አፄ ኃይለሥላሴ ከአባታቸው በውርስ ያገኙትን ቤተ መንግሥት “ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ” ብለው በመሰየም መርቀው የከፈቱት ከ58 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታህሳስ 9 ቀን 1954 ዓ.ም ነበር።
ጥቅምት 23 ቀን 1952 ዓ.ም ተቋቁሞ “ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አዲስ አበባ” በመባል ይታወቅ የነበረው የትምህርት ተቋም በኋላ ታህሳስ 9 ቀን 1954 ዓ.ም ስድስት ኪሎ የሚገኘውን ገነተ ልዑል ቤተ መንግስት መቀመጫ በማድረግ “ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ” በሚል ስያሜ ተመርቆ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በቃ። ከ12 ዓመታት በኋላ የዘውዳዊው መንግሥት ሥርዓት መውደቅን ተከትሎ የተመሠረተው ወታደራዊ መንግሥት የቀደመ ስሙን ሽሮ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲል ጠራው።
ማክሰኞ ታህሳስ 10 ቀን 1954 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ 21ኛ ዓመት ቁጥር 297 እትም ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲውን መርቀው ሲከፍቱ ያደረጉትን ሙሉ ንግግርና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኬኔዲ እንዲሁም ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ዕለቱን በማስመልከት የላኩትን መልዕክት አስነብቦ ነበር።
አፄ ኃይለሥላሴ “ይህን ቤተ መንግስት ከቦታው ጋር ለኢትዮጵያ ህዝብ አበርክተናል” በሚል ርዕስ ተከታዩን ንግግር አድርገው ነበር።
“በዚህ የታሪክ ስፍራ ላይ ዩኒቨርሲቲ እንዲመሰረትበት የፈቀድነው በትምህርት ስራ ላይ ላደረግነው የረጅም ጊዜ ትግልና ለህዝባችንም ባለውለታነት ምስክርና የጋራ ሐውልት ሆኖ እንዲኖር በማሰብ ስለሆነ ይህ ቦታ ከዚህ ዓላማ ውጭ ለሆነ አገልግሎት እንዳይውል አደራውን የምንተወው ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ ነው። … ይህ ዛሬ የምንመርቀው ዩኒቨርሲቲ እንዲመሰረትበትና የእኛና የህዝባችን ሐውልት ሆኖ እንዲኖር ከአባታችን ከልዑል ራስ መኮንን የወረስነውን የግል ርስታችንን ይህን ቤተ መንግስት ከቦታው ጋር ለኢትዮጵያ ህዝብ አበርክተናል። ይህን ዩኒቨርሲቲ ስንመርቅ ፣ ይህ ቀን በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርትን ለማስፋፋት ላደረግነው የረጅም ዘመን ድካም አክሊል ይሆናል ብለን በመገመት ነው። ”
በወቅቱ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት የነበሩት ፕሬዚዳንት ኬኔዲ የዩኒቨርሲቲውን ተመርቆ መከፈት አስመልክተው ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በላኩት መልዕክት”… ታላቅ ዩኒቨርሲቲ ያቋቋመውን መንግስት ብቻ ሳይሆን መላውን የሰው ልጅ ሊያገለግሉ የሚችሉ ልዩ ልዩ ሃሳቦችንና ፍልስፍናዎችን ሊያስገኝ የሚችል ነው። በዚህ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የጋራ የትምህርት መግባቢያ ሥፍራ በሳይንሳዊና ባህላዊ ጉዳዮች ረገድ ታላቅ መገኛ ቦታ ይኖራታል። … ለኢትዮጵያ ህዝብ ዩኒቨርሲቲ ይውል ዘንድ ቤተ መንግስትዎን ከነ ርስቱ በሰጡበት ዕለት በሀገሬና በራሴ ስም ሆኜ የጋለ የወዳጅነትና ከልብ የመነጨ መልካም ምኞቴን ስገልጽ ክብር እየተሰማኝ ነው” ብለው ነበር።
የእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲም ዕለቱን በማስመልከት አዲስ አበባ በሚገኙት የእንግሊዝ አምባሳደር በኩል በላከው መልዕክት “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ለሚመረቅበት ለዚህ ለማይረሳና እጅግ ለሚያስደስት ሁናቴ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ለግርማዊነትዎ የጋለ ደስታውን ሲገለጽ ከፍ ያለ ደስታ ይሰማዋል። … በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም ለብዙ ጊዜ የነበረው ምኞት ከፍጻሜ ስለደረሰ በጣም ተደስተናል። ” ብሎ ነበር።
የ58 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ጥናት በማድረግ፣ የቀጣና ደረጃን የጠበቀ ጥናት በማድረግ ፣ በማሳተም ፣ በመጽሐፍ አቅርቦት ፣ ኮንፈረንሶችን በማካሄድና ‘ሳይት’ በመደረግ ብቃት አፍሪካ ውስጥ ካሉ ምርጥ 10 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ መሆኑን የዓለም ዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ አውጭ ተቋም ጥናት አመልክቷል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታህሳስ 8/2012
የትናየት ፈሩ