የተወለዱትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በቀድሞው ባሌ ክፍለሃገር መንደዮ አውራጃ ደንበል በምትባል ትንሽ ከተማ ውስጥ ነው። ሁለተኛ ደረጃ ሲደርሱ ግን በአካባቢያቸው ሁለተኛ ደረጃ ባለመኖሩ ወደ ባሌ ሮቤ ተሻግረው ዘጠነኛና አስረኛ ክፍልን ተምረዋል። 12ኛ ክፍል ሲደርሱም ባሌ ጎባ በሚገኘው ባቱ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በመቀጠልም የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናቸውን በማለፍ ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በፎረስትሪ ትምህርት ክፍል ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ። በወቅቱ ታዲያ በብሄረሰቦች ላይ ይደረግ የነበረውን የፖለቲካ ጫና በመቃወም በኦነግ ይመራ የነበረውን የተማሪዎችን እንቅስቃሴ ተቀላቀሉ። አልፈው ተርፈውም ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ትምህርታቸውን እርግፍ አድርገው በመተው ጫካ ገቡ።
ለስልጠናም ጅቡቲና
ኢትዮጵያ እየተመለላሱ በኦነግ ትግል ውስጥ የበኩላቸውን እንቅሳቀሴ ማድረግ ቀጠሉ። የደርግ መንግስት መውደቂያው ሊቀረብ ሲልም ጅቡቲ
ሆነው ትግላቸውን ቀጥለው እያለ ካናዳ የመሄድ እድሉ ይፈጠርላቸዋል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 20 ዓመታት ኑራቸውን ካናዳ ያደርጋሉ፤
በአንድ በኩል ትግሉን ሳያቆሙ በሌላ በኩል ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስሬሽን ትምህርት መስክ ተምረው በሙያው መስራታቸውን ቀጠሉ። ትዳር
መስርተውም የአንድ ወንድ ልጅ አባት ለመሆን ችለዋል። እኚህ የዛሬው የዘመን እንግዳችን በቅርቡ መንግስት በውጭ ተሰደው ለሚገኙ
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የፈጠረውን ምቹ እድል ተጠቅመው ወደ አገራቸው ከተመለሱ ፖለቲከኞች አንዱ ናቸው። ወደ አገራቸው
ከተመለሱ በኋላም ለውጡን በመደገፍ የበኩላቸውን ሚና እያበረከቱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ የኦሮሚያ ክለላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት
አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከአቶ አሚን ጁንዲ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይዘንላችሁ
ቀርበናል ፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- ከሁለት አስርታት በኋላ ወደ አገርዎ ተመልሰው ህዝቦን ለማገልገል ምክንያት የሆኖት አብይ ጉዳይ ምንድን ነው?
አቶ አሚን፡- እንዳልሽው እኔ አገሬንና ቤተሰቤን ጥዬ ከወጣሁ በድምሩ 26 ዓመታት ይሆናል። በእነዚህ ዓመታት ካለችበት አስከፊ ሥርዓት እንድትላቀቅ በፖለቲካ ድርጅቴ በኩል የበኩሌን ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ። ይሁንና ከነበረው ሁኔታ አስከፊነት የተነሳ ዳግም አገሬ ለመግባት የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይፈጠራል የሚል እምነት አልነበረኝም። ለነገሩ እንደ እድል ሆኖ ድርጅቴ ኦነግ ሁሉም ህዝቦችና ማህበረሰቦች በአንድነትና በእኩልነት በመከባበር የሚኖሩባትን ኢትዮጵያ እንገነባለን የሚል እምነት ቢኖረውም ጥቂት የማይባሉ ሰዎች እንደአገር ገንጣይና ከፋፋይ አድርገው ይቆጥሩት ነበር። ያ ኦነግ ሲታገልለት የነበረው ዓላማ ደግሞ በሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ሲሳካ ሳይ እኔ ከዓላማ ጋር እንጂ ከፖለቲካ ድርጅቱ ጋር የግድ መቆራኘት የለብኝም ብዬ ስለማምን ወደ አገሬ ለመመለስ ወስኛለሁ።
በተለይም ደግሞ ባለፉት 26 ዓመታት ያካበትኩት እውቀቴ ብዬ የምለው ነገር ቢኖር የምከተለው ፓርቲ የሚታገልለት ዓላማ ሌላ ለየት ያለ ፓርቲ የሚያሳካው ከሆነ ያንን ፓርቲ መደገፍ እንዳለብኝ መረዳቴ ነው። በነገራችን ላይ እኔ ፓርቲን ነፃ ለማውጣት የምታገል ሰው አይደለሁም። በመሆኑም እኛ ስንታገልለት የነበረው 27 ዓመቱ የትግል ግብ አገር ውስጥ ባሉት የኦዲፒ ታጋዮች፣ በቄሮዎቻችንና በፋኖዎቻችን ብሎም በተቀሩት ማህበረሰቦች ትብብር ሊሳካ በመቻሉ ደስተኛ ነኝ። ያ ላለፉት 27 ዓመታት አገሪቷን ወደ አስከፊ ሁኔታ ሲመራት የነበረውና በህዝቦች መካከል ጥላቻ ሲዘራ የነበረው፣ በፌዴራሊዝም ሰበብ በህዝቦች መካከል መከፋፈልንና መገዳደልን ያመጣውን ሥርዓት ሲገረሰስ ማየት በራሱ ለእኔ ትልቅ ህልም ነበር። ለውጡ በመጣበት ወቅት ታዲያ ኢትዮጵያ ወደተሻለ ሥርዓት እየተሻገረች መሆንዋን ስለተረዳሁና የቆምኩለት ዓላማ በሌሎች ክፍሎች ሲሳካ ሳይ በመጀመሪያ በልቤ ውስጥ የመጣው ይሄ ጥሩ አጋጣሚ ነው። ምክንያቱም እንደነገርኩሽ ስታገልለት የነበረውም ዓላማ ይሄ ነው። አሁን ወደአገሬ መመለስና ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ያለኝን ዓላማ ለማሳካትና ይህንን ህዝብ በቀረኝ እድሜዬ ማገልገል አለብኝ ብዬ ነው የመጣሁት።
አዲስ ዘመን፡- ከመጡበት ዓላማ አንፃር አገርዎ ከገቡ በኋላ ሁኔታዎችን እንደጠበቁት ነው ያገኙት?
አቶ አሚን፡- ያለፈውን ሥርዓት በውጭ ሆኜ ከምሰማው በዘለለ ብዙ ስለማላውቀው ብዙ መናገር አልችልም። ይሁንና ከሚታሰሩት፣ ከሚባረሩት፣ ከሚንገላቱት ከምንሰማው አንፃር 27 ዓመት የነበረችው ኢትዮጵያና አሁን በአይን የምናያት ኢትዮጵያ በጣም ልዩነት አላት። ኢትዮጵያ ዛሬ ጋዜጠኞች በሰላም የሚፈልጉትን የሚፅፉባት፥ የሚናገሩበት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በፈለጉበት መንገድ የሚንቀሳቀሱባት፣ እስርቤቶቻችን በፖለቲካ ተቃዋሚዎች ያልተሞሉበት አገር ሆናለች። እነኚህን ለውጦች ሳይ ትናንት ከነበረው የተሻለች ሀገር መሆኗን ተረድቻለሁ።
በሌላ በኩል ግን ወደዚህ ስመጣ ከጠበቅኩትና ከገመትኩት ውጭ ያጋጠመኝና ብዙ ጊዜ የሚያናድደኝ ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፉት 27 ዓመታት በጣም አስከፊ በሆነ ሥርዓት ውስጥ እንዳለፈ ይታወቃል። ሰዎች የመፃፍ፣ የመናገር፣ የመደራጀት መብት እንዳልነበራቸውና ይሄንን ሁሉ ተነፍገው እስርቤት ሲማቅቁ፣ ሲገደሉ፣ የነበረባት አገር እንደነበረች እየታወቀ ከለውጡ በኋላ የተፈጠረውን ሰላማዊና የዴሞክራሲ ምህዳር ለምን አድንቀን ልናስቀጥለው ያለመፈለጋችን ግርም ይለኛል። ቢያንስ ቢያንስ ከውጭ የመጣነው አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች የዴሞክራሲን ሂደት ጊዜ እንደሚፈልግ መረዳት አለመቻላችን ያሳዝነኛል። ዴሞክራሲ በአንድ ጊዜ ሊመጣ እንደማይችል እየታወቀ «ለውጡ ግብታዊ አይደለም፤ በቦታው አልደረሰም» ብሎ ማለት በጣም ያስገርመኛል።
እስከላሁን የመጡትን ለውጦች ማሳደግ ሲገባን ሁሉን ነገር የማጣጣል ነገር ስሰማ ከጠበቅሁት ውጭ ሆኖ ነው የሚሰማኝ። በተለይም ደግሞ ጥቂት የማይባሉ ጋዜጠኞች ከስርቤት ያወጣቸውን ይህንኑ ሥርዓት ተመልሰው በዚያው በተመሰሳይ ሁኔታ ሲያወግዙት ስመለከት እነዚህ ሰዎች የመቃወም ሱስ አለባቸው ወይ? ብዬ እንድጠይቅ ያደርገኛል። በተጨማሪም «በወያኔ ሥርዓት ተኮላሸን፤ ተንገላታን» ሲሉ የነበሩ ፖለቲከኞች ዛሬ ተፈተው ደግሞ በዛው በተመሳሳይ ሁኔታ ውጭ ሆነውና የመቃወም መብታቸው ተጠብቆላቸው እያለ ዶክተር አብይ የሚመራውን መንግስት ሲያወግዙ ሳይ እነዚህ ሰዎች የአዕምሮ ችግር አለባቸው እንጂ በእርግጥ ትናንትም ወያኔ ራሱ ምንም አላደረጋቸው ይሆን እንዴ? የሚል ነገር ውስጥ ነው የሚያስገቡኝ።
እኔም ሆነ አንቺ በትክክል የምናውቀው ነገር ቢኖር መታሰራቸውን
ነው። ያንን ሁኔታ ታዲያ ከሰማሽ በኋላ የትናትናውን ከአሁኑ ጋር አታወዳድሪውም። ስትታሰሪም ተቃውመሽ! ተፈተሽ ነፃነቱ ሲሰጥሽም
የምትቃወሚ ከሆነ ተቋውሞሽ በራሱ ጥያቄ ውስጥ ነው የሚገባው። እንዳልኩሽ እኔ ወደዚህ አገር ስመጣ ይህ አይነቱ ነገር ያጋጥመኛል
ብዬ አልጠበኩም ነበር። ይህንን ስል ዴሞክራሲያዊ መንገድን ተከትሎ የመንግስትን ህፀፅ መንቀፍ አይገባም ማለቴ እንዳልሆነ እንድትገነዘቢልኝ
እፈልጋለሁ። አሁን እየሆነ ያለው ይህ አይደለም። መንግስት ያሉበትን ክፍተቶች የሚያሳዩ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 11 ቀን 2012 ዓ.ም
ታኅሣሥ ፲፩/፳፻፲፪
ተቃውሞዎችን ከማቅረብ ይልቅ ብሄርን በብሄር ላይ በማነሳሳት፣ የአንዱን ብሄር ጀብደኝነት በማውራት የሌላውን ደግሞ በማንቋሸሽ የሚደርግ ተግባር አፀያፊ ነገር ነው። በእኔ እምነት የትኛው ብሄረሰብ ከሌላው የሚበልጥበት ጀብዱ የለውም። ሁላችንም ከአንድ ማህበረሰብ የወጣን በአንድ ህይወት ውስጥ ያለን በአንድ ዣንጥላ ስር ሆነን ዝናብ የምንጠብቅ ሰዎች ነን። ይህንን ሀቅ ነው ሰዎች እየሳቱት ያለው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንፃር እነዚህ ጉዳዮች የለውጡ ስጋት ናቸው ብለው ያምናሉ?
አቶ አሚን፡- ስጋት ነው የምላቸውን ጉዳዮች በሁለት በኩል ነው የማያቸው። አንደኛ መንግስት እንደመንግስት ዴሞክራሲን እተገብራለሁ ከሚለው አቋሙ ጋር የአገሪቱን ደህንነት ጥያቄ ውስጥ እያስገባ መሆኑን የተገነዘበው አይመስለኝም። በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ጎረቤት አገራትም ሳይቀር ሰላምን ለማምጣት በሚጥርበት ጊዜ የሚያስተዳድረው ህዝብ ዴሞክራሲ ሂደት ማለት ምን ማለት መሆኑን የተረዳ አይመስለኝም። ለዚህ ነው እንግዲህ ዴሞክራሲን በመተግበርና የአገርንና የህዝቦችን ደህንነት የመጠበቁ ጉዳይ እየተጋጨ የመጣው። ስለሆነም መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ካላደረገ በስተቀር አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ስጋት አለኝ። ምክንያቱም በዚህች አገር ሰዎች ስለዴሞክራሲ ሲያወሩ ስለግዴታ አያወሩም። ዴሞክራሲ መብት ብቻ የሚመስላቸውም በርካቶች ናቸው። ዴሞክራሲ የራስሽን ፍላጎት ማሳካትና መተግበርን ስትጀምሪ ከአጠገብሽ ካሉት ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ሁኔታን የማትመኚ ከሆነ የአንቺ ዴሞክራሲ ከግምት ውስጥ ሊገባ አይችልም። ጎረቤትሽ ችግር ውስጥ እየታመሰ አንቺ ሰላም ውስጥ ነው ያለሁት ማለት አትችይም። ሁላችንም ሰላማችን እንደሚያስተሳስረን ሁሉ መብትና ግዴታችን ያስተሳስረናል። ህግ ባለበት አገር ሁሉ ነገሮች ሁሉ ከህግ በታች መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ይመስለኛል። ህግን ለሚያስከብረው መንግስት ያለን ክብር ካልታወቀ ዴሞክራሲ ትርጉም አልባ ነው የሚሆነው።
ህዝባችን ያገኘውን የዴሞክራሲ መብት በትክክለኛው የምርጫ ኮሮጆ የሚፈልገውን ፓርቲ ወይም አመራር መምረጥ እየተቻለ ለምን በጠብመንጃ በየመንደሩ ተማሪዎቻችንን መግደል እንደሚፈለግ አይገባኝም። ይሄ ሁኔታ ለእኔ ሌላው ስጋት ነው። ይህም ሲባል ሁኔታውን ግን ማባባስና ማቀጣጠል አለብን እያልኩ አይደለም። አንድ ተማሪ ጎንደር ውስጥ ስለሞተ ተመሳሳይ ጉዳይ ሰጥተን ኦሮሚያ ውስጥ ወይም ደቡብ ውስጥ ተማሪ መሞት የለበትም። እይታችን አመለካከታችን ጎንደር ውስጥ የሞተው ተማሪ ከኦሮሚያ ይምጣ፤ ከትግራይ ወይም ደግሞ ከደቡብ የኛ ተማሪ ነው የሚል አስተሳሰብ ህዝባችን ውስጥ መፈጠር አለበት። አሁን ላይ በሁላችንም ዘንድ ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ነው የጠፋው። ፖለቲከኞቻችንና አክቲቪስቶቻችንም ይህንን ጉዳይ ከማባባስ ባሻገር መንግስትን ለመጣል የሚጠቀሙት ስትራቴጂ አድርገው ነው እየተጠቀሙበት ያለው። ይህ አስተሳሰብ እስካለ ድረስ ችግሩ አስከፊ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አቶ አሚን፡- በእኔ እምነት መንግስት የሚጣለው አመፅ በማስነሳት አይደለም። ህዝቦችን በህዝቦች ላይ በማነሳሳት የሚመጣው የመንግስት ለውጥ ተመሳሳይ መንገድን የሚያስጉዝ አካሄድ ነው የሚሆነው። በእርግጥ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ህዝብን የሚገድል፣ ህዝብን ያለሥርዓት የሚያስር ከሆነ በህዝባዊ አመፅ ሊወድቅ ይገባል። አሁን ሰው የሚገድል መንግስት የለም። ለምሳሌ በትዕዛዝ አንቺ የማነሽ ጋዜጠኛ? እንዴት የመንግስት አመለካከት አታራምጅም? ብሎ የሚገልሽ ወይም የሚያስርሽ አካል የለም። ይህንን የፖለቲካ ድርጅት ተቀላቅለሻል ተብለሽ አትታሰሪም። ሰላማዊ ሰልፍ ስለወጣሽም አልታሰርሽም፤ አልተገደልሽም። ስለዚህ መንግስት ላይ ሰላማዊ የሆነ የትግል መስመር መከተል ስንችል ሰዎችን ከሰዎች ጋር ማጋጨት ወይም ለጦርነት ሰዎችን መጋበዝ ለምን አስፈለገን?። በተለይም በአሁኑ ወቅት ተማሪዎቻችንን በየትምህርት ቤቱ በተለያዩ አሻጥሮች እየገደሉ ህዝቦችን ከህዝቦች ጋር ለማጋጨት የሚደረገው ሙከራ ለእኔ በጣም የሚያሰጋ ጉዳይ ነው።
ስለሆነም ህብረተሰባችን ከዚህ ወጣ ባለ መንገድ ቢያስብ ይህችን አገር በሰላም ልናስቀጥላት የምንችለው መተሳሰብ ሲኖር ነው የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም ሁላችንም ምንም ነገር የሚለየን ነገር አለ ብዬ ስለማላምን ነው። ሁላችንም አንድ አይነት ደም ነው ያለን። በነገራችን ላይ «ኦሮማራ» የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ያወጣሁት እኔ ነኝ። ይህንን ቃል ዛሬ ብዙ ሰዎች ይናገሩታል። ዛሬ ምንአልባትም እኔ አሮሞ አንቺ አማራ ልትሆኚ ትችያለሽ፤ አንቺ አማራ እኔ ኦሮሞ እየተባባልን ብቻ አንድ ላይ ሆነን በመካከላችን የሚፈጠረውን ጥላቻ ልናስቀረው እንችላለን። እናም በእኔ አመለካከት ጥያቄያችንን ከዘር ጋር ባናያይዘው ደስ ይለኛል። ለምሳሌ አማራ ክልል ስንል አማራ ክልል ውስጥ አማራ ብቻ እንደሌለ ግንዛቤ ውስጥ በመክተት የአማራ አገር ነው ከምንል አማርኛ ተናጋሪዎች የሚኖሩበት አገር ብንል የተሻለ ይመስለኛል። ኦሮሚያንም በዚሁ መልክ ብንመለከት ከዘር ጥያቄ እንወጣለን ብዬ አስባለው።
ባለፉት በ27 ዓመታት የተሰራው ሌላውና ትልቁ ስህተት ብዬ የማምነው የዜጎች መታወቂያ የብሄር ማንነት የተገለፀበት ነው። ይህ ለእኔ በጣም ፀያፍ ነገር ነው። ቢያንስ ቢያንስ በክልል ደረጃ ቢያስቀምጡት የተሻለ ይሆን ነበር። ግን ያንን ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት ብዬ የማምነው የሩዋንዳውን ጭፍጨፋ በእኛም አገር ለመድገም ታስቦ ስለነበር ነው። ስለዚህ አሁን መቀየር አለባቸው ከምላቸው ጉዳዮች ዋነኛውና ትልቁ ነገር መታወቂያ ላይ የተቀመጠው የብሄር ማንነት ጉዳይ ነው። እኔ አሁንም ቢሆን ማንን ከማን ለመለየት ተብሎ እንደመስፈርት መቀመጡ አይገባኝም። ለመለያ ማስቀመጥ ከተፈለገም የምትኖሩበት አካባቢ መግለፅ ይችል ነበር። እነኚህ ነገሮች ደግሞ ፌዴራሊዝም ሥርዓቱን ራሱ በመቀልበስ ወደ ሌላ መስመር እንዲመራ አድርጎታል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ተቀልብሷል እያሉ ነው?
አቶ አሚን፡- አዎ! እኔ ባለፉት 27 ዓመታት መንግስት ፌዴራሊዝም በአግባቡ አልተተገበረም ባይ ነኝ። በእርግጥ የተቀመጠው ሥርዓት የሚያዋጋ፣ የሚያጋድልና ዘርን ከዘር የሚለይ አይደለም። ሥርዓቱ ላይ ግን አልተሰራበትም። የህዝቦች እንቅስቃሴ ገደብ ነበረው። ከትግራይ ክልል ብቻ ሄደሽ ነው ደቡብ ላይ ወይም ኦሮሚያ ላይ መስራት የምትችይው። ይህንን ደግሞ ልክ በህግ እንደዚያ ተደርጎ እንደተቀመጠ አድርገው ነበር ሲሰሩበት የነበረው። ግን በህገመንግስቱ ላይ ከየትኛው ክልል የመጣ ሰው በፈለገበት አካባቢ መስራት እንደሚችል በግልፅ ነው የተቀመጠው። ሁሉም ደግሞ በዚህች አገር ውስጥ እኩል ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው በህገመንግስቱ ተደንግጓል። ይሁንና በመሬት ላይ ያለው እውነታ ይህ አልነበረም። ስለዚህ ላለፉት 27 ዓመታት የተሰራባቸውና የተከማቹት ቁርሾዎች አሁን ለምናደርገው የመለያየት የመጋጨት መንስኤ ናቸው ብዬ አምናለሁ። እነኚህ ጉዳዮች ደግሞ ዛሬም ስጋቶች ናቸው። ለዚህ ደግሞ መፍትሄ የሚሆነው የዶክተር አብይ የመደመር ፍልስፍና ነው። ለዚህም ነው እኔም የምደግፈው።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ ይህ ፍልስፍና በተለይም በኦሮሞ ስም የተቋቋሙ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ፌዴራሊዝም ሥርዓትን ያጠፋል፣ ማንነትን ደፍጥጦ ወደ አሃዳዊ ሥርዓት ይመልሰዋል የሚል ስጋት አላቸው?
አቶ አሚን፡- ይህንን ሃሳብ በፍፁም አልቀበለውም። የፌዴራሊዝም ሥርዓት አሁን ያለው የአብይ የመደመር ፖሊሲ ምንም ከፌዴራሊዝም ጋር የሚያጋጨው ነገር የለም። አስቀድሜ እንዳልኩሽ ፌዴራሊዝም ተቀምጦ በአገሪቷ ውስጥ ሲሰራ የነበረው ህግ ያልተፃፈ ህግ ነበር። ሰዎች የሚያውቁት ያልተተገበረውን የፌዴራሊዝም እውነተኛውን ቅጂ ሳይሆን የወያኔ ሥርዓት ሲተገብረው የነበረው ሌላውን ሥርዓት ነበር። እናም የእኛ አክቲቪስቶች ምንአልባት የሚያወሩት ያንን ወያኔ ሲሰራበት የነበረውን የፌዴራሊዝም ፍራቻ ይሆናል። ግን ደግሞ ዶክተር አብይ እየተናገረ ያለው በትክክል የኦሮሞ አክቲቪስቶችን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም የፖለቲካ ጥቅማጥቅም የሚፈልጉ ሃይሎችም እየነቀፉት ነው። እነሱ ቢቃወሙትም እውነታው አሁን እየተዘረጋ ያለው ሥርዓት ፌዴራሊዝም የሚነካ ሳይሆን ይልቁንም የሚያጠናክርና በትክለኛው መንገድ እንዲተገብር የሚያደርግ መሆኑ ነው። አሃዳዊ መንግስትን ለመፍጠር ታስቦ ነው የሚለውን ሃሳብ አልቀበለውም። ደግሞም አንዳችም ይህንን የሚመስል ነገር አላየሁበትም።
በእኔ እምነት ፌዴራሊዝም ሥርዓት እንዳይተገበር እስካሁን የነበሩት ችግሮች በፓርቲዎች ወይም ደግሞ በክልል መንግስታት በኩል የተደበላለቀ የአሰራር ሥርዓቶች መኖራቸው ነው። በነገራችን ላይ የትኛውም ፓርቲ መዋሃድ ሆነ የራሱን የሆነ ፖሊሲ ማስቀመጥ መብት አለው። ይህም ደግሞ ከፌዴራል ስርዓቱ ጋር የሚያያይዘው ምንም ነገር የለም። አሁንም ቢሆን አገሪቱ የምትዳደርበት የፌዴራል ሥርዓቱ አልተነካም። ኦሮሚያ ክልል አሁንም ክልል ሆኖ ይቀጥላል። የአማራ ክልልም እንዲሁ። ግን ከዚያ ክልል የሚወጡት የፓርቲ ተወካዮች አንድ ላይ የፈጠሩት የብልፅግና ፓርቲ ከፌዴራል ሥርዓቱ ጋር የሚያጋጨው ነገር የለም። ፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ተቀምጦ እያለ አገሪቱ ውስጥ ሲሰራ የነበረው ህግ ሌላ ህግ ነበር። በውስጡ አንዳንድ የህዝቦችን ግንኙነት ለማጠናከር የሚደረጉ እንቅስቅሴዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ የፌዴራል የስራ ቋንቋዎችን መጠን ለመጨመር የሚደረጉት ጥረቶች እንደውም ይበልጡኑ የህዝቦችን ጥያቄ የሚመልስና ፌዴራሊዝሙን የመተግበር ጉዳይ እንጂ ያንን የፌዴራል ሥርዓት የሚነካ ጉዳይ አይደለም። የአንዳንድ ሰዎች ጥያቄ ላለፉት 27 ዓመታት ስንሰራበት የነበረው አካሄድ እንቀጥል ነው ወይ? አይገባኝም። ምክንያቱም ያኛው ፌዴራሊዝም እንዳልነበር ግልፅ ነው። እናም አሁን ይበልጥኑ የፌዴራል ሥርዓት በትክክለኛ መንገድ የሚሰራበት መንገድ ነው እንጂ የተቀመጠበት የፌዴራል ሥርዓቱን ወደ አህዳዊ ሥርዓት የሚቀይርበት መንገድ የለም ባይ ነኝ። ይህ ማደናገርያና ከእውነት የራቀ ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በሌላ በኩል የኢህአዴግ ፓርቲን ውህደት አለመቀበል ማለት ከዚህ ቀደም በፓርቲው ውስጥ አባል ያልነበሩትን ፓርቲዎች የሚወክሉትን ህዝብ እንደመናቅ ነው ብለው የሚናገሩ ሰዎች አሉ። በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ አሚን፡- በትክክል! ተመልከች እንግዲህ፤ ኢትዮጵያ
ካሏት ዘጠኝ ክልሎች ውስጥ ውህደቱን የተቃወመው አንድ ክልል ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ራሱ ይሄ ለምን ሆነ ብሎ ራሱን መጠየቅ
አለበት። ይህንን ክልል የሚመራው ፓርቲ ደግሞ ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ሲያደርግ የነበረው ሰቆቃ እና የሰራውን ግፍ
ብሎም በኢኮኖሚው ላይ ምን ያህል ዝርፊያ ሲያካሂድ የነበረ ፓርቲ እንደሆነ ሁላችንም የምናውቀው ነው። ይህ ፓርቲ ያጠፋውን አጥፍቶ
ዛሬም ተመሽጎ የሚገኝ ፓርቲ መሆኑን መርሳት የለብንም። ደግሞም ውህደቱን የሚቃወሙት አማራው፣ ትግሬው ኦሮሞው፣ ደቡቡ፣ ሶማሌው፣
አፋሩና ሃደሬው አይደሉም። ውህደቱን መቃወም ማለት «ኢትዮጵያዊ እኛ ብቻ ነን፤ እኛ ከሌሎች ኢትዮጵያውያኖች የተለየን ነን» ከሚል
አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው። በእኔ እምነት ግን የውህደቱ እውን መሆን እስካሁን ድረስ ተገፍተው ውጭ የተቀመጡትን ሁሉ እናንተም ከሌሎች
ኢትዮጵያውያኖች ጋር እኩል ናችሁ እንደማለት ነው። በተጨማሪም እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች የመምረጥም የመመረጥም መብት አላችሁ
ብሎ እድል መስጠቱ ትልቅ እምርታ ነው ባይ ነኝ። ይህንን የሚገፋው ግን የዝርፊያና የግድያ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 11 ቀን 2012 ዓ.ም
ታኅሣሥ ፲፩/፳፻፲፪
ሥርዓት ሲመራ የነበረው ሃይል ዛሬ ተመልሶ በዚያው መንገድ ለመቀጠል ምኞት እንዳለው ግልፅ ነው። በተጨማሪም ዛሬም በኋላ በር ያንኑ ተግባር ለመመለስ የሚፈልጉ ሃይሎች ካልሆኑ በስተቀር የብልፅግና ፓርቲ በትክክል ለኢትዮጵያ ህዝብ ከአግላይነት ወደማቀፍ፤ ከመግፋት ወደ መቀበል የሚያመጣ አካሄድ ነው እየተከተለ ያለው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ይህንን ቢሉም አንዳንድ ሰዎች ግን በዶክተር አብይ የሚመራው መንግስት ልክ ትናንት ህውሃት ያደርገው እንደነበረው ሁሉ ለአንድ ወገን ያደላ ነው ይላሉ። እንዳውም ስልጣኖች ሁሉ ወደ ኦሮሚያ ክልል እየሄዱ እንደሆነም ነው የሚናገሩት። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ አሚን፡- አዎ! እንደዛ የሚባል ወሬ እኔም እሰማለሁ። ያ አስተሳሰብ የኦሮሞን ማህበረሰብ ነው እየጠቀመ ያለው የሚለው ድምፅ ይሰማል። የሚሰማው ጆሮ አጣ እንጂ! ዶክተር አብይ በእናቱ አማራ ስለሆነ በጠቅላላ የሚያግዘውና የሚሰራው ያችኑ አህዳዊ ኢትዮጵያን ለመመለስ የተቀጠረ የአማራ ቅጥረኛ አድርገው የሚያስቀምጡም ወገኖች አሉ። ሁለቱም የተሳሳቱ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ውህደቱን ተከትሎ በቅርቡ በኦዴፓ መሪዎች የተፈጠረው ልዩነት ፓርቲውን ለሁለት ይሰነጥቀዋል የሚል ሃሳብ የሚሰነዝሩ ምሁራን አሉ። በእርሶ እምነት ይህ ጉዳይ ምን ያህል ውሃ የሚያነሳ ነው?
አቶ አሚን፡- በመሰረቱ እኔ ውስጥ አዋቂ አይደለሁም። አስተያየቴን ልሰጥሽ የምችለው እንደማንኛውም ከውጭ መረጃውን እንደሰማ ሰው ነው። ከዚህ አኳያ እንግዲህ ሰዎች የራሳቸው የሆነ አመለካከት አላቸው። ለዚህ ነው የተለያየን ሰዎች የሆነው። የተለያየ አመላከከት ኖሮን አብረን መቀጠል የምንችል ሰዎች መሆናችንን ብዙዎቻችን አንረዳውም። በዶክተር አብይና በለማ መካከል ችግር አለ ብዬ አጋንኜ መናገር አልፈልግም። ምክንያቱም አሁን ከተፈጠሩት ትናንሽ ችግሮች በላይ አብረው ያሳለፉት መልካም ጊዜ ይበልጣል። አንዷን ነጠላ ጉዳይ አንስተን እንደተለያዩ አድርገን ማውራት አይገባንም። ይህንን ቀዳዳ ለመጠቀም የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች አሉ። ምክንያቱም የእነዚህ ሁለት ሰዎች አንድነት ተደምሮ ነው ይህንን ለውጥ ያመጣው። እንሱ ደግሞ የዚህ ለውጥ መሪዎች ነበሩ። የወደቁት ደግሞ ጠላት አድርገው የሚያስቀምጡት እነዚህን ሰዎች ነው። ስለዚህ የእነሱ ልዩነት ከማንም በላይ የሚያስደስታቸው እነዚህን የወደቁትን ሃይሎች ነው። ስለዚህ ወሬውን ማባባስና ማናፈስ የሚፈልጉት እነዚህ ሃይሎች ናቸው። ይህ ማለት ደግሞ ምንም አይነት ችግር አልነበረም ማለት አይደለም። ድርጅቱን አይጎዳም ማለት አይደለም። ግን ደግሞ ለረጅም ጊዜ አንድነቱን ጠብቆ የቆየ ድርጅት እንደመሆኑ የሁለቱ ሰዎች ልዩነት ያን ያህል ድርጅቱን ይከፍለዋል ብዬ አላምንም። ዶክተር አብይና ኦቦ ለማ ችግሮቻቸውን መፍታት ባይችሉ እንኳ ድርጅቱ ምንም አይሆንም። ግን ደግሞ ሁለቱንም በእኩል ደረጃ የሚወዳቸውና የሚከተላቸው ህዝብ ስላለ ችግሮቻቸውን እንደሚፈቱ እምነት አለኝ። ስለዚህም ሁላችንም ማጤን አለብን ብዬ የማስበው ትንሽዋን ችግር በማራገብ የእነሱን መለያየት የሚፈልጉ ሃይሎችን ማስደሰት እንደሌለብን ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለውን ሁኔታ ዘመነ መሳፍንት በሚመስል ሁኔታ የፌዴራል መንግስቱ አቅም ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፤ ህዝቡን ከጥቃት የመጠበቅ አቅሙ መዳከሙንና ከዛ ይልቅ የክልል መንግስታትና አንዳንድ ፖለቲከኞች በጉልበት የፈለጋቸውን የሚያደርጉበት ሁኔታ ተፈጥሯል ይባላል። እነዚህን ጉዳዮች ያምኑባቸዋል?
አቶ አሚን፡- ይህንን ሃሳብ በሁለት መንገድ ነው የማየው። አንደኛው በቅን ልቦና ተነስተው እውነት አገሪቱ ያለችበትን ችግር አይተው መንግስት ውሳኔ መወሰን አለበት ከሚል የመነጨ ከሆነ ፤ ይሄ መንግስት እየተዳከመ ነው፤ የመንግስት አሰራር በዚህ አይነት መሆን የለበትም፤ ህግ ማስከበር አለበት፤ የአገሪቱን የደህነነት ሥርዓትም ማጠናከር አለበት የሚለውን ሃሳብ እጋራለሁ። በትክክልም ይታየኛል። ይሄ መንግስት የመንግስትን ሃላፊነት መወጣት አለበት፤ ዴሞክራሲን ብቻ ሳይሆን ህግን ማስከበር አለበት የሚል እምነትም አለኝ።
በሌላ በኩል ደግሞ በሴራ የተጠነሰሱ ሃይሎች አሉ። ራሳቸው ሴራውን እየጠነሰሱ ሰዎችን የሚያስገድሉ፣ የሚገድሉ፣ ጠብመንጃ የሚያመላልሱ፤ ህዝቦች እንዲፋጁ የሚያደርጉ፤ በሚሰሩት ሚዲያ ላይ ህዝቦችን ከህዝቦች እያጋጩ፤ በሚሞተው ህዝብ ቁጥር ልክ በመንግስት ላይ ፕሮፖጋንዳ መንዛት የሚፈልጉና መንግስት ህጋዊ እርምጃ እንኳ ቢወስድ ያንን በቪዲዮ ቀርፀው የመንግስትን አምባገነንነት ለመግለፅ የሚፈልጉት በሁለተኛው ጎራ የሚቀመጡ የፖለቲካ ጥቅማጥቅም ፈላጊዎችና ሴረኞች ናቸው። እነሱ የሚያደርጉት ጉዳይ መንግስት በትክክለኛ መንገድ ወስዶ ወደ ህጋዊ መንገድ አገሪቱ እንድትመለስ ብቻ ሳይሆን የሚፈልጉት የአብይን አምባገነንነት ለማጉላት የሚጣጣሩ ናቸው። ግን ይህም ሆነ ያ መንግስት ህዝቦች እየተጋደሉ አምባገነን ላለመሆን ብሎ በመንግስት ቢሮ ውስጥ ተቀምጠው ህዝብ እየሞተ ማየት ያስጠይቃል ባይ ነኝ። ትናንት መንግስት ከሚፈለገው በላይ እየገደለ፤ ህዝቦችን ሲያሸብር ውጡልን ነበር የሚባሉት። አሁን ደግሞ መንግስት ናልን የሚባልበት ዘመን ላይ ደርሰናል። እናም በዚህ ጉዳይ ላይ ዶክተር አብይ የሚፈራበት ወይም ደግሞ የሚያቅማማበት ጉዳይ የለም ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- የህግ የበላይነት ባልተከበረበት ሁኔታ የመንግስትን አቅም ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት ነገር የለም ባይ ነዎት?
አቶ አሚን፡- በትክክልም አለ፤ መንግስት ምንም ቢሆን ምን ህግ ማስከበር አለበት። አሁን ግን መንግስት በትዕግስት መረብ ውስጥ ራሱን ተብትቦ ቁጭ ብሏል። ትዕግስቱ ሲባዛ ደግሞ ይባሱኑ መንግስትን በመናቅ ከህዝቦች ጋር በማጋጨት እና አገሪቱን በማሸበር መኖርም እንደሚቻል እያረጋገጡ ነው። ስለዚህ ይህን መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማቆም ይገባዋል። በሰለጠኑት ወይም በአደጉት አገሮች ጋዜጠኛ ሆንሽ ፖለቲከኛ አክቲቪስት ሆንሽ የፈለግሽውን ወጥተሸ ብትዘባርቂ የምትፈልጊውን ነገር ብታወሪ የማህበረሰቡ ብስለት ደረጃ ከፍተኛ ስለሆነ አክቲቪስት ነኝ ብለሽ የምትወረውሪውን የመርዝ ቋንቋ ሁሉ ህዝቡ አይቀበለውም። የነቃ ማህበረሰብ በመሆኑ ይመዝናል፣ በስሜታዊነት አይመራም ፤ የሰዎችን ሃሳብ በማመዛዘን የሚወስድና የሚጥል ማህበረሰብ በመሆኑ ብዙም ችግር ላያስከትል ይችላል። በመሆኑም በውጭው ዓለም ጋዜጠኛ የፈለገውን ቢያወራ ወይም አክቲቪስት የፈለገውን ቢል የፖለቲከኛ ተቀናቃኞችም የፈለጉትን እውነት አስመስለው ወሬ ቢነዛ ሰዎች ሳያጣሩ ባገኙት መረጃ ብቻ ሰላማዊ ሰልፍ አይወጡም። እዚህ ግን ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ስም ያፈሩትና ታላቅ ሰዎች የተባሉት የሚጠቀሙት ህዝብ ፖለቲካ ብስለቱና የዴሞክራሲ ግንዛቤው ከፍተኛ ስላልሆነ በቀላሉ የምታነሳሽው ማህበረሰብ ነው። በመሆኑም የዶክተር አብይ አስተዳደር ይህንን በደንብ መገንዘብ ይገባዋል።
አክቲቪስቶች በቀጥታ ለመንግስት የሚናገሩ ቢሆኑ ወይም ፓርላማ ውስጥ ሆነው የሚከራከሩበት የፖለቲካ ድርጅት ቢሆኑ እውነታውን ፊት ለፊት ተጋፍጦ ማስተካከል ይቻላል። ይህ አክቲቪስት ነኝ የሚለውና በየፌስ ቡኩና በተለያዩ ብዙሃን መገናኛ የሚናገረው ለመንግስት ሳይሆን ለልጆቻችን ነው። ገና የፖለቲካ ብስለቶቻቸው በቂ ያልሆነ፣ የማገናዘብ ሁኔታቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባና ፖለቲከኛ ላልሆነው ማህበረሰብ የሚያስተላልፉት መልዕክት መርዘኛ ነው። የማስተዋልና የማገናዘብ አቅማቸው በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ የሚመጡትን ነገሮች በሙሉ እውነት እየመሰለው እንደሚታየው አይነት ሁኔታ እየታየበት ነው። በዚህ አገር እኮ ከአንድ ሳምንት በፊት ለዶክተር አብይ ሽልማት የድጋፍ ሰልፍ የወጣው ህዝብ ከሳምንት በኋላ ደግሞ ለተቃውሞ ሲወጣ ይስተዋላል። ህዝቡ እንደዚህ የሚሆንበት ምክንያት ሲነሳ የግንዛቤ እጥረት ጥያቄ ውስጥ ይገባል። የመንግስት አመራሩ ይህንን ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ መገንዘብ አለበት ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ ማህበረሰብን የሚያነሳሱት አካላት ተከታዮቻቸው በርካታ ከመሆኑ የተነሳ በቀጣይ ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ በተለይ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ዶክተር አብይ ተቀባይነቱን ያሳጣዋል የሚል ስጋት በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ ፈጥሯል። እርሶ ስጋቱን እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ አሚን፡- በአደጉትም ሆነ ባላደጉት አገራት የፖለቲካ መስመር የሚያሲዙት ሊሂቃኖችና የፖለቲካውን አካሄድ የሚረዱ ሰዎች ናቸው። በተራው ማህበረሰብ ላይ የሚጠቀሙት አንቺ እንዳልሺው ፖለቲከኞችም፣ የፖለቲካ አመራሮችና አክቲቪስቶች አሉ። ግን እነዚህን ሁሉ ነገሮች መሬት ላይ ካለው ነገር ጋር ስትረጂው ሰዎች በአንድ ጊዜ፣ በአንድ ዘመን ነገሮችን የማመዛዘን ነገር እየተፈጠረላቸው ነው የሚመጣው። ለምሳሌ ዶክተር አብይን ዛሬ ኦሮሚያ ውስጥ የመመረጡ ነገር ጥያቄ ውስጥ ይገባል የሚለው ጥናት ከየት መጣ? ምናልባት የፌስ ቡክ ጥናት ነው። ፌስቡክን ደግሞ የሚጠቀመው ምን አይነት ማህበረሰብ ነው?። የፖለቲካ ብስለቱ ምን አይነት ነው? የሚደረገው ውይይትስ? የፖለቲካ ክርክር አለበት? ሰዎች ከሁለቱም ጥጎች ተወክለው ሃሳባቸውን የሚቀያየሩበት ቦታ ነው? ወይስ አንዱ ወጥቶ ልክ እንደ ሃይማኖት ሰባኪ ለተቀመጠው ማህበረሰበ የሚሰብከው ነው?። በአግባቡ መረዳትና ማገናዘብ የሚችሉና የሰዎችን የፖለቲካ ቁማር በደንብ መረዳት ለሚችሉት ዶክተር አብይ እንደሚያሸንፍ ምንም ጥያቄ የለውም።
ተመልከቺ! አንዳንድ ሰዎች ነገር ለመጫር በጣም ጎበዝ ናቸው። አንዳንዶች ደግሞ ሰዎችን ወደ ተቃራኒ መንገድ ለማስኬድ በጣም ታታሪዎች ናቸው። አንዳንዴ የብስለት ደረጃው በጣም ዝቅተኛ የሆነ ማህበረሰብ ደግሞ ቁስሉን የሚያክለት እንጂ የሚያድንለትን ሰው አይመለከትም። እንደዚህ አይነት ፖለቲከኞችንና አክቲቪስቶችን ሰው እየለያቸው የሚሄድበት ጊዜ ይመጣል። ማነው የሚያድነኝና ለጊዜያዊነት ሊያሽለኝ የሚችለውን ህዝቡ በአግባቡ መለየት ሲችል ዶክተር አብይ እንደሚመረጥ ምንም ጥርጥር የለኝም። እኔ ሙሉ መተማመን በእርሱ ላይ አለኝ።
ተቃዋሚ ናቸው የሚባሉ የበሰሉ ፖለቲከኞ ፌስቡክ ላይ ከሚንጫጩት ጋር ከምታወዳድሪልኝ ይልቅ አብይን እንመርጣለን ነው የሚሉት። ይህ የሚያሳይሽ ሰዎች ምንም እንኳን ዶክተር አብይን አካሄዱንና ድርጊቱን ባይረዱለትም ብስለቱን፣ እውቀቱን፣ ተቀባይነቱን፣ እንደ ኢትዮጵያን ሊያስቀጥል የሚችል መሪ መሆኑን፣ ኢትዮጵያውያንን በእኩልነት ማየት የሚችል መሪ መሆኑን ብዙዎች እየተገነዘቡት መጥተዋል። ሌላው ተስፋ የሚሰጠኝ ማንኛውም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በብሄር ደረጃ ተደራጅተው የብሄርን ጥያቄ የሚያነሱት ከእኛ ድርጅት ጀምሮ ብዙዎች እንደ ኦጋዴን፣ አፋርን፣ ትግራይን የመሳሰሉ ድርጅቶች ዛሬ ወደ ህብረ ብሄር መጥተዋል። ኢትዮጵያዊነት የሚለው ነገር ውስጥ እየገቡ ሲመጡ ተስፋ ነው። ይህንን መምራት የሚችል ከዚህ ቀደም እንዳልኩት ሁሉ ዛሬም እደግመዋለሁ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያውያንን በአንድ አይን አይቶ ሁሉን ማህበረሰብ በአንድ አስተሳስሮ ማስቀጠል የሚችል መሪ ዛሬ ለእኔ አብይ ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም አመሰግናለሁ።
አቶ አሚን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 11/2012
ማህሌት አብዱል