በተለምዶ ዕድገት በሕብረት በመባል የሚታወቀው “የዕድገት በሕብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ” ክተት በዓል የተከበረው ከ45 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታህሳስ 12 ቀን 1967 ዓ.ም ነበር።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች “ወደ ገጠር ዘምተን እናስተምር እንቀስቅስ እናደራጅ” በሚል ባነሱት ጥያቄ መነሻነት የታንዛንያና የናይጀሪያ ተማሪዎች ወደ ገጠር ዘምተው ገበሬውን ማደራጀታቸው እንደተሞክሮ ተወስዶ የእድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ በ1966 ዓ.ም ክረምት ተፀነሰ። ከዚያም ዘመቻው እንዴት እንደሚካሄድ፤ ምን ዓይነት ድርጅታዊ መዋቅር እንደሚኖረውና በዘመቻው ምን ያህል የሰው ኃይል እንደሚሳተፍ በማጥናት የዘማቾችን ተግባርና ኃላፊነት የሚጠቁም ኮሚቴ በመስከረም አጋማሽ 1967 ዓ.ም ተቋቋመ። ጥናቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ጥቅምት 16 ቀን 1967 ዓ.ም የዕድገት በሕብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ ጠቅላይ መምሪያ ተቋቁሞ ሥራውን ጀመረ። ሻምበል ኪሮስ አለማየሁም ዘመቻውን እንዲመሩ በሊቀመንበርነት ተመደቡ።
ኢህአፓንና የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ኃይሎችን የሚደግፉ ወጣቶች “ደርግ እኛን ገጠር ልኮ እሱ በከተማ ሊጠናከር ነው” በማለት ዘመቻውን ተቃወሙ። ሌሎች ደግሞ ከሕዝባችን መሐል ገብተን ፊደል ማስቆጠር አለብን በማለት ዘመቻውን ደገፉ።
የዕድገት በሕብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ እነማንን እንደሚያካትት ዓላማና ግቡንም በተመለከተ አዋጅ ቁጥር 11/1967 ለህዝብ ይፋ ሆነ። ፍቅረሥላሴ ወግደረስ “እኛና አብዮቱ” በተሰኘ መጽሐፋቸው እንደገለፁት 60 ሺህ የሁለተኛ ደረጃና የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ከመምህሮቻቸው ጋር በመላ አገሪቱ በሚገኙ ስድስት ቀጠና ማስተባበሪያ ማዕከላት፣ 57 የክፍለ አገር ማስተባበሪያዎች፣ 517 ምድብ ጣቢያዎችና እያንዳንዳቸው 30 ተማሪዎች ወዳቀፉ ጣቢያዎች ለመላክ ታቅዶ ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ መንግሥት ያወጣው ሪፖረት ግን ዘማቾች በ51 ማዕከላትና 397 ጣቢያዎች መዝመታቸውን፤ ቁጥራቸውም 48 ሺ ብቻ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
ታህሳስ 12 ቀን 1967 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የአዲስ አበባ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከየጠቅላይ ግዛቱ ከተወከሉ ተማሪዎች ጋር በጃን ሜዳ የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት በደማቅ ሠልፍ አደረጉ። ፍቅረሥላሴ የሰልፉን ሁኔታ ሲገልፁ “መለዮአቸውን በማውለብለብ በሆታና በጭፈራ “ቪቫ መንግሥቱ” ፤ “ቪቫ መንግሥቱ” እያሉ ሲቃ እየተናነቃቸው በመጮህ አለፉ። አንዳንዶቹ የመንግሥቱን እጅ ለመጨበጥ ወደትሪቡን የሚመጡ ነበሩ። ” ይላሉ።
ገስጥ ተጫኔም “ነበር” በተሰኘውና ከዘነበ ፈለቀ ብለው ባሳተሙት መጽሐፋቸው የክተት በዓሉን ድባብ እንደሚከተለው ገልፀውታል። “ታህሳስ 12 ቀን 1967 የዕድገት በሕብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ የክተት በዓል በመላ አገሪቱ ተከበረ። ለዘመቻው የተዘጋጁ 60 ሺህ ተማሪዎችን የወከሉ የአዲስ አበባ ዘማቾች በዓሉን ለማክበር በጃንሜዳ ተሰለፉ። ሰልፉን ለመጎብኘትና በዓሉን በጋራ ለማክበር ብርጋዴል ጀነራል ተፈሪ በንቲና ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም በስፍራው ተገኝተው ነበር። ሰልፈኛው በየተመደበበት የዘመቻ ቀጠና በረድፍ እንደቆመ ጃንሜዳን ከምዕራባዊ ጫፍ እስከ ምስራቃዊ ጫፍ ሞልቶት ነበር። “
ዘማቾቹ ህዝቡን ሊያነቁና ሊያስተምሩ በተንቀሳቀሱበት ወቅት
በደስታ በዕልልታ እንደሸኘናችሁ
በሳቅ በፈገግታ እንቀበላችሁ
በህይወት ግቡ በህይወት
ዘመቻ የምትሄዱ ለዕድገት በህብረት።
እያለ በሆታና በዕልልታ በመሸኘት በሚያልፉባቸው ከተሞችም ምሣና ራት እየጋበዘ ማረፊያ ቦታ አዘጋጅቶ በመቀበል አስተናገዳቸው። በመላ አገሪቱ የገጠር ክፍሎች ተሰማርተው ሥራቸውን ጀመሩ። ገበሬውን በእርሻ ሥራና በዕለት ተዕለት ኑሮው እያገዙት ማንበብና መጻፍን አስተማሩት። ፖለቲካዊ ንቃት እንዲኖረው ለማድረግና መብቱን እንዲጠይቅ አስለጠኑት። በሂደቱ የራሳቸውን ትግል ጀምረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በማድረጋቸው በርካቶች ታስረዋል።
ቀስ በቀስ በየጣቢያው ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ መሆን ጀመሩ። በዚህም በርካቶች ጣቢያቸውን ጥለው ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመለሱ። በዚህ ጊዜ ደርግ “ወደ ዘመቻው ተመለሱ” ሲል ጥሪ አቀረበ። ጥሪውን ተከትሎም ጥቂቶች ወደ ዘመቻ ተመለሱ። በቁጥር ላቅ የሚሉት ግን ሳይመለሱ ቀሩ።
የዕድገት በሕብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ በመላ አገሪቱ ለሁለት ዓመታት ያህል የዘለቀ ነበር። የመጀመሪያው ዙር ዘመቻ በወጉና በሥርዓቱ እንዳይፈፀምና ሌላ ዙር ዘመቻ እንዳይቀጥል ኢህአፓ ተጽዕኖ አሳድሯል የሚሉ ጸሐፍት አሉ። ለዚህም የኢህአፓ ልሳን የነበረው ዲሞክራሲያ ቅጽ 2 ቁጥር 25 ህዳር 23 ቀን 1968 ዓ.ም “ዘመቻው ከሁለት አንፃር” በሚል ርዕስ ዘመቻውን በመቃወም ይዞት የወጣውን ተከታዩን ጽሑፍ ማስረጃ አድርገው ይጠቅሳሉ።
“ዘመቻው ዓላማ ቢስ በመሆኑ ውድቅ ነው። ያልታሰበበት ያልተጠና በመሆኑ ውድቅ ነው። ወንጀሉን የሚያስፈፅሙ የሚፈፅሙና የሚተባበሩ ሁሉ ተጠያቂ ይሆናሉ። አሁን ያለው ምርጫ ሁለት ብቻ ነው። የተሞከረው ሁሉ ፉርሽ መሆኑን ፣ በዚህ አይነት መቀጠሉ የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑን አምኖ መቀበል። ጣቢያዎቹን መዝጋት፣ ዘማቾችን ወደየመጡበት ፣ ተማሪውንና መምህሩን ወደየቤቱ፣ ወታደሩን ወደየጦር ሠፈሩ መመለስና መምሪያውን ማፍረስ። አለበለዚያ ይህንን እምቢ ማለትና የሕዝቡን ታሪካዊ ፍርድ ለመቀበል መዘጋጀት።”
ዘመቻው ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ ይፋ በሆነው መግለጫ 5 ሚሊየን 537 ሺህ ገበሬዎች በ19 ሺ 341 ማህበራት መደራጀታቸውን፤ 63 ሺ 500 የፍርድ ሸንጎዎች እና 55 ሺህ የመከላከያ ኮሚቴዎች መቋቋማቸው ተገልጿል። በመሠረተ ልማት በኩልም 264 ክሊኒኮችና 158 ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን፤ 750 የጤና ረዳቶች መሰልጥናቸውና 500 ሺ የቀንድ ከብቶች መከተባቸው ተገልጿል። በዘመቻው 116 ዘማቾች በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች መስዋት መሆናቸው ይፋ ተደርጓል። ይህ ቁጥር ዘማቾች ግዳጃቸውን ፈፅመው ሲመለሱ ሐምሌ 10 ቀን 1968 ዓ.ም በቀረበ ሪፖርት ብዙ የአሃዝ ለውጥ ተደርጓል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 8/2012
የትናየት ፈሩ