የአፍሪካ ሪፖርት በ2020 (እኤአ) በመላው አፍሪካ በሚካሄደው ምርጫ ምን እንመለከታለን? የሚሉ ትንበያዎችን አስደግፎ በርካታ ጽሁፎችን አውጥቷል። አፍሪካና ከፊት ለፊቷ የተደቀኑት ብሔራዊ ምርጫዎች ዛሬም በስጋትና ተስፋ ተከበዋል ይለናል የአፍሪካ ሪፖርት ባስነበበው ትንታኔ።
ለአፍሪካ ምርጫ ተቆጣጣሪዎች በብሩንዲ፤ ኮት ዲቯርና ሱዳን የሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ የሰላም ድባብ የሰፈነበት ይሆናል ብሎ መገመት ይከብዳል። ቀዳሚ ዜናዎቻቸው በሙሉ በነበሩ የእርስ በእርስ ጦርነቶች የተሞሉ ናቸው። ተተኪው ማን እንደሆነ አይታወቅም። በአካባቢው የውስጥ ግጭቶች አሉ። በዚህ ጽሁፍ ስር ያልተሸፈነችው ጊኒ በመሬት ላይ ያሉ ውጥረቶችን በማስወገድ የምርጫ ቀኑ ከምንም ተቃውሞና አቤቱታ ነጻ እንዲሆን ለማድረግ እየሰራች መሆኗ ነው። በመጪው ጊዜ በአፍሪካ የምንከታተላቸውን ዋነኛ ምርጫዎችና አዲስ የጀመርነው የ2020 (እኤአ) ትንበያ እንቃኛለን።
በጋና ለፕሬዚደንትነት የስልጣን ወንበር በታህሳስ 2020 (እኤአ) ምርጫ ይካሄዳል። የጋና ዋነኛው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ የቀድሞው ፕሬዚደንት ጆሀን መሀማ የአሁኑን ፕሬዚደንት ናና አኩፎ አዶን እንዲፎካከሩ መርጧል። በዚህም መሰረት ሁለቱ መሪዎች ዳግም በሶስተኛው ምርጫ ይፋጠጣሉ። ምርጫው ውጤት ለማስመዝገብ የሚደረግ ከፍተኛ ፍልሚያ የሚካሄድበት እንደሚሆን ይጠበቃል። በዚህም ጋናውያን በመጪው አራት ዓመታት የበለጠ ማን እንደሚመራቸው ይወስናሉ፤ ይመርጣሉ።
የብሔራዊ ዴሞክራቲክ ኮንግረሱ መሀማ ወደስልጣን የመጡት የቀድሞው ፕሬዚደንት ጆን አታ ሚልስ በሐምሌ 24/2012 (እኤአ) ከሞቱ በኋላ ነበር። በኋላም በታህሳሱ 2012 (እኤአ) ምርጫ አኩፎ፤ አዶን አሸንፈዋል። እንደገናም መሀማ በ2016 (እኤአ) ምርጫ ተሸንፈዋል። የሽንፈታቸው ምክንያት አስተዳደራቸው ከሚገባው በላይ ወጪ በማባከኑ፤ በበጀቱ ውስጥ የ 1.6 ቢሊዮን ዶላር ጉድለት በመታየቱ ነበር። የመሀማ አስተዳደር በሙስና፤ በበጀት ጉድለት፤ ኢኮኖሚው ያልተረጋጋ በመሆኑና ሌሎችም በርካታ ክሶች ቀርበውበት ነበር ይለናል የአፍሪካ ሪፖርት ዘገባ።
የመሀማ ደጋፊዎች የሸቀጦች በተለይ የካካዎ፤ ወርቅና ዘይት ዋጋ ማሽቆልቆል በ2016 (እኤአ) ለተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስና ፈተና ምክንያት ነበር ይላሉ። የአንዳንዶቹ ሸቀጦች ዋጋ ተመልሶ ማንሰራራቱን ይገልጻሉ። ይህ የደጋፊዎቻቸው አስተያየት የመሀማን አስተዳደር ለመከላከል በቂ አልነበረም።
ኢኮኖሚው ከሁሉም በላይ የሕዝቡን ትኩረት ይስባል። አኩፎ አዶ በአሁኑ ሰአት ለ2020 (እኤአ) ምርጫ ጠንካራ የሆነ ኢኮኖሚ እየመሩ ይገኛሉ። የኢኮኖሚ እድገቱ በአማካይ በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው 6% ደርሷል። የዋጋ ግሽበቱ ወርዶ በስድስት ዓመታት ውስጥ ዝቅ ብሎ ታይቷል። የነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪው በተሻለ ደረጃ አንሰራርቷል። አኩፎ አዶ የጋናውያንን ፍርሀትና ስጋት በመቀነስ ረገድ ቀደም ሲል የገቧቸውን አንዳንድ ቃሎች ባለመፈጸማቸው ጥቂት ፈተናዎች ሊገጥሟቸው ይችላሉ።
የገቢ እጥረት መስተካከልና የወጪ መቀነስ ከሚ/ር አኩፎ አዶ ፓርቲ ይጠብቁ ነበር። በርካታ ጋናውያን ብዙ የስራ መስኮችንና ሰፊ መሰረተ ልማቶችን አሁን ከአዲሱ አርበኞች ፓርቲ (ከኤን ፒፒ) ይጠብቃሉ።
ማን ያሸንፋል የሚለው ጥያቄ በምርጫዎች ሁሉ ይነሳል። የጋና ምርጫዎች ሁል ጊዜም ዝግ ናቸው። ስለዚህም የሚታይ ድል አትጠብቁ። አሁንም ራሳቸው ፕሬዚደንት አኩፎ ዳግም መመረጥን ካልፈለጉ ወይንም እጩ ሆነው ባይመረጡም ጭምር ባስመዘገቡት የኢኮኖሚ እድገት ሪከርድ ብቻ በጣም ለድል (ለአሸናፊነት) የቀረቡ ናቸው። ኤንዲሲ ፓርቲ አዲስ ፊት ለማስተዋወቅ ባለመቻሉም እድሉን ያጣል።
የጋና የፖለቲካ ታሪክ በአብዛኛው የሚያስተምረን አብዛኛዎቹ አሸናፊ እጩዎች ባለፉት ምርጫዎች የሕዝብ ድጋፍ ያጡ ናቸው። ይህም በመሆኑ ስማቸውን ወደፊት ለሚደረገው ምርጫ ሲሉ ያወጣሉ። ይህ አይነቱ አካሄድ በተለይ ለኤንዲሲ እጩ ምርጫ ሊጠቅም ይችላል።
የታንዛኒያን ምርጫ በተመለከተ የፓርላማ አባል የሆነው ሚቴራ ሉሲንዴ እያዘነም ቢሆን በጥሩ ሁኔታ ለገዢው ፓርቲ ባልደረቦቹ ታንዛኒያ ውድ የሆነ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በ2020 (እኤአ) የምታካሂድበት ምክንያት የላትም። ምክንያቱም ማንም ፕሬዚደንት ጆን ፖምቤ ማፉሊን ማሸነፍ አይችልም ሲል ነግሯቸዋል።
ሊሲንዴ በተጨማሪም ለ2020 (እኤአ) ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የተያዘው ገንዘብ ለልማት ፕሮጀክቶች ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል ብሏል። ቻማ ቻ ማፒንዱዚ ፓርቲ ሁለተኛው ግዙፍና ረዥም ጊዜ በአፍሪካ ያስተዳደረ ፓርቲ ነው። ከደቡብ አፍሪካው ብሄራዊ ፓርቲ ቀጥሎ። ማጉፉሊ በዳግም ምርጫ ሊመረጡ ይችላሉ የሚለውን ምናልባታዊነት ሉሲንዴ ሙሉ በሙሉ አልሰረዘም። ሆኖም ግን አንዳንዶች እንደሚያስቡት ያን ያህል ከፍተኛ አይደለም። በታንዛኒያ ተቃዋሚዎች ያላቸውን የድጋፍ ደረጃ መገመት ቀላል አይደለም። በአጠቃላይ በቅድመ ምርጫ ጊዜ ነው የሚያካሂዱት። ,
ተቃዋሚው ፕሬዚደንታዊ እጩ ኤድዋርድ ሎዋሳ የቻማ ቻ ዴሞክራሲያ ና ማኤንዴሎ( ቻዴማ) ፓርቲን ወክለው ይወዳደራሉ። በ2015 (እኤአ) ምርጫ ሲሲኤም ፓርቲ ማጉፉሊን ለምርጫ ሲያቀርብ ሎዋሳ ከሲሲኤም ፓርቲ ለቀው ወጥተዋል። በቅድመ ምርጫ ድምጽ መስጫ በ2015(እኤአ) 25% እና 30% ድጋፍ ያገኙ ናቸው። በትክክለኛው ምርጫ ወቅት ደግሞ 40 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል። እነዚህ ቁጥሮች ቢያንስ የሚያሣዩት ለተቃዋሚ እጩ ድጋፍ መኖሩን ነው። በተለይም በአካባቢው ‹ቲንክ ታንክ› በመሆን የሚንቀሳቀሰው የቲዋዌዛ ቡድን በ2018 (እኤአ) ያካሄደው ጥናት ፕሬዚደንት ማጉፉሊ ያላቸው የህዝብ ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ እንደቀነሰ ያሳያል።
ሥርዓቱን የሚተቹና የሚነቅፉ ድምጾች ፀጥ እረጭ እንዲሉ ተደርጓል። የቱዋዌዛ ቲንክ ታንክ ቡድን በጥናቱ የደረሰባቸው ቁጥሮች በ2018 (እኤአ) የማጉፉሊ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ከነበረበት 71 በመቶ ወደ 55 በመቶ ማሽቆልቆሉን ያሣየ ሲሆን ይህ ደግሞ ከጀርባ ሆነው ማጉፉሊን ለመፎካከር ለሚጠብቁት ተስፋ አሳድሮባቸዋል። ሪፖርቱ በታንዛኒያ ለምን ተቃዋሚው በከባዱ እንደሚደፈቅም ምልክት ሰጥቷል።
የቱዋዌዛ ሪፖርት መለቀቁን ተከትሎ ዳይሬክተሩ አይዳን ኢያኩዙና ሌሎችም ባልደረቦች ማስፈራሪያና ዛቻ ደርሶባቸዋል። ፓስፖርታቸው ተወርሷል። የዜግነት ደረጃቸው ምርመራ እየተደረገበት ይገኛል። ጋዜጠኛ ኢሪክ ካቤንዴራ ማጋፉሉን በመውቀስ ድምጹን በማሰማቱ በአሁኑ ወቅት በዜግነቱ ላይ ማጣራትና ምርመራ እየተደረገ ሲሆን እንደገናም ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እስከ የተደራጀ ወንጀልን ማገዝ (መርዳት) የሚል ክስ ተመስርቶበታል።
ሁሉንም ትችቶች ወደጎን ይዞ ሲታይ ዛሬም ማጉፉሊ ጠንካራ ድጋፍ አላቸው። በታንዛኒያ የንጹህ ውሃ ተጠቃሚዎች ቁጥር ጨምሯል። የተሻለ የጤና አገልግሎት የሆስፒታል አልጋዎችና መድሃኒቶችንም ጭምር ያገኛሉ። በአብዛኛው የገጠር ነዋሪዎችና ጥቂት የከተማ ነዋሪዎች ታንዛኒያ ውስጥ በውጭ ዜጎች በተያዙ አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ላይ ማጉፉሊ የወሰዱትን እርምጃ ያደንቃሉ። በ2020 (እኤአ) በሚካሄደው ምርጫ ማጉፉሊ እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል። ምናልባትም ተቃዋሚው ሊሳካለትም ይችላል።
የአፍሪካ ሪፖርት እአአ በ2020 በአፍሪካ የሚካሄዱ ሁሉንም ምርጫዎች እኩል ትኩረት ሰጥቶ አልዘገባቸውም። ከእነዚህ ምርጫዎች ውስጥ ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ይገኝበታል።
ወንድወሰን መኮንን
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 23/2012