የሀይማኖት መቻቻል ችግር ወቅታዊነት የሀይማኖት መጠንከርና በማህበረሰባችንም ሆነ በዓለም ህብረተሰብ ማንኛውም ህይወት ውስጥ ተጽእኖ ማሳደር መገለጫው ነው። ኢትዮጵያ የብዙ ሀይማኖቶች፣ የብዙ ብሄረሰቦች ሀገር መሆኗ እውነት ነው። ከአስራ ሰባት ዓመት የኮምኒዝም ኣስተሳሰብ ፖለቲካ ተጽእኖ በኋላ መልካምም ደካማም ጎን ያለው ከፍተኛ የሆነ ሀይማኖትን የማቀንቀን እመርታ ታይቷል።
በኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ኣስር ተኩል ዓመታት ሀይማኖት ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው ተደርጎ ብዙ አፍራሽ ነገሮች ተሰርቶበታል፣ ሁለቱም ቤተእምነቶች የነበራቸው ተሰሚነትና ተቋማዊ ጉልበት በመሸረሸር እንዲዳከሙ ተደርጓል፤ ምንም እንኳ አሁን ተሀድሶ በማድረግ ኣዝጋሚ ሂደት ላይ ቢገኙም። ይህ በተለይ በሁለቱ ትላልቅ ቀዳሚ ሀይማኖቶች በክርስትና እና በእስልምና ላይ ያተኮረ ነው።
ከሁሉም ኣቅጣጫ ሀይማኖትን መሰረት ያደረገ ጥግ የደረሰ ትንኮሳ፣ ሀብትና ንብረትን ማጥፋት በተለይ ቤተእምነቶችን በእሳት ማቃጠልና ማጋየት ተከስተዋል፣ ዛሬም ይህ እኩይ ምግባር ኣልቆመም። የሰሞኑን የሞጣ ቤተ እምነቶች ቃጠሎም እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል።
የሀይማኖት ጽንፈኝነት ምክንያት አልባ ነው። ከሌሎች የጽንፈኝነት አስተሳሰቦች ጥግ የረገጠና በጣም ስር የሰደደም ነው። መቻቻል ወይም መታገስ ለጽንፈኞች የዜሮ ድምር ነው።
መቻቻል ቃሉ “Tolerant” – ከላቲን Tolerantia ከሚለው ይመዛዛል፣ ይህም መታገስ፣ ትዕግስተኝነት፣ መቀበል፣ እንግልትን ወይም ስቃይን በፈቃደኝነት መሸከም፣ የሌሎችን አመለካከት፣ የህይወት ዘይቤ፣ ጠባይና ልማድን መታገስ የሚገልጽ የስነማህበረሰብ ቃል ነው። ትእግስተኝነት ከግድየለሽነት ጋር አንድ ኣይደለም። የሌሎችን አመለካከትና የህይወት ዘይቤም በድፍኑ መቀበልም ማለት አይደለም። ይልቁንም ሌሎችን በግል ወይም በራሳቸው አመለካከት፣ ባህል፣ ዘይቤና ወግ መሰረት እንዲኖር የሚያስችላቸውን መብት አለመጋፋት ማለት ነው።
ትግስተኝነት ከተለያዩ ሕዝቦች፣ ብሄረሰቦች፣ ሀይማኖቶች (ባህል፣ዘይቤ፣ ወዘተ.) ጋር በተገናኘ አስፈላጊ ነው። ይህም ለሚፈልቁት ሀሳቦች ሁሉ ክፍት የመሆን ምልክት፣ ከሌሎች ሀሳብና አመለካከት ጋር ማነጻጸርን ወይንም ማወዳደርን የማይፈራና መነፈሳዊ ውድድር (ፉክክርን) የማይሸሽ፣ በራስ የመተማመን ምልክትና በግል አቋም የህሊና ጥንካሬ ነው።
የሀይማኖት ትእግስተኝነት ማነስ ችግር የሌሎችን እምነት፣ እሴቶችንና ሀይማኖታዊ ስሜቶችን ያለመቀበልና ያለመታገስ ደም አፍሳሽ ጦርነቶችን፣ የማህበረሰብንና የመንግስትን መፍረስ ኣስከትሏል፣ ዛሬም በአግባቡ ካልተያዘ ይህን መሳይ ነገር ሊያስከትል ይችላል። በማህበረሰብ ውስጥ ሀይማኖታዊ ትእግስት አልባነት፣ የሀገሮችን መፍረስ ከማስከተል አኳያ በሚበጣበጥ ማህበረሰብ ውስጥ የጠቡ መነሻ ዋና ምንጭ ነው። በዚህ የተነሳ ከጥንት ጀምሮ የሚቻለው ሁሉ ተልእኮ ይከናወናል፣ ይህን ተከትሎም ከሀይማኖት ሀሳብ ባሻገር በጭንብል የተከለለ የፖለቲካ አላማ ይራመዳል። ለምሳሌ ማህበረሰብን ከውስጥ ለማፋለስ መሰረታቸው ያልታወቀ መሰልና የተለዩ ሀይማኖቶችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ማስፋፋት፣ ሀገር በቀሉን በመበረዝ ስር እንዲሰዱ ጥረት ማድረግ ዋነኛ ጠባያቸው ነው።
የግጭቱ መፈጠር በተለያዩ የሳይንስ መስኮች በተለያየ መልኩ ትርጉምና ትንታኔ ይሰጠዋል። ለምሳሌ የሶሻል ዳርዊኒዝም አቀንቃኞች በሰው ልጅ ማህበረሰብ ውስጥ ለመኖር የሚደረግ ትግል በተለያዩ ግጭቶች የታጀበ ነው ብለው ያምናሉ። ግጭት በማንኛውም መልኩ የማይቀር የሰው ልጅ ህይወት አካል ነው። ከዚህ የተለየው ነጥብ፣ ግጭት የሚፈጠረው የማህበራዊ ጠባይ ባላቸው ምክንያቶች ተጽእኖ ነው የሚል ነው። የሃያኛው ክፍለ ዘመን ኣጋማሽ ጀርመን-አሜሪካዊ የስነማህበረሰብ ሊቅና የስነማሀበረሰብ ግጭት መስክ ጥናት መስራች ከሆኑት ውስጥ አንዱ የሆነው ሉዊስ ኮዘር ግጭትን የተመለከተው “Tunnel vision” (ጠባብ አመለካከት) በሚለው ጽንሰ ሀሳብ ላይ መሰረት በማድረግ ነው። ይህውም “ የእሴት ግብግብ፣ ትግል ወይም የደረጃ የበላይነት ጥቅም ፉክክር፣ ለስልጣንና በብዛት ለሌለ ውድ የተፈጥሮ ሀብት ሽኩቻ ነው፤ የተጻራሪዎቹ ወገኖች አላማ የበላይነት መጎናጸፍ ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪዎቻቸውን ማምከን ወይም ማስወገድም ጭምር ነው በሚል ያብራራዋል። ግጭት፣ በሉዊስ አመለካከት – የማህበራዊ መስተጋብር ዋነኛ ኢለመንት ነው። እያንዳንዱ ማህበረሰብ መጠነ ሰፊ ግጭትን ያዘለ ነው።
ሀይማኖታዊ መቻቻል በኢትዮጵያ ብሄረሰቦች የስነምግባር ባህል ውስጥ ስር የሰደደና ረጅም እድሜ ያስቆጠረ ነው። ሀገራችን የብዙ ብሄረሰቦች፣ የብዙ ጎሳዎች፣ የብዙ ቋንቋዎች፣ የብዙ ሀይማኖቶች ማሰሮ እንደመሆኗ ሁሉ ነገር ኣልጋ ባልጋ ወይም የተመቻቸ ነው ማለት አይቻልም። በዚህ በአንጻራዊ ትንሽ በማይባል መልከአምድር ላይ አንዱ ከሌላው ጋር በባህል፣ በስራ፣ በቤት ውስጥ ልማድ፣ በእለት ተእለት ህይወት የሚለያዩ ሕዝቦች ይኖራሉ። የዚህ አይነቱ የአኗኗር ዘይቤ የተመሰረተው ጥንት ሆኖ ለብዙ መቶ ዓመታት ዘልቆ ዛሬም ድረስ ይኖራል።
“ የሀይማኖት መቻቻል” ሕዝብን የሚያዋህድና አንድ የሚያደርግ ምክንያት (ፋክተር) ነው። የእምነት ትእግስት በሁለት ደረጃዎች ይታያል፤ አንደኛ፣ የተለያዩ ሀይማኖቶች በሚከተለው ምእመናን መካከል ያለ የመቻቻልና አንዱ ሌላውን የመታገስ ግንኙነት፣ አንዱ ሌላውን የማክበር፣ አንዱ የሌላውን የመኖር፣ እምነቱን የማራመድ፣ የመስራት መብት የመቀበል፣ እውቅና የመስጠት መርህ ላይ የተመሰረተ ነው። ሁለተኛ፣ መንግስት የተለያዩ ሀይማኖቶችን የመኖር መብት እውቅና መስጠቱ፣ ሀይማኖታዊ መቻቻል፣ በሌላ አነጋገር ለሌሎች ባህልና ልማድ፣ ስሜትና አስተሳሰብ ቀና አመለካከት መኖር ማለት ነው።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ሀይማኖታዊ መቻቻል በመጀመሪያ ደረጃ ሌሎችን መታገስ ነው። ይህም የሚያነጣጥረው በማህበረሰቡ ውስጥ የተለያዩ የሀይማኖት ተቋማትን በጋራ ማወቅና አንዱ የሌላውን እሴት ስርዓት በማክበር ማበልጸግና ማስረጽ ነው። በዚህ አግባብ የማህበረሰቡን ንቃተ አእምሮ፣ ባህል የሚመሰርቱና የሚቀርጹ በተለያዩ የሀይማኖት ቡድኖች መዋቅሮች መካከል የጋራ ትልቅ ትርጉም ያለው ትስስር አለ። ይህም መሰረታዊ የሚሆነው ለሀይማኖታዊ መቻቻል ብቻ ሳይሆን ለማህበረሰቡ ህብረት፣ አንድነትና የጋራ ጥቅም መዳበር፣ መጠናከርና መሰባሰብ ነው። የሀይማኖት ትዕግስተኝነት የህዝቦች መልካም ባህል ነው። የሌሎችን ሕዝቦች ሀይማኖት፣ ቋንቋ፣ ልማድ፣ ባህል የመማርና የማወቅ መልካም አጋጣሚ ነው።
ምንም እንኳ በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ከሁሉም ወገን የሀይማኖትን ልዩነት ለፖለቲካ ፍጆታ ለመጠቀም በማራገብ ደፋ ቀና የሚሉ የመካከለኛው ዘመን አስተሳሰብ ያለቀቃቸው ቡድኖች መኖራቸው እውነት ቢሆንም በወጣቱ ማህበረሰብ መካከል ለሌላው የብሄረሰብ ወይም ጎሳ አባል፣ ለሌላ ሀይማኖት ተከታዮች ያላቸው መልካም አመለካከት ከፍተኛ መሆኑን ምርምሮች ይጠቁማሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሌላ ብሄረሰብ ወይም ጎሳ አባል የሆኑ ሰዎች አንዱ ለሌላው እውቅና እንዲሰጠው፣ በማንነቱ እንዲቀበለው፣ ሊረዳው እንዲችል፣ የተለያዩ አውደ ጥናቶችንና ሴሚናሮችን በመደበኛ ሁኔታ በማዘጋጀት የሌሎችን ብሄረሰቦች አባሎች የመታገስ ባህል እንዲዳብር ጠንክሮ መስራት ይገባል። የዚህ ውጤት በወጣቱ ማህበረሰብ ውስጥ በብሄረሰቦች፣ ጎሳዎችና ሀይማኖት ትእግስት ለማዳበርና ለማጎልበት ለሚደረግ ተከታታይ ጥናት መሰረት ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ።
ከወጣቱ ጋር ለመስራት የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ መንደፍ አስፈላጊ ነው። ዋናውን ምክንያት ከግምት ያስገባ ትዕግስተኝነትን ለማሳደግና ለማስፋፋት የሚያስችል ሰፊ ስራ በመላው የሀገራችን ክፍሎች መስራት አስፈላጊነት ከምንጊዜውም በላይ የላቀ ነው።
ሀይማኖትና ትዕግስተኝነት – ሰዎችን አንዱን ከሌላው ጋር የሚያዋህድ ምክንያት(ፋክተር) ነው። ሀይማኖት ለሰው የማመን እድል ይሰጣል፤ ትዕእግስት ደግሞ የእያንዳንዱ ሰው ስነምግባር የታነጸበት መሰረት ነው።
ስነምግባር – ደግነት፣ ታማኝነት፣ ንጽህና፣ አክብሮት፣ ሰውን መረዳት፣ ይህውም የራሱ የሆነ ጠባይ ያለውና አንድና ተመሳሳይ እምነት የሚከተሉ ቡድን ሰዎች መኖራቸውን የሚገንዘብ ነው።
ኢትዮጵያውያን እንደሰለጠነ ሕዝብ፣ እንደሰለጠነ የዓለም ማህበረሰብ አካል በራሳችን ምሉእ ሆነን ለመኖር ገና ብዙ መስራት ይጠበቅብናል። ብዙ የሰለጠኑ ሀገሮች እንዳደረጉት ሁሉ ለመስማማት ተስማምተን በሀገር ውስጥ ፍጹም ሰላምን ፈጥረን ከሰራን ሌሎች አገሮች የደረሱበት የእድገት ደረጃ ላይ ልንደርስ የማንችልበት ምንም አመክኗዊ ምክንያት የለም።
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 17/2012
ክብሩ ቸርነት (ዶክተር)
Kibruk@yahoo.com