አፍሪካዊያን በተጋድሏቸው ፖለቲካዊ ነጻነታቸውን ከተቀዳጁ ብዙ አስርታትን ቢያስቆጥሩም ኢኮኖሚያዊ ነጻነታቸውን ማረጋገጥ ግን አልቻሉም፡፡ የአብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚ ዛሬም ከቀድሞ ቅኝ ገዥዎቻቸው ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ዛሬም ኢኮኖሚያቸው ከባዕዳን ጣልቃ ገብነት መላቀቅ አልቻለም፡፡ የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነታቸው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከቀድሞ ገዥዎቻቸው ጋር እጅጉን የተቆራኘ ነው፡፡ አንዳንዶች የቀድሞ ቅኝ ገዥዎቻቸውን መገበያያ ገንዘብ እንደ መገበያያ ገንዘባቸው ሲጠቀሙ እነሆ ግማሽ ምዕተ ዓመት አለፋቸው፡፡ ሀገራቱ የቀድሞ ገዥዎቻቸውን ገንዘብ እንደገንዘባቸው አድርገው መጠቀማቸው ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነታቸውን እንዳያረጋግጡ ጋሬጣ ከመሆኑ ባሻገር የችግሮች ምንጭ ሲሆንም ተስተውሏል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ከዚህ ኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት ለመላቀቅ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቆይተዋል፡፡ ኢኮኖሚያቸው በከፍተኛ ሁኔታ ከቀድሞ ቅኝ ገዥዎቻቸው ጋር ከተቆራኙት የአፍሪካ ሀገራት መካከል የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) አባል የሆኑ ቤኒን ሪፐብሊክ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ጊኒ ቢሳው፣ አይቮሪኮስት፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ሴኔጋል፣ ቶጎ ሪፐብሊክ የቀድሞው የፈረንሳይ መገበያያ የሆነውን ሲ ኤፍ ኤ ፍራንክ ከቅኝ ግዛት ዘመን አንስተው እስካሁን ድረስ ሲጠቀሙ ቆይተዋል፡፡
ሀገራቱ የፈረንሳይን ገንዘብ መጠቀም በማቆም የራሳቸውን የጋራ ገንዘብ ለመጠቀም ላለፉት 30 ዓመታት ብዙ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ብዙ ድርድሮችም ሲደርጉ ቆይተዋል፡፡ ጥረታቸው ውጤት ሳያፈራ ለሶስት አስርታት ጥረት ሲደርጉ ቆይተው በመጨረሻ ምኞታቸው ሰምሯል፡፡ ስምንቱ ሀገራት ከሰሞኑ አንድ ትልቅ ውሳኔ አስተላልፈዋል፡፡ ሲ ኤፍ ኤ ፍራንክን ከአገልግሎት ውጪ በማድረግ የራሳቸው የሆነውን “ኢኮ” የተሰኘ የጋራ ገንዘብ መጠቀም ለመጀመር ወስነዋል፡፡
ይህን ውሳኔ ካስተላለፉት ከስምንቱ ሀገራት መካከል ከጊኒ ቢሳው በስተቀር ሰባቱ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ እና ሲ ኤፍ ኤ ፍራንክን እንደ መገበያያ ገንዘባቸው ሲጠቀሙ የቆዩ ናቸው፡፡ የናይጄሪያው ፕሪሚየም ታይምስ ከአይቨርኮስት አቢጃን እንደዘገበው፤ የአይቨርኮስቱ ፕሬዚዳንት አላሳኔ ኦታራ ከፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ከኢማኑኤል ማክሮን ጋር በሰጡት መግለጫ ይፋ እንዳደረጉት ስምንቱ ሀገራት ሲ ኤፍ ኤ ፍራንክን መጠቀም ለመተውና ከኢኮዋስ ጋር በመነጋገር ኢኮ የተሰኘውን አዲሱን ገንዘብ የጋራ መገበያያ ገንዘብ አድርገው ለመቀበል ተስማምተዋል፡፡ እ.አ.አ ከ2020 ጀምሮ ገንዘቡ ወደ ስራ ይገባል ተብሏል፡፡
በ56ኛው የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት አላሳኔ ኦታራ እንዳብራሩት የቀድሞ የአካባቢው ሀገራት ቅኝ ገዥ ፈረንሳይም ስምንቱ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የራሳቸውን የጋራ ገንዘብ ለመጠቀም መወሰናቸውን እንደሚደግፍ መግለጹን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦታራ እንደተናገሩት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ስምንቱ ሀገራት የጋራ ምንዛሬ ለመጠቀም የደረሱበትን ውሳኔ “ታሪካዊ ለውጥ” ሲሉ አሞካሽተውታል ሲል አስነብቧል፡፡
ገንዘቡ የሀገራቱ መገበያያ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉና ከቀጣይ የፈረንጆች ዓመት ጀምሮ ኢኮ የአካባቢው ሀገራት መገበያያ ሆኖ ሲያገለግል የማየት ጉጉት እንዳደረባቸው ማክሮን መናገራቸውን ኦታራ ተናግረዋል፡፡ ስምንቱ ሀገራት ኢኮን የጋራ መገበያያ አድርገው ለመጠቀም መወሰናቸው ኢኮዋስ በቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ውህደትና የገበያ ትስስርን ለመፍጠር እያደረገ ያለው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን ያላቸውን ቁርጠኝነት አመላካች መሆኑን ተነግሯል፡፡
ሀገራቱ ከ1945 ጀምሮ ይህን ገንዘብ ሲጠቀሙ የቆዩ ሲሆን ፈረንሳይም ይህንኑ ገንዘብ በመጠቀም በድህረ ቅኝ ግዛት ዘመንም ጫና ስታሳድር ቆይታለች፡፡ በእርግጥ ስምንቱ ሀገራት የጋራ ገንዘብ ከመጠቀም ባሻገር ከፈረንሳይ ተፅዕኖ ያላቅቃል ያሉትን ሌሎች ውሳኔዎችን አስተላልፈዋል፡፡ ካስተላለፉት ውሳኔዎች መካከል የጋራ ገንዘብን መጠቀም አንዱ ነው፡፡ ከጋራ ገንዘብ ባሻገር ሀገራቱ ከተጠባባቂ ገንዘባቸው 50 በመቶውን በፈረንሳይ ግምጃ ቤት ማስቀመጥ ለማቆምና ፈረንሳይ መንግስት በሀገራቱ ገንዘብ ነክ የአስተዳደር ጉዳዮች ላይ ያለውን ጣልቃ ገብነት መከላከል ስምንቱ ሀገራት ከተስማሙባቸው መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በሲ ኤፍ ኤ ተቋማት ውስጥ የነበሩት የፈረንሳይ ተወካዮችም ከስራቸው እንዲሰናበቱ ይደረጋል፡፡
እንደ ፕሪሚየም ታይምስ ዘገባ የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሞሃመዱ ቡሃሪም በጉባኤው ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡ ኢኮ እውን መሆን ለቀጣናው ልዩ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ለቀጣናዊ ውህደትና ትስስር የሚኖረው ፋይዳ የላቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የፈረንሳይ መንግስትም ኢኮ እውን እንዳይሆን አሉታዊ ጫና ባለማድረጉ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ሐምሌ ወር ኢኮ የጋራ መገበያያ እንዲሆን ውይይት ሲደረግ የኢኮዋስ አመራሮች እንደገለጹት፤ የኢኮ ስራ ላይ መዋል 15ቱ የኢኮዋስ አባል ሀገራት አንድ የጋራ ገንዘብ እንዲጠቀሙና ቀጣናዊ ውህደትን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡
የቀጣናው ሀገራት ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ ከስምምነት መድረሳቸውን ተከትሎ የተለያዩ አካላት የተለያዩ አስተያየቶችን እየሰነዘሩ ናቸው፡፡ የኢኮ እውን መሆንን የሚደግፉ ምሁራን ኢኮ ለአካባቢው ያበረክታል ያሉትን በረከቶች እየዘረዘሩ ናቸው፡፡ ኢኮ ንግድ በማፋጠንና በአካባቢው የተፋጠነ ክፍያ እንዲኖር በማድረግ ለአካባቢያዊ ውህደት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው እየተናገሩ ነው፡፡ የቀጣናው ሀገራት ከሌሎች ቀጣናዎች ጋር የሚኖረው የንግድ ግንኙነት እንዲሳለጥም የላቀ ሚና እንደሚጫወት እየተነገረ ነው፡፡
የናይጄሪያ የገንዘብ ሚኒስትር ዘይነብ አህመድ ከአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት ስምንቱ ሀገራት የጋራ ገንዘብ ለመጠቀም መወሰናቸው መልካም ጅምር ነው፡፡ ነገር ግን የራሳቸውን ገንዘብ መጠቀማቸው ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ሁሉም የኢኮዋስ አባል ሀገራት በተናጠልም ሆነ በጋራ ቀጣናዊ ውህደቱን የተሳካ ለማድረግ ጥረት ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 16 /2012
መላኩ ኤሮሴ