እዚህ ቦታ ላይ ሰማይንም መሬትንም ማየት አይቻልም።ወደላይም ተመልከት ወደታች የምታየው ጥቅጥቅ ደን ነው።ይገርምሃል ከዛፎች ሥር እንኳን መሬት ማየት አትችልም፤ የምታየው ጥቅጥቅ የሳር አይነቶችና ትንንሽ የቅመማቅመም ተክሎች ነው።ከትልቅ ዛፍ ሥር ትንንሽ ዛፍ ማለት ነው።ለካ ተፈጥሮ እንዲህ ናት ያሰኛል።እያወራን ያለነው ስለ ኢትዮጵያዊው ብቻ ሳይሆን ስለ ዓለም አቀፋዊው የሸካ የተፈጥሮ ደን ነው።ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ‹‹የኢትዮጵያ አገር በቀል የተፈጥሮ ደን›› ሲሉ ያሞካሹታል።ይህ የሸካ አገር በቀል የተፈጥሮ ደን በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበ ነው።
በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሸካ ዞን እንገኛለን።በእርግጥ በዚህ ክልል ውስጥ በየትኛውም አቅጣጫ ቢሄዱ ሰማይን ማየት የሚቻለው ለመኪና መንገድ በተገለጠው መስመር ላይ ብቻ ሆነው ነው።ከዚያ ውጭ ያለው አማራጭ ምናልባት ዛፉ ላይ ወጥተው ከሆነ ነው።አለበለዚያ የዛፉን ቅርንጫፍ ብቻ ነው ማየት የሚችሉት።እዚህ ቦታ ላይ ከፍቅረኛው ጋር የሚዝናና ወጣት ‹‹ተመልከቻት ይቺን ጨረቃ›› ማለት የሚችል አይመስለኝም፤ ‹‹ተመልከችው ይሄን ጉሬዛ›› እያሉ መዝናናት ነው።በነገራችን ላይ ጉሬዛ በጣም የዋህና ሰው የማይተናኮል እንስሳ እንደሆነ የአካባቢው ሰዎች ነግረውኛል።እንዲያውም ፍቅረኞች ቃል ሲገባቡ ‹‹ልብህን የጉሬዛ ያድርግልኝ›› ቢባባሉ ጥሩ ነው።
በዓለም አቀፋዊው የሸካ ጥቅጥቅ የተፈጥሮ ደን ውስጥ እያቆራረጥን ወደ ዞኑ ዋና ከተማ ማሻ እየሄድን ነው።በዚህ መስመር ሲሄዱ እንኳንም ሾፌር ያልሆንኩ ያሰኛል።እንዲያውም የአንድ ሾፌር ብቃት መለካት ያለበት በዚህ መስመር መሆን ነበረበት።እያወራሁ ያለሁት ስለመንገዱ አስቸጋሪነት እንዳይመስላችሁ (እሱን በኋላ እናወራዋለን)።እዚህ ቦታ ላይ የሾፌር ብቃት የሚደነቀው ቀልብን ሰብስቦ በመያዝ ነው።ያንን ድንቅ ተፈጥሮ ጨክኖ ባለማየት ትኩረትን መንገዱ ላይ ብቻ ማድረግ ብቃት ይጠይቃል።በዚህ መንገድ ላይ የሚሄድ ሾፌር የአካባቢውን ተፈጥሮ አይቶ አይቶ የወጣለት መሆን አለበት። ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚሄድ ሾፌር ግን ትዕግስቱን ይስጠው!
በዚህ ጥቅጥቅ የተፈጥሮ ደን ውስጥ እየሄድን የፈረደበት ፖለቲካ ተነሳ። ፖለቲካዊ ወሬ ለማንሳት ያስገደደን ደግሞ ያየሚያምር የተፈጥሮ ሀብት ነው።ለዓለም ህዝብ የሚበቃ የተፈጥሮ ሀብት ይዘን ዛሬም ‹‹ጠላታችን ድህነት ነው›› ከሚል መፈክር አልተላቀቅንም።ከዚህ የተፈጥሮ ሀብት መቶ ሜትር ርቀት ሳይሆን የሚለምኑ እናቶችና ሕጻናት እናገኛለን።ዛሬም ወጣቶች ስደት ላይ ናቸው።ዛሬም ዳቦ አጥተው ረሃብ ያጠወለጋቸው ሕጻናትን የያዙ እናቶች በየመንገዱ እናያለን።
ይሄን ሁሉ የተፈጥሮ ሀብት ይዘን ምድረ በዳ ከሆኑ አገራት እንበደራለን።ምድረ በዳ ወደሆኑ አገራት እንሰደዳለን።ለምለም ዛፍ የማይታይባቸው አገራት የሀብት ማማ ላይ ናቸው።ተፈጥሮ ያልሰጠቻቸውን ፀጋ በሰው ሰራሽ ተክተውታል።እኛ ግን ተፈጥሮ የለገሰችንን መጠቀም ተስኖናል።ለትምህርት ኖርዌ ቆይቶ የመጣ አንድ ጓደኛዬ የነገረኝ ነገር ትዝ አለኝ።ከቤት እስከ መጓጓዣ ቦታዎች፣ ከመማሪያ ክፍል እስከ ማደሪያ ክፍል፣ ከመሥሪያ ቤት እስከ ንግድ ቤት… የሚኖሩት በማሞቂያ አማካኝነት ነው።የአየር ሁኔታው የበረዶ ግግር ነው።ያንን የሚቋቋሙት በሰው ሰራሽ መንገድ ነው።ከፍተኛ ሙቀት ባላቸው አገራትም እንደዚሁ ነው።በሰው ሰራሽ ማቀዝቀዣ መንገዶች ነው የሚኖሩት።
የኢትዮጵያ አየር ንብረት ሁኔታ ግን ምቹነቱ በዓለም የተመሰከረለት ነው።‹‹የ13 ወር የፀሐይ ጸጋ›› የሚለው መለያዋ ነው።በዓለም የማይገኙ የተፈጥሮ እጽዋትና እንስሳት ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ።ለምን እነዚህን ሀብቶች ይዘን አሁንም ድሃ ሆንን? ወደድንም ጠላንም ወደ ፖለቲካ ያስገባናል።በአገሪቱ ውስጥ የሚፈጠሩ ብጥብጦች የፖለቲካ ውጤት ናቸው።ይባስ ብሎም ያሉትን መሰረተ ልማቶች ማውደም ጀምረናል።
አንድ ነገር ልብ በሉማ! እስኪ የትኛው ፖለቲካ ነው ስለሥራ ፈጠራና ስለኢኮኖሚ ሳይንስ የሚተነትን? በየሬዲዮና ቴሌቭዥኑ፤ በየጋዜጣና መጽሔቱ የሚጋበዘው የፓርቲ መሪና ፖለቲከኛ ሁሉ የሚያወራው ስለብሄር ፖለቲካ ነው።ሐኪምም ይሁን መሐንዲስ፣ የህግ ባለሙያም ይሁን መምህር፣ ነጋዴም ይሁን አርቲስት… በቃ ታዋቂ የሆነው ሁሉ የሚያወራው ፖለቲካ ብቻ ነው።እስኪ ቴሌቭዥን ላይ የሥራ ፈጠራ ክርክር፣ የኢኮኖሚ ትንተና ክርክር ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ከድህነት የምንላቀቀው? የአንዲት አገር አቅም ደግሞ ሀብት ነው።የዓለም ሃያላን አገራት ሃያል የተባሉት በአስማት ሳይሆን በኢኮኖሚ አቅም ነው።የአገራችን ፖለቲከኞች ግን ስለቋንቋ እልህ አስጨራሽ ክርክር ሲያደርጉ፤ የሥራ ፈጠራ፣ የቢዝነስ ስልት፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ የሳይንስ ምርምር… ጉዳያቸው አያደለም፤ ወይንም ደግሞ ከዚህ ዕውቀት ነጻ ናቸው።ለመገናኛ ብዙኃኑም ሰልተፈጥሮ ሀብት ማውራት ትንሽ ጉዳይ ነው።የአድማጭ ተመልካች ቀልብ አይስብም ተብሎ ይታሰባል።
ወሬያችንን በፖለቲካም በአድናቆትም እያወራረድን ወደ ዞኑ ዋና ከተማ ማሻ ተቃረብን።በዞኑ ውስጥ አንድ ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ የለም።ዝርዝር ጉዳዩን በዚሁ ጋዜጣ በዜና የምንናገረው ቢሆንም ትዝብታችንን ግን አሁን እናውራው።ያ ድንቅ የተፈጥሮ ጥቅጥቅ ደን ከተመራማሪዎች ውጭ ነው።ከዕይታ ውጭ ነው።በእንዲህ አይነት የተፈጥሮ ደን ውስጥ ብዙ አይነት የሳይንስ ግኝት ይኖራል።ከመድሃኒት ጀምሮ ብዙ ነገሮች የተፈጥሮ ውጤት ናቸው።እዚያ ጫካ ውስጥ ለምግብነት የሚውሉ፣ ለመድሃኒትነት የሚውሉ፣ ለውበት የሚሆኑ፣ ለተለያዩ ዕቃዎች ግብዓት የሚሆኑ ብዙ ነገሮች ይገኛሉ።ዳሩ ግን ማንም አያያቸውም።እንኳን የሳይንስ ተመራማሪ ተማሪ እንኳን እዚያ አይደርስም።መንገዱ አቧራ ነው፤ ዝናብ ሲዘንብ ጭቃ ነው።አካባቢው ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ዝናብ የሚያገኝ አካባቢ ነው።
በዚሁ የጠጠር መንገድ ላይ ሲሄዱ ግራና ቀኝ የተንጣለለ የሻይ ቅጠል ማሳ ያያሉ።ለዓይን እስከሚታየው አድማስ ድረስ የተንጣለለው የሻይ ቅጠል ማሳ ሀሴት ይፈጥራል።በፋብሪካ ብቻ የሚመረት የሚመስለን የሻይ ቅጠል እዚህ ጋ አረንጓዴ ሆኖ ውበትና ደስታን ይፈጥራል።የተንጣለለው የሻይ ቅጠል ላይ ጠጠር ቢጣልበት መሬት ጠብ የሚል አይመስልም።ገጠር አካባቢ አርሶ አደሮች የሚጠቀሙት አንድ አገላለጽ ትዝ አለኝ።የማሽላ ሰብል በጣም ሲያምርና ጥቅጥቅ ሲል ‹‹እባብ ያንሻልላል›› ይሉ ነበር።እንደሚታወቀው እባብ እግር የለውም።መሄድ የሚችለው በመሳብ ብቻ ነው።ክፍተት ያለውን ነገር መራመድ አይችልም።እናም ማሽላው ክፍተት ስለሌለው እባብ ሳይቸገር ይንሻለልበታል ለማለት ነው።የሸካ ዞን ሻይ ቅጠልም እባብ ያንሻልላል።
እንዲህ ነን እንግዲህ እኛ! የዓለም ደረጃ የያዘ የከብት ሀብት እያለን የቆዳ ውጤቶች በውድ ዋጋ የምንገዛ፣ የአትክልት አይነት በየማሳው እየባከነ የአትክልት ውጤቶች በውድ ዋጋ የምንገዛ፣ ጥጥ እና ሌሎች ለልብስ ግብዓት የሚሆኑ ሀብቶች በየጫካው እየበሰበሱ ልብስ በውድ ዋጋ ከውጭ የምንገዛ፣ የራሳችን ሀብት ተቀምሞ የሚሸጥልን ነን።
እንዲህ አይነት የተፈጥሮ ሀብቶቻችን ጥቅም ላይ ይውሉ ዘንድ የተማረ የሰው ሀይል መፈጠር አለበት፤ የመሰረተ ልማት ተደራሽ ሊሆኑ ይገባል።አገርን የሚያሳድገው ታሪክ እያነሱ መናቆር ሳይሆን ባለው ላይ መወያየት ነውና ፖለቲከኞቻችንም ስለኢኮኖሚና ሥራ
ፈጠራ አውሩ!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
ዋለልኝ አየለ