ከበርካታ ባህላዊና መንፈሳዊ እሴቶቻችን አንዱ ሥነ-ቃል ነው። በተለይም እሴትነቱ ከአገራዊና ህዝባዊ ፋይዳው አኳያ ሲመዘን ከዚህ በመለስ ሊባል የሚችል አይደለም። ይህ ፅሁፍም “የሥነቃል ምንነት”ን እና “የስነቃል ፋይዳ”ን ባጭሩ፤ ምናልባትም በማስታወሻ መልክ እንዲመልስ ሆኖ የተዘጋጀ ነው።
በበርካታና ተደጋጋሚ ጥናቶች እንደተገለፀው የኢትዮጵያ ህዝብ ሲደሰትም ሆነ ሲከፋ ስሜቱን የሚገልፀው፣ በደል ሲደርስበት ብሶቱንና ቁጭቱን የሚወጣው በዘፈን፣ በቀረርቶ፣ በፉከራ፣ በእንጉርጉሮ፣ በለቅሶ ዜማና በመሳሰሉት፤ እሱ እራሱ በፈጠራቸው ቃል ጥበብ ውጤቶቹና ቃላዊ ቅርሶቹ አማካኝነት ነው።
“ሥነቃላዊ ቅርስ የማህበረሰቡን ወግና ሥርዓት፣ ባህልና ልምድ፣ እምነትና ፍላጐት በአጠቃላይ የኑሮ ዘይቤውንና ፍልስፍናውን ወዘተ አጠቃሎ የሚይዝ፤ የአንድ ማህበረሰብ ቁሳዊና መንፈሳዊ እሴት መግለጫ፣ የኑሮውና የስሜቱ ነፀብራቅ ነው።” የሚለው ያለተቃውሞ እዚህ የደረሰ የበርካታ የመስኩ ተመራማሪዎች ድምዳሜ ነው። ተጨማሪ ካስፈለገም የሰሎሞን ተሾመን “ፎክሎር፤ ምንነቱ እና የጥናቱ የትኩረት አቅጣጫ” መጽሐፍ ማየት ጠቃሚ ነው።
በተለይ እንደኛ ባሉ በኢኮኖሚ ታዳጊ አገራት የገበሬው ህይወት፣ የጤናው ሁኔታ፣ አለባበሱ፣ አኗኗሩ ወዘተ… እጅግ አሳዛኝና ከእጅ ወደ አፍ በሆነበት ድህነት፣ ብሶት፣ ፍትህ ማጣት፣ መበደል፣ ቁጭት፣ ወዘተ … የመሳሰሉት ስሜቶችና ችግሮች የሚገለጹበት አንዱ መንገድ ሥነቃል፤ በተለይም ቃል ግጥም ስለመሆኑ የብዙዎቻችን ስምምነት አለ።
መሰረቱ ቃላዊ የሆነውና በቃላዊ ተስተላልፎነቱ እዚህ የደረሰው ሥነቃል ከጥልቅ መልእክት አስተላላፊነቱ፣ የዘመን መንፈስ (Zeitgeist)ን ከመግለፁና ታሪክ ነጋሪነቱ፤ ትውልድን ከትውልድ ማጋመዱና ከመሳሰሉትም ባሻገር የማስተማር፣ ማስመለጥ፣ ማዝናናት፣ ማፅናት … ተግባራትን ሁሉ አጣምሮ የያዘ ማህበራዊ እሴት ነው።
ይሁን እንጂ የሥነቃልን ምንነትና ማህበረ-ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ተያያዥ ድርሻው ባደባባይ ሲገርለት ብዙም አይታይም። “አለ” ከተባለም ከጥቂት አካዳሚያዊ ስራዎች እና በሰዎች የእለት ተእለት ሀሳብ ልውውጥ ሂደት የሃሳብ ማጠናከሪያ፣ የንግግር ማሳመሪያ፣ የአድማጭ ትኩረት መሳቢያ … ሆኖ አገልግሎት ላይ ሲውል መታየቱ ነው።
ይህንኑ መነሻ አድርገን ማህበረሰቡ በስነቃል አማካኝነት ብሶቱን፣ የታፈነ ድምፁን፣ ብልሹ አሰራርን፣ ኢ-ፍትሀዊነትን ወዘተ እንዴት እንደሚገልፅ እንመልከት። ይህንኑም ለመመልከት ብዙ ጊዜ የሚደረገውን ወደ ኋላ ርቆ የመሄዱን ጉዳይ ተወት አድርገን ወደ ቅርቡ፤ ሥርዓት ላይ እንምጣና የህዝቡን ስሜትና ፍላጎት በተወሰነ አካባቢ ናሙናነት እንመልከት።
ኪሩቤል ዘሩባቤል የተባሉ ፀሀፊ ከ1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ በኋላ የምስራቅ ጎጃም ገበሬዎች የገጠሟቸውን ፖለቲካዊ ግጥሞች (እንጉርጎሮዎች) ያቀረቡ ሲሆን፤ ቃለ ግጥሞችንም ሰብስበዋል።
“የግጥሞቹ ዋነኛ ጭብጥ በወቅታዊ የገጠር አስተዳደርና በገበሬዎች ማህበራዊ ሕይወት ላይ የሚያተኩር ሲሆን በመንግስት ባለስልጣናት፣ በአገር አንድነት ጥያቄና በተለይም ደግሞ በ1989 ዓ.ም በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተካሄደውን የገጠር መሬት ሽግሽግ ፖሊሲ አፈፃፀምና ሽግሽጉ ያስከተለውን ተፅዕኖ. . .” የሚቃኙ ናቸው።
በተጨማሪም ባንድ በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በገጠሩ ማህበረሰብ ዘንድ እየተባባሰ የመጣውን መንግስትን የመጠራጠር፣ የእርስበርስ ጥላቻና ተቃውሞ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የምግብ እጥረት፣ የምርት ማሽቆልቆል፣ ድህነት፣ ስደትና በሰላም አብሮ የመኖር ተስፋ መጨለም ያሳሰባቸው መሆኑን የጎጃም ገበሬዎች ብቸኛ ሀብታቸው በሆነው ዘይቤያዊና ቅኔ ለበስ አማርኛ ቃለ ግጥም (Amharic oral poetry) ስሜትን የሚኮረኩሩና ልብን የሚነኩ መልዕክቶች የያዙ መሆናቸውን በምሳሌ አስደግፎ ያቀርባል።
በአብዛኛው የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዘንድ እንደሚስተዋለው ገበሬዎች ቃለ-ግጥምን፣ ዘፈንን፣ እንጉርጉሮን፣ ቀረርቶን፣ ፉከራን ወዘተ በዕለት ተዕለት ህይወታቸው በለዛና በዘይቤ እየቀመሩ ይጠቀሙበታል። ድንቅ በሆነ የቋንቋ ቅመራ ችሎታቸውም ግጥምን ለጀግና ሙገሳ፣ ለፈሪ ወቀሳ፣ ለኀዘን እንጉርጉሮ፣ ለተበዳይ እሮሮ፣ ለፍቅር መግለጫ፣ ለሀሜት ማሽሟጠጫ፣ ለችሎት ምልልስ፣ ለአቤቱታና ክስ ወዘተ ለዘመናት ሲገለገሉበት መኖራቸውን የሚናገረው ኪሩቤል “የገበሬዎቹ ስነልቦናዊ አስተሳሰብ፣ ባህላዊ ዕውቀትና ስለአካባቢ ያላቸው ጥልቅ ግንዛቤ፣ ስለባህላዊ ዳኝነትና አስተዳደር፣ ስለልማትና መሬት አያያዝ ወዘተ የሚያቀርቧቸውን ሐሳቦች የሚገልፁበት አንዱ መንገድ ለዘመናት ባካበቱት የሥነቃል ቅርስ አማካኝነት በመሆኑ፣ በማህበራዊ ሳይንስና በገጠር ልማት ተመራማሪዎች፣ በስነትምህርት፣ በስነሰብእና፣ በስነቃል ምሁራን፤ እንዲሁም በመንግስት ፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በጥንቃቄ መሰብሰብና በጥልቀት መጠናት እንዳለበት” ምክረ-ሃሳቡን ይሰጣል።
ፀሀፊው በጥናቶቹ ያካተታቸው ቃለ ግጥሞች ዋነኛ ጭብጥ በወቅታዊ የገጠር አስተዳደርና በገበሬዎች የግልና ማህበራዊ ሕይወት ላይ የሚያተኩር ሲሆን በመንግስት ባለስልጣናት፣ በአገር አንድነት ጥያቄና በተለይም ደግሞ በ1989 ዓ.ም በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተካሄደውን የገጠር መሬት ሽግሽግ ፖሊሲ አፈፃፀምና ሽግሽጉ ያስከተለውን ተፅዕኖ የሚቃኙ መሆናቸውን ገልፇል። ከመሬት ጋር በተያያዘም፡-
አሥራት ቀረ ብዬ አርፌ ስተኛ
ኮር ቀረ ብዬ አርፌ ስተኛ
የኮር አባል መጣ የባሰው ቀማኛ
መሬቴን ወሰደው ሰፍሮ በመጫኛ።
ጣሊያን አልመጣብን ተኩስ አልተተኮሰ
ወይ ወራሪ አልመጣ ችግር አልደረሰ?
በኮር የተነሳ አገሩ ፈረሰ።
ወትሮም ነገረኛ ነበር ተጥንት
ኮር ነው ያስቸገረን ጠማማው እንጨት።
እኔስ አርስ ነበር የገበሬው፣ የገባሩ ልጅ
መሬቴን ቢለኩት ቢወስዱት ነው እንጅ።
የሚለውን ቃል ግጥም በምሳሌነት ወስዶ የተነተነ ሲሆን፤ በትንታኔውም “ገጣሚው (መሬቱ የተወሰደበት ገበሬ) ከመንግስት አገዛዝ፣ ከመሬት ሥሪት፣ ከግብር እና ከመዋጮ ጋር የተያያዙ ሦስት ታሪካዊ እውነታዎችና የመንግስት አገዛዞች ያነፃፅራል። የመጀመሪያው ግጥም በአፄው ዘመነ መንግስት የነበረውን የ“አስራት” ክፍያ፤ ሁለተኛው በደርግ አገዛዝ የነበረውን እህል በግዳጅ የመነጠቅን ወይም “ኮታ”ን – “አረፍሁ” ብሎና ተስፋ አድርጎ የነበረበትን፤ ሶስተኛ በዘመነ ኢህአዴግ “የኮር አባል” የሚባል ካድሬና ከበፊቶቹ “የባሰ ቀማኛ” መጥቶ መሬቱን በመጫኛ ሰፍሮ እንደወሰደበት ምሬቱን” የገለፀበት ቃል ግጥም መሆኑንም ይናገራል።
“የኮር አባላት በመሬት ሽግሽጉ ወቅት ገበሬውን በማንገላታት፣ እርስ በርስ በማጋጨትና መሬቱን በመውሰድ፣ ለኢህአዴግ መንግስት ታማኝነታቸውን ያስመሰከሩ “የቁርጥ ቀን ልጆች” መሆናቸውንና እነዚህ የኮር አባላትም ለአገሩ መፍረስ ተጠያቂዎች” መሆናቸውን በትንታኔ የደረሰበትና ቃለ ግጥሙ የሚያስተላልፈው ዋና መልእክት እንደሆነም ፀሀፊው አመልክቷል።
እንደ ኪሩቤል ዘሩባቤል ድምዳሜ ከረጅሙ በተከታታይ ሥልጣን ላይ የወጡ መሪዎች (መንግሥታት) ገበሬውን በግብር፣ በመዋጮ፣ በዘመቻና በልዩ ልዩ የጉልበት ሥራዎች ከማዋከብ በስተቀር የተሻለ ሕይወት እንዲመራ አላስቻሉትም። ሌላው ቀርቶ በዚያው ኋላቀር በሆነው የእርሻ መሣሪያ እንኳ መሬቱን አርሶ፣ ቤተሰቡን እንዳይመግብ በየጊዜው የሚወጡት የመሬት ይዞታ ፖሊሲዎችና አዋጆች እንዲሁም የመንግስት ሹማምንት ያደረሱበትና እያደረሱበት ያሉት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሰብአዊ፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ በደል መሪር ሲሆን ሁሉንም መዘርዘር ያስቸግራል።
ስናጠቃልለው፤ ሥነቃል መነሻውም ሆነ መድረሻው ሰውና ሰብአዊነት ነው። ፋይዳውም ሰብአዊ ሲሆን ተግባሩም አንደበት የመሆን፤ ለታፈኑ ድምፆች ድምፅ ነው።
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 24/2012
ግርማ መንግሥቴ