ዕደ ጥበብ ልክ እንደ ባህል ሁሉ የአንድ ማህበረሰብ መገለጫ ነው። አንድን መገልገያ ዕቃ በማየት የየትኛው አካባቢ (ማህበረሰብ) መገልገያ እንደሆነ እናውቃለን። ለዚህም ነው በባህል ፌስቲቫል ላይ ባህላዊ የመገልገያ ዕቃዎች ለዕይታ የሚቀርቡት። ምናልባት አሁን አሁን የመገልገያ ዕቃዎች በዘመናዊ የፋብሪካ ውጤት ዕቃዎች እየተተኩ ቢሆንም አሁንም ግን ባህላዊ ዕቃዎች የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መገለጫዎች ናቸው።
እነዚህ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ኪነ ጥበብ ናቸው። ማንም ሰው ሊሰራቸው አይችልም። የዚያው ማህበረሰብ ተወላጅ ሆኖ እንኳን ሁሉም ሊሰራቸው አይችልም። ለምሳሌ ገበሬ ሆኖ ሞፈር ቀንበር መገጣጠም የማይችል አለ፤ በባህላዊ ቤት ውስጥ እየኖረ የቤት አሰራሩን የማይችል አለ። እነዚህን ነገሮች የሚችሉ የአካባቢው ሰዎች እንደ ጥበበኛ ነው የሚታዩት። ለማይችሉት ሰዎችም ጥበባቸውን ያጋራሉ፤ያለማምዳሉ። የእጅ ጥበብ ያላቸው ሰዎችም በአካባቢው የተከበሩ ናቸው። ለዚህም ነው የዕደ ጥበብ ሥራዎች እንደ ጥበብ የሚታዩት።
እነዚህ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ዓለም አቀፍ እውቅናም አላቸው። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህልና ድርጅት (ዩኔስኮ) እንዲህ አይነት የጥበብ ሥራዎችንም ይመዘግባል። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2003 በተደረገው ስምምነትም ለሚዳሰሱ የጥበብ ቅርሶች የተሰጠው ትርጉም የሚያሳየው የዕደ ጥበብ (የእጅ ጥበብ) ሥራዎችን ነው።
‹‹አዲስ ያማረኛ መዝገበ ቃላት›› የተሰኘው የደስታ ተክለወልድ መዝገበ ቃላት ‹‹ዕደ ጥበብ›› የሚለውን ቃል እንዲህ ይተረጉመዋል። የእጅ ብልሃት፣ ማንኛውም የሥራ ዘዴ፤ እነዚህም እንደ ጽፈት፣ስፌት፣ሥዕል፣ሕንጻ፣ቅጥቀጣ፣ፈትል፣ሸማ ሥራ… ናቸው። እነዚህ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ማህበረሰቡ በአካባቢው ከሚያገኛቸው ግብዓቶች የሚሰራቸው ናቸው። ለዚህም ነው ከአካባቢ አካባቢ የተለያዩ የሚሆኑት፤ለዚህም ነው የአንድ አካባቢ መገለጫ የሚሆኑት። የሚገኙት ግብዓቶች ራሱ ከአካባቢ አካባቢ ይለያያሉ። የተክል አይነቶች፣ የአፈር አይነቶች ይለያያሉ። ለዚህም ነው በባህል ዓውደ ርዕይ ላይ ከሰሜን አካባቢ የመጣ የደቡብ የዕደ ጥበብ ሥራዎችን ገዝቶ ይሄዳል። ከደቡብ የመጣ የሰሜን የዕደ ጥበብ ሥራዎችን ይዞ ይሄዳል። ከምሥራቅና ከምዕራብም እንደዚሁ።
ለዛሬ ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የአገራችን ክፍል እንሄዳለን። የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በ2009 ዓ.ም ‹‹የሶማሌ ብሔረሰብ ባህላዊ የእንጨትና የቆዳ ሥራ ውጤቶች አሰራርና ጠቀሜታ እና የአርጎባ ብሔረሰብ አፋዊ ትውፊቶችና መገለጫዎች ጥበቃ ጥናት›› በሚል ርዕስ በአገኘሁ አስረስ አጥኚነት ያሳተመውን መጽሐፍ ዋቢ አድርገን ስለሶማሌ የዕደ ጥበብ ሥራዎች እናስነብባችኋለን።
ከዚያ በፊት ግን አንድ የራሴን አስተውሎት ልንገራችሁ። በ2008 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ ለአንድ ሳምንት ያህል የመቆየት ዕድል ነበረኝ። የሄድኩበት ምክንያት ደግሞ የባህል ሳምንት መሆኑ የሶማሌን ባህልና የዕደ ጥበብ ሥራዎች ለማየት ሰፊ ዕድል ፈጥሮልኛል። ከቤት አሰራራቸው ጀምሮ የመገልገያ ዕቃዎቻቸው ሁሉ በአገር በቀል እውቀት የተሰሩ ናቸው። ከእንጨትና ከቆዳ የሚሰሩ የመገልገያ ዕቃዎች ይበዛሉ። በእነዚህ የመገልገያ ዕቃዎች የሚጠቀሙባቸው ነገሮች ራሱ አገር በቀል ሀብቶች ናቸው፤ ለምሳሌ ምግቦችና መጠጦች ማለት ነው።
ወደ መጽሐፉ ስንመለስ።
ለመሆኑ እነዚህ የዕደ ጥበብ ሥራዎች እንዴት ተለመዱ?
አጥኚው እንደሚነግሩን፤ በሶማሌ ክልል አፋዴር ዞን ሐርጌሌ ወረዳ ሙያው በጥንት ጊዜ በገቦዬ ጎሳ አባላት ይከወን ነበር። የጎሳው አባላት በወቅቱ ሌላ መተዳደሪያ አልነበራቸውም። ከጊዜ በኋላ ግን አንዱ ሌላውን በማየት ሙያውን እዚህ ደረጃ ላይ አድረሰውታል። የእውቀት ሽግግሩም ከቤተሰብ ይጀምራል። የሚችሉት ለማይችሉት እያለማመዱ አሁን በሁሉም አካባቢዎች እየተሰራ ነው።
አባት የሙያው ባለቤት ከሆነ ልጆችም አባታቸውን እያዩ ይማራሉ። ቀለል ያሉ ሥራዎችም ለልጆች ይሰጣሉ። ይሄም ምናልባት እንኳን ቢያበላሹት ተብሎ ነው። አንዳንድ ጊዜም ለልጆች መለማመጃ ተብሎ የሚሰጥ እንጨት ወይም ቆዳ ሊኖር ይችላል። ይህ የሙያ ውርርስ በልጆች ብቻ አይደለም። አዋቂዎችም ቢሆን ካልቻሉ ከጎረቤት ሰው ይለምዳሉ። ከዚያ በኋላ የግብርና መሣሪያዎችንም ራሳቸው ይገጣጥማሉ። እነዚህ የሚሰሯቸው የመገልገያ ዕቃዎች ከራስ አልፎ ለሽያጭ የሚውሉም ይሆናሉ። የቆዳ ውጤቶች ግን በአብዛኛው በፋብሪካ ዕቃዎች ስለተተኩ ገበያቸው የቀዘቀዘ ነው።
ጥናቱ እንደሚነግረን በሶማሌ ብሔረሰብ ውስጥ የእንጨት ሥራዎች በብዛት በወንዶች የሚሰሩ ናቸው። በእርግጥ በሌሎችም አካባቢዎች በአብዛኛው በወንዶች የሚሰሩ ናቸው። በእንጨት ሥራዎች ውስጥ ጉልበት ያስፈልጋል። ዛፍ መቁረጥ፣የተቆረጠውን ዛፍ መሸከም፤ለሚፈለገው ቁስ የሚሆነውን ቅርጽ መምረጥ ሥራው የሚፈልጋቸው ነገሮች ናቸው። ይሁን እንጂ የማሳመር ሥራው ግን የሴቶች ናቸው። አሰል የተባለ የዛፍ ልጥ መፈለግ የሴቶች ሥራ ነው። ከዚህ ልጥ የሚገኘው ቀለም የመገልገያ ዕቃውን ለማስዋብ የሚያገለግል ነው። እንደ ዘንቢልና የወተት መናጫ የመሳሰሉ ዕቃዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ በሴቶች የሚሰሩ ናቸው።
ከጥናቱ የምንረዳው ነገር፤ አገር በቀል እውቀትን በተመለከተ አሁንም ያልተስተካከለ አመለካከት እንዳለ ነው። በሶማሌ ክልል ውስጥ በእንዲህ አይነት ሥራዎች ውስጥ ያሉ ሰዎችን ዝቅ አድርገው የሚያዩ አሉ። ‹‹ለምን አታርሱም፣ለምንከብት አታረቡም›› ይሏቸዋል። የሚገርመው ግን የሚታረሰው ነገር የሚበላው በእነዚህ ዕቃዎች ነው፤ መጀመሪያው ም የሚታረሰው እኮ በእነዚህ ዕቃዎች ነው። በከብት እርባታ የሚተዳደር ሰው ከከብቶች የሚያገኘውን ውጤት ሁሉ መጠቀም የሚችለው በእነዚህ ዕቃዎች ነው። ይህን እያወቁት ዛሬም ለእንዲህ አይነት ሥራዎች ተገቢውን ክብር አልተሰጠም።
ሌላው ለእነዚህ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ተግዳሮት የሆነው የጥሬ ዕቃ ችግር ነው፤ በተለይም ከደን መመናመን ጋር ተያይዞ ችግሩን አባብሶታል። ዛፍ ለመቁረጥ ረጅም ርቀት ይሄዳሉ፤ ሄደውም አያገኙም፤ በሌላ በኩል ደግሞ የዛፍ መቆረጥ ሌላ አሉታዊ ውጤት ያስከትላል። የቆዳ ውጤቶች ደግሞ በፕላስቲክና በብረት ዕቃዎች ተተክተዋል። ልጆችም እንዲህ አይነት ሙያ ከመማር ይልቅ ትኩረታቸውን ወደ ዘመናዊው ትምህርት ብቻ ያደርጋሉ።
የዕቃዎቹ አሠራር
ከእንጨት ለሚዘጋጁ ዕቃዎች የሚሆነው እርጥብ እንጨት ነው። ምክንያቱም እርጥብ እንጨት በሚፈልጉት ቅርጽ ለመጥረብ ያመቻል። በአንዳንድ አካባቢ ግን ከደረቀ በኋላም የሚሰሩት አሉ። የእነዚህ ደግሞ ምክንያታቸው በእርጥቡ ከተሰራ ሲደርቅ ቅርፁ ይበላሻል በሚል ነው። ወይም ትክክለኛ የዕቃውን መጠን አይገልጽም፤ ሲደርቅ ይጣመምና ይኮማተራል። በአብዛኛው ግን በእርጥቡ ነው፤ ቅርፁ እንዳይበላሽ እየተከታተሉ ያስተካክሉታል። ለዚህ ያመች ዘንድ ደግሞ መጀመሪያውኑም የሚመረጡት የዛፍ አይነቶች ታስቦበት ነው። የተገኘው ዛፍ ሁሉ አይሆንም። ጥንካሬያቸውና ምቾታቸው የታወቁ ዛፎችን ነው። ምናልባት እንኳን የሚፈለገው የዛፍ አይነት ሲጠፋ የተገኘውን ቢያደርጉም ጥራቱ ግን ይለያያል። ከእንጨት የሚሰሩ የሶማሌ ብሔረሰብ የዕደ ጥበብ ዕቃዎች፤ሄሮ (የመመገቢያ ሰሀን)፣ፈንዳል (ማንኪያ)፣መኑን(ኩባያ)፣ቶብኬ(ወተት ማለቢያ)፣ሲዶሌ (ወተት መያዣ)፣ሞዬ(ሙቀጫ)፣ ኢርቤ(ማማሰያ)፣በርኪን(ማማሰያ)፣በርኪን(ትራስ) የመሳሰሉት ለተለያየ አገልግሎት ይውላሉ።
እነዚህ ዕቃዎች ለገበያ የሚቀርቡት በሁለት መንገድ ነው። አንደኛው ዕቃውን በቀጥታ ለተጠቃሚው መሸጥ ሲሆን ሁለተኛ በጅምላ ለነጋዴ መሸጥ ነው። ለተጠቃሚዎች ሲሸጥ ገበያ በመሄድ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ተጠቃሚዎች ራሳቸው ባለሙያዎች ቤት በመሄድ ሊሆን ይችላል። በተለይ የመመገቢያ ዕቃዎች ከፕላስቲክና ከብረት ከሚዘጋጁ የፋብሪካ ዕቃዎች በተለየ ምግብን ያጣፍጣሉ ተብሎም ይታመናል። ምግብ ሳይበላሽ የማቆየት፣ምግብ እንይዳደርቅ የማድረግ አቅም አላቸው። የምግቡን ቃና ተጠብቆ እንዲቆይ ያደርጋሉ። ዋጋቸውም (እንደየ ዕቃው ይለያያል)ከ25 እስከ 400 ብር ነው (ከ2009 ዓ.ም በፊት የነበረ ዋጋ ነው)።
የቆዳ ውጤቶችም እንዲሁ ለተለያየ አገልግሎት ይውላሉ። ለወተት መያዣና መናጫ፣ ቅቤ ማስቀመጫ፣ የጉድጓድ ውሃ መቅጃ፣ ለመኝታና መስገጃ፣ ቀንበር ለማሰርና ለሌሎች የግብርና ሥራዎች ያገለግላሉ። እነዚህ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኙ መደረግ አለበት። በዓመት አንድ ጊዜ የባህል ዓውደ ርዕይ ጠብቆ ከማሳየት ባለፈ የገቢ ምንጭም ሊደረጉ ይገባል። ከጥናቱ የተረዳነው ነገር ራሳቸው ባለቤቶች እንኳን ክብር እንዳልሰጡት ነው። ክብር ያልሰጡት ደግሞ የራሳቸው ስለመሆኑ፣ አኩሪ ስለመሆኑ በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስላልተሰጠ ነው። ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ባለቤት ናት ሲባል እኮ ማስረጃዎቹ እነዚህ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ናቸው። የተገላቢጦሽ ግን የተማረ በሚባለው በኩል ያለው አመለካከት የተዛባ ሆኗል። ሥልጣኔ ማለት ኒኩለር ማብላላት ብቻ መሰለን። እናቶቻችን በባህላዊ መንገድ የሚያወጡት አረቄ ኋላቀር ተብሏል። ለዛሬው ኮምፒተር መነሻው የድንጋይ ጽሁፍ መሆኑን አላወቅንም። ለዛሬው ትራክተር መነሻው ገበሬዎች የፈለሰፉት ከእንጨት የተዘጋጀ ሞፈርና ቀንበር መሆኑን አላወቅንም። ለእንዲህ አይነት የዕደ ጥበብ ሥራዎች ሁላችንም ክብር ልንሰጥና ልንኮራባቸው ይገባል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 11/2012
ዋለልኝ አየለ