አፍሪካ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2019 ድህነቷ ባይጠፋ ችግር ቀንሶላታል። ፖለቲካው፣ ግጭቱ፥ ቁርቁሱ እና ውዝግቡ ባይወገድላትም፣ በመጠኑም ቀሎላታል። ዜጎቿ በሚፈልጉትና በሚገባቸው ልክ ሰላም፣ ፍትህ፥ ዕድገት ብልጽግና ባይሰርፅባት መሻሻልም አሳይታለች። አህጉሪቱ በዓመቱ ባስተናገደቻቸው በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ክስተቶች ጥሩም መጥፎም ዜናዎች ተሰምተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት፤ ዓመቱ ለአህጉሪቱ ሙሉ በሙሉ የብርሃን ባይሆንም፣ ጨለማም አልነበረም።አንዳንድ ሁነቶች የደስታ ሌሎች ደግሞ የሐዘን ነበሩ። ደስታን የሚፈጥሩትን በማስቀደም አንዳንድ ሁነቶች በወፍ በረር ስንቃኝ ለዓመታት በመንበረ ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ጉምቱ መሪዎች የተሰናበቱበትን ሁኔታ መጥቀስ እንችላለን።ዓመቱ የአህጉሪቱ ልጆች አንድነት ሃይል፤ ሕብረትም የድል ምስጢር መሆኑን በቅጡ በመረዳት ለዘመናት ሥልጣን ላይ የቆዩ መሪዎቻቸውን በቃችሁ ያሉበት ሆኖም ተስተውሏል። ለዚህ ደግሞ ሱዳን ቀዳሚ ምስክር ናት፡፡
አፍሪካዊቷን ግዙፍ ሀገር ሱዳን እ.ኤ.አ ከ1989 አንስቶ ለሦስት አስርት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት የመሩት ኦማር ሐሰን አልበሽር በዳቦና ነዳጅ ዋጋ መናር ሳቢያ ‹‹በቃዎት›› በሚል ህዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን የወረዱት ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት ነው፡፡
አልጀሪያን ለ20 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት የመሯት የ82 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ አብዱልአዚዝ ቡቶፍሊካ ከተሳናባቾቹ መሪዎች ተርታ ስማቸው ይጠቀሳል። ቡቶፍሊካ ለ5ኛ ዙር ምርጫ ለመወዳደር ፍላጎት ማሳየታቸውን ተከትሎ ከአገሬው ህዝብ በደረሰባቸው ጠንካራ ተቃውሞ መንበረ ሥልጣናቸውን ሳይወዱ በግድ እንዲለቁ ተደርገዋል፡፡
ከአዛውንቶቹ መሪዎች ስንብት ባሻገር ትክክለኛ ምርጫ ማካሄድ በሚፈራበት ከተካሄደም ሽንፈቱን በፀጋ ከመቀበል ይልቅ መንግሥት ወይም ገዢውን ፓርቲ አጭበርብሯል ብሎ ደጋፊዎቹን ወደ ጎዳና ማስወጣትና መውጣቱ በተለመደባት እንዲሁም ከሐሳብ ይልቅ ጉልበት በሚቀድምበት አህጉር፣ ባሳለፍነው ዓመት በተለያዩ አገራት ምርጫዎችም ተካሂደዋል፡፡
ምርጫ ሲነሳ ደግሞ ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ በቅድሚያ ትጠቀሳለች። በማዕድን ሀብቶች የናጠጠችውን አገር እ.ኤ.አ በ2001 የአባታቸውን መገደል ተከትሎ አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት በመምራት ለ18 ዓመታት የመሩት ጆሴፍ ካቢላ፣ ሳይወዱ በግድ በህዝብ ምርጫ ሥልጣናቸውን ተነጥቀዋል። አገሪቱ ከቅኝ ገዥዋ ቤልጄም ነፃ ከወጣችበት 1960 ወዲህ የመጀመሪያውን ሰላማዊ የሥልጣን ርክክብ ባደረገችበትና እ.ኤ.አ ባለፈው ታህሳስ 30 በተካሄደው ምርጫም የተሻለ የህዝብ ድምፅ አግኝተዋል ያለቻቸውን ፌሊክስ ሽስኬዲ ፕሬዚዳንትነት አድርጋ መርጥለች፡፡
ይሁንና በሀብትና ንብረቷ የዜጎቿን ሕይወት መለወጥ የተሳናትና በአሁኑ ወቅት ድህነት ጥርስ አግጥጦ ከሚታይባቸውና ፍትሐዊነት ከማይታይባቸው አገራት ከግንባር ቀደሞቹ የምትሰለፈውን አገር ለመምራት የተመረጡት የ56 ዓመቱ ፌሊክስ ሽስኬዲ መንግሥት የካቤኔ አወቃቀር በርካታ ቅሬታዎች ይቀርቡበታል። ይህን የተመለከቱ ወገኖችም ካቢላ ሥልጣን ለቀቁ ቢባልም በጓሮ በር መልሰው እጃቸውን አስገብተዋል በሚል ይተቻሉ፡፡
ናይጄሪያም ሌላኛዋ ምርጫ ያስተናገደች አገር ናት። በነዳጅ ሀብት በናጠጠችው በዚህች አገር በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ሙሃመዱ ቡሃሪ በድጋሚ ተመረጠዋል። ምንም እንኳ ተቀናቃኛቸው ቅሬታ ቢኖራቸውም፣ ፕሬዚዳንቱ ግን ለሌላ አራት ዓመት ለሥልጣን ያበቃቸውን ድምፅ ማግኘት ችለዋል።
ዓመቱ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ገዢው ፓርቲ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ በሥልጣን የሚያቆውን ድምፅ ያገኘበትም ሆኗል። ከጃኮብ ዙማ ስንብት በኋላ በሲሪል ራማፖሳም እየተመራ በምርጫው 57 ነጥብ 5 በመቶ ድምጽ ያገኘው ገዢው ፖርቲ፣ አገሪቱ ከአፓርታይድ አገዛዝ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ለ25 ዓመታት መርቷል።
ዓመቱ በሴኔጋል በተካሄደው ሁለተኛ ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ -ማኪ ሳል የሥልጣን ቆይታቸውን ያራዘሙበት ሆኖም አልፏል። የ57 ዓመቱ ማኪ ሳል ከተሰጠው ጠቅላላ ድምፅ ውስጥ 58 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆነውን ተቀዳጅተዋል። በምርጫው ፍልሚያ ለሦስተኛ ጊዜ በዕጩነት የቀረቡት የ85 ዓመቱ ፕሬዚዳንት አብዱላይ ዋድ ሽንፈታቸውን በፀጋ በመቀበል አህጉሪቱን ከዲሞክራሲ ልዕልና ጋር ካስተዋወቁ ግለሰቦች ተርታ ስማቸውን አጽፈዋል፡፡
ሰሜን አፍሪካዊቷ አልጄሪያም ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ካካሄዱት አገራት መካከል ስሟ ጎልቶ ይነሳል። አልጄሪያን ለ20 ዓመታት የመሯት የ82 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ አብዱልአዚዝ ቡቶፍሊካ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ በተካሄደው ምርጫም የ74 ዓመቱ አዛውንት የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አብደልማጂድ ቴቡኔ ማሸነፋቸውን የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ይፋ አድርጓል።
ይሁንና ምርጫውን በመቃወም በመዲናይቱ አልጀርስና በተለያዩ ከተሞች በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተዋል። ተቃዋሚዎች አብደልማጂድ በአልጄሪያውያን የተጠሉት የቀድሞው ፕሬዚዳንትና አስተዳደራቸው አካል እንደነበሩ በመጥቀስ በእሳቸው ላይ እምነት እንደሌላቸው ሲናገሩም ተደምጠዋል፡፡
አህጉሪቱ ካስተናገደቻቸውና በአሳዛኝነታቸው ከሚታወሱት መካከል ደግሞ ከወደ ዙምባቤዌ የተሰማው ዜና ቀዳሚ ሆኖ ይጠቀሳል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1924 የተወለዱት ሮበርት ሙጋቤ ዚምባብዌን እ.ኤ.አ በ1980 ነፃነቷዋን ከተጎናፀፈችበት ጊዜ አንስቶ የመጀመሪያው መሪ በመሆን አገሪቱን ለ37 ዓመታት መርተዋል።
ምዕራባውያንን አጥብቆ በመተቸት የሚታወቁት ሙጋቤ ከሁለት ዓመታት በፊት በሀገሪቱ ወታደራዊ ኃይል ከሥልጣን መወገዳቸው ይታወሳል። ሙጋቤ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት በህመም ሳቢያ በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትም በዚሁ በሳለፍነው ዓመት ነው፡፡
የአየር ንብረት ለውጥም የዓመቱ አፍሪካ ፈተና ሆኖ ታይቷል። በደቡባዊ አፍሪካ አገራት የተከሰተው ከባድ ዝናብና አውሎ ንፋስ ተራራ እየናደ መኖሪያ ቤቶችን እስከ መቅበር ደርሷል። ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት ወድመዋል። ከአደጋው የተረፉትም ኮሌራን ለመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች ተጋልጠዋል። ሞዛምቢክ ዚምባቡዌና ማላዊን የመሳሰሉት አገሮች አደጋው ባስከተለው ጉዳት የዜጎችን ሕይወት ተነጥቀዋል፤ ኢኮኖሚያቸውም ክፉኛ ተፈትኖባቸዋል።
ከጎርፍ፣ ድርቅና ረሃብ ፈተና ባሻገር አህጉሪቱ በሽምቅ ታጣቂ አሸባሪዎች ምክንያት ዜጎቿ ተሰውተዋል፤ ንብረቷም ወድሙአል። በተለይ ድንበር የሚጋሩት ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር የመሳሰሉት አገራት በአሻባሪዎች ቡድን ሰላማቸውን እያጡ ዜጎቻቸውን በተደጋጋሚ ተነጥቀዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2014 የተከሰተውና እስካሁን 11ሺ ለሚሆኑ ዜጎች ህልፈት ምክንያት የሆነው ኢቮላም ባሳለፍነው ዓመትም በተለይ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ከባድ ራስ ምታት ሆኖ ታይቷል። በተለይ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የኢቮላ ቫይረሱ እንደገና በተቀሰቀሰ በአንድ ዓመት ውስጥ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሺህ 200 በላይ ደርሷል፤ ከ3 ሺህ በላይ ዜጎች በቫይረሱ መያዛቸውም ታውቋል፡፡
ትናንትን በወፍ በረር ባስታወስናቸው መሰል ሁነቶች የሸኘችው አፍሪካ፣ ከአሮጌው ማንነት በተሻለ በአዲሱ ዓመት የሰላም፣ ፍትህ፥ ዕድገትና ብልጽግና አህጉር ትሆን ዘንድ በበርካቶች ምኞትና ምርቃት ታጅባ ለዜጎቿ ለቅሶ ሳይሆን ፍስሐን ለማምጣት ወደፊት መራመዷን ጀምራለች።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም
ታምራት ተስፋዬ