የ መንግስት ሰራተኞችን ጠዋት ወደ ቢሮ እና ማታ ወደ ቤት የሚወስደው ሰማያዊው አውቶብስ
(ፐብሊክ ሰርቪስ የሚባለው ማለት ነው) አብዛኞቹ ሾፌሮች ከጎልማሳነት በላይ ሲሆኑ አንዳንዶቹም ሽማግሌ በሚባለው ዕድሜ ላይ ያሉ
ናቸው። በነገራችን ላይ እነዚህ ሾፌሮች በጣም ለህግ ተገዥ ናቸው፤ አንዳንዴ ስበሳጭ ግን ‹‹አቤት ክፋት›› ብየም ወቅሻቸው አውቃለሁ።
ይሄን ያልኩት ከራሴው ጥቅም አንፃር እንጂ እነርሱ ህግን ተከትለው ነው የሚሰሩት።
ለምን ይደበቃል! ግልጽ የሆነ ክፋትም አለባቸው። ለምሳሌ ሰው አስገብተው በሩን እየዘጉ ሳለ አንድ ሰው መታወቂያ እያሳየ ‹‹እባክችሁ ልግባ›› የሚል መማጸን ሲያሳይ ዝም ብለው ይዘጉታል፤ መልሰው ቢከፍቱለት ቅንነት እንጂ ህግ መጣስ አይደለም። እንደየሚመጡበት ሰፈር ለመቆም የተፈቀዱላቸው ቦታዎች አሉ፤ ከእነዚያ ቦታዎች ውጭ አይቆሙም። ሌሎች ሰርቪሶች የሚቆሙበት ቦታ ላይም አይቆሙም። እዚህ ቦታ ላይ ቢቆሙ ህግ መጣስ አይደለም፤ ግን አንድ ሰው መታወቂያ እያሳየ ዝናብ ሲቀጠቅጠው እያዩ ዝም ይላሉ። ህግ አክባሪነታቸው ግን ከየትኞቹም ሾፌሮች በተለየ የሚደነቅ ነው።
ሌላኛው ከእነዚህ ሾፌሮች ያስተዋልኩት ነገር በአውቶብሱ ውስጥ የሚከፍቱት የሬዲዮ ጣቢያ ነው። ስም መጥቀሱን ልተወውና በአብዛኞቹ አውቶብሶች ውስጥ የሚሰማው አንድ ዜና የሚያዘወትር ኤፍ ኤም ሬዲዮ ነው። ቀይረውት እንኳን ቢሆን ሌላ ዜና የሚናገር ሬዲዮ ላይ ነው። የስፖርትና የመዝናኛ ጣቢያዎች ብዙም አይከፈቱም። ከዚህ የተረዳሁት ነገር፤ ሾፌሮች አዋቂነት ዕድሜ ላይ ስለሚገኙ ከስፖርት ይልቅ አገራዊ ጉዳይ እንደሚያስበልጡ ነው። በሌላ በኩል ተጓዡም የመንግስት ሰራተኛ ስለሆነ ከስፖርት ይልቅ አገራዊ ክንውኖችን መስማት አለበት በሚል ታሳቢነት ይሆናል።
ከሰሞኑ ግን አንድ ያለመድኩት ነገር አጋጠመኝ። በዚህ አውቶብስ ከአንዴም ሁለቴ ስሄድ ሰውየው በተመስጦ የሚሰሙት አንድ ስፖርት የሚያዘወትር ኤፍ ኤም ሬዲዮ ነው። ወጣቶችንም ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት ብየ ብዙም ትኩረት አልሰጠሁትም። ነገሩን ትኩረት እንዲሰጠው ያደረገኝ ይሄኛው አጋጣሚ ነው። በአውቶብሱ ውስጥ የተከፈተው ኤፍ ኤም ውስጥ እየተቀባበሉ የስፖርት ወሬ በለው ይላሉ። ሰዓቱ ደግሞ ጠዋት የአንድ ሰዓት ዜና የሚሰማበት ነው። ከአጠገቤ ያለ አንድ ወጣት በስልኩ ሌላ የኤፍ ኤም ጣቢያ ከፍቶ ዜና ይሰማል። ወጣቱ አገራዊ ሁነቶችን ለመስማት ዜና ሲከፍት ሽማግሌው ቀልባቸውን የሳበው የስፖርት ወሬው ነው።
አንድ ገጠመኝ በአናቱ ልጨምርበትና ወደ ሌላ ሀሳብ እንሄዳለን። ከሁለት ዓመት በፊት ያጋጠመኝ ነው። ከአዲሱ ገበያ ወደ ፒያሳ እየመጣን ታክሲ ውስጥ የተከፈተው ሬዲዮ ሃይለኛ የስፖርት ትንተና ላይ ነው። ሾፌሩም ወጣት ነው፤ ብዙ ጊዜ ታክሲ ውስጥ ስፖርት የተለመደ ቢሆንም ይሄኛው ወጣት ምን እንደነካው ባላውቅም በድንገት ጣቢያውን ቀይሮ ዜና ላይ አደረገው። አንድ ከኋላ የተቀመጡ ሽማግሌ ‹‹ለምን ቀየርከው›› ሲሉ ከፍተኛ ቁጣ አስከተሉ። ሳይቃወምም ሳይደግፍም የነበረው ተሳፋሪ ቀልቡን ወደሰውየው አደረገ። አንዳንዱ እየሳቀ፣ አንዳንዱም በትዝብት ከንፈሩን እየመጠጠ ዝም አለ። አንድ በጎልማሳነት ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰውየ ግን አላስቻለውም ተናገራቸው። ‹‹አሁን እርስዎ በዚህ ዕድሜዎ ኳስ ላይ ካልተደረገ ብለው ይሳደባሉ?›› ሲል በትህትና ጠየቃቸው። ቁጣቸውን ከሾፌሩ ወደዚህ ሰውየ አደረጉ። ቀጥሎም የአገሪቱ ሁኔታ ከስፖርት ውጭ ሌላ ነገር ሊሰማበት እንደማይገባ አወሩ። ዜናዎች ሁሉ የውሸት ስለሆኑ ስፖርት መስማት እንደሚገባ በቁጣ ሲናገሩ ቆዩ። የታዘበም ታዝቦ የተናገረም ተናግሮ በየምንወርድበት ወረድን፡
እንዲንገረም ያደረገን ሰውየው ሽማግሌ መሆናቸው ነው። መስማት የለበትም ማለት አይደለም። ዳሩ ግን ከሌላው አገራዊ ጉዳይ ይበልጣል ማለት እንኳን ከሽማግሌ ከወጣትም አይጠበቅም። ብዙ ጊዜ ጋዜጣና መጽሔት የሚያነቡ፣ ዜናዎችን የሚከታተሉ ከወጣቶች ይልቅ ታላላቆች ናቸው። ይሄ ምንም ጥናት የሚያስፈልገው ነገር አይደለም፤ አራት ኪሎ አካባቢ ካሉ ካፌዎች ብትገቡ ጋዜጣና መጽሔት ይዘው የሚታዩት በብዛት በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች ናቸው።
በነገራችን ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወጣቶች የኳስ ፍቅር እየቀነሰ ነው። እስኪ ቀደም ከነበረው ጋር አነፃፅሩ። እውነት እንደበፊቱ ነው? አንድ ነገር የተቀየረ ይመስለኛል። ወጣቶች ከፖለቲካ ርቀዋል የሚል ወቀሳ በዝቶ ነበር፤ አሁን ያንን ለማካካስ ይሁን በሌላ ምክንያት ባይታወቅም ወጣቶች ከኳስ ይልቅ ፖለቲካ ሲያወሩ ነው የሚሰማው። በየታክሲው፣ በየካፌው፣ በየተገናኙበት አጋጣሚ ሁሉ የሚያወሩት ትናንተ ማታ ስለተደረገ ጨዋታ እንጂ ስለፖለቲካ አልነበረም። ወጣቶች እርስበርስ የሚፎካከሩት የተጫዋችና የአሰልጣኝ ስም በመያዝና በኳስ ትንታኔ እንጂ በፖለቲካ ትንታኔ አልነበረም።
እውነት የወጣቶች የኳስ ፍቅር እንደበፊቱ ቢሆን ፌስቡክ ሌላ ነገር ይወራበት ነበር? ገፆች ሁሉ የአውሮፓ ፕሪሜየርሊግ አይሆኑም ነበር? ግን እንደምታዩት የሚወራው ሁሉ ፖለቲካ ነው። ከዚያ አለፍ ካለም ቀልድና ሌሎች የመዝናኛ ገጾች ናቸው።
ወጣቶች ለምን ከስፖርት ራቁ ብየ እያማረርኩ አይደለም። ከዚህ በፊት የነበረው ወቀሳ ከኳስ ውጭ ሌላ ነገር ማወቅ አልቻሉም የሚል ነበር። ወጣቱ አገራዊ ጉዳይ ላይ ተሳታፊ አልሆነም የሚል ነበር። በወጣቶች በኩል ደግሞ ዕድል አልተሰጠንም የሚል ኩርፊያም በየመድረኩ ይሰማ ነበር። ኧረ እንዲያውም ኳስ ወጣቱን ማደንዘዣ ነው ሲባል ሁሉ ነበር።
አሁን ኳስ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጉዳዮችንም መከታተላቸው ጥሩ ነው። ወጣቱ ምንም ይሁን ምን የአገሩን ጉዳይ ካልተከታተለ አገር ተረካቢ ሊሆን አይችልም። አገር ተረካቢ የሚሆነው አገሩን በማወቅ ነው። እንደዚያ ታክሲ ውስጥ ከስፖርት ውጭ ሌላው ውሸት ነው እንዳሉት ሽማግሌ መሆን የለበትም። ዜናዎች ሁሉ እውነት ናቸው እያልኩ አይደለም፤ ዳሩ ግን ሽማግሌው ለስንፍናቸው መደበቂያ ተጠቀሙት እንጂ ሰምቶ ነው መገምገም የሚቻለው። እንደ እሳቸው አይነት ሽማግሌ አኩርፎ ከተወው ማነው ታዲያ የሚያስተካክለው? ስለዚህ አባቶች ወጣቶችን ነው መምከር ያለባቸው። ከወጣቱም ባልተናነሰ ሀገራዊ ጉዳይም ሊያሳስባቸው ይገባል። እንደዚያ ሲሆን ነው ወጣቱንም ገስጸው ወደ መስመር ማስገባት የሚችሉት።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 11/2012
ዋለልኝ አየለ