተጽዕኖ ነበረው።
አዲስ ዘመን ፦እንዴት ? ችግሮችን ቢያብራሩልን፤ ለምሳሌ ልትሰሩት ያሰባችሁትንና እንዳሰባችሁት ያልሆነበትን ምክንያት ቢያብራሩልኝ?
አቶ ትዕግስቱ ፦ የእኛ ሃሳብ በጋራ፤ በድርድር፤በመነጋገር፤ ነገሮችን መፍታት ነው። ምክንያቱም ፖለቲከኛ በንግግር የሚያምን በመሆኑ ውይይት የማይፈታው ችግር የለም ብለን እናምናለን።ስለዚህ ይህንን የሚያመቻች መድረክ ይሆናል ብለን ነበር ያሰብነው።ህውሃት ቢጠራንም የተሰባሰበውም የፖለቲካ ሀይል ከእነሱ ጋር ተግባብቶና ተስማምቶ የመስራት ዕድል ይኖረዋል ብለን ነው ወደ መቀሌ የሄድነው። ለምሳሌ የመጀመሪያው መድረክ ላይ ኦፌኮም ኦነግም ሰው ወክለዋል ፤ ግን ሰዎች የሚያውቋቸውን ሰዎች ባለማየታቸው ያልተሳተፉ ሊመስላቸው ይችላል። ሁለተኛው ፎረም ላይ ግን እነዚህ ሀይሎች አልተገኙም።
ስለዚህ እነዚህ ሁሉ የተሰባሰቡበት አንጋፋ ልምድ ያላቸው ሰዎች የሚመሩት ፓርቲ የተሳተፉበት መድረክ ላይ የሆነ የምትማረው የምትሰማው ነገር አለ።ይህም ቢሆን ግን ምንም አይነት ህጋዊ ጋብቻ ከእነዚህ ሰዎች ጋር አልተፈጸመም። ይህ ፎረም እንግዲህ ያንን ህጋዊውን መስመር የሚያዘጋጅ ስብስብ ነው ብለህ ነው የምትወስደው። ስለዚህ ስብስቡ ላይ ተሳትፈህ ሁኔታውን ታየዋለህ።ከዛ ደግሞ የራስህን የፖለቲካ መስመርና አካሄድ ከመጻኢው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አድል ጋር አገናዝበህ የምትወስናቸው ነገሮች ይኖራሉ። በግብዣ ብንሳተፍም ግብዣው ውጤት የሚኖረው ስንሳተፍ ነው በሚል አመራር ውስጥ ገብተን ስንንቀሳቀስ ቆይተናል።በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ጥሩ የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ አለመኖሩና ሌሎች አዝማሚያዎችም መታየታቸው ፎረሙን ለቀን እንድንወጣ አድርጎናል።
አዲስ ዘመን ፡- ፎረሙ ሲመሰረት ዓላማው ምንነበር?
አቶ ትዕግስቱ፡- ፎረሙ ይህ ነው የሚባል የስምምነት ሰነድ የለውም ።ይሄ ግልጽ መሆን አለበት።ፕሮግራም አይደለም ፤ርዕዮተ አለምም አይደለም ።በስብስቡ ላይ በጂኦግራፊ የሚያምኑ ፌዴራሊስቶችም በብሔር ወይም ደግሞ በማንነት የሚያምኑ ፌዴራሊስቶችም ተገኝተዋል፡ የፕሮግራምና የርዕዮት ጉዳይ ሳይሆን ህብረብሔራዊ ፌደራሊዝምና ሕገመንግስቱን ማዳን የሚለው ላይ ነው ነበር ትኩረት የተደረገው።ሌላ ዝርዝር ጉዳይ
የለውም።ወደ ውስጥ ሲገባ ግን የመስመር ልዩነት መምጣቱ አይቀርም።እዛ ውስጥ ሳይገባ ገና ልዩነቶች መፈጠር ጀመሩ። የፌደራሊስት ኃይሎች ሊቀመንበሩ ደጋግመው ከሚገልጹት ውስጥ ፡ ህውሃት እንደ አንድ ፓርቲ ነው እንደ ፌዴራል ኃይል ሆኖ የሚቀጥለው ሲሉ ይደመጣሉ።ይህን ማለት ለምን አስፈለገ።ህውሃት አሁንም ቢሆን የበላይ ሆኖ አስተሳሰቡን በሌሎች ላይ እየጫነ የመቀጠል ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ ነው።
አዲስ ዘመን ፡- ባለፉት 27 ዓመታት እውነተኛ ፌደራሊዝም ነበረ ብለው ያምናሉ?
አቶ ትዕግስቱ አወል ፡- በመሰረቱ በስልጣን ላይ የነበሩት አካላት እንኳን በተግባር ሊያረጋግጡት ቀርቶ ሕብረብሔራዊ ፌደራሊዝም የሚለውን ቃል ሲጠቀሙ ሰምተናቸው አናውቅም። አከላለሉ ፌዴራላዊ ይሁን እንጂ በአንድ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭነት ሲመራ ነበር የቆየው።ፓርቲና መንግስት ደግሞ ድንበር የለሽ ሆኖ በመቆየቱም ትክክለኛ ፌዴራሊዝም ተግባራዊ ሆኗል ብሎ መናገር ያስቸግራል ።ኢህአዴግ ከህብረብሄራዊ ፌዴራሊዝም ይልቅ ልዩነትን የሚሰብክ ድርጅት ነው።
ባለፉት 27 ዓመታት ልዩነት ሲሰበክ ነው የቆየው።በዚህም የተነሳ የህብረተሰቡ አብሮ የመኖር ዕሴት ተሸርሽሯል። ሆኖም ግን የታሰበው ያህል ህዝቡ አልተጫረሰም።ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ የአንድነት እሴቱ፣ አብሮ የመኖር እሴቱ፣ የህዝባዊ ዝምድና እሴቱ ዝም ብሎ የተፈጠረ ሳይሆን በረጅም ጊዜ ሂደት የተፈጠረና የተዋለደ በመሆኑ ዝም ብሎ የሚበተን አይደለም።በ2010 የመጣው የለውጥ እንቅስቃሴ እና አሁን የመጣው ውጤት ለዚህ ምስክር ሊሆን ይችላል።
አዲስ ዘመን ፡- ፌዴራሊስቶች የብሄር ፌዴራሊዝም እንደሚከተሉ የታወቀ ነው።እርሶ ደግሞ በጂኦግራፊያዊ ፌዴራሊዝም ነው የሚያምኑት።ከዚያ በተጨማሪ እርሶ የብሄር ፌዴራሊዝም ልዩነት እየሰፋ ነው ብለው ያምናሉ።የእናንተና የፌዴራሊስቶች ሀሳብ ፍጹም የተለያየ ነው። ታዲያ በፌዴራሊስት ፎረም ውስጥ እንዴት ሊመረጡ ቻሉ?
አቶ ትዕግስቱ ፤- እየነገርኩህ ነው።ስብስቡ ምንም አይነት ጋብቻ የለውም።ገና ሊፈጠር ነው።ሎሚ ውርወራ ላይ ነው ያለው።አቋምህን ይዘህ አረጋግጠህ የምትመጣበት መንገድ ገና ነው።ያ ስብስብ የወደፊቱን ጋብቻ ለመፍጠር የፌዴራሊስት ሀይሎች ፎረም የሚባለው ስብስብ አመቻች ነው።በዚህ ሂደት ውስጥ ሰዎቹ እኔንም ድርጅቴንም ስለሚያውቁኝ መጀመሪያ የተደረገው ሶስት መሪዎችን መምረጥ ነው።የመጀመሪያው 31 ድምጽ በማግኘት አቶ ደረጀ ሊቀመንበር ሆኑ፣ እኔ ደግሞ 27 ድምጽ በማግኘት ምክትል ሊቀመንበር ሆንኩ፣ ከዚያ ቀጥሎ ያለውን ድምጽ ያገኘው ደግሞ ጸሃፊው ነው።ስለዚህ 5 ተወዳዳሪዎች ቀረብን ማለት ነው።ይህ እንግዲህ የሰዎች ፍላጎት ነው።እዛ ላይ የተቀመጠ ሰነድ የለም።ወደ ሰነዱ ሲመጣ ግን ልዩነቱ ሰፊ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም።ስለዚህም እንደ አንድነትና አንድነት መሪ የተገነዘብኳቸው ነገሮች በፎረሙ እንድንቀጥል የሚያስችሉን አይደሉም።
አዲስ ዘመን፤- ባለፉት 27 ዓመታት ህገ- መንግስቱ በተግባር ነበር ወይ?
አቶ ትዕግስቱ አወል ፤ ህገ-መንግስቱማ ተተግብሮ አያውቅም።ትክክለኛው ፌዴራሊዝምም አልተተገበረም። በአፈፃፀም እየተሸፈነ ነው የሄደው። ህገ-መንግስቱ በራሱ መሻሻል ነበረበት። የማንነት ጥያቄዎች ከህውሃት አስተሳሰብ የሚመነጭና የሚስማማ ካልሆነ በስተቀር መፍትሔ ያገኘ ጉዳይ የለም። ለምሳሌ የሲዳማ ክልላዊ ጥያቄን ማንሳት ይቻላል። ይህ ጥያቄ ትናንትም የነበረ ሲሆን መፍትሔ ያገኘው አሁን በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ነው። በነፃነት የመናገር መብት ያልነበረና ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት በመረገጣቸው ምክንያት የብሔር ጥያቄ አልተመለሰም። ስለዚህ ደግሞ ህገ-መንግስቱ አልተከበረም። በመሆኑም ችግሮች ተደማምረው ነው የመጣውን ለውጥ ማየት የተቻለው።
አሁን የሚቀነቀነው የብሔር ፌዴራሊዝም በጭራሽ ተከብሮ አያውቅም። የብሔር ጥያቄው ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ባለመፈታቱ ምክንያት ዛሬ የብሔር ጥያቄ በተለየ ሁኔታ ጎልቶ ወጥቷል። በመጀመሪያው ስብሰባ ላይ ስብሰባውን የጠራው አካል ነው ሞቶውን ያስቀመጠው። ጋባዥ እስከሆኑ ድረስ የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ። ሀሳቡ ከእነሱ የመነጨ ነው እንጂ የተጋባዥዎቹ አቋም አይደለም።በእነሱ አረዳድ ህገ-መንግስቱ እየፈረሰ ነው፤ አሃዳዊ ስርዓት እየተገነባ ነው ሲሉ ይሰማሉ።በዋነኝነት ህገ መንግስቱን ሲጥሱ የነበሩት እነዚሁ ወቃሽ ሃይሎች ናቸው።
አዲስ ዘመን- በምን እና እንዴት ከፌዴራሊስት ሀይል ስብስብ ውስጥ ሊወጡ ቻሉ?
አቶ ትዕግስቱ አወል፤- በቆየንባቸው ጊዜያት ውስጥ የተገነዘብኩት ዋነኛ ጉዳይ ህወሓት አሁንም ወደ ቀድሞው የበላይነቱ የመመለስ ዓላማ አለው።አሁንም የመከፋፈልና አንዱ አንዱን በጥርጣሬ እንዲያይ የማድረግ ሴራ አሁንም አይቻለሁ።በአመራሩ መካከል በጥርጣሬ እንዲተያዩ የማድረግ ባህርያቶች ተገንዝቤለሁ።በብሔር የተደራጁ ድርጅቶችና ሀገር አቀፍ እንደኔ አይነቱን ለያይቶ የማየት አካሄድ አሁንም ይስተዋላሉ ።ሌላው በተለያዩ ህዝባዊ መድረኮች ሰላማዊ የሚመስል ነገር አይታይም።በተለይ የሚጠቀሙባቸው ቃላቶች ሀይለ ቃላቶች የሚበዙባቸው ናቸው።ለምሳሌ ከነሱ አመራር ውስጥ አንዱ ተነሱ ዝመቱ ሲል ሰምቸዋለሁ።በሌላ በኩል ደግሞ በህዝቦች መካከል ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን አብሮ የመኖር ዕሴት ለመናድ ሲሞክር አስተውያለሁ።ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይ ህዝብ ስጋት እንደሆነ አድርጎ የማቅረብ አካሄድ ተመልክቻለሁ።ይህንንም ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ የትላንትናዎቹ ፈረሶች አዳዲስ ፈረሶችን እየመለመሉ ይገኛሉ።የፌዴራሊስት ኃይሎች በሚልም የተለያዩ ቡድኖችን እያደራጁ ነው።
አዲስ ዘመን፤- ከሚያደራጇቸው ኃይሎች ጋር ምን ያህል ዴሞክራሲያዊ ግንኙነት አላቸው?
ለ 30 አመታት ዲሞክራሲያዊ ነን ብለው ነው ሲናገሩ የሚሰሙት።ፈጽሞ ግን ዴሞክራሲያዊ ሆነው አያውቁም።አሁን ወደ ጥግ መገፋታቸው ያሳደረባቸው ስሜት ነው ከባድ በመሆኑ ወደ መሃል ለመምጣት የማይቆፍሩት ድንጋይ የለም።አሁን ከፌዴራሊስት ሀይሎች ጋር እንሰራለን የሚሉት ይህንን ለማድረግ አስበው ነው።የትላንትናው አስተሳሰብ ለመድገም ነው የሚሰሩት።መስመራችን ሀይላችን ነው ብለዋል ። ያ ማለት የትላንትናው መስመር የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ነው።ይህ ደግሞ ስርዓቱን የሚደግፉ ሀይሎችን ለመፍጠር ስለሆነ እኔ ደግሞ ከድርጅቴ አላማና ተልዕኮ አንፃር የሚሄድ ስላልሆነ እና ሰላምን የሚያመጣ ስላይደለ ልከተለው አልፈለኩም።ስለዚህም የነበረኝን የፎረሙ ምክትል ሊቀመንበርነቴንም ሆነ ድርጅቴ በፎረም ሊስት ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ሙሉ ለሙሉ መሰረዙን ለማሳወቅ እወዳለሁ።
በአጠቃላይ የህውሃት አካሄድ ትላንትም ሆነ ዛሬ ዴሞክራያዊ አይደለም።በመጀመሪያ ጫፍ ተይዞ ዴሞክራሲያዊነት የሚባል የለም።ዋልታ ረገጥ ዴሞክራሲ የለም።አንድነት ከተረገጠ አካባቢያዊ ብሄርተኝነት ነው የሚታየው እንጂ ኢትዮጵያዊነት አይደለም።ያለውን ሀብት ተጠቅሞ ህዝቡን ለማሰባሰብ የሚደረገው ነገር ዴሞክራሲያው አይደለም። ሌላኛው ነገር ሁሉንም አማራጭ እንጠቀማለን ተብሏል።የህወሀት ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ሁሉንም አማራጭ ሲል ምን ማለቱ ነው።እንደኔ አንዱና ብቸኛው አማራጭ ዴሞክራሲያዊነት ነው።ሌላው ደግሞ የሀይል አማራጭ ነው።ሁሉንም ካልክ ከዴሞክራሲያዊ አማራጭ ውጪ ሌላ አማራጭ ትጠቀማለህ ማለት ነው።ሁሉንም አማራጮች ማለት ጥሩ አይደለም።
ሁለተኛው ነገር ተነስ ዝመት የሚለው ቃል ለእኔ በፍፁም አልተመቸኝም።ይህ የዘመቻ ጥሪም ለኢትዮጵያና ለትግራይ ህዝብ ጭምርም ይመቻል የሚል እምነት የለኝም።ምክንያቱም አብሮ የኖረ ህዝብ ነው።አሁን በተፈጠረው ችግር እንኳን ምን ያህል ስጋት ውስጥ እንዳለ ለማየት ይቻላል።ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ቆም ብሎ ማሰብ መቻል አለበት።ከሚነገረው ትርክት ባሻገር ለዘመናት የቆየውን አብሮ የመኖር ዕሴት ማሰብ ያስፈልጋል።የፖለቲካ ድርጅቶች እዛም ያሉ ቢሆን እያሰቡ መንቀሳቀስ ካልቻሉ ችግሩ ለሁሉም የሚተርፍ ነው።
አዲስ ዘመን -፤ የፌደራሊስት ሀይል የተደራጀው በዋናነት ከዚህ በፊት ራሱ ጠፍጥፎ የሰራቸውና አካላትና አላማውን የሚያስፈፅሙለት ስብስቦች ናቸው ተብሎ ይነገራል ፤ በዚህ ላይ ምን ምላሽ ይሰጣሉ።
አቶ ትዕግስቱ ፤-ህውሀት ያሰባሰባቸው ፤ያደራጃቸው ወደሚለው ዝርዝር ውስጥ ከገባን ችግር ነው። ይሄ አባባል የኛን የፖለቲካ አካሄድ የማይደግፉ ሰዎች የሚሉት አባባል ነው ። ህወሀት ያላደራጀው ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ለምሳሌ ፌዴራሊስት ፎረም የሚለው ሁለተኛ መድረክ ላይ ተፈጠረ እንጂ በመጀመሪያ መድረክ ላይ የኦነግ፤ የኦፌኮ፤ ሶሻል ዲሞክራት በነፕሮፌሰር በየነ የሚመራው፤ ሲአን ባጠቃላይ ከአረና በስተቀር የመድረክ አባል ድርጅቶች ነበሩ። በዛ ግዜ የመድረክ ድርጅት አባል የነበረ አንድ ተወካይ አረና ለምን አልመጣም ብሎ ጠይቆ እንደነበር አስታውሳለሁ። ስለዚህ የእነሱ እጅ ያልገባበት አለ ለማለት ያስቸግራል።
ህወሀት በሀያ ሰባት አመት ቆይታው የሰራውን እናውቃለን።ከዚህ በፊት ዝርዝር ነገሮችንም ተናግሬያለሁ። እዚች ሀገር ላይ አዲስ የተፈጠረ የፖለቲካ ፓርቲ የለም ፤ አንዱ ከአንዱ እየተፈነቀለ የመጣ ፓርቲ ነው። ይሄ ሁሉ ቁጥር የሚታየው ግለሰቡ ሳይመቸው ሲቀር እየተቧደነ የሚወጣና የሚፈጥረው ነው። አንዱ አመራር ከአንዱ ጋር ሲጣላ ፓርቲ ይመሰርታል።አሁንም የቀድሞ ወዳጆች ናቸው የሚለው ቀደም ሲል በሱ አመራር ስር የነበሩም አሉ። አሁን ከአመራሩ የተወገዱ ሀይሎች የብሄር ድርጅት እየመሰረቱ የተጋበዙበት እድል ይኖራል ብዬም አስባለሁ። ቢኖርም ግን ዛሬ የሚነሳ አጀንዳ አይደለም ፤ አንድም አያደርገንም።
የኢህአዴግ አደረጃጀት የሚሆነው ስትራቴጂካል፤ ታክቲካል ነው። አሁን ያለው ግን ሀገርን ወደ ዲሞክራሲ እንድትሸጋገር አንድነቷን ጠብቆ የመሄድና ያለመሄድ ጉዳይ ነው። የሀገር ህልውና ጉዳይ ሲመጣ በዛ መስመር የተሰለፈው ሀይል ልዩነቶችም ችግሮችም ቢኖሩ በመግባባትና በንግግር ሊፈታው ይገባል። በቅርቡም ወደ ምርጫም ሊገባ በመሆኑ ውይይትና ምክክር ያስፈልጋል።
እኛ መቀሌ በተገኘንበት ወቅት ህውሃት ራሱ የሆነ የመነጠል ሴናሪዮ እንዳለው ተረድቻለሁ።ለእነሱ የሚመች አካሄድ ካገኙ አሁንም የበላይ ሆነው ለመቀጠል ይመኛሉ፤ካልሆነ ግን የመነጠል ፍላጎት አላቸው።የመነጠል ፖለቲካ የህወሀትና የህወሀት ብቻ አይደለም።በተመሳሳይ መልኩ የሚያስቡ በሌላ ክልልም ላይ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ።
ትላንት አብረው ነበሩ ራሱ የፈጠራቸው ናቸው ለሚለው ማንም ሊፈጥርህ ይችላል። እንደ አንድነት ግልጽ ለማድረግ በመንግስትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ባለው ግንኙነት ሶስት አይነት አቀራረቦች አሉ። አንዱ አፍራሽ አንዱ ተባባሪነት አንዱ አማካሪ በመሆን ፓርቲዎች ይኖራሉ። አንድነት ተባባሪ ነው በመተጋገዝ መቃወም አለ እየተቃወምክ መተጋገዝ ይቻላል።
ስለዚህ አንድነት በባህሪው የሕብረት ድርጅት(ኮፕሬቲቭ) ነው።ምክንያቱም በመተጋገዝ መቃወም ይቻላል።እየተቃወምክ መተጋገዝ ሊኖር ይችላል።መንግስት በነበረ ጊዜ ነው ያ የሚሆነው፤ አሁን ግን የፌዴራል መንግስት ናቸው፤ በዚህ አሁን ባለው ሁኔታ።ስለዚህ አሁንም ቢሆን ከመንግስት ጋር ያለህ ግንኙነት በጣም ዴሞክራሲያዊ የሚያደርግህ ወይም ደግሞ አብረህ ስትሰራ ነው።አብረህ ስትሰራ ወዳጅ ትሆናለህ።ፖለቲካ ፓርቲዎች መንግስት ሆንክም አልሆንክም አብሮ በመስራት ነገሮችን ማጥበብ ይቻላል።
ምክንያቱም ምልልስ ይኖራል አብረህ ስትሰራ፤መግባባት ይፈጠራል፤ሀገርን መሰረት ካደረግክ፣ ማለት ነው።የግል ድርጅታዊ ፍላጎትህን ካደረግክ ግን ከማንም ጋር አትስማማም።ስለዚህ ይሄ የፖለቲካ የጥላቻ ንግግር ነው ብዬ ነው የምወስደው።የጠፈጠፋቸው፣ ማን የጠፈጠፋቸው፣ሻዕቢያ ነው የጠፈጠፋቸው ነው ያሉት! ምን ወሬ ያስፈልጋል።ወደዚያ አንግባ ነው ጥያቄው።ሻዕቢያ የጠፈጠፋቸው ወገኖች ወይም ደግሞ እዚያ እሱ የፈጠራቸው ሀይሎች ዛሬ ዴሞክራሲያዊ ነን
ብለው አስበው የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች አሉ።ወደዚያ ከመጣን ሁላችንም ወደ ስራችን እንሄዳለን፤ ጥሩ አይሆንም።ለጠየቅከው ጥያቄ ለመመለስ ነው እንጂ አሁን ግን አቋማችንና አቅማችን እየተፈተሸ መሄድ አለበት የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ድርጅትዎን ይዘው ወደዚህ የስብስብ ሀይሎች ሲመጡ ሕውሃት ከዚህ በፊት የሰራቸው በደሎች አሉ ተብሎ ይነሳል፤ ስብሰባ ላይ መገኘትዎ በራሱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አያጣላዎትም ወይ?
አቶ ትዕግስቱ፡- አንድ ነገር ግልጽ ላድርግልህ በጎዳና ላይ በተደጋጋሚ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ብትሄድ ሚስቱ ናት ብሎ መደምደም አይቻልም።ስለዚህ መቀላቀል ማለት በአንድ መርህ ላይ በአንድ አቋም ላይ ወይም አደረጃጀት ላይ የራሱ የሆነ ሕጋዊ የሆነ አሰራር የኖረው ሲሆን ነው መቀላቀል።አሁን ግን ቅድም እንዳልኩህ ሎሚ ውርወራ ማለት ፍለጋ ነው አይደል።እነሱ እየወረወሩ ነው።ጥሪ አድርገውልን ነው የሄድነው እንጂ በእኛ ተነሳሽነት አይደለም።እዛ ደርሰን ከመጣን በኋላ ግን በምንም መንገድ ልንገናኝ እንደማንችል አውቀነዋል።ከህውሃት ጋር አራምባና ቆቦ ነን። በአስተሳሰብና በአደረጃጀት አንገናኝም።
አሁን ህውሃት እየተከተለ ያለው አካሄድ የኢትዮጵያን ሕዝብ ብሎም ትግራይን ጨምሮ ሊያስለቅስ የሚችል አካሄድ ነው።ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ውስጥ አንሳተፍም።ስለዚህ መንግስት በነበረበት ጊዜ እንደ መንግስት ከፓርቲ ጋር ግንኙነቶች ሊኖሩ ይችላል።ይህ አለምአቀፍ አሰራር ነው።አሁን ግን አቋም የያዝንበት ነው።አካሄዱ አልተመቸንም።የመሰባሰቡ ሁኔታ አልተመቸንም።ልክ እንደኔው ሌሎቹም ተገንዝበው የራሳቸውን አቋም ሊይዙ ይችላሉ።ባለፈው ጉባኤያቸው ከፍተኛ የህወሃት አመራር በማንነት ነው የኛ ፌዴራሊዝም፤ ከዚህ ውጭ የሆነው ጂኦግራፊ ነው።ጂኦግራፊ ጠላታችን ነው ሲሉ አድምጫለሁ።ስለዚህ የተለየ ሃሳብ ሲኖር ጠላት አድርጎ የማየት ሁኔታ የኖሩበት ነው፤ አሁንም የቀጠሉበት ነው ማለት ነው።በእነሱ የፖለቲካ አካሄድ ሁለት ነገር ነው ያለው፤ ጠላትና ወዳጅ።በፖለቲካ ውስጥ ጠላትና ወዳጅ የሚባል ነገር በተለይ በዴሞክራሲዊ ሁኔታ ውስጥ የለም።
በአንድ ወቅት የነሱ ሰው በአንድ ቃለምልልስ ላይ ሲናገር አብዮታዊ ዴሞክራሲ ማለት ጠላትና ወዳጅ መሆኑን አሁን ነው ያወኩት ብሏል።አብዮታዊ ዴሞክራሲ ራሱ ተግባብተህ መስራት ሳይሆን ጠላትና ወዳጅ ፈርጀህ መንቀሳቀስ ነው።ስለዚህ ዛሬ እንደትላንትናው አስተሳሰባቸው አይጠቅምም ተብሎ ተጥሏል።እዚያም ትግራይ ውስጥ ብዙ አስተሳሰቦች እየመጡ ነው፤ ስለዚህ ይህ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ዛሬም እንዲቀጥል መፍቀድ ትላንት የታገልከውን ሁኔታ ዛሬም አብረህ እያገዝክ መሄድ ተገቢ አይደለም።ህዝብን ማስቀየም ነው በቃ።የትላንቱን የፖለቲካ አካሄድ መደገፍ ህዝብ ዳግም እንዲበደል እያገዝክ ነው ማለት ነው።ስለዚህ በምንም መልኩ ይህ አስተሳሰብ ደግሞ እንዳይመጣ መታገል ይገባናል።
አሁንም ቢሆን የቁጭት ፖለቲካ ነው ህወሃት እያካሄደ ያለው።የቁጭት ፖለቲካ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም። ስትቆጭ ሃይልህንም ጭምር ነው ለመጠቀም የምትሞክረው ።ስለዚህ ይህ ጥሩ ስለማይሆን ከዚህ ሃይል ጋር አብሮ መስራት ጥሩ አይደለም።ሌሎቹ ከተመለሱና ዝግጁ ከሆኑ አብረን እሰራለን።ይህ ሃይል ባለበት ስብስብ ውስጥ አብሮ መስራት ግን ከባድ ነው።ይህ ሃይል አሁንም ቢሆን ሁሉንም አማራጭ ይጠቀማል።እኛ ደግሞ አንድ አማራጭ ነው ያለን፤ ዴሞክራሲያዊ መንገድ።እንደቀድሞውም ፈረስ ሆነን ማንም እንዲጋልበን መሆን አያስፈልግም፤ ዳግም ተላላኪ መሆንም አያስፈልግም።ለዚህ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፤ እኛ ግን አቋማችንን አረጋግጠናል።በቀድሞ መንገድ መቀጠል አንፈልግም።
አዲስ ዘመን- ብዙ ጊዜ በህገመንግሥቱና በፌዴራሊዝም ዙርያ ክስ ሲቀርብ እንሰማለን።በዚህ ረገድ በብልጽግና ፓርቲና በህውሃት መካከል የመርህ ልዩነት አለ ብለው ያምናሉ?
አቶ ትዕግስቱ አወል- ሁለቱ ድርጅቶች ከፍተኛ የሆነ ልዩነት አላቸው።ብልጽግና ፓርቲ ከኢህአዴግ የወጡ ድርጅቶችና ሌሎች ድርጅቶች የተዋሃዱበት አደረጃጀት ነው።አደረጃጀቱ ሁለቱንም እሴት ያማከለ ነው ብዬ አምናለሁ።የማንነትን አደረጃጀትና የዜግነትን አደረጃጀት የያዘነው ብዬ አምናለሁ።ህገ መንግስቱ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሚል መንደርደርያ አለው።ይህ የህገመንግስት አስተሳሰብ በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ይታያል።ኢትዮጵያ ውስጥ የሀገረመንግስት ግንባታ ተጀምሮ የቀረ ነው።ህውሃትም ሲመራው የነበረው ኢህአዴግ ዲሞክራሲ ላይ አልሰራም።ዛሬ የምናያቸውም ችግሮች የዚያ ነጸብራቅ ነው።ዛሬ ህውሃት ዴሞክራት መስሎ ቢቀርብም ዲሞክራሲ ላይ ግን ሲሰራ አልታየም።ስለዚህም የብሄርንም ዜግነትንም ጉዳዮች ይዞ መሄዱ የብልጽግና ፓርቲ አንዱ ጠንካራ ጎኑ ነው።ህውሃት የብሄር ማንነት ብቻ ተነጥሎ መከበር አለበት ይህ ካልሆነ ሀገር ትፈርሳለች የሚለው ውሃ የሚቋጥር አይደለም።ይህ ጫፍ የረገጠ አስተሳሰብ ነው።
ህውሃት ላለፉት 27 ዓመታት የብሄርን መብት አስጠብቃለሁ ብሎ ቢለፍፍም አንዱን ብሄር ከሌላው እያጋጨ ስልጣኑን ለማራዘም ሲሞክር ታይቷል።ይህ በመሆኑ በጋራ ለመልማት አልቻልንም።ግጭትና መፈናቀል ዋነኛ መለያችን ሆኗል።አማራ ከኦሮሞ፤ ሶማሌ ከኦሮሞ፤ሶማሌ ከአፋር ወዘተ በጠላትነት እንዲተያይ አድርገውታል።ይህ የሴራ ፖለቲካ ነው።ዛሬም መቀሌ ሆነው ለ27 ዓመታት ሲጠቀሙበት የነበረውን የሴራ ፖለቲካ ለማራመድ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።ወደፊትም በሚፈለፍሏቸው ሃይሎች አማካኝነት ይህች ሀገር መልሳ ወደ ሴራ ፖለቲካ እንዳትገባ ስጋት አለን።ህዝብ በህዝብ ላይ ተነስቶ አያውቅም።ይህ በሴራ ፖለቲካ አቀንቃኞች አማካኝነት የሚጠነሰስና የራስን ስልጣን ለማራዘም የሚደረግ ዕኩይ ተግባር ነው።ስለዚህም ይህን የሴራ ፖለቲካ የሚጸየፉ ወገኖች የራሳቸው መንገድ መምረጣቸው ትክክል ነው።ተመሳሳይ አቋምና አስተሳሰብ ያላቸውም አካላት መዋሃድ መብታቸው ነው።በኢህአዴግ ስም ያለው 25 ወንበር ብቻ ነው።የአዲስ አበባ 23 እና ድሬዳዋ 2 ሌላው የተቀረው በሙሉ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ድርጅቶች ያላቸው መቀመጫ ነው።
ስለዚህም ሁሉም የሚያዋጣውን የመወሰን መብት አለው።በአዲሱ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅም የውህድ ፓርቲ ዕዳንም ሆነ ትርፍን ይወርሳል የሚል አንቀጽ እናገኛለን።የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ውርስን ይጨምራል።የተለያዩ ፓርቲዎች በራሳቸው ፍላጎት መዋሃድ ከፈለጉ የሚከለክላቸው ነገር አይኖርም።የማይፈልግ ደግሞ ልዩነቱ ጠብቆ መጓዝ መብቱ ነው።የህወሃት ወንበር ቢነሳም ገዢው ፓርቲ አምስት መቶ የሚጠጋ ወንበር ስለሚኖረው መንግስት ሆኖ የመቀጠል መብት አለው።ስለዚህም ባልተመረጠበት ፕሮግራም ሀገር እያስተዳደረ ነው የሚለው የሚያስኬድ አይደለም።ስለዚህም ብልጽግና ፓርቲ በምርጫና በፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ላይ እንዲሁም በህገ መንግስቱ የተቀመጡ ሃሳቦችን እየተገበረ የሚገኝ ፓርቲ ነው ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፤-የህውሃት ጥረት የቀደመ የፖለቲካ ሴራን በአዲስ መልክ ለማምጣት ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ህውሃት በዚህ አቋሙ ሊገፋበት ያስቻለው ጉዳይ ምንድን ነው
አቶ ትዕግስቱ አወል፤-ህውሃት ከስሙም ከአመጣጡም ስንመለከተው ነጻ አውጪ ነኝ ባይ ነው።ነጻ የሆነን ህዝብ ነጻ አወጣለሁ ብሎ የሚፎክር ነው።ህውሃት የአስተሳሰብ ለውጥ አላመጣም።በ1980 ዎቹ አካባቢ ነጻ አውጪ ሆኖ ታግሏል።ደርግ ከወደቀ ወዲህ ግን ህዝቡ ነጻ ወጥቷል።ስለዚህም መንግስት ከመሰረተ በኋላ ነጻ አውጪ ነኝ ብሎ ቀጥሏል።በሁለት ነገሮች ያምናሉ።አንደኛው በሴራ ፖለቲካ ማመናቸው ነው።ይህ ደግሞ በዋነኛነት ህዝብን ከህዝብ ፤ብሄርን ከብሄር በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ዘወትር ይሰራሉ።አንዱን ብሄረሰብ ከሌላው ጋር ማጋጨት ዋነኛ ማጠንጠኛቸው ነው።ሀገርን በትርምስ ውስጥ መምራት የሚከተሉት ስልት ነው።ይህንን የሚያቀነባብሩና የሚመሩ ነባር አመራሮች ናቸው።
ከጫካ ጀምሮ ልምዱና ተሞክሮ ያላቸው ነባር አመራሮች የዚህ ሴራ ዋነኛ ጠንሳሾች ናቸው።ሁለተኛው ደግሞ የመነጠል ፖለቲካ ነው።ብዙ መስዋዕትነት የከፈልነው እኛ ነን።ስለዚህም የተለየ ጥቅም ይገባናል የሚል ነው።ህዝቡ በእነዚህ መንገዶች የተጎዳም ቢሆን እነሱ ይህንን አስተሳሰብ ለመተው ፍቃደኞች አይደሉም።ለእኔ ይህ በሽታ ነው።ይህን ነገር ለማስቀረት በሚደረገው ጥረትም የሚያነሳሱት የትግራይን ህዝብ ነው።ተበድለሃል፤ተጎድተሃል እያሉ ዘወትር የህዝቡን ስነ ልቦና ለመለወጥ ጥረት እያደረጉ ነው።ሄደው ሄደው የሚያዋጣ ካልመሰላቸው የመነጠል ፖለቲካ መከተላቸው አይቀርም።ይህ ግን ዕውን ሊሆን የሚችለው ህዝቡ ካመነበት ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፤- ብልጽግና ፓርቲ አሐዳዊ መንግስት ለመመስረት እየጣረ ነው የሚል ክስም ሲያነሱ ይሰማል፤ ይህንን እንዴት ያዩታል?
አቶ ትዕግስቱ አወል፤-ብልጽግና ፓርቲ አሐዳዊ መንግስት ሊመሰርት ነው የሚለው ዋነኛ ማደናገሪያቸው ነው።የብሄር ፖለቲካ የሚከተሉ ወገኖችን ቀልብ ለመሳብ ነው።አሃዳዊ የሚል ሃሳብ የትኛውም ፓርቲ ውስጥ የለም።ጭራሽ አሁን እየታሰበ ያለው ጸረ ፌዴራሊስት የሚል ስም ለመስጠት ነው።መቀሌ ላይ የተሰባሰቡ እና ከዚህ የሄዱ ኃይሎች ይህንን ስም ለመለጠፍ እየተሯሯጡ ነው።በተለይም የምሁራን ፎረም የሚባለው ይህን ለማድረግ እያሰበ ነው።ይህንን በዋነኛነት ከአማራው ጋር ለማገናኘት ነው።አማራውን ልክ እንደ አሃዳዊ አስተሳሰብ አፍቃሪ እንዲቆጠርና ሌሎችም ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው ለማድረግ ነው።ልክ 1983 አካባቢ ሀገሪቱን ሲቆጣጠሩ በነበረበት ወቅት የነበረው አስተሳሰብ ውስጥ ነው ያሉት።አሃዳዊ በማለት አንዱን በአንዱ ላይ ለማነሳሳትና ጥርጣሬ ለመፍጠር ሆን ተብሎ የሚነዛ ወሬ ነው።ይህ ግን አያዋጣም።ሀቁ ሲገለጥ ሴረኞች አብረው መጋለጣቸው አይቀሬ ነው።
አዲስ ዘመን-ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን
አቶ ትእግስቱ አወል-እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012 ዓ.ም
አዲሱ ገረመው