የዛሬ የዘመን እንግዳችን አቶ ሙላቱ ገመቹ ይባላሉ። የተወለዱት ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ አውራጃ ቦጂጨቆር በሚባል ወረዳ ውስጥ በ1945 ዓ.ም ነው። እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ የቦጂ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዘማናዊ ትምህርትን ተከታተሉ።የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በጊምቢ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ተከታትለዋል። በመቀጠልም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብተው በአኮኖሚክስ የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ሌላኛውን ዲግሪቸውን ሰርተዋል። የስራ ዓለምንም አሃዱ ብለው የተቀላቀሉት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ህንፃ ስራ በሚባል ድርጅት ሲሆን ኮንስትራክሽን ባለስልጣን፥ ግብርና ሚኒስቴር እንዲሁም አለማቀፉ የእንሳስት ሀብት ኢንስቲትዩት (ኢርሊ) ለ25 ዓመታት አገልግለዋል። ከ2003 ዓ.ም ወዲህ ግን ስራቸውን በገዛ ፍቃዳቸው በመልቀቅ በግል ስራ መተዳደር ጀምረዋል። ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት የሆኑት እኚሁ ግለሰብ ታዲያ ከተማሩበት የኢኮኖሚክሱ ዘርፍ ወጣ ብለውም ኢህአዴግ መራሹን መንግስትን በማቃወም ለበርካታ ዓመታት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አድርገዋል። በአሁኑ ወቅትም በመድረክ ስር ከተሰባሰቡት ፓርቲዎች አንዱ ሆኖ በሚገኘው ኦፌኮ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። እኚሁ የዛሬው እንግዳችን በተለይም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ስላሉት አንገብጋቢ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርግዋል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ፖለቲካው የገቡበትን አጋጣሚ አስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ሙላቱ፡- እኔ ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ እንደማንኛውም ወጣትና ተማሪ ጥያቄዎች ነበሩኝ። ምንም እንኳ በፓርቲዎች ውስጥ ባልታቀፍም መሬት ላራሹ እና በብሄረሰቦች መብት ዙሪያ የሚነሱ ተቋሞዎችንም እደግፍ ነበር። ከደርግ ውድቀት በኋላም ኦፌዴን የሚባል ድርጅት በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ሲቋቋም ከመጀመሪያዎቹ ሰዎች አንዱ ነበርኩ። በተለይም ከአለም አቀፉ የእንስሳት ሀብት ተቋም ከለቀቅኩ ጀምሮ ኦፌዴን ውስጥ በኋላም በፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ከሚመራው ኦፌኮ ጋር ሲቀላቀል ከመጀመሪያዎቹ ሰዎች ውስጥ ነበርኩ። ከ2004 ዓ.ም ጀምሮም የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ሆኜ ተመርጫለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በምርጫ ተወዳድረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቡበት አጋጣሚ አለ?
አቶ ሙላቱ፡- ፓርላማ ገብቼ አላውቅም። በ2007 ዓ.ም ምርጫ ዘመን ተወዳድሪያለሁ። በወቅቱ ታዲያ እንደምታውቂው አሸናፊም፤ ተሸናፊም ነበርኩ። ምክንያቱም መቶ በመቶ ያሸነፈው ኢህአዴግ ስለሆነ እውነተኛ ምርጫ እንዳልተካሄደ እሙን ነው። ስለዚህ ከመወዳደር ባለፈ ገብቼ ፓርላማ የመግባት እድል አላጋጠመኝም።
አዲስ ዘመን፡- ተቃዋሚ ፓርቲ ሆነው ሲሰሩ እንደሌሎች ባልደረቦቾ በገዢው ፓርቲ አልታሰሩም?
አቶ ሙላቱ፡- እኔ ፈሪም ስለሆንኩና ብዙም ስለማልጋፈጣቸው አላሰሩኝም። ነገር ግን በኢህአዴግ ዘመን ከነበሩት 24 ኦፌኮ አመራሮች ውስጥ 13 ታስረውበት ስለነበር የባልደረቦቼን እስር በመቃወም እጮህ ነበር። ከሁሉ የሚያስዝነኝ ግን ያን ጊዜ ጩኸት በምናሰማበት ወቅት ህዝቡ በከፍተኛ ደረጃ ስጋት ውስጥ ነበር። በወቅቱ እኛ የነበረን አማራጭ አንድም ተቃውሞውን በመግፋት ከሌሎች ባልደረቦቻችን ጋር መታሰር፥ ሁለትም አገር ለቆ መውጣት ነበር። ለእኔ ግን በወቅቱ አለመሰደዴም ሆነ አለመታሰሬ ጥያቄ ይፈጥርብኝ ነበር። ያም ሆነ ይህ ግን የእኛ ትግል ሰላማዊ ስለነበር ዋና አላማችን በሰው ጭንቅላት ላይ በመስራት እምቢ የሚል ትውልድ መፍጠር ነው። ያንን ስለፈጠርንም ነው ስድስት ዓመት ሙሉ ኦሮሚያ ውስጥ ከፍተኛ ግድያ እስራትና ስደት ይበዛ የነበረው። ያም ሆኖ ግን የማይፈራ ወጣት ትውልድ በመምጣቱ ነው ለውጡ የመጣው።
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ወዲህ የታገላችሁበት ነገር ተሳክቷል ማለት ይቻላል?
አቶ ሙላቱ፡- ከለውጡ ወዲህ መጥተዋል የምላቸውን መልካም ጉዳዮች በኋላ ላይ እነግርሻለሁ። በመጀመሪያ ግን አሉ የምላቸውን ችግሮችና ስጋቶች ነው ልነግርሽ የምፈልገው። በአጠቃላይ እኔ ለውጡ ለኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም የመጣው ባይ ነኝ። ስለዚህ ለውጡ ለውጥ ነው አልልም።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን የሚሉበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ሙላቱ፡- ምክንያቱም ትክክለኛ ለውጥ የህብረተሰቡን ጥያቄ የሚመልስ መሆን አለበት ብዬ ስለማምን ነው። ለዚህ አብነት ልጥቀስልሽ። እንደምታውቂው በቀደሙት መንግስታት የተማሪዎች፥ የብሄር ብሄረሰቦችና የአርሶአደሩ የመሬት ጥያቄ ስር ሰዶ የሃይለስለሴን መንግስት ከስሩ እየሰረሰረ ነው የገነደሰው። ደርግም 17 ዓመት ሙሉ ያን ሁሉ የህዝብ ጥያቄ ባለመመለሱ የህዝብ ተቋውሞና የነፃ አውጪዎች እንቅስቃሴ በማየሉ ነው እስከመገርሰስ የደረሰው። ያ ልምምድ በኢህአዴግ ውስጥም በተመሰሳይ ሁኔታ ታይቷል። እንደምታስታውሺው ከለውጡ በፊት በነበሩት ጥቂት ዓመታት ህዝብ በከፍተኛ ደረጃ በየአቅጣጫው የትጥቅ ትግል ውስጥ ገብቶ ነበር። ገዢው ፓርቲ ትግሉ በየአካበቢው ስለበዛበት እና እንደቀደሙት መንግስታት አይነት ችግር እንደሚያጋጥመው ስለተረዳ አስቀድሞ ሙሉ ለሙሉ ከመውደቁ በፊት ያመጣው ለውጥ ነው ብዬ ነው የማምነው። በእኔ እምነት በወቅቱ ኢህአዴጎች እንዴት አድርገን ነው ለውጥ ልናመጣ የምንችለው? የህዝብን ቅቡልነት አግኝተን አፈርልሰን ዳግም መነሳት የምንችለው? በምን አይነት ዘዴ ነው የህዝብን ይሁንታ የምናገኘው ብለው አስበው ያመጡት ለውጥ ነው። ለዚህ ደግሞ ዋቢ ማድርግ የሚቻለው የ17 ቀኑ የኢህአዴግ ሱባኤ ነው። ይህንን ለውጥ ያመጣው ይህ ሱባኤ ነው።
እንደምታስታውሽው በዚያ ወቅት የነበረው ዋነኛ ጥያቄ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይነሳ፥ የታሰሩ ይፈቱ የሚል ነበር። ይህንን ተከትሎ ከዚህ ቀደም አሸፈረኝ ሲል የነበረው ኢህአዴግ መጋቢት ላይ ለውጥ አደረገ። ይሄ ለውጥ ግን ለእኔ የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም። በነገራችን ላይ ለውጡ ከመምጣቱ በፊት እንደመድረክ አገሪቱ ባለችብት ሁኔታ የምትቀጥል ከሆነ ኢህአዴግ ከእንግዲህ ወዲያ እንደመንግስት ሆኖ መቀጠል ስለማይችል ኢህአዴግ ያለበት አንድ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ጠይቀን ነበር። ሁሉም የሚሳተፍበትና የፌዴራሊዝም ስርዓቱንና ህገመንግስቱን አክብሮ የሚቆይ ህብረብሄራዊ መንግስት ይቋቋም የሚልም ሃሳብ ሰጥተን ነበር። በዚያ ድርድር ውስጥ እያለን ለውጥ መጣ። ለውጡን ተከትሎ ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ ሌላ የሽግግር መንግስት አያስፈልግም እኔ አሸጋግራችኋለሁ አሉ። እኛ ግን ይህ አይሆንም ብለን ስንቃወም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ለውጡን ያመጣው ወጣቱ ሃይል ሆኖ እያለ ለውጡ የህዝብ አይደለም ማለት እንችላለን?
አቶ ሙላቱ፡- ለውጥ መጣ የሚባለው
ህዝብን ሲጠቅም ነው። መታገሉ ብቻ ለውጥ መጣ አያሰኘውም። ቄሮ ታግሎ እያለ በቄሮ ሰበብ ኢህአዴግ ጥቅሙን ለራሱ አደረገ። ኢህአዴግ
27 ዓመታት በሙሉ በሄደበት አካሄድ ያበላሸውን ሊያቃናው አይችልም። ስለዚህ የጥፋቱ አውራ የሆነው አካል ሊያስተካክለው አይችልም።
ስለሚጠየቅበትም ይፈራል። በወቅቱ ህዝብ ይጠይቀው የነበረው ለምሳሌ ኦሮሚያ ውስጥ በትግሉ ጊዜ ወደ 10 ሺ ሰው ነው ያለቀው፤ እናም
ለእነዚህ ሰዎች አንድም ሰው ተጠያቂ አልሆነም። እናም ገዢው ስርዓት በራሱ ተጠያቂ ነው የሚሆነው። ለውጡን ያመጣው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 18 ቀን 2012 ዓ.ም
ታኅሣሥ ፲፰/፳፻፲፪
ኢህአዴግ ራሱ ሆኖ እያለ ራሱን ተጠያቂ ማድርግ ስለማይችል ለውጡ እውን አይሆንም የሚል ምልከታ ነበረን። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ያቀረቡት ንግግር ጥሩ፥ የሚያማልልና ተቀባይነት ያለው ንግግራቸው ፍቅርን ሰላምን አንድነትን የሚሰብክ ነበር። በአንፃሩ ደግሞ ከዚህ ቀደም ኢህአዴግን የምንሰማው የነበረው አብዮታዊ ዴሞክራሲን ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ንግግራቸውን የጀመሩት በቅዱስ መፃፍ ቃልን በመጥቀስ ስለነበር ከፍተኛ ተቀባይነትን አገኙ። ያን ጊዜ ታዲያ እኛም ደፍረን ልታሻግረን አትችልም ለማለት አልቻልንም። ከውጭ የመጡት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይቀሩ «አብይ ማለት ነብይ ነው፤ ለማ ደግሞ ሙሴ ነው» አሉ። ያ በሆነበት ጊዜ እንደፖለቲካ ሰው የተለየ ነገር ብታነሺ ቅቡልነት አይኖርሽም።
አዲስ ዘመን፡- ግን በወቅቱ ከኢህአዴግ ውጭ ሌላ አገርን ማስተዳደር የሚችል ፓርቲ ነበር? ደግሞስ የምርጫ ዘመኑ ሳይጠናቀቅ ሌላ መንግስት ማቋቋም ኢ-ህገመንግስታዊ አይሆንም?
አቶ ሙላቱ፡- ዴሞክራሲን እና ፈዴራሊዝም ከተቀበልን በሰላማዊ መንገድ ሌላ ሃይል መምጣት ይችላል። ደግሞም ህዝቡ አስተዳድረኝ ብሎ እንደመረጠው ሁሉ አትሆነኝም ብሎ ማንሳት ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ያ ሊሆን የሚችለው ግን በምርጫ አይደለም እንዴ?
አቶ ሙላቱ፡- ለአምስት ዓመት የማስተዳደር ኮንትራት ቢሰጠውም በኮንትራቱ መሰረት እስካልሰራ ድረስ ህዝቡ የማባረር መብት አለው። ህብረብሄራዊ መንግስት የሚቋቋመው ሁላችንም በስምምነት ነው። በጉልበት የሚኖር መንግስት ዴሞክራሲያዊ አይደለም። በነገራችን ላይ ፌዴራሊዝም ማለት ያልተማከለ ዴሞክራሲ ነው። ያልተማከለ ዴሞክራሲ ደግሞ ሁሉም ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ነው። ኢህአዴጎች ግን ያልተማከለውን ዴሞክራሲ የተማከለ አደረጉት። ዴሞክራሲ ጠፋ። ፌዴራሊዝሙ ቀርቶ አህዳዊ ሆነ። አሁንም ለውጥ መኖር አለበት የምንልው ፈዴራሊዝምና ህገመንግስቱ መሬት ላይ ስላልሰራ ነው። ለዚህም ነው ኢህአዴግ አምስት ዓመቱን ሳይጨርስ ቢሆን መነሳት አለበት የምንለው። አሁንም ህዝብ ይጠይቃቸው የነበሩ ጥያቄዎች አልተመለሱም።
አዲስ ዘመን፡- ለ27 ዓመታት የደነደነ ችግር ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መመለስ አለባቸው እያሉ ነው? ደግሞስ ይህን ሲሉ የእስረኞች መፈታት፥ የተሰደዱ ሰዎች ወደ አገራችው መግባት መቻላቸው፥ ሰዎች እንደፈለጉ መናገርና መፃፍ መቻላቸው ከለውጥ አይቆጠርም ማለት ነው?
አቶ ሙላቱ፡- አይደለም! አትሳሳቺ! አሸባሪ የተባሉና ከአገር የሸሹ ዜጎች የገቡት የኢህአዴግን ቅቡልነት ለማስገኘት ነው። ኢህአዴግ ራሱ ለውጥ አመጣለሁ ያለው ራሱ ያባረራቸውን መልሶ አስገባ፥ አሸባሪ ያላቸውን ከአሸባሪነት መዝገብ ሰረዛቸው፤ ያሰራቸውን መልሶ ፈታ፤ ሌላ አካል እኮ አይደለም የፈታቸው። በእኔ እምነት ኢህአዴግ ይህንን ያደረገውም እድሜውን ለማራዘም ሲል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዓለማው ምንም ይሁን ምን ከእስር በመፈታቱም ሆነ ወደ አገር በመግባቱ የተጠቀሙ የሉም እያሉ ነው?
አቶ ሙላቱ፡- ተጠቃሚ ነው። አንቺም ብትሆኚ ለራስሽ ዝና ብለሽ ገንዘብ ብትሰጪን እጠቀማለሁ። ግን አንቺ ያደረግሽው ለራስሽ ዝና ነው። ይህ ሊታወቅ ይገባል። ለመኖር ሲባል የተደረገ ነው። ባለፉት ጊዜያት እኮ ብዙ ህዝብ አልቋል፤ ቤተሰብ ተበትኗል፤ ደምም ተቃብተናል። ስለዚህ በእኔ እምነት አሁንም ቢሆን ለውጡ የሚፈለገው ቦታ አልደረሰም። ለውጡ ህዝብ የሚፈልገው አይነት አይደለም። የህዝብ ጥያቄ የነበረው ኢህአዴግ በሁለቱ ዓመት ውስጥ ዴሞክራሲን እንዲያሰፍን፥ በተቻለ መጠን ምርጫ ቦርድ ታዓማኒ ያለው ተቋም እንዲሆን፥ ህዝቡ ራሱን በራሱ የራሱን አስተዳደሮች መምረጥ የሚችልበት ስርዓት እንዲፈጠር ነው። እስካሁን ግን ይህንን ነገር ማየት አልቻልንም። ምርጫ ቦርድ አሁን ላይ እስራለሁ ቢልም ዳተኝነት ይታይበታል። ይህ ደግሞ አምስት ዓመቱ ከማለቁ በፊት ምርጫ ካልተካሄደ ወደ ሌላ አጀንዳ ውስጥ ያስገባናል። ህዝብ ያልወከለው መንግስት፥ ኮንትራት ያልሰጠው አካል፥ ህዝብን ያስተዳድራል? አገሪቱስ ወዴት ነው የምታመራው?። እናንተም እንደጋዜጠኛ ከሰኔ 30 በኋላ ይህች አገር እጣፈንታዋ ምን ሊሆን ይችላል? ብላችሁ መጠየቅ ይገባችኋል።
በእኔ እምነት የዶክተር አብይ መንግስት አሁንም ቢሆን ለምርጫው የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን እያመቻቸ አይደለም። አሁንም በአብዛኛው የኦሮሚያ ክልል ውስጥ ኮማንድ ፖስት ነው ያለው። ሰላም ማረጋገጥ አልተቻለም። በዛሬው እለት እንኳ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የምናጣው ነፍስ፥ የሚቀጠፉ ተማሪዎች አሉ። ይሄ ደግሞ የሚሆነው የዩኒቨርስቲው አስተዳዳሪዎች ባሉበት፥ የዩኒቨርስቲው ፀጥታ ክፍል ባለበት፥ የዚያ አካባቢ አስተዳዳሪዎች ባሉበት፤ ፖሊስና መከላከያ ሰራዊት ባለበት አካበቢ ሰው ሞቶ የገደለው የማይታወቅበት፥ መስጂድና ቤተክርስቲያን እየተቃጠለ ዝም የሚባልበት ሁኔታ ነው ያለው። «ይህንንስ አስቀድሞ መከላከል አይቻልም ነበር ወይ?» ብለሽ ከጠየቅሽኝ ይቻላል ነው ምላሼ የሚሆነው። ምክንያቱም የሰለጠነ ፖሊስ አለ፥ ሰራዊት አለ።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንዶች ለዚህ ሁኔታ መፈጠር መንግስት ዴሞክራሲውን ያለገደብ መልቀቁ እንደሆነ ያነሳሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ሙላቱ፡- በእርግጥ ልክ ነሽ፤ መንግስት ሆደ ሰፊ መሆን እንዳለበትና ይቅርታ በማድረግ ነው የሚያምነው። ለእኔ ግን እንዳለፉት መንግስታት «ገዳዮች መባል አንፈልግም» በሚል ሽፋን የሚደረግ ውሸት ነው። ምክንያቱም ዴሞክራሲ ገደብ አለው። ገደብ የሌለው ነገር የለም። ሳከብርሽ ነው የምታከብሪኝ። ለመከበር አንቺን ማክበር አለብኝ። ይሄ የተለመደ ነው። ካዋረድኩሽ እኔም ውርደት ይከተለኛል። በተለይም በዚህ ጊዜ በጣም እንቆቅልሽ የሚሆንብኝ ነገር የእምነት ተቋማትን አቃጥሎ ማን እንዳቃጠለ አናውቅም የሚባለው ነገር ነው። በኢህአዴግ አሰራር ደግሞ አንቺም እንደምታውቂው አንድ ለአምስት ጥርነፋ አለ። ይህ ባለበት ሁኔታ ያለመንግስት እውቅና አንዳችም ነገር ልሰራ አልችልም። ምክንያቱም ስርዓቱ በራሱ አያሰራኝም። የፀጥታው ሃይልም ሆነ ደህንነቱ በዚህ አሰራር ተጠርንፎ እያለ ነው እንግዲህ በአሁኑ ወቅት ይህ ተግባር እየተፈፀመ ያለው።
እንደአጠቃላይ ግን ጥናቶችም እንደሚያሳዩት አገር ከተረጋጋና ሰላም ካገኘ ህዝብ የመብት ጥያቄዎችን ይጠይቃል። ይህንን ጥያቄ መንግስት መመለስ ካቃተው በተቻለ መጠን ይህንን የህዝብ ትኩረት ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመመለስ ይገደዳል። አሁን በአገራችን ያለው ይህ ሁኔታ ነው። በነገራችን ላይ ይሄ የተጀመረው አሁን አይደለም። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ኢህአዴግ ወደ ለውጥ ከመምጣቱ በፊት አንድ ሚሊዮን ኦሮሞን ያፈናቀለው ሃይል ማነው? ሲባል «የአብዲ ኢሌ ታጣቂ ሃይል» ተባለ። በእኔ እምነት አብዲ ኢሌ ሌላ መንግስት የለውም። በኢህአዴግ ስር ያለ የክልል መንግስት ነው። ይህንን ሲያደርግ መንግስት ለምን አልተከላከለም? የኦሮሚያ መንግስትስ ለምን ዝም አለ? ህግ መንግስቱ አንቀፅ 30 ላይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ መኖር እንደሚችል ይደነግጋል። ይሁንና ይህንን ድንጋጌ ማስከበር አልተቻለም። በተመሳሰይ ወቅት ግን ሌላ የመብት ጥያቄ ተነስቶ ነበር። የቋንቋ ችግር አለ፤ የፊንፊኔ ችግር አለ፤ በየቦታው ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ አለ፤ እነዚህ ያልተፈቱ ጥያቄዎች አሁንም አሉ።
ልብ እንድትይልኝ የምፈልገው ነገር ሱማሌ ክልል ውስጥ የነበረው ኦሮሞ አብሮ ሲበላ፥ ደስታና ሃዘንን ሲካፈል የቆየ ህዝብ መሆኑን ነው። የሱማሌ ህዝብ የኦሮሞን ህዝብ አላፈናቀለም። በመሳሳይ በጌድዮና በጉጂ መካከል ካድሬዎች በፈጠሩት ጫና ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ ተፈናቅሏል። የጌድዮ ህዝብ አካላችን ናቸው። የእኛ ወገኖች ናቸው። አሁንም እነዚህን ህዝቦች ማነው ያፈናቀላቸው? ሲባል ህዝብ ለህዝብ ይባላል። አሁን አሁን እኔና አንቺን ማፈናቀል ቀላል መሆኑን እንድናምን ተደርገናል። በተመሰሳይ እስከዛሬ ታይቶ በማይታወቅበት ወለጋ ውስጥ 200 ሺ ሰው ሲፈናቀል እንደምክንያት የተጠቀሰው የብሄር ብሄረሰቦች ግጭት እንደሆነ ነው። እውነታው ግን ይሄ አይደለም። ህዝባችን ለዘመናት ተቻችሎ ተፋቅሮ ነው የኖረው። በነገራችን ላይ የብሄር ግጭት ቢኖር እኮ በአንድ ቦታ አይቆምም። እኔ እና አንቺም እንፈላለግ፤ እንገዳደል ነበር። እውነታው ግን ይህ አይደለም። በእኔ እምነት የብሄር ግጭት ነው የሚያሰኙት በዚህ ተጠቃሚ የሚሆኑ አካላት ናቸው እንጂ ህዝብ ለህዝብ የተደረገ አይደለም። በየጊዜው በየቦታው የሚያግጥሙት ችግሮች የመንግስት እጅ ያለበት ነው። ለዚህ ነው ምርጫ መደረግ አለበት ብለን በየጊዜው የምንጮኸው።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ በእርሶ እምነት በየአካባቢ ለሚፈጠረው ግጭት ሁሉ ተጠያቂ መሆን ያለበት መንግስት ነው?
አቶ ሙላቱ፡- አዎ!መቶ በመቶ፤ መንግስት እኮ ሆነ ብሎ አንድ አካባቢ ላይ ቃጠሎ እንደሚኖር አስቀድሞ እያወቀ እንኳን እስኪቃጠል ጠብቆ ከተቃጠለ በኋላ ነው የሚደርሰው፤ ከተቃጠለ በኋላ ማን እንዳቃጠለ አናውቅም ይላሉ። ሌላው ይቅርና ቃጠሎው የመንግስት እጅ ካለበት እኮ እንዳይጠፋ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- ይቅርታ ላቋርጦት፤ አስቀድመው መንግስት መልካም ነገሮች ሁሉ የሚያደርገው ስልጣኑን ለማራዘም እንደሆነ ገልፀውልኛል። አሁን ደግሞ ስልጣኑን ለማራዘምና የህዝብን አቅጣጫ ለማሳት ሲል ብቻ ግጭት እንዲፈጠር ያደርጋሉ ብለዋል። እነዚህ ሁለት ሃሳቦች በራሳቸው አይጣረሱም?
አቶ ሙላቱ፡- እሱ እኮ ነው ለእኔም ለአንቺም እንቆቅልሽ የሆነው!። በአንድ በኩል ሲቃጠል ዝም ብሎ፤ በሌላ በኩል ማን እንዳቃጠለ አላውቅም ይላል። ለምሳሌ ሰሞኑን ሞጣ ላይ የተደረገው ነገር የተደራጁ አካላት ናቸው የፈፀሙት። የከተማው አስተዳደር ባለበት፥ መከላከያ ባለበት፤ ፖሊስ ባለበት፤ ይህ ሃይል ይህንን እኩይ ተግባር ሲፈፅም መንግስት አያውቅም ማለት የዋህነት ይመስለኛል። በነገራችን ላይ መንግስት እኮ የተለየ ታዕምር የሚፈጥር አካል አይደለም። እኔና አንቺ ማድረግ የማንችለውን ነገር እንዲሰራልን ነው። መንግስት ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ዘብ እንዲቆምላቸው ነው የመረጡት እንጂ እንዲያስራቸውና እንዲገድላቸው አይደለም። ዜጎች ወጥተው መግባት ስላልቻሉ ነው መንግስት የለም የምንለው። ግን ሙሉ ለሙሉ እንደዛ እንዳንል ደግሞ ሰራዊትም ሆነ አስተዳደሩ አለ። እናም እነዚህ ሁሉ የተደረጉትና እየተደረጉ ያሉት የኢህአዴግን ቅቡልነት ለማሳደግ ተፈልጎ ነው። በሆነ ጉዳይ ደግሞ ሁኔታው ሲያፈተልክ አንዳንድ ቦታ ላይ በኮማንድ ፖስት ነው እያስጠበቀ ያለው። ለምሳሌ ኦነግ እዚህ ቢሮ ተሰጥቶት እየተንቀሳቀሰ እያለ በሌላ በኩል ደግሞ ጫካ ውስጥ ሰው እየገደለ ነው ይባላል። እናም እነዚህን ነገሮች ማስታረቅ ካልቻልን አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ የህብረተሰቡን ችግር እንደምቹ ሁኔታ መውሰድ አይገባውም የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በለውጡ ተፈጥረዋል የሚሉትን መልካም ነገሮች አሁን ላይ ሊነግሩኝ ይችላሉ?
አቶ ሙላት፡- አዎ! አስቀድመን እንዳልነው አዲሱ የኢህአዴግ አመራር ቅቡልነት ለማግኘት ሲልም ቢሆን እስረኞችን መፍታቱ፥ አሸባሪ የተባሉትን ወደ አገራቸው እንዲገቡ ማድረጉ፥ ለህዝቡ ነፃነት መስጠቱ፥ እንደመልካም ከምወስዳቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው። በተጨማሪም አንዳንድ አሳሪ የሆኑ ህጎችን እንዲሻሻሉ ማድረጉ ጥሩ ነገር ነው። እነዚህን ነገሮች ካሰፋናቸው ደግሞ ወደ ዴሞክራሲ ያመሩናል የሚል እምነት አለኝ። ይህ ሲሆን ደግሞ ህዝቡ በምርጫ የሚፈልገውን መንግስት መምረጥ የሚችልበት እድልን ያሰፋል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለውጡን ተከትሎ የመጡ ለውጦች በአለም ደረጃ ከፍተኛ እውቅና ቢያገኙም፤ አንዳንድ ኢትዮጵያውያኖች ግን በአደባበይ ተቃውሞቸውን መግለፃቸው ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ሙላቱ፡- እንግዲህ አንዳንድ ጊዜ እንናተ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችም ትንሽ ነገር ስታገኙ ሰማይ
አሳክላችሁ ነው የምታወሩት። አንቺም እንደምታውቂው ዶክተር አብይ የኖቤል ሽልማት ሲያገኙ 100ኛ ሰው ናቸው። በእርግጥ ሽልማቱ
ጥሩ ነው። በተለይም ላለፉት 20 ዓመታት ሰላም ሆነ ጦርነት ሳይኖር ከኤርትራ ጋር የነበረብንን ችግር ዶክተር አብይ ከፕሬዚዳንት
ኢሳያስ ጋር ተነጋግረው መፍታት መቻላቸው የሚያስመሰግናቸው ነው። ይሁንና የአልጀርሱ ስምምነት እስካሁን ድረስ የቤት ስራ ሆኖ ነው
ያለው። የአልጀርሱ ስምምነት እስካሁን ድርስ ምን እንደሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ አያውቅም። አሁንም ቢሆን ድንበሩ እስካልተካለለ ድረስ
አሁን የተከፈተው በር ተመልሶ ተዘግቷል። እነዚህ ሰዎች ሲስማሙ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 18 ቀን 2012 ዓ.ም
ታኅሣሥ ፲፰/፳፻፲፪
የባድመ ጉዳይ ምን ይሆናል? የሚለው ጉዳይ አሁንም ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል። በሁለቱ ህዝቦች መካከል ድንበር አያስፈልግም፤ ተባብለን ተስማምተናል? ወይስ ባድመ ለኤርትራ ተሰጥቷል ወይ? እነዚህ ጥያቄዎች አሁንም አልተመለሱም።
አዲስ ዘመን፡- በእርሶ እምነት ሁለቱ ህዝቦች ደግም መተያየት ማቻላቸው በራሱ እንደአንድ ትልቅ ጉዳይ ሊወሰድ አይችልም?
አቶ ሙላቱ፡- እሱ እኮ ለሁላችንም ደስታ ነው። ግን በጣም አጋናችሁ የምትዘግቡበትን መንገድ አልቀበለውም። ሰው ዛሬ ይገናኛል፤ ነገ ደግሞ ይጣላል። ትንሽ ጊዜ ድንበሩ ተከፈተ ተባለ ብዙም ሳይቆይ ተዘጋ። እኔ የምስማማው በመሰረተ ሃሳቡ ነው። ስለዚህ የምንሰራው ስራ ወጥነት ሊኖረው ይገባል። ከዚህ አንፃር እንግዲህ ወጥነት ያለው የዲፕሎማሲ ስራ ነው ወይ እየተሰራ ያለው? ነገ ችግር ውስጥ የሚከተንን ነገር እየሰራን አይደለም ወይ? በእኔ እምነት እነዚህ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው። ስለዚህ ይንን ነገር ቢቋጩት ጥሩ ነገር ይመስልኛል። በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ ሳተላይት ማንጠቋ የሚበረታታ ጉዳይ ነው። ነገር ግን በአፍሪካ እኮ 10ኛ ነች። ስለዚህ ብዙ ልንገረምበት አይገባም ባይ ነኝ። ምክንያቱም ወቅቱ ቴክኖሎጂን የሚጠይቅ በመሆኑ ከጊዜው ጋር መራመድ አስፈላጊ ነው። እንዳውም እኔ ዘግይተናል ባይ ነኝ። አሁን አልነበረም መሰራት የነበረበት። በእርግጥ የነበሩት መሪዎች አስቀድመው መንቃት ነበረባቸው። አሁን ሳተላይቱን የተኮሱልን ቻይናዎች ናቸው። ይህም ሊታሰብበት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ይቅርታ ግን ከዚህ ቀደም ያልተደረገ ነገር አሁን መደረጉ በራሱ ሊደነቅና ሊበረታታ አይገባም? ደግሞስ በአለም አደባባይ ላይ የተደረጉትን ነገሮች ከማመስገን ይልቅ በመቃወም የምናተርፈው ምን ነገር ይኖራል?
አቶ ሙላቱ፡- ጥሩ ነው፤ ግን ድቤ መምታት የለብንማ! ምንድነው ደግሞ የምንቃወመው? ተቃውሞው እኮ ለምን ተሰራ አይደለም። ግን ዘግይተናል የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ። እናንተ እኮ አዲስ ነገር እንደሰራን አድርጋችሁ ነው እያቀረባችሁ ያላችሁት። አዲስ ነገር ከሰማይ እንዳወረድን ተደርጎ ሲገለፅ ሰውም ይታዘበናል እኮ!። በዶክተር አብይ ጊዜ ይሄ ሁሉ ተደረገ ብለን ለምርጫ ቅስቀሳ የምንጠቀምበት ጉዳይ ሊሆን አይገባም ነው። ሽልማቱንም ለሌላ አለማ እንድንጠቀምበት አታድርጉት።
አዲስ ዘመን፡- ይህ የእርሶዎ አስተሳሰብ ብዙዎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁሉንም ነገር ከማድነቅና ከማበረታት ይልቅ መቃወምንና ማጥላላትን ትመርጣላችሁ እየተባላችሁ ለምትወቀሱበት ነገር ዋቢ አይሆንም?
አቶ ሙላቱ፡- የለም! ሁሉንም ነገር መደስኮር አይገባንም። ሁሉም ነገር ከግምት በላይ መሆን አይገባውም። ተቃውሞ ከሌለበት አገር እድገት የለውም። የምንቃወመው በአግባቡ ነው። ሁሉንም አይደለም። አስቀድሜ እኮ ሳተላይት ማምጠቃችንን ጥሩ እንደሆነ ተናግሪያለሁ። ነገር ግን ለምርጫ ግብዓት ሲባል በአለም ላይ እንዳልተደረገ አድርጎ ማቅረብ ተገቢ አይደለም። እናንተም ጋዜጠኞች መንግስትን ስታበረታቱ ወደኋላ የቀረበትን ነገር መጥቀስ ይገባችኋል። ከአሁን በፊት መሰራት ነበረበት። ያለፉት መንግስታት ማሰብ ነበረባቸው። ወደፊትም ቶሎ ብለን የሚመጡትን ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም አለብን በሚለው ብንወስድው የተሻለ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ሌላ ጉዳይ ስንገባ እንደሚያ ውቁት ኢህአዴግ በቅርቡ ውህደት ፈጥሯል፤ ስሙንም ወደ ብልፅግና ቀይሯል፤ ይህንን ውህደት እንዴት አዩት? የእርሶ ፓርቲስ በዚህ ረገድ ምን እየሰራ ነው?
አቶ ሙላቱ፡- «አንተ ሰውዬ ሁሉንም ነገር መቃወም ነው ስራህ» እንዳትይኝ እንጂ ብልፅግና የሚለውን ስም ከየት እንዳገኙት አላውቅም። በእኔ እምነት ብልፅግና በአንድ ጊዜ አይመጣም። በኢኮኖሚክስ መርሆ በመጀመሪያ እድገት ይመጣል፤ በመቀጠልም ልማት ይመጣል፤ ከዚያ ነው ብልፅግና የሚመጣው። ብልፅግና የሚለው ስም ሀብታምነትን ነው የሚገልፀው። ይህንን ስም እንዴት እንደመረጡት፥ ለምን ጉዳይ እንደመረጡ? ባይገባኝም ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እንዴት አብሮ ሊሄድ ይችላል? ከፓርቲው ገፅታ ጋርስ አብሮ መሄድ ይችላል ወይ? ወይስ ሀብታሞች ተጠቃለው እዛ ውስጥ እንዲገቡ ተፈልጎ ነው?። ለነገሩ ይህ አካሄዳቸው ያዋጣቸው አያዋጣቸው እነሱ ናቸው የሚያውቁት። ነገር ግን ውድድራቸው በምርጫ እስከሆነ ድረስ ህዝብ ተቀብሏቸው ከመረጣቸው እሰየው ነው።
በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት እንደምታውቂው በኢትዮጵያ ውስጥ ከ150 ያላነሱ ፓርቲዎች በየእለቱ እየተፈበረኩ ናቸው። የፓርቲዎች መብዛት እኛን ብዙም የሚረብሸን ነገር የለም። ምክንያቱም ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ሶስት ደርዝ ያላቸው የፖለቲካ መስመሮች ናቸው ያሉት። አንደኛው ፍፁም ንፁህ የሆነ ፌዴራሊዝም የሚፈልጉ ሃይሎች ሲሆኑ፤ በሌላ በኩል ሲናገሩ ፌዴራሊዝም ይላሉ ግን አንድነትን የሚከተሉ ሃይሎች አሉ። ሌላው የዜግነት ፖለቲካን የሚከተሉ ናቸው። ከዚህ አንፃር አንድ አይነት ርዕዮተ አለም የሚከተሉ ፓርቲዎች ውህደት መፈጠራቸው ወሳኝ ጉዳይ ነው። ለጋራ ጥቅም ሲባል አብዛኛው ፓርቲ አቅም ለማግኘት ሲል መዋሃዱን የሚፈልገው ይመስለኛል። ከዚህ አንፃር የእኛም ፓርቲ መድረክ ውስጥ ከነበሩት አምስት ድርጅቶች በተጨማሪ እንደአፋር ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና የወላይታ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዲሁም ሌሎችም ከእኛ ጋር አብረው ለመስራት እየመጡ ነው። በነገራችን ላይ ህወሃትም ቢሆን አብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመሩን አውጥቶ ከጣለ እኛን መቀላቀል የማይችልበት ምክንያት አይኖርም።
አዲስ ዘመን፡- ፓርቲያችሁ ህወሃትንም ቢሆን ለመቀበል ዝግጁ ነው እያሉ ነው?
አቶ ሙላቱ፡- የትግራይ ህዝብ እስከወከለው ድረስ ለምን አንቀበለውም? አንድ ግለስብ ወንጀለኛ ከሆነ ወንጀሉን አብጠርጥረን ለይተን ልናወጣው እንችላለን እንጂ የትግራይን ህዝብ እንዴት ልናገለው እንችላለን?
አዲስ ዘመን፡- የትግራይን ህዝብ ማለቴ አይደለም። ህወሃት ግን ትናንትና አሰረን ገደለን ስትሉት የነበረ ፓርቲ እንደመሆኑ ዛሬ ላይ በምን አግባብ ነው አብራችሁት ልትሰሩ የምትችሉት?
አቶ ሙላቱ፡- ፓርቲ ውስጥ ሆኖ ብቻ ሳይሆን መሪ ሆኖ ቢመጣ ወንጀለኛ ከሆነ በወንጀሉ እንፋለመዋለን። እዚህም ካሉት ጋር እንፋለማለን። አሁንም ቢሆን ችግሩ አልቆመም። ኢህአዴግ አሁንም ስልጣን ላይ ስላለ ችግሩ የረገበ ይመስልሻል እንጂ ችግሩ አሁንም አለ። ስለዚህ ህወሃት እንደ ህወሃት የትግራይ ህዝብ መርጦ የኔነው ብሎ እስከላከው ድረስ የትግራይ ህዝብ ጋር አብሮ መኖር ግዴታችን ነው። አንቀበልህም አንለውም። አንቺ ወንጀል ሰርተሽ ዳግመኛ ካባ ለብሰሽ ብትመጪ በህግ ነው የምትጠየቂው። እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ ህወሃት ወደ እኛ አልመጣም።
አዲስ ዘመን፡- ግን ህወሃት ወደፊት ሊደፈጥጠን ይችላል ብላችሁ አትሰጉም?
አቶ ሙላቱ፡- ከብዙ ምሁራን ጋርም የማንግባባው ጉዳይ ይሄ ነው። ፌዴራሊዝምን እስከተቀበልን ድረስ እንዲህ አይነት መንግስት አይመሰረትም።መንግስት የሚመሰረተው ሁሉም በእኩል መንገድ እስከሆነ ድርስ የምትይው ችግር ይፈጠራል ብዬ አልሰጋም። አሁንም ቢሆን ኩቡር ጌታዬ የሚባልበት ዘመን አልፏል። ብሄር ብሄረሰቦችን እኩልነት እስካላረጋግጥን ድረስ መቼም ቢሆን ሰላም ይመጣል ተብሎ አይታሰብም።
አዲስ ዘመን፡- ለመሆኑ የዶክተር አብይን «መደመር» የተሰኘውን መጽሐፍ አንብበውታል? ካነበቡት እንዴት ተገነዘቡት?
አቶ ሙላቱ፡- አዎ፤ አንብቤዋለሁ። የተረዳሁትም ሁላችንም ያለንን ሃሳብ ወደ አንድ አምጥተን ብንሰራ አንድ ውጤት ላይ እንደምንደርስ የሚያስገነዝብ ነው። የሚጥምሽንም ሆነ የማይጥምሽንም ሁሉ ተቀብለሽ ለአንድነት ስትይ የምትኖሪበት አካሄድ ነው። በነገራችን ላይ ይህ አስተሳሰብ ድሮም የነበረ ነው። አዲስ ፍልስፍና አይደለም። ደግሞም ፍልስፍና አይደለም። ግን በየሙያው ያለው ሰው የራሱን አስተዋፅኦ ያበረከተበት ነው። በእኔ መረዳት መጽሐፉ ወደ አህዳዊ ስርዓት የሚሄድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ መጽሐፉ ላይ በግልፅ አህዳዊ ስርዓት ነው የምንከተለው የሚል ነገር አልተገለፀም?
አቶ ሙላቱ፡- መጽሐፉን ካነበብሽው በብሄር ተከፋፍለን መኖር የለብንም ይላል። በእኔ እምነት ኢትዮጵያዊነት የሚባለው የብሄር ብሄረሰቦችን እኩልነት ስትቀበይ ነው። ቋንቋውንም ማንነቱንም ስታከብሪው ነው። መጽሐፉ ከተለያዩ ምንጮች ተጠናቅሮ የተፃፈ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ዋልታ ረገጥ አመለካከት ላላቸው ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች የሚያስተላልፉት መልዕክት አለ?
አቶ ሙላቱ፡- እንደምታውቂው እንግዲህ እኛ ክልል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች አሉ። የኦሮሞ ህዝብ ደግሞ የሚታወቀው በአቃፊነቱ ነው። ከሁሉም ጋር ተቻችሎ የሚኖር ህዝብ ነው። የእኛም ፓርቲ በህገመንግስቱ የተቀመጠውን «ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ መኖርና ሀብት ማፍራት ይችላል» የሚለውን ድንጋጌ አክብረን ነው ስንቀሳቀስ የቆየነው። አሁንም ይህንን ነው የምንከተለው። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ፅንፈኛ የሚሉት ከራሳቸው እይታ አንፃር ነው። አንዳንዶቹ ፅንፈኛ የሚሉት ኦሮምኛ ቋንቋ በመጠቀሙ፥ ኦሮሞ በመሆኑ፥ በገዳ ስርዓት ነው መተዳደር የምፈልገው በማለቱ ነው። ይሄ ፅንፈኛ የሚያሰኝ ከሆነ ኦሮሞ በሙሉ ፅንፈኛ ነው ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡-ምንም አይነት ዋልታ ረገጥ አመለካከት ያለው ፖለቲከኛም ሆነ አክቲቪስት የለም እያሉ ነው?
አቶ ሙላቱ፡- እንደፖለቲካ ይህንን ያህል ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ ፅንፈኛ ፓርቲ አለ ብዬ አላምንም። አንድ አማራ ኦሮሚያ ውስጥ ሲኖር ልክ እንደ አንድ ኦሮሞ እኩል መብቱ የተጠበቀ ነው። በእርግጥ ከዚህ ቀደም አንዳንድ የኦፒዲዮ ካድሬዎች ወንበዴዎችን አስተባብረው ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ዜጎችን ቤት የሚያቃጥሉበት ሁኔታ እንደነበር እናውቃለን። አሁን ግን ይህ አይነት ነገር አለ ብዬ አላምንም።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ሙላቱ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
ማህሌት አብዱል