የዛሬው
የዘመን እንግዳችን የ47 ዓመት አባት ናቸው። እኚሁ የሃይማኖት አባት ታዲያ ውልደታቸውና እድገታቸው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ
ቢሆንም በአገልግሎታቸው ምክንያት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለመኖር ተገደዋል። እንግዳችን ለትምህርት ባላቸው ልዩ ፍቅርና ብርታት
ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እስከ10ኛ ክፍል እስከሚደርሱ ድረስ የአንደኝነትን ደረጃ ማንም አልቀማቸውም። በተለይም ደግሞ በሳይንስና
በሂሳብ ትምህርት ባላቸው ልዩ ፍቅርና ክህሎት ምክንያት መምህራኖቻቸው ሳይቀሩ ከፍተኛ የሆነ አመኔታና አድናቆት ነበራቸው።
በዚህ ብቻ ሳያበቁም የዛኔው ታዳጊ የሳይንስ ተማሪ ወደፊት ዶክተር ሆኖ አገሩን እንደሚያስጠራ እርግጠኞች ስለነበሩ ለዚህ ህልማቸው መሳካት ከቤታቸው አስጠግተው እያኖሩት በቅርበት ይከታተሉትና ያግዙት ያዙ። ይሁንና እንግዳችን መምህራኖቸቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸው የጣሉባቸውን እምነትና አደራ ወደ ጎን ትተው ወደ መንፈሳዊው ህይወት ጭልጥ ብለው ገቡ። ለሳይንስ ትምህርት ከነበራቸው ልዩ ፍቅር ይልቅ ለፈጣሪያቸው ያላቸው ፍቅር በለጠና ገና በ14 ዓመታቸው ቅዱስ ቁርባንን ተቀበሉ። ያንን ያዩ ዘመድ አዝማዶቻቸው እንዲሁም መምህራኖቻቸው ቢመክሯቸውም ሆነ ቢያስመክሯቸው አሻፈረኝ አሉና ከፈጣሪያቸው ጋር ተጣበቁ። ቤተሰቦቻቸው የልጃቸውን እምቢተኝነት ሲረዱ የሚያደርጉላቸውን ድጋፍ አቋረጡባቸው። ይሁንና የተማመኑት ፈጣሪያቸው እንዳልጣላቸው የሚናገሩት እኚሁ አባት ታዲያ ከድቁንና ጀምሮ አሁን እስከደረሱበት የምልኩስና ዘመናቸው ድረስ ደጋፊዎችን እያዘጋጀላቸው በጥሩ ሁኔታ መኖር መቻላቸውን ይገልፃሉ።
በጎና ቅን ማሰብን የህይወት መርሃቸው አድርገው የሚኖሩት እኚሁ የዛሬ እንግዳችን ከራሳቸው ቤተ ዕምነት አልፈው ፈፅሞ ማንም ሊያምነው በማይችልበት መልኩ ከሙስሊም ወገኖቻቸው ጋር በመሆን ዘመናዊ መስጊድ ለመገንባት ደፋ ቀና በማለት ላይ ናቸው። ለመሆኑ እኚህ ግለሰብ ዛሬ አንዱ ያንዱን ቤተ እምነት በጥርጣሬ በሚያይበት በዚህ ዘመን ይህንን ለማድረግ ምን አነሳሳቸው? ስለዚህና ስለ ሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች የሚሉት አላቸው። በምስራቅ ሐረርጌ አገረ ስብከት በሃረር ዙሪያ ወረዳ ቤተክህነት በቀርሳ ወረዳ የላንጌ ቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያንና የቢላል መስጂድ አሰሪ ከሆኑት ከዛሬው እንግዳችን መላዕከ ህይወት ቆሞስ አባ አክሊለማርያም ኋይለ ስላሴ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው እናቀርበዋለን።
አዲስ ዘመን፡- በልጅነቶ ሰቃይ ተማሪ እንደነበሩ ሰምቻለሁ፤ ግን ደግሞ ትምህርቱን አቋርጠው ወደ መንፈሳዊ ህይወት ገብተዋል፤ ምክንያቶ ምን እንደነበር ይግለፁልኝ?
አባ አክሊለማርያም፡- እኔ ትውልዴና እድገቴ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ በሃረር ዙሪያ አካባቢ ነው። የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያን ተከታይ የሆኑት ቤተሰቦቼ እድሜዬ ለትምህርት እንደደረሰ የሳይንስ ትምህርት ቤት ነው ያስገቡኝ። አንቺም እንዳልሽው ለትምህርቴ ልዩ ፍቅር ስለነበረኛ በርትቼ አጠና ስለነበር 10ኛ ክፍል እስከምደርስ ድረስ ከክፍልም ሆነ ከትምህርት ቤቴ አንደኛ ነበር የምወጣው። የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ እንኳ 97 አምጥቼ ነው ያለፍኩት። በነበረኝ የትምህርት ፍቅርና አቅም ምክንያት ወላጅ አባቴ፥ አሜሪካ የሚኖረው አጎቴና መምህራኖቼ ሳይቀሩ ልዩ የሆነ ድጋፍ ነበር የሚያድርጉልኝ። በተለይም መምህራኖቼ ለሂሳብና ለፊዚክስ የነበረኝን ፍቅር አይተው ወደፊት ዶክተር እንደምሆን እርግጠኞች ነበሩ። ለዚህም ይረዳኝ ዘንድ አንድ መምህሬ እኔ በቅርበት እከታተልሃለሁ ብሎ ቤቱ እንድኖር አደረገኝ። አሜሪካ የሚኖረው አጎቴም በየቀኑ ሆቴል የምመገብበትን ዶላር ይልክልኝ ነበር።
እኔ ግን በወቅቱ ከትምህርቱ ፍቅር በላይ እጓጓ የነበረው ስነምግባርና ግብረገብነት እንዲኖረኝ ነበር። በተለይም ንፅህና እና ቅድስናን ይዞ መኖርን ነበር የሁልጊዜ መሻቴ። እነሱ ከሚሉኝ የዶክትሬት ትምህርት በላይ የምጠማውና የምራበው በጎ ሰው መሆንን ነበር። በዚህ ምክንያት ከ10 ወደ 11ኛ ክፍል ካለፍኩ በኋላ ትምህርቴን አቋርጬ ወደ መንፈሳዊ ህይወቴ ገባሁ። አሁን ላይ የሊቃውንት ጉባኤ አባል የሆኑ አንድ አባት በ14 ዓመቴ ቅዱስ ቁርባን ካልተቀበልኩ ብዬ ጠየቅኳቸው። እኚህ አባት ግን አንተ ልጅ ነህ አሁን ቅዱስ ቁርባን ብትቀበል ሴይጣን ያሳስተሃል አሉኝ። እኔ ግን ጌታችን እየሱስ ስለአንተ ነው የሞተው ብለውኝ አልነበር ወይ? ብዬ ጠየቅኳቸው። ስለእኔ የሞተው እየሱስንን ብቻ ነው መከተል የምፈልገው ብዬ አሻፈረኝ አልኳቸው። እናም ለቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ ነግረዋቸውና እሳቸው ፈቅደው ሁለቱም አብረው ሆነው ካባ አድርገውልኝ በ1979 ዓ.ም ነሃሴ 14 ቀን በደብረሃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ቁርባን ተቀበልኩኝ። በዚያን ጊዜ ቅዱስ ቁርባኑን ስቀበል የሚያቀብሉኝ አባቶች እንዴት በዚህ እድሜ ይቆርባል ብለው አዝነው ከንፈራቸውን ይመጡ ነበር። አይችለውም የሚል ጥርጣሬም ነበራቸው። እኔ ግን የቅዱስ ገብርኤልን አምላክ በመማፀን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዓመቱ በጨመረ ቁጥር የእግዚአብሄር ፍቅር በእኔ ውስጥ እየጨመረ ሄደ። በዚህ ምክንያት ለጊዜው የሳይንስ ትምህርቱንም ሆነ መንፈሳዊ ህይወቱን በአንድነት ይዞ መሄድ ስለሚከብድ ትምህርቴን አቋርጬ ወደ ብህትና ገባሁ። በምስራቅ እና በምዕራብ ሃረርጌ አገረ ስብከት በአጠቃላይ በእግሬ እየተዘዋወርኩኝ አገለግል ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ወደ መንፈሳዊ ህይወት ሲገቡ ገና ለጋ እድሜ ላይ እንደመሆንዎ ከቤተሰቦችዎ ተቃውሞ አላጋጠሞትም?
አባ አክሊለማርያም፡- በጣም እንጂ! በተለይ አባቴ አብዷል ነው ያለኝ። በዚያን ጊዜ ቤተክርስቲያን መቃብር ቤት ውስጥ ነው የማድረው። አባቴ ይህንን በሰማ ጊዜ በቃ ልጄ አብዷል አለ። እንደዛ በትምህርቱ ጎበዝ የነበረ ልጅ አሁን ይህንን መንገድ መያዙ በጤናው አይደለም ብሎ አመነ። ቤተሰቦቼ ተሰብስበው ሊይዙኝና ሊያስጠምቁኝም አስበው ነበር። ግን ደግሞ እየተዘዋወርኩ ወንጌሉን ስሰብክና ሳስተምር ሲያዩኝ አብዷል የሚለውን ጥርጥሬያቸውን ይተውታል። በተለይ አባቴ የሚማር ሰው ይወድ ስለነበር ትምህርቴን በማቋረጤ በጣም ነበር ያዘነው። አሜሪካ ሊወስደኝ ቃል የገባልኝና ይረዳኝ የነበረው አጎቴም ከደጀ ሰላም ምግብ እንጂ ምን ይገኛል ብሎ ብዙ ነበር የተቃወመኝ። በኋላ ያደርግልኝ የነበረውን ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ አቋረጠብኝ። እኔ ግን የተሻለ መስመር ላይ ነኝ ብዬ ስለማምን ውጭ አገር የመሄዱ ጉጉት አልነበረኝም ነበር። ድጋፉም በመቋረጡ ምንም አይነት ስሜት አልተሰማኝም ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ እኔ አስብ የነበረው ያለምንም ጭንቀት በጎዳና ላይ የሚኖሩትን እብዶች ነበር። እነዚያ እብዶች ጎዳና ላይ በመኖራቸው ምንም አይሆኑም፤ ተባይ ምንም አላደረጋቸውም። ስለዚህ እኔ ለመኖር ምን የሚያቅተኝ ነገር አለ ብዬ አምን ነበር። ስለዚህም የቤተሰቦቼንና የመምህራኖቼን ተግሳፅ ወደ ጎን ትቼ በመንፈሳዊ ህይወቴ እየገፋሁ ሄድኩኝ።
በተለይም ደግሞ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ክርስቲያን ወገኖችን አገኘሁና የተለያየ ድጋፎችን እያደረጉልኝ መንፈሳዊ ትምህርቴን መከታተል ቻልኩ። ከዚያም ደብረሊባኖስ ገዳም ለትምህርት ገባሁ። በነገራችን ላይ ደብረ ሊባሎስ ገዳም ነው ውዳሴ ማርያም፣ መልካ ማርያም፣ መልካ እየሱስ እንዲሁም ዳዊትን የተማርኩት። ቅዳሴ ከጀመርኩ በኋላም የምኖረው ብዙ ክርስቲያኖችን አስቸግሬ ስለነበር በጉራጌ አገረ ስብከት ምሁር ገዳም እዛው ምግብ እየተሰጠኝ የማስተምርበትን እድል አገኘሁ። በዚህም ምክንያት ምሁር ገዳም ሄጄ ትምህርት ጀመርኩ። ይሁንና ስራው ይበዛ ስለነበር ተመልሼ መጣሁ። እንደአጋጣሚ ሆኖ ደብረሊባኖስ ስማር ያውቀኝ የነበረ አንድ መምህር በኬማርያም አስተዳዳሪ ስለነበሩ እዛ ጠርተውኝ ቅዳሴ ኪዳን እንድማር እድሉን ሰጡኝ።
አዲስ ዘመን፡- ግን በዛ ለጋ እድሜዎት ያለቤተሰብ ድጋፍ መቆየት አይከብድም?
አባ አክሊለማርያም፡- እይከብድም፤ በነገራችን ላይ እኔ እዚህ እስከምደርስ ስለምግብ እኔ አስቤ አላውቅም። አሁንም ቢሆን ቁርስ፣ ምሳ መብላት እኔ ጋር የለም። መክሰስማ በጭራሽ አይታሰብም። ከተገኘ ማታ አንድ ጊዜ እበላለሁ። ደግሞም ለምግብ አልቸገርም። ሁልጊዜ የሚጎድለኝ ፅድቅ ስለሆነ እኔ ዋናው እግዚአብሄርን የምለምነው የነበረው የጀመርኩትን መንገድ እንዲያበራልኝ ነው። አንድም ቀን ችግሬን ያስወግድልኛል ብዬ ወደ ሰው ተመልክቼ አላውቅም። እኔ ሁልጊዜ የምመለከተው ወደ ፈጣሪዬ ብቻ ነው። በእርግጥ እንደሰው ስታስቢው ማንም ሰው ያለ ስራ መኖር አይችልም። እኔ ግን ስራ አልነበረኝም። መኖር ብቻ ሳይሆን ትልቅ ቤተክርስቲያን እና ትልቅ መስጂድ እያሰራሁም ነው የምገኘው።
እንዳልኩሽ የእኔ ችግር ፅድቅ ማጣት ስለሆነ ሌሎቹን እንደችግር አልቆጥራቸውም። ብዙ ሰው አሁን ስራ ከሌለኝ፤ ምግብ ከሌለኝ እንዴት እኖራለሁ ይላል። እኔ እነዚህ ነገሮች ጥያቄዎቼ አይደሉም። ዋናው ጥያቄዬ ከእግዚአብሄር ጋር መሆን ነው። ከእሱ ጋር ከሆንኩኝ ደግሞ አልራብም፤ አልጠማምም። ማታ አንድ ጊዜ በፔስታል ከምግብ ቤት ገዝቼ እበላለሁ። በዚህም ምንም አይነት ሃዘን አይሰማኝም። ሊሰማኝ የሚችለው ግን ፅድቅን ሳጣና ሃጥያት ስናገር ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደነገሩኝ በሳይንስ ትምህርት ከፍተኛ ውጤትና አቅም ነበርዎት፤ ያንን አቅም ስራ ላይ ማዋል አለመቻልዎት ቁጭት አያድርቦትም?
አባ አክሊለ ማርያም፡- የሚገርምሽ
አሁንም እድሜዬ እዚህ ደርሶ እማራለሁ ብዬ ነው የማስበው። አብዛኛውን
ጊዜዬንም ያጠፋሁት በመማር ነው። በተለይም በመንፈሳዊ ህይወቴ ከስጋ ምኞት አምልጬ በመንፈስ ምኞት ጉዞ በመጀመሬ፥ ከአይን አምሮት ድኜ የነፍሴን አምሮት ለማሳካት መንገዴን ማቅናቴ፥ ከገንዘብ ትምክህት ርቄ የነፍሴን ትምክህት መከተል መቻሌ በራሱ ለእኔ ትልቅ ትምህርት ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ በመንፈሳዊ ህይወቴ የማደርገው ዝንባሌ እንዳውም ከሳይንሱም የሚበልጠው ጥበብ ነው። ይህ መንፈሳዊ ትምህርት ደግሞ ሰይጣንን ስለሚያሳይ አስተሳሰብን፤ አነጋገርን፤ ስራን ከእውነተኛው ከእግዚአብሄር ምንጭ ለማግኘት ስለሚያስችል ትልቅ ትምህርት ነው። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ቶሎ ቢሳኩ ኖሮ እኔ ቶሎ ወደ ሳይንስ ትምህርት እገባ ነበር።
በሌላ በኩል ግን በአሁኑ ዘመን በሃይማኖት አስተምህሮ የጎደሉ ነገሮች አሉ ብዬ አስባለሁ። ሃይማኖት ውስጣዊ መነሻም መድረሻ ነው። ይህንን ሃሳብ በምሳሌ ላስረዳሽ፤ አንድ ሰው የህክምና ትምህርት ሳይማር የሃኪም ጋዋን ቢያደርግ በሽተኛን ከመጉዳት የበለጠ ምንም የሚያመጣው ጥቅም የለም። እንዲሁም በመንፈሳዊ ህይወት ደግሞ ከስር ጀምሮ የመንፈሳዊ ህይወት ማዕረግ ሳይበለፅግ ልብሰተክኖውን ቢለብስ ሰው ከማሰናከል በስተቀር የእውነት መንገድን ሊያሳይ አይችልም። አንድ ዲያቆን ውስጡ ዲያቆን ከሆነ በውጭው የድቁናን ማዕረግ ሲለብስ አገልግሎቱ የተሟላ ይሆናል። አሁን በዘመናችን የጎደለን ይህ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ከሌሎች አባቶች ለየት ባለ መልኩ ካሉበት በቤተ-ዕምነት አልፈው መስጊድም እያስገነቡ ነው። ይህንን ለማድረግ ምን አነሳሳዎት?
አባ አክሊለማርያም፡- እንግዲህ ልጄ፤ አንቺም እንደምታውቂው ኢትዮጵያ ከዓለም ለየት የሚያደርጓት የበርካታ ታሪኮች ባለቤት ናት። በተለይም የእስልምና ሃይማኖት ነብይ የሆኑት የተከበሩት ነብዩ ሞሀመድ እስልምናን በ610 መካ ላይ ሲጀምሩ በዛው በመካ ባሉ ወጎናቸው ዘንድ ተቀባይነት አላገኙም። ቁርኤሾች እሳቸውንና ተከታዮቻቸውን እጅግ አድርገው ያስጨንቋቸውና ያሳድዷቸው ነበር። በ614 ላይ የቁርኤሾች ተፅእኖና ረብሻ እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ደረሰ። በዚህን ጊዜ ነብዩ ሞሃመድ ለተከታዮቻቸው ይህንን አባታዊ መመሪያ አስተላለፉ። ‹‹እናንተ እነሆ በኢስላም የምታምኑ አሁን እንግዲህ በዚህ መኖር አልተቻለም። ከዓለማችን ፍትህ ርትዕ ያለባት፥ ህዝቦቿ ፍቅር ያላቸው፥ በቀለም በእምነት ልዩነት ሳይሆን ሰውን የሰው ልጅ ነው ብለው ወደሚያምኑት የሃበሻ ምድር መሄድ ግድ ነው›› አሉ። ስለዚህ በዚህ አማካኝነት የመጀመሪያው ጉዞ ሂጅረቱል ሀበሻ (ጉዞ ወደ ሀበሻ) አደረጉ። በነገራችን ላይ እኔ የምነግርሽ ታሪክ ከራሳቸው ከሙስሊም ወንድሞቼ ቅዱስ መፃሀፍ ረሂቁል መክቱብ የሚባል የነብዩ መሃመድ ታሪክ ክፍልን ጠቅሼ ነው። እናም በዚያ ክፍል ላይ እንደተፃፈውበመጀመሪያው ጉዞ 12 ወንዶችና አራት ሴቶች ናቸው የመጡት። ከዚያ ውስጥ አንደኛዋ ሩቂያ የምትባል የራሳቸው የነብዩ መሃመድ ሴት ልጅ ናት። እኚህ አባት ልጃቸውን አምነው ወደ እዚህ አገር መላካቸው ከየትኛውም ዓለም የበለጠ ይህችን አገር እንዴት እንደሚወዷት ማስረጃ ነው።
በዚህ ምክንያት ቁርኤሾች አማኞቹ ሌሊት እንዳይወጡ ይጠባበቋቸው ነበር። እነሱ ግን አምልጠው ወደ ኢትዮጵያ መጡ። በመፃሃፉ ላይ እንደተፃፈው ቁርኤሾች ሙስሊሞችን ዱካ ዱካቸው እየተከተሉ ሲያሳድዷቸው በኢትዮጵያ ግን መልካም አቀባበል ተደረገላቸው። ይህ ታሪክ ዛሬም ድረስ ልቤን ይነከዋል። ምክንያቱም ጥንታውያን ኢትዮጵያውያን ምን አይነት እንግዳ ተቀባዮች እንደነበሩ በመረዳቴ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ምን እያሰበች ነው? በእውነት አንዱ ኢትዮጵያዊ ሌላውን ኢትዮጵያዊ በፍቅር መቀበል እኮ አልቻለም! አንዱ ክልል ሌላውን ክልል በፍቅር መቀበል አልቻለም። ውጣልኝ፤ አትድረስብኝ መባል ላይ ተደርሷል። እነዚያኞቹ አባቶቻችን ግን የማያውቋቸውን ሙስሊሞች በፍቅር ነው የተቀበሏቸው።
በሁለተኛውም የሂጅረቱል ሀበሻ ጉዞ 83 ወንዶች 19 ሴቶች የመጡ ሲሆን ቁርኤሾች ሙስሊሞች በሃበሻ ምድር ማረፊያ፥ መጠለያ፥ እንዲሁም እንደልባቸው ማምለክ መቻላቸውን ሲሰሙ የወርቅ እና የብር እጅ መንሻ ይዘው ሙስሊሞቹን ወደ መካ እንዲመልሷቸው ለንጉስ አርማ ጥያቄ አቀረቡ። ንጉሱ ግን ሁለቱንም በጠረጴዛ ዙሪያ ካወያየ በኋላ እውነቱን በመረዳቱ ቁሬሾችን የየዛችሁትን እጅ መንሻ ይዛችሁ በሳላም ሂዱ አላቸው። ከዚያ ወዲህ እንግዲህ ኢትዮጵያ የሙስሊምም አገር ሆነች። ይህ ታሪክ ለእኔ ልዩ ነው። አሁን ይህንን ታሪክ ስነግርሽ በዚህ ታሪክ አማካኝነት የኢትዮጵያውያኖችን መልካምነት ያሳያል። እርግጥ ነው ቅዱስ ቁርዓን የተፃፈው ስለሙስሊም ነው። ግን ቅዱስ ቁርዓን ላይ ስለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች መልካምነት ይገልፃል። ክርስቲያኖቹ ብቻ ሳይሆኑ በዘመኑ ይመሩ የነበሩ ቀሳውስቶችም ለህዝቡ ልዩነት የሌለው ፍቅር እንደሚያስተምሩ ቁርዓን ላይ ተቀምጧል።
እንግዲህ ልጄ እግዜር ያሳይሽ! ከዚህ ሌላ አንድነት አለ? ክርስርስቲያኖችም ብንሆን ወንጌላችን ባልንጀራችንን ብቻ ሳይሆን የሚያሳድዱንንም እንድንወድ፤ የሚረግሙንን መመረቅ እንዳለብን ያዘናል። ስለዚህ እኛ ክርስቲያኖች የጌታን ቃል መተግበር ይጠበቅብናል። መፃሃፍ ቅዱስ እንደሚለው ጌታ የሁሉ ፍቅር ነው። ይህ የሁሉ ፍቅር የሆነ ጌታ የመጣው ነጭን፥ ወይም ጥቁርን አልያም አንድ እምነት ሊያድን አይደለም። ጌታ የመጣው ለዓለም ነው። ይህ በሁሉም ክርስቲያኖች ዘንድ ሊታወቅ ይገባል። ክርስቲያኖች ጠባብ መሆን የለባቸውም። ስለዚህ መድሃኒያለም ያዘዘንን መፈፀም ይገባናል። ዛሬ ክርስቲያን ነኝ ብሎ ሌላውን ማጥላላት የለበትም። ሁሉም ራሱን ይመልከት።
አብዛኛው ክርስቲያን ክርስቶስን ትቷል፤ ብል አልተሳሳትኩም። እውነተኛ ክርስትና እንደእኔ ቀሚስ መልበስ፥ ቆብ ማድረግ፥ አንገት ላይ ክር ማሰር፥ በእጅ መስቀል መያዝ አይደለም። እንግዲህ ቅድም እንዳልኩሽ ንፅሃ ነፍስ ላይ የደረሱ አባቶች የሚኖራቸው ፍቅር ለሰዎች ሁሉ አንድ ነው። ነጭ የለ፤ ጥቁር የለ፤ ሙስሊም የለ፤ ፕሮቴስታንት የለ፥ ካቶሊክ የለ፤ ዋቄ ፈታ የለ፤ በቃ ለሁሉም የሰው ልጅ በመሆኑ ብቻ መውደድ ይገባናል። በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነው ፍቅር ነው። እንዲሁም ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንድኖር መፃፍ ቅዱስ ያዘናል። ከዚህ በተጨማሪም ሰዎች ሊያስቡል ሊያደርጉልን የምንፈልገውን ነገር እኛም እንዲሁ እንድናስብ እንድናደርግ ያዘናል። ይህ ለእኛ ማንዋላችን ነው። በዚህ ማንዋል መኖር የሁሉም ክርስቲያን ግዴታ ነው። ለዚህም ነው ጥንታውያን ክርስቲያኖች ይህንን ተግባር የፈፀሙት። እናም እኔ መስጊድ እንድገነባ ያነሳሳኝ ይህ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በተክርስቲያኑንም ሆነ መስጊዱን የመገንባት ሃሳብ በአንድ ላይ እንዴት ሊመጣልዎት ቻለ?
አባ አክሊለማርያም፡- ሐረርጌ የተወለድኩበትና ያደኩበት ስፍራ ቢሆንም እናቴና አባቴ የምላት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ነው። እዚያ ስፍራ ግን በ2007ዓ.ም ቁልቢ ገብርኤል እሳለማለሁ ብዬ ነው የሄድኩት። የላንጌ ቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያን ከቁልቢ በቅርብ ርቀት ላይ ስለሚገኝ በተመለከትኩበት ጊዜ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለማስተዋል ቻልኩ። እናም በወቅቱ ታዲያ ይህንን ችግር አይቶ ብቻ መሄድ ስላልሆነልኝ እዛው ያንን ችግር ለመቅረፍ ወደ ትግል ገባሁ። መጀመሪያ ንዋየ ቅድሳት አልነበሩም። በአንድ ዓመት ውስጥ ንዋየ ቅድሳቱ በሙሉ በጥሩ ሁኔታ ተሟሉልን። ከዚያም ወዲያውኑ ቤተክርስቲያኑ ወደ ሚሰራበት ስፍራ ተጓዝን። በአዲስ አበባ አገረ ስብከት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የራጉኤል ቤተክርስቲያን እንዲሰራ ደብዳቤ ከተሰጠኝ በኋላ በጥቂት ቦታዎች ባደረግነው እንቅስቃሴ በግለሰብ ክርስቲያኖች አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ 300 ሺ ብር መሰብሰብ ቻልን። አሁንም በበጎአድራጊ ክርስቲያን ባለሙያዎችና ባለሀብቶች ድጋፍ የቤተክርስቲያኒቱን አጥር ገነባን። የዋናውን ቤተክርስቲያንና ባለሁለት ፎቅ ህንፃ ግንባታ ጀመርን።
እናም ይህ ግንባታ በጥሩ ሁኔታ መሳካቱን ሳይ እግዚአብሄር እኛን እንዲህ ከረዳን በዛው አካባቢ ደግሞ በተመሳሳይ ችግር ውስጥ የነበሩ ሙስሊሞችን ለምን አንረዳም የሚል ሃሳብ መጣልኝ። እኛ ከትንሹ ይልቅ በትልቁ ቤተ- መቅደስ ማምለክ እንደምንፈልግ ሁሉ እነሱም የተሻለ መስጊድ እንደሚያስፈልጋቸው አመንኩ። የእኛን ቤተክርስቲያን ግንባታ እውን ያደረጉት በአዲስ አበባ ያሉ ጥቂት ክርስቲያኖች በመሆናቸው ብዙ ሀብታም ሙስሊሞች ለምን ሙስሊም ወንድሞቻችንን አይረዱም? በማለት እስልምና ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ማመልከቻ 2011 ዓ.ም መስከረም ላይ አቀረብኩ። በወቀቱ የነበሩት ፕሬዚዳንቱና ምክትሉ በጣም ደስ አላቸው። «ይሄ ትናንትና በኢትዮጵያ ነብያችን እስልምናን ይዘው ሲመጡ የነበረ እሴት ነው፤ ስለሆነም በደስታ ነው የምንቀበሎት» አሉኝ። እናም በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ፃፉልኝ። የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ፕሬዚዳንቱም «የእርሶ ደብዳቤ በእኔ ቲተርና በእኔ ፊርማ ነው የሚወጣው » አሉና በአዲስ አበባ በሚገኙ መስጂዶች ሁሉ ገንዘብ እንዳሰባስብ ፈቀዱልኝ።
የሚገርምሽ ከእኔ በፊት በርካታ ወረፋ የሚጠብቁ ሰዎች እያሉ በሄድኩበት መስጂድ ሁሉ እኔን ነው የሚያስቀድሙኝ። በእውነት ነው የምልሽ እኔ ስናገር ምዕመኑ እያለቀሰ ነበር ድጋፉን የሚያደርግልኝ። ይህንን በምመለከትበት ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬም ወንድማማችነትን የሚጠማ መሆኑን ለመገንዘብ ችያለሁ። እኔ ከሙስሊሙ ወገኖች ውጭ ኑር ብትዩኝ አልችልም። አሁን አሁን አንዳንድ ያልገባቸው ሰዎች ህዝቡን ልከፋፍል እያሉ ሲቸገሩ አያላሁ፤ ይህ ግን የሚሳካ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ሰውን በሰውነቱ የሚወድ ነው። ስለዚህ እኔ በየመስጂዶቹ ስዞር የሚሰጡኝ ፍቅር፥ እያለቀሱ የጥንቱ ወንድማማችነት ሊመለስ ነው እያሉ ምስጋና ሲያቀርቡ ከመስማት በላይ ለእኔ የሚያስደስተኝ ነገር የለም። አንዳንዶቹም እርሶ ዳግማዊ ዶክተር አብይ ኖት ይሉኛል። በእኔ ላይ እምነት ስላደረባቸው ነው አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 270 ሺ ብር ማግኘት ቻልኩ። አሁንም ግለሰቦች በተናጠል እየመጡ ድጋፋቸውን እየለገሱ ነው የሚገኙት። የማያውቀውን ሰው እንዲሁ አምኖ ገንዘብ የሚሰጠው ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ ምነኛ ውብ ነው?። እንደዚህ አይነት የማይጠረጥርና ለጋስ ህዝብ ከየትም ዓለም ብትሄጂ አታገኚም።
በህዝቡ ትብብብር የቢላል መስጂድ ግንባታ ተጀምሯል። በአሁኑ ወቅት ከመሰረት ባለፈ ምሰሶዎቹ ቆመዋል። ሰሞኑን እንዳውም ብረት ለመግዛት ብር በማሰባሰብ ላይ ነን ያለነው። በእዚህ አጋጣሚ እንግዲህ ሙስሊም ወገኖቼና እውነቱ የገባቸው ክርስቲያኖች በዚህ የአንድነት ምንጭ የመስጊድ ግንባታ ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ስል ጥሪዬን አቀርባለሁ። ምክንያቱም የምንሰራው መስጊድ ብቻ አይደለም፤ አገርን ጭምር እንጂ!። አሁን አገራችን ለገባችበት ችግር መፍትሄው ይሄ ነው። በእኛ አገር ያለው ልዩነት የሚጠፋው በዚህ መልኩ ስንደጋገፍ ነው። ስለዚህ እንዲተባበሩ በፈጣሪ ስም መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን መስጊድ የመገንባት ስራ ሲጀምሩ በተለይ እርሶ ከሚከተሉት ቤተ እምነት ተቃውሞ አላጋጠሞትም?
አባ አክሊለማርያም፡-
እንዳውም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖችን ከልቤ ነው የማመሰግናቸው። በተለያዩ መገናኛ
ብዙሃን አማካኝነት ያስተላለፍኩትን መልዕክት ተመልክተው በርካታ ክርስቲያኖች ይኖሩበታል ከሚባለው ጎንደር ሳይቀር በርካታ ምዕመናን
ድጋፋቸውንና ምስጋናቸውን ገልፀውልኛል። እርሶ ልዩነት የሌለውን ፍቅር በእውነት አሳይተውናል ብለውኛል። በሙስሊሙና በክርስቲያኑ
መካከል ልዩነት የሚያሰፉ ነቀርሳዎች አሉ። አሁንም እናገራለሁ እነዚህ ሰዎች አያልፍላቸውም። የኢትዮጵያ ህዝብን አንድ ማድረግ እና
እሴቱን ጠብቆ እንዲኖር ማድረግ ነው እንጂ የሚያዋጣው ሌላው ሀገርን ያፈርሳል። ምክንያቱም ከመሰረቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ያማረ ነው።
የእኛ አባቶች ሃይማኖታቸው እኮ የተለያየ ነው ፤ አስተሳሰባቸው ግን አንድ ነው። ይህ ነው ለእኔ እድገት!። ይሄ ነው ስልጣኔ!።
በእውነቱ እኔ አብዛኞዎቹ በተለይ አሁን የቢላል መስጂድ ኢማም የሆኑት ሼ አህመድ አብረን ስንሄድ ሻይ ቡና ስንባባል ሲያዩ በርካቶች
ይገረማሉ። ስንለያይ ደግሞ ስንተቃቀፍ ሲመለከቱ ይህንን ነው እኮ ያጣነው እያሉ አንዳንዶቹም ፎቶ ያነሱናል። ይህ የሚያሳየው አሁንም
ህዝቡ አንድነት በውስጡ መኖሩን ነው። እርግጥ ነው ከእኔም የሚበልጡ አባቶች አሉ። እነሱም እያደረኩት ባለሁት ስራ በጣም ደስተኞች
መሆናቸውን አውቃለሁ። ደግሞም ይህ ተግባር ለእኛ አዲስ አይደለም፤
የእምነታችን አንዱ ክፍል እንጂ!። በእርግጥ እምነቴ የግሌ ነው፤ ነገር ግን ፍቅሬ የመላው ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ነው። የቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ የሚያስተምረንም ይህንኑ ነው። ስለዚህ የጀመርነው ስራ እንደሚሳካ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ስራዎ በቢላል መስጊድ ይቆማል? ወይስ ይቀጥላል?
አባ አክሊለማርያም፡- የሚገርምሽ ቅድም እንደነገርኩሽ የእኔ አገልግሎት ቦታ በኬ ማርያም ነው። ምስራቅ ሀረርጌ ጥምቅተባህር ዋና ፃሃፊና ስብከተ ወንጌል ሃላፊ እንዳውም የሃገረ ስብከቱ ተንቀሳቃሽ ስብከተ ወንጌል ሃላፊ አድርገው መድበውኝ ነበር። ግን አንድ ወር ሳገለግል በዚህ ስራ ምክንያት ቅዳሜ ብቻ ነው የምሄደው። እኔ እግዚአብሄር በመራኝ እየዞርኩ ነው የማስተባብረው። ስለዚህ አንድ ቀን ብቻ አገልግዬ ሳምንቱን ሙሉ ከሚያገለግሉት ጋር ደመወዝ መውሰድ የማላውቀው ጭንቀት ያን ጊዜ ያዘኝ። ከዚያም በእኔ ቦታ ሌላ ሰው ተኩ ብዬ እንዲለቁኝ ጥያቄ አቀረብኩ። ከብዙ ውትወታ በኋላ አሁን ለቀውኝ በሙሉ ልቤ እያገለገልኩ ያለሁት የራጉኤልና የቢላል መስጂድ ግንባታ የሚጠናቀቅበት ሁኔታ ለይ ነው። ይህንን እንደጨረስኩ እንግዲህ የሚሆነው አይታወቅም።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ታዲያ ለመኖር የሚያስችሎትን ክፍያ ከየት ነው የሚያገኙት?
አባ አክሊለማርያም፡- እኔ ከየትም ምንም አላገኝም። እስቲ አንቺን ልጠይቅሽ፤ በእውነቱ ከዚህ የበለጠ ክፍያ አለ? ህዝቡ እኮ ለእንጀራ ሲኖር መንግስትም ተቸገረ። በአሁኑ ወቅት የእኛ ህዝብ በመንፈሳዊ ህይወቱ ወድቋል። እኔ ከሰው ፊት ቆሜ ለምኜ የእነዚህን ቤተ እምነቶች አስገንብቼ መጨረሴ በራሱ ከምግብም ሆነ ከምንም ነገር ይበልጣል። ምግቤን አላስታውስም። ምክንያቱም ፈጣሪዬ ምግብ የሚያዘጋጅልኝ ሰው ያዘጋጅልኛል። እኔ ገንዘብ ቢኖረኝ ሲጀመርም ከሰው አለምንም ነበር ። ራሴ ቤተክርስቲያኑንም ሆነ መስጊዱን እገነባው ነበር። እስቲ አንቺ ፍረጂ፤ ቤተክርስቲያን ገንብተሽ ሰዎች እግዚአብሄርን እንዲያውቁና እንዲያመልኩ ከማድረግ ሌላ ምን ትልቅ ነገር አለ። እንዲሁም ደግሞ እኔ እምነቴ ባይሆንም ቤተክርስቲያኑ በጥሩ ሁኔታ ሲገነባ መስጊዱ ጥሩ ቢሆን ደስ ይለኛል። ስለእምነታቸው እኔን አያገባኝም። በነገራችን ላይ በየመስጊዱ ስለግንባታው ሁኔታ ሳስረዳ ሃይማኖታዊ ትንታኔ ውስጥ በፍፁም አልገባም። እኔ የንግግር እርዕሴን የምጠቀመው እነሱ በሚገባቸው በአረብኛ ነው የምጠቀመው። እኔ የምፈልገው ሃይማኖት አይደለም። የእኔ እምነት ግን እንኳን ሙስሊሞች ወንድሞቼን የሚጠሉኝንም እንድወድ ነው ያዘዘኝ።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ መስጊድ በሚገነቡበት በዚህ ጊዜ በሌላ በኩል መስጊድንና ቤተክርስቲያኖችን የሚያቃጥሉ ሰዎች ተበራክተዋል፤ ይህ ተግባር ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?
አባ አክሊለማርያም፡- መቼም ከእኔ የበለጠ ብዙ መናገር የሚችሉ ሊቃውንቶች አሉ። በሙስሊሙም ዘንድ እንዳውም ስለሙስሊም ሃይማኖት በድፍረት መናገር ባልችልም በእርግጠኝነት ግን ልናገር የምወደው የክርስትናውን እምነት የሙስሊሙም እምነት አስተምህሮ እንኳን የሚያመልከበትን ስፍራ መኖሪያን ማቃጠል ፀያፍ ነው። መስጊድንም ማቃጠል ፈጽሞ የተከለከለ ነው። ስለዚህ እኔ ቤተክርስቲያንን የሚያቃጥል ሙስሊም እንዲሁም መስጊድን የሚያቃጥል ክርስቲያን አለ ብዬ በጭራሽ አላምንም። እኔ እኮ መስጊድ ለመገንባት የምጥረው እስልምና መልካምነት መሆኑን ከራሳቸው ቅዱስ መፃሃፍ ተገንዝቤ ነው። ቁርዓኑ መልካም ባይሆን ኖሮ እንዴት እዛ ውስጥ እገባ ነበር። ቁርዓኑ እንደሚለው አላህ እጅግ በጣም ደግና አዛኝ ከሆነ አማኞችም የአላህን መስመር የሚከተሉ ከሆነ እንዴት የክርስቲያኖችን ቤተክርስቲያን ሊያቃጥል ይችላል?። ስለዚህ ይህ ሰው ሴጣናዊ እንጂ ሙስሊም አይደለም።
ክርስቲያኖችም ደግሞ ክርስትና ማለት እንኳን የሚያመልክበትን ስፍራ ይቅርና መጽሀፍ እንደሚለው አርነት የወጣ አርነቱን ለክፋት መሸፈኛ ማድረግ አይጠበቅበትም። ክርስቲያን የክፋት ሰራዊት ሊሆን አይችልም። የክርስቶስን ፍቅር መሸፈን ነው። ክርስትና ማለት ሁሉን ማክበር ነው። ወንድሞችን መውደድ፥ ንጉስን ማክበር፤ እግዚአብሄርን መፍራት ነው። ስለሆነም ለክርስቲያኖች የማስተላልፈው መልዕክት ተጠንቀቁ የሚል ነው። ክርስቲያን ጠማማውን የሚያሸንፈው በፍቅር ነው። ክርስቲያን የእምነት ሰው እንጂ የታሪክ ሰው አይደለም። ዛሬ ክፉ የምንላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ክፎዎቹ ሊመለሱ ይችላሉ። ክርስቲያኖች እኛ እንጠንክር። ክፉዎች የሚመለሱት በእኛ ነው። ደግሞም እነዚህ ሰዎች ጠላቶቻችን አለመሆናቸው ልንገነዘብ ይገባል።
እኔ እንደአጠቃላይ መናገር የምችለው ቤተ እምነቶችን የሚቃጥሉት የእምነት ሰዎች ሳይሆኑ የጥፋት ሃይሎች ናቸው። ክርስትናም የከበረ እምነት ነው። መስጂድ የሚያቃጥሉና ግን ክርስቲያን ነን የሚሉ ስሙን ሊይዙ ይችላሉ ግን ክርስቲያኖች አይደሉም። የስሜትና የቃል ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በክርስትና የሚገድሉንም ሳይቀር ይቅር እንድልን ነው የሚያስገድደን እንጂ የሚወሰድ እርምጃ የለም። በእስልምናም እንዲሁ ነው። ስለዚህ ይህንን ተግባር የሚፈፅሙት የጥፋት ሃይሎችን ፀጥ ረጭ ማድረግ የምንችለው ሁላችንም ህብረት ሲኖረን ነው። በነገራችን ላይ የእኛ አገር በእውነቱ በጣም ታሳዝናለች! ከሃይለስላሴ ጀምሮ መሪዎች እየከፉ ነው የመጡት። በተለይም በኢህአዴግ ሥርዓት በጣም ነው የማዝነው። ይህንን መልካም ህዝብ ለማስተዳደር የመጣ መሪ ለህዝቡ መሞት ነው ያለበት። ራሱንና የራሱን ብሄር መውደድ የለበትም። ስለዚህ በኢትዮጵያ ያሳለፍነው ታሪክ ዴሞክራሲያዊ ነበር እያሉ ወሬ ያወራሉ ዴሞክራሲዋን ግን ንክች አያደርጓትም። ራሳቸውን ይወዳሉ። ይህች አገር አሁን እዳ በእዳ የተተበተበችው እነሱ በወሰዱት ብር ነው። በዚህ መልኩ ህዝቡን ለያዩት። የጥፋት መልዕክተኛ ሆኑ። እኔ መሪ በመሆናቸው አከብራቸዋለው። ያለፉት መሪዎች እድሉን ባለመጠቀማቸው ግን ያሳዝኑኛል። ደርግን አሸንፈው እንዲመጡ የረዳቸው እግዚአብሄር መሆኑን አውቀው ይህችንን ታሪካዊ አገር መለወጥ ይገባቸው ነበር። ታሪካዊ የሆነውን ህዝብ ወደ አንድንት ማምጣትም አልቻሉም። አሁን ደግሞ ያለውን አመራርም እጅጉን የላላ ነው። የዶክተር አብይ አካሄድ ጥሩ ነው፤ መለወጥ ግን አለበት። በፍቅር ለሚገዙ በፍቅር እንዲሄዱ ማድረግ እንጂ እንደህፃን ማባበል አያስፈልግም።
አዲስ ዘመን፡- እሹሩሩ ይብቃ እያሉ ነው?
አባ አክሊለማርያም፡- ሲጀመርም እሹሩሩ አያስፈልግም ነበር። በቃ መንግስት እኮ የራሱ ድርሻ አለው። ቤተክህነት የራሱ ድርሻ አለው። መንግስት ማድረግ የሚገባው ራሱ መሞት ነው። አንድ መሪ ራሱ ካልሞተ ይታወራል። መሪ ወደ ቀለም ወይም ወደ ብሄር የሚያደላ ከሆነ ይታወራል። ራሱን ነው የሚጎዳው። ስለዚህ ካለፈው ከ27 ዓመት ታሪክ መማር አለበት። እኔ ዝም ብዬ ወሬ ማውራት አልፈግም። ምክንያቱም የመሪነት ስራ ከባድ ነው። ዶክተር አብይን እወዳቸዋለሁ። አከብራቸዋለሁ። አሁን ያመጡትን ልዩነት የሌለውን አካሄድ እንዲገፉበት እኔም በፀሎቴና ባለኝ አቅም ሁሉ እደግፋቸዋለሁ። ግን አካሄዱ በትክክል በህግ የበላይነት መሄድ መቻል አለበት። ማንንም ሊፈሩ አይገባም። በተለይ ደግሞ ሁሉም ነገር የአደባባይ ሚስጥር በሆነበት ዘመን። አሁን ያለው አመራር ገና ለገና እከሌን ብንነካ ተከታዮቹ ይጮሃሉ ተብሎ የሚያደርጉት ነገር ራሳቸውን ነው የሚጎዳው።
እኔ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የማደንቅበት አንዱና ዋናው ጉዳይ በአቋማቸው የፀኑ ሰው መሆናቸው ነው። የአቋማቸውን ያህል ፍቅር ቢኖራቸው ኖሮ ሁልጊዜም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን እንዳደነቅን እንኖር ነበር። ስለዚህ ዶክተር አብይ ጠንካራ መሪ መሆን ይገባቸዋል። እሹሩሩ ሊኖር አይገባም። የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን እየተጎዳ ነው ያለው። ይቅርታ አድርጊልኝ ዛሬ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪ ይልቅ የመዋለህፃናት ተማሪ ተሽሏል። የሚማረውን ተማሪ ከፎቅ ላይ ወርውሮ መጣል ምን ይሉታል አሁን? ስለዚህ መንግስታችን አቋሙን ሊያስተካክል ይገባል። መንግስት እስከመቼ ነው የጥፋት ሃይሎችን እሹሩሩ የሚለው? በአጭር ጊዜ የህግ የበላይነት እስከሌለ ድረስ አገሪቱን በነበረችበት ማስቀጠል አይቻልም። ለአንድ መሪ ሹመት ላወቀበት ሺ ውበት ነው፤ ከላለወቀበት ሺ ሞት ነው።
እንግዲህ ልጄ አሁን ያለንበት ወቅት በጣም የሚያሳስብ ነው። ስለዚህ አዋቂዎች እንደመሆናቸው በህግ የበላይነት ነገሮችን ሁሉ ማስኬድ ይጠበቅባቸዋል። እስካሁን እሹረሩ የተባለው ይበቃል። እስከመቼ እየቀለድን እንኖራለን? አንድ ኢትዮጵያን የሚመራ መሪ ኢትዮጵያን እስከወደደ ድረስ አገሩን እንዳትጎዳ የራሱን ማንነት መጉዳት አለበት። የራሱን የስጋ ምኞት መጉዳት አለበት። የራሱን የአይን አምሮት መጉዳት አለበት። ህጉ የመታው መመታት አለበት። ህጉ የገደለው መሞት አለበት። በአሁኑ ሰዓት ምንም ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ህግ ማስከበር ነው።
አዲስ ዘመን፡-ለመጪው የገና በዓል እንደመሆኑ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎት?
አባ አክሊለማርያም፡- ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የማስተላልፈው መልዕክት የልደት በዓልን ስናከብር ከመብላት ከመጠጣቱና ከመልበሱ በላይ በቤተልሄም ስለእኛ ሲል የተወለደውን ኢየሱስ የእውነት በልባችን እንዲወለድና የእሱን አርዓያነት በተጨባጭ መከተል ይገባናል። በተለይም አሁን ያለውን የአገራችን ገፅታ ለመቀየር የአምላካችንን መስመር ልንከተል ይገባል የሚል መልዕክት ነው ያለኝ። ያለልዩነት አንዱ አንዱን መውደድና ማክበር ይጠበቅበታል። ይህ ሲሆን ኃይማኖታዊም ሆነ ሀገራዊ ግዴታችንን መወጣት እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አባ አክሊለማርያም፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012