አዲስ አበባ፡- ከእርግዝናና ወሊድ ጋር በተያያዘ እናቶችን ለሞት የሚዳርጉ መንስኤዎች አሁንም እንዳልቀነሱ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ የጤናማ እናትነት ወርን አስመልክቶ ትናንት በስካይ ሆቴል በተካሄደው ኮንፍረንስ ላይ እንደተናገሩት፤ ለእናቶች ሞት የሚዳርጉ አብዛኛዎቹ መንስኤዎችን ማዳንና መከላከል የሚቻል ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ በእርግዝና ወቅት፣ በወሊድና ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የደም መፍሰስ የሚመጣ ነው።
እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለከፍተኛ ህመምና ለህልፈተ ህይወት እየዳረጉ ያሉ መንስኤዎች በተገቢው መንገድ አሁንም ላለመቀነሳቸው ሶስት መሰረታዊ ምክንያቶች መኖራቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል።
ከእነዚህ ውስጥ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆንና ይህንኑ ተከትሎ እናቶች ከእርግዝና ጀምሮ አስፈላጊውን የህክምና ክትትልና ድጋፍ አለማድረግ ብሎም በቤት ውስጥ መውለድ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በገጠር አካባቢዎች ላይ እናቶች ወደጤና ተቋማት በመሄድ የህክምና ክትትል ማድረግ ቢፈልጉም ከመንገድ፣ ትራንስፖርት፣ ከገንዘብ እጥረትና መወሰን ካለመቻል ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት ወደጤና ተቋማት ዘግይቶ መድረስ ለእናቶች ሞት መጨመር ሁለተኛ መንስኤ መሆኑን አመልክተዋል።
ወደጤና ተቋማት ዘግይተው ከደረሱ በኋላም በጤና ተቋማት ውስጥ ከህክምና መሳሪያዎች እጥረት፣ ከጤና ባለሙያዎች ክህሎትና ስነምግባር ችግሮችና ተገቢውን አገልግሎት ባለማግኘታቸው የችግሩ ሰለባ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።
በተለይም ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች ምክንያት የእናቶችን ህይወት መታደግ የማይቻልበት ሁኔታ መኖሩን ያስረዱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ አብዛኞቹ ግን መከላከልና መቆጠር የሚቻሉ ከመሆናቸው አኳያ ጠንካራና ተደራሽ የሆኑ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጤናማ እናትነት ጉዳይ ከጤና ሚኒስቴር በተጨማሪ በርካታ ሴክተሮችንና ባለድርሻ አካላትን የሚመለከት ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የእናቶችና የህፃናት ሞትን ለመቀነስ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባው አመልክተዋል።
‹‹እናት የቤተሰብና የሃገር ምሶሶ ናት›› በሚል መሪ ቃል ትናንት በአገር አቀፍ ደረጃ ለ14ኛ ግዜ በተከበረው የጤናማ እናትነት ወርና ይህንኑ አስመልክቶ በተዘጋጀው ኮንፍረንስ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የጤና ሚኒስቴርና የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ከወሊድ ጋር በተያያዘ እናቶችን ለሞት የሚዳርጉ መንስኤዎችን ለመቀነስ የጤና ሚኒስቴርና የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች የጋራ ስምምነት ፊርማ ተፈራርመዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012
አስናቀ ፀጋዬ