ማንም እንደሚያውቀው የአንድ መጽሐፍ የሽፋን ሥዕል ጌጥ አይደለም። የሽፋን ሥዕል የግል ስሜት ማራገፊያም ሆኖ አያውቅም። እግረ መንገድ ካልሆነ በስተቀር ለገበያ ፍጆታ ይውል ዘንድም ሙያውም ሆነ ገፁ አይሹም። የሽፋን ሥዕል የተገኘ ቀለም ሁሉ የሚገለበጥበት የቀለሞች ቤተ-ሙከራ ገፅም አይደለም። የሽፋን ሥዕሎች የሚያርፉባቸው የፊትም ሆነ የኋላ ገፆች ሰዎች በደመነፍስ የሚረጯቸው የቀለም አይነቶችና የሚደረድሯቸው ቁሶች ማከማቻ ባዶ ስፍራዎችም አይደሉም።
የሽፋን ሥዕል ምክንያታዊ እንጂ ዘፈቀዳዊና አይደለም። ለአንዳች ሰብአዊ ፋይዳ ሲባል ተምጦ የሚወለድ የግዙፍ ሃሳብ ወካይ እንጂ ዝርዝር ጉዳይ መቁጠሪያ አይደለም። ገፁ ከየድረ- ገፆች ላይ እያነሳን እንለጥፍበት ዘንድ የተፈጠረ ሳይሆን የዘመን መንፈስን፣ ታሪክን፣ ቅርስን፣ ማንነትን ባህላዊም ይሁን ታሪካዊ እሴትን እንዲገልፅ ሆኖ በባለሙያ የሚዘጋጅ እንጂ የነሸጠው ሁሉ የሚሰማራበት አይደለም። የሽፋን ሥዕል የላቀ ጥበብና ብቃትን የሚፈልግ የፈጠራ ተግባር ነውና።
ሚሊዮን በለጠ በ”ፍኖተ ጥበብ” (2007 ዓ.ም) መጽሐፉ “በሳይንስ እስከ አስራ ስድስት ሚሊዮን የቀለማት አይነቶች እንዳሉ ይነገራል።” ይለናል። አንዳንዶች እነዚህን በሙሉ ቢያገኟቸው የስራዎቻቸው የፊት-ኋላ ሽፋን ላይ ከመድፋት ወደ ኋላ የሚሉ አይመስሉም።
ዘመኑ መነጣጠቅ፣ የሰውን ኮፒ ራይት መድፈር፣ ለገበያ ፍለጋ ሲባል የራስን ስራ መልሶ መላልሶ (አበላሽቶም ጭምር) መድገምና መደጋገም . . . የፈጠራ ስራን የተካበት ዘመን ሲሆን፤ ከሽፋን ሥዕል ጥበባዊነት አንፃርም የተጎዳና የተጎሳቆለ ቢኖር ይሄው ያለንበት ምስኪን ዘመን ነው።
ይህ ለምን ሆነ? ብሎ ለጠየቀ መልሶቹ በርካታ ሲሆኑ ምክንያቶቻቸውም አታካች ናቸው። ባለፈው አመት ዘፈኖቻችንን በተመለከተ ጥናት ያቀረበው አብረሃም ወልዴ ለጥበባችን መውደቅ ዋናው ችግር “ድህነት ነው” በማለቱ የተወደደለት ባይሆንም (በየበረንዳው እንደሰማነው)፤ “ድህነት አይደለም” በማለት ግን የሱን ጥናት ውድቅ ያደረገ ሰው እስካሁን የለም። “የዘመኑ ፀሀፊዎች ወደ ፈጠራ ስራ ብቅ የሚሉት ባንክ ደብተራቸው ላይ ያሉት ቁጥሮች ማሽቆልቆላቸውን ሲያዩ ነው” ያለውን አፍሪካዊ ሃያሲም “ተሳስቷል” ለማለት በሚያስቸግር ደረጃ ላይ እንገኛለን። ብርሀኑ ደቦጭም በየ”ፍትህ” መጽሄት መጣጥፉ (ከጥቂቶች በስተቀር) “እንቶ ፈንቶ” መሆናቸውን መግለፁም ለዘመኑ የሥነጽሁፍ ስራዎች ሁለመናዊ ውድቀት ጥሩ ማሳያ ነው።
አስቀድሞ፤ ገና በ60ዎቹ፣ የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ወርቃማው ዘመን ላይ በነበረበት ወቅት “የዘመኑ ሥነ-ጽሑፍ ጥራቱ ድክመቱን አጉልቶ ማሳየቱ ነው።” ያለውን ዮሀንስ አድማሱንም እዚህ ላይ በትንግርት ማስታወስም ትክክለኛ ቦታው ይሆናል። (የዛሬዎቹን ቢያይ ምን ይል ይሆን ያሰኛል።)
የዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን ወደ ሆነውና ብዙም ወዳልተለመደው፣ የረባ ትኩረት ወዳልተሰጠው፤ ሌላው ቀርቶ በሥነ-ጽሑፍ ኮርሶች ውስጥ እንኳን ስሙ ሲነሳ ተሰምቶ ወደማይታወቀው የመጻሕፍት ሽፋን ጉዳይ ስንመጣም ያለው እውነታ ያውና ተመሳሳይ ነው። ዘርፉ ጥበብ የጎደለው፣ ያጠረውና የራቀው ሲሆን፤ የመጻሕፍቶቻችን ፊቶች ቀለም በቀለም ሆነው እንጂ ጥበብ ቤት ሰርቶባቸውና ነግሶባቸው አይታዩም። ገና ከርቀት ላያቸው ዶሮ በጭቃ እግሯ ሽርሽር የተመላለሰችበት መድረክ ከመምሰል ያለፈ ውበት ብሎ ነገር የላቸውም።
እዚህ ላይ አንድ ሰው እናንሳ፤ ባለቅኔው ጎሞራው (ሀይሉ ገብረ ዮሀንስ)ን። በ60ዎቹ ከአንድ መጽሄት “የአሁኑን ዘመን የሥዕል ስራዎች እንዴት ታያቸዋለህ?” ተብሎ ለቀረበለት የግምገማ ጥያቄ “ገረወይና ሙሉ ቀለም ይደፋና ‘ምንድ ነው?’ ሲሉት ‘አብስትራክት ነው’ ይላል” ሲል መመለሱ ከአሁኑ በላይ ወደ ፊት ተደጋግሞ የሚጠቀስለት ጊዜ የሚመጣ ስለመሆኑ መጠራጠር አይቻልም። የወደፊቱን ለመተንበይ ያሁኑን በጥልቀትና ጥንቃቄ ማየት በቂ ነውና ነው እንዲህ ማለት ላይ የተደረሰው።
በዚህ በኩል ዘመኑ፤ ባለሙያዎች ሲሉ እንደሚሰማውም ሆነ እኛም እንደምንታዘበው፤ ከሠዓሊ ነን ባዮቹ ባለ ንፁህ ህሊናዎቹ ህፃናት ይበልጣሉ። ምነው ቢሉ እነሱ የሚስሏቸው “የእንኳን አደረሳችሁ መልካም አዲስ አመት መግለጫ ሥዕሎች ብሩህና የሚያማምሩ” ናቸውና ነው። (ይህችን ሀሳብ የኢዜአን “ነጋሪ” መጽሄት ያነበበ ይረዳታል።)
በዚህ ጽሑፍ “የመጽሐፍ የሽፋን ሥዕል” (Book cover) ስንል የመጽሐፉን የፊትና ኋላ ገፅታ፣ ርዕስ፣ ንኡስ ርዕስ (ካለው)፣ የደራሲውን ስም፣ ፎቶዎችን፣ የምስሉን የጀርባ/ መደብ፣ ግራፊክስ፣ የጀርባ አስተያየት እና ሌሎች መሰል አላባውያንን እንደሚያካትት፤ ያፃፃፍ ዘዬ፣ የፊደላቱን አቀማመጥና የተፃፉበትን ቀለም ሁሉ ታሳቢ በማድረግ ነው። ከሁሉ አስቀድመን ግን ይህ ጽሁፍ ከመጽሐፍ ፊት-ኋላ ሽፋኖች መካከል ያሉ ገፆች (book block)ን እንደማይመለከት መግለፅ እፈልጋለሁ።
የመጻሕፍት የሽፋን ሥዕል አዲስ ነገር ሳይሆን ቀደም ባሉ የሥነጽሑፍ ስራዎቻችንም የነበረ የጥበብ ስራ ነው። ልዩነቱ የያኔው በእውቀትና ብቃት ላይ የተመሰረተ፤ መነሻው ጥናት፣ መድረሻውም ችግር መፍታት፤ ፋይዳውም ሰብአዊ መሆኑ ላይ ነው። ምሳሌዎችን ወስደን ብናይ ይሄንኑ የሚያረጋግጡ ሆነው ነው የምናገኛቸው።
ዳኛቸው ወርቁ ለ“እንቧ በሉ ሰዎች” የሥነ-ግጥም መድበሉ የመረጠውና የተጠቀመውን የሽፋን ሥዕል ያየ ደራሲው ሥዕሉን ከመጽሐፉ አጠቃላይ ጭብጥ ጋር ለማገናኘት የለፋውን ልፋት፣ የአገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ ለማሳየት የሄደበትን ርቀት፣ ስንፍና በወለደው ረሀብና ድርቅ ምክንያት የደረሰውን ሰብአዊ ቀውስና እልቂት፣ የአገሪቱን ለምነት ያመላከተበትን ሁኔታ በውል ይገነዘባል። ዳኛቸው ይህን ሁሉ ሲያደርግ አንድም የሚጎረብጥም ሆነ የሚያጥበረብር ቀለም አልተጠቀመም። ሁሉ አይቅርብኝም አላላም። ኢኮኖሚስት ነው፤ ቀለም ቆጥቧል። ቦታ ቆጥቧል። ለአንባቢያን መንቀሳቀሻ ክፍት ቦታዎች እንደልብ አስተርፏል።
ወደ በአሉ ግርማ ስንመጣም ተመሳሳይ ሁኔታን ነው የምናገኘው። የ“ከአድማስ ባሻገር” የሽፋን ሥዕል በሁለት የቀለም አይነቶች ብቻ የተመሰረተ ነው፤ ለዛውም እርስ በእርስ በማይገፋፉ ቀለሞች። ሁለት የቀለም አይነቶችን ብቻ በመጠቀምና ሙሉ ገረወይናን ከመድፋት መቆጠቡ በአሉንም ሆነ “ከአድማስ ባሻገር”ን የጎዳቸው ነገር መኖሩ አልተሰማም፤ ወይም ከደረጃ ሰንጠረዥ ሲያወርዳቸው አልታየም።
“ፍቅር እስከ መቃብር”ስ ቢሆን በሶስት ቀለማት ላይ እራሱን መገደቡና እንዳሁኑ ዘመን መጻሕፍት “ሁሉ አይለፈኝ” አለማለቱ ምን አሳጣው? ሀዲስ አለማየሁንስ ምን ጎዳቸው? ምንም። አቤ ጉበኛ፣ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ መስፍን ወልደማሪያም፣ አዳም ረታና ሌሎችም በዚህ የሽፋን ሥዕልን በእውቀት፣ ምርምርና ብቃት ላይ ተመስርቶ በመስራት በኩል የተሳካላቸው ደራሲያን ለመሆናቸው ስራዎቻቸውን መመልከት ነው።
እዚህ ላይ ለሥነ-ጽሑፉ አለም አንድ መርዶ አርድተን እንለፍ፡፡ የመጻሕፍትን ፊት ገጽ ስነጥበባዊ ፋይዳ አይን ለማጥፋት ባለሚናዎቹ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ተቋማትም የመሆናቸው ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ ለጥበብ፣ ንባብ፣ ትምህርት ወዘተ እጨነቃለሁ የሚለው ሜጋ አሳታሚ ድርጅት ሲሆን ለዚህም ማስረጃችን “ፍቅር እስከ መቃብር”ን ለ25ኛ ጊዜ ሲያሳትም የመጽሐፉን የፊት ገፅ የድርጅቱ ማስታወቂያ ሰሌዳ የማድረጉ የከፋ ሀጢያት ነው። (ነፍሳቸውን ይማረውና ሀዲስ ቢኖሩ “እኔ ፃፍኩት ወጋየሁ ነፍስ ዘራበት” ያሉትን ያህል ሜጋንስ ምን ይሉት ይሆን???)
ባንድ ገጠመኝ ላብቃ። ከሁለት አመት በፊት የጋዜጣ ጽሑፎቹን ወደ መጽሐፍ የቀየረና በሰው ያወኩት ሰው እንድገዛው ጠየቀኝ፤ ገዛሁት። ሁለተኛ ሲታተም የሽፋን ሥዕሉ ርእሱም፣ ቀለሙም፣ ዋጋውም ተቀያይሯል። “ምነው?” ስል ላቀረብኩት ጥያቄም የሰጠኝ መልስ “የማተሚያ ቤቱ ባለቤት ‘አዟሪዎች አይወስዱልኝም’ ብሎ ነው እንደዚህ ያደረገው።” የሚል ነበር። በቃ ዘመኑ የመጻሕፍት ማንነት እንደዚህ በቀላሉ የሚቀየርበትና ውስጡን የማያውቅ ሰው የሽፋን ሥዕል የሚያዘጋጅበት (ደራሲውን በማዘዝ) ዘመን ነው። የዚህ አይነቱ በጥበብ ላይ የሚሰራ ግፍ አብቅቶ ለማየት ያብቃን።
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 10/2012
ግርማ መንግሥቴ