የዛሬው የዘመን እንግዳችን ዶክተር አለማየሁ አረዳ ይባላሉ።ተወልደው ያደጉት በቀድሞው አርሲ ጠቅላይ ግዛት በ1942 ዓ.ም ነው። ያሳደጓቸው አባታቸው መምህር ስለነበሩ በሥ ራቸው ባህሪ ምክንያት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸው በግዛቱ ስር ባሉ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለመማር ችለዋል።ከእነዚህም መካከል ኮፈሌ፣ አሳሳ፣ ጢቾና አሰላ ከተማ ይገኙበታል።11ኛ ክፍል ሲደርሱ ደግሞ አዳማ በሚገኘው ራስዳርጌ ትምህርት ቤት ከተከታተሉ በኋላ ወደ 12ኛ ክፍል ለመዘዋወር የሚያስችል ከፍተኛ ውጤት በማምጣታቸው ምክንያት አዲስ አበባ በሚገኘውና በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ስር በነበረው ልዑል በዕደማርያም ላብራቶሪ ትምህርት ቤት የመግባት እድል ያጋጥማቸዋል።የ12ኛ ክፍል መልቀቂያንም በከፍተኛ ውጤት በማለፍ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በኬሚስትሪ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ።በዚህም ሳያበቁ በዛው ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኋላም በእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ለንደን ዶክትሬታቸውን ማግኘት ችለዋል።
እንግዳችን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዳገኙ የተቀጠሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደብረዘይት እርሻ ኮሌጅ ነው፡ ፡በወቅቱ ደብረዘይትና ሀረማያ እርሻ ኮሌጅ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ነበሩና በሁለቱም ተቋሞች ለሰባት ዓመታት እየተዘዋወሩ አስተምረዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከሰሩ በኋላ ጅማ እርሻ ኮሌጅ ለሶስት ዓመታት የኮሌጁ ዲን በመሆን በኃላፊነት ሰርተዋል።ከለንደን ከተመለሱ በኋላ ግን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ቢሆንም ከማስተማሩ ጎን ለጎን የከፍተኛ ትምህርት ዋና መምሪያ ኃላፊ ሆነው ለስምንት ዓመታት አገልግለዋል። የአሁኑን ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የቀድመውን ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ካቋቋሙና ለአራት ዓመታት ከመሩ በኋላ በገዛ ፍቃዳቸው ለቀው ወጥተዋል።ከዚያም በተለያዩ የልማት ድርጅቶችና ዓለም አቀፍ ተቋማት በከፍተኛ ኃላፊነት በቦርድ ሊቀመንበርነትና በአማካሪነት ሰርተዋል።ወደ ፖለቲካው በማዘንበልም መንግሥትን ተቃውመው የቅንጅት ሥራ አመራር አባል ሆነውም ነበር፡፡አሁን ደግሞ በግሉ ዘርፍ የዘቢደር ቢራ ፋብሪካን በቦርድ ሊቀመንበርነት እየመሩ ይገኛሉ።በቅርቡ ደግሞ የኢትዮጵያን መፃኢ እድል ለመለየት ከተሰየሙት 50 የአገሪቱ ሊሃቃንና ፖለቲከኞች መካከል ሆነው ተመርጠው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ።ከእንግዳችን ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይዘንላችሁ ቀርበናል።መልካም ንባብ፤
አዲስ ዘመን፡- በመንግሥት ተቋም የመጨ ረሻዎ የሆነውን የሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ኃላፊነት በገዛ ፍቃድዎ ለመልቀቅ የፈለጉበት ዋነኛ ምክንያት ምን እንደነበር በማስታወስ ውይይታችን ብንጀምርስ?
ዶክተር አለማየሁ፡- አይ እኔ በመጀመሪያ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ደግሞ እኔን ለማነጋገር እዚህ ድረስ በመምጣቱ ያለኝን ታላቅ አክብሮት በመግለፅ ነው መጀመር የምፈልገው።ወደ ጥያቄሽ ስመለስ አንቺም እንዳልሽው ከኃላፊነት መነሳት የፈለግሁት በገዛ ፍቃዴ ነበር።ዋና ምክንያቴ ደግሞ በመጀመሪያም ወደዚያ ስፍራ የተላኩት ዩኒቨርሲቲውን ማቋቋም ብቻ ነበርና አቋቁሜ ስለጨረስኩና ኃላፊነቴን ስለተወጣሁ ጥያቄ አቅርቤ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የምስጋና ደብዳቤ አግኝቻለሁ።እኔ እንዳውም የተቋሙን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን ሰርተን ከጨረስን በኋላ ለሁለት ዓመት ብቻ ነበር ለመቆየት ያሰብኩት የነበረው።ይሁንና በአጋጣሚ አቶ ታምራት ላይኔ የታሰሩበት ወቅት በመሆኑ በዚህ ሁኔታ ልልቀቅ ማለት ተገቢ ሆኖ ስላላገኘሁት መልቀቂያዬን ለሁለት ዓመት አራዘምኩት፡፡
በነገራችን ላይ እኔ የከፍተኛ ትምህርት አስተዳደር ሙያ ቢኖረኝም መደበኛ ሙያዬ ግን የተፈጥሮ ሳይንስ ስለሆነ ሌሎችም ሥራዎች መስራት ስለምችል በወቅቱ እዛ ቦታ ላይ የምቆይበት ምክንያት አልታየኝም።ለዚህ ነው በራሴ ፈቃድ የለቀቅኩት።የሚገርምሽ እኔ ወደ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ስሄድ ብዙዎች ወደ እዛ እንዲሄድ አይፈልጉም ነበር።ዋና ምክንያታቸውም የፖለቲካ ትምህርት ቤት እንደሆነ ያስቡ ስለነበር ነው።ግን እኔ ዩኒቨርሲቲውን ያቋቋመበትን አላማ አውቅ ስለነበር በደስታ ነው የሄድኩት።በእርግጥ የፖለቲካ ድርጅት አባላት የሆኑ ሰዎች እዛ የሚማሩ የነበረ ቢሆንም የምናስተምረው አካውንቲንግ፣ ኢኮኖሚክስና ማኔጅመንት ትምህርቶችን ነው።ዛሬም ለአገሪቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ያለ ተቋም ነው።የፌዴራል መንግሥቱ ሲመሰረት ለየክልሎቹ የሚሆን የሰው ኃይል አልነበረንም።በወቅቱ ለእነዚያ ክልሎች ያ ኮሌጅ ነው የደረሰላቸው ብዬ አምናለሁ።ችግሮችም ቢኖሩት ዩኒቨርሲቲው የአቅም ግንባታ ተቋም ሆኖ አገልግሏል ባይ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ አሁንም ቢሆን ዩኒቨርሲቲው ያለው ዝና የፖለቲካ ተቋም ብቻ እንደሆነ ነው የሚታመነው።ስለዚህ ለስርዓቱ እንጂ ለአገር ግንባታ አስተዋፅኦ አበርክቷል ማለት ይቻላል?
ዶክተር አለማየሁ፡- በእኔ እምነት ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመበትን ዓላማ አሳክቷል።ትልቁ ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሊሂቅ ማየት ያልቻለው ለምሳሌ ደርግ የራሱ የፖለቲካ ትምህርት ቤት ነበረው።ስለደርግ የፖለቲካ ትምህርት ቤት ዛሬ እየነቀፈ ሲያወራ ሰምተሽ ታውቂያለሽ? ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በመላው ዓለም ትላልቆቹ ሀገራት ሳይቀሩ ሲቪል ሰርቫንቱን ለፖለቲካ ስርዓቱ አገልጋይ እንዲሆን የሚያስተምሩበት የራሳቸው መሰል ተቋም አላቸው።ለምሳሌ አሜሪካ፣ ፈረንሳይና እንግሊዝን መጥቀስ ይቻላል።እንዳውም እኛ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የሚለውን ስም ያመጣነው ከእንግሊዝ ነው።እኔ እነዚህን ሁሉ ተቋማት ዞሬ ጎብኝቻለሁ።እናም በእኔ እምነት አንድ መንግሥት ከመደበኛ የትምህርት ተቋማት የራሱን ቢሮክራሲ ተሸክመውለት የሚሄዱ ሰዎች ሊያገኝ አይችልም።እነዚህ የንድፈ ሃሳብ ምሁራን ናቸው።አይረባም ከተባለ ለምን አይዘጉትም ታዲያ? ስለእውነት ነው የምልሽ የአፋርና የቤኒሻንጉል ክልሎች ስለ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ እንዲናገሩ ቢደረግ ደስ ይለኝ ነበር።በእርግጥ ስርዓቱ ብዙ ስህተቶች ነበሩበት፤ ግን ደግሞ ብዙ በጎ ነገሮችም ነበሩት።በኋላም ተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥም ገብቼ የማውቀውን የመንግሥት ተቋማዊ አደረጃጀት በተቃዋሚነት ለማሻሻል ነው የሞከርኩት።
ስለዚህ ስለሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በሚመለከት የሚነሳው ነገር በዓለም ላይ የሌለ ነገር አይደለም የመጣው። ዛሬ ላይ ታዲያ ለምን ማንም ሰው አይናገርም?።ምን ለውጥ መጣና ነው ዛሬ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የማይሰደበው? ለምሳሌ እኛ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ሲደራጅ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው የዲግሪ ፕሮግራም ይሰጥ የነበረው።አሁን እንደዛ አይደለም።የምርምር ተቋም ነው።አሁን ትላልቅ የሚባሉ ሰዎች የልማታዊ አስተዳደር ሙያ የሚማሩበት ተቋም ነው፡፡ለ አብነት እንኳን መጥቀስ ካስፈለገ እነ ለማ መገርሳ፣ እነ ገዱ አንዳርጋቸው በኮሌጁ ገብተው የአመራር ሙያ ተምረው የወጡበት ተቋም ነው።ደግሞም ልክ እንደማንኛው ተቋም ሰዎችን አሰልጥነን ለማውጣት ብቻ አይደለም ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅን ያቋቋምነው፡፡የሲቪል ሰርቪሱን አገልግሎት ውጤታማነትና ምርታማነት የሙያ ብቃት የመገንባት አላማ ይዞ ነው የተቋቋመው፡፡ስለዚህ ብዙ ወደ ተግባር የሚያደላ ስለነበር ዛሬም ቢሆን የለውጡ መሪ ይህንን ተቋም በእንክብካቤ መያዝ አለበት የሚል እምነት አለኝ።ይህም ሲባል ግን ማረም የሚገባቸው ነገሮች የሉም ማለቴ አይደለም።እንደአጠቃላይ ግን ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ አንድ ብቻ ሳይሆን በየክልሉ ሊኖር ይገባል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከመንግሥት ቤት ከወጡ በኋላ በቀጥታ ነው ወደ ተቃዋሚ ፓርቲ ያመሩት?
ዶክተር አለማየሁ፡- ከመንግሥት ቤት ከወጣሁ በኋላ በቀጥታ የገባሁት አንድ የጀርመን ድርጅት ውስጥ ነው።ነገር ግን ከሁለት ዓመት በላይ አልሰራሁም። ከዚያ ወጥቼ ደግሞ አንድ ቸር ኢትዮጵያ ድርጅት ውስጥ በበጎ ፍቃድ ዳይሬክተር ነበርኩ።በሲቪል ሶሳይቱም መስመር የሲ.አር.ዲ.ኤ የቦርድ ሊቀመንበር ነበርኩኝ።በዚያ በኩልም አገልግሎቴን ሰጥቻለሁ።ከዚያም የራሴን የምክር አገልግሎት ድርጅት ነው ያቋቋምኩት፡፡በዚያ ድርጅት አማካኝነት ለልማት ድርጅቶች፣ ለመንግሥት ተቋማት ለግሉ ዘርፍ የማማከር ሥራዎችን ሰርቻለሁ።የዘቢዳር ቢራ የቦርድ ሊቀመንበር ነኝ።በፖለቲካውም የቅንጅትም የሥራ አስፈፃሚ አባል ነበርኩ።ነገር ግን የመንግሥትን አሰራር አውቅ ስለነበር ብዙ የመጯጯህ ሁኔታ ውስጥ ስላልገባሁ ብዙ ሰዎች ፖለቲካ ውስጥ የነበረኝን ሚና አያውቁም ነበር።
አዲስ ዘመን፡-ከመንግሥት ኃላፊነት ተነስተው ወደ ተቃዋሚነት ለመምጣት ምክንያቱ ምን ነበር?
ዶክተር አለማየሁ፡- ይህንን ከመናገሬ በፊት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ማወቅ ያለበት ነገር ብዬ የማስበው ተቃዋሚ እና ጠላትነት የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን ነው።እኔ ተቃዋሚ ከመሆኔ በፊት ኢህአዴግን በደንብ አውቀዋለሁ።ስምንት ዓመት አብሬው ስሰራ በኢህአዴግ መንገድ ኢትዮጵያ የተሻሻለ ሁኔታ ውስጥ ትገባለች የሚል እምነት ይዤ ነው። ስምንት ዓመት ከሰራሁ በኋላ ግን የኢህአዴግ መስመር በተወሰነ ደረጃ ካልተሻሻለ በስተቀር አገሪቱ ወደመልካም ጎዳና እንደማትገባ ስረዳ አስተዋጽዎዬን ሰላማዊ በሆነ መንገድና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት የፖለቲካ ድርጅት አቋቁሜ መታገል ወሰንኩ፡፡ይህንን ማድረጌ ለኢህአዴግ ለራሱ ውለታ እንደመዋል ነው የምቆጥረው።ጠላትነት ግን አይደለም።ለእኔ ይሄ ነው በደንብ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ፡፡እዚህ አገር ተቃዋሚዎችም በህገመንግሥቱ መሰረት ተመዝግበው ወደ ተቃዋሚነት ሲገቡ የሚያወሩት ስለጠላትነት ነው።ምክንያቱም በአገራችን ውስጥ የባላንጣነት ፖለቲካ ነው የሚሰራው።ተቃውሞ ማለት ተቃራኒ ሃሳብ ይዞ መቅረብ ነው።በእኔ እምነት በወቅቱ አገሬ ልትሻሻል የምትችልበትን የፖለቲካ አጀንዳ ነው ያራመድኩት።ስለዚህ ኢህአዴግ እኔን ሊያመሰግነኝና እጄን ስሞ ሊያደንቀኝ ሲገባው ጠላት አድርጎ ነው የተመለከተኝ።
አዲስ ዘመን፡- ይህ አስተሳሰብ አሁንም አለ ብለው ያምናሉ?
ዶክተር አለማየሁ፡- ለዚህ እኮ ነው እኔ ትኩረት እንዲሰጠው አበክሬ የምናገረው!።ለምሳሌ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በንጉሱ ዘመን ከየትኛውም ሚዲያ በላይ ታዋቂ ጋዜጣ ነበር።ምክንያቱም የነፃ ውይይት መድረክ ስለነበር ነው።አሁንም ቢሆን አዲስ ዘመንና ኢትዮጵያ ሬዲዮ ካላቸው ሽፋን አኳያ አሁንም ወሳኝ ቦታ ያላቸው በመሆኑ ተቃዋሚነት ማለት ጠላትነት አለመሆኑን ማስተማርና በህዝቡ ዘንድ ማስረፅ አለበት። እኔ በተቃዋሚነት ለመመዝገብ የምችለው ህገመንግሥቱን ሳምን ነው። ከተመዘገብኩ በኋላ ህገመንግሥቱን ተቀብያለሁ።ከተመዘገብኩ በኋላ እንደገና ይሄ ህገመንግሥት ገደል ካልገባ በስተቀር አይሰራም ብል ራሴን ነው የማታልለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን ደግሞ ኢዜማ ውስጥ እንዳሉ ሰምቻለሁ፤ ይህ መረጃ ምን ያህል ትክክል ነው?
ዶክተር አለማየሁ፡- አሁን ፖለቲካ ውስጥ አይደለሁም። በእርግጥ የፖለቲካ ትንታኔዎች እሰጣለሁ፤ የፖለቲካ ጉዳዮች
ላይ እሳተፋለሁ።ኢትዮጵያን
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4 ቀን 2012 ዓ.ም
ታኅሣሥ 4/፳፻፲፪
አስጨንቀው በያዟት ጉዳዮች ላይ የግሌን ምክረ ሃሳብ እሰጣለሁ።ሰሞኑንም እንዳየሽው የምንፈልጋት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ያሉትን አራት አማራጮች በዴስቲኒ ኢትዮጵያ ከተመረጡት 50 ሰዎች ውስጥ እኔም አንዱ ነኝ። እኔ የማንኛውም የኢ ዜማም ሆነ የማንኛው የፖለቲካ ድርጅት አባል አይደለሁም።ይህንን ስልሽ ደግሞ የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆን ስህተት ነው ማለቴ እንዳልሆነ እንድትገነዘቢልኝ እፈልጋለሁ። አሁን የተሻለ ሥራ ልሰራ ወደምችልበት ወደሚዲያው እየገባሁ ነው።ሰሞኑን «ከእለተሀሳብ» የምትል መፅሄት ወጥታለች የዚህች መፅሄት መስራችና ሥራ አስኪያጅ ነኝ። እንዲሁም በተለያዩ መድረኮች ላይ «እውነታችንን እንፈልግ» በሚል ርዕስ ዲስኩርና የፖለቲካ ትንታኔዎች አደርጋለሁ።ይሄ ማለት ግን የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል አይደለሁም፡፡
አዲስ ዘመን፡-አሁን ያለውን የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ በእርሶ እይታ ምን ይመስላል?
ዶክተር አለማየሁ፡- ይህንን ከመናገሬ ትንሽ ወደ ኋላ ልመልስሽ፤ ኢህአዴግ ህገመንግሥቱን አርቅቆ ተግባራዊ ካደረገ በኋላ የሰራቸው መልካም ነገሮች አሉ።ለምሳሌ የልማታዊ መንግሥት ውስጥ ዴሞክራሲ እንዴት አብዮታዊ ይሆናል የሚለውን ጭቅጭቅ እንተወውና በዚያ የርዮት ፓኬጅ ውስጥ ብዙ መልካም ነገሮች ተሰርተዋል።አገሪቱ በታሪኳ አይታ የማታውቀው የመሰረተ ልማት እድገት ነው ያየችው።ግን ዴሞክራሲውን በተመለከተ ደግሞ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ነው ወደኋላ ነው የሄደችው።ሰብአዊ መብትን በማክበር፣ መልካም አስተዳደርን በመመስረት ረገድ፤ የአገሪቱን አንድነት ሊጠብቅ በሚችል መልኩ የፌዴራል አወቃቀሩ ትክክል ከማድረግ፣ ሙስናን ከመከላከል እና ሥራ አጥነትን ከማጥፋት አንጻር በጣም ከፍተኛ የሆኑ ጉድለቶች ታይተዋል። እነዚህም ጉድለቶች ናቸው የህዝብን ስሜት ቀስቅሰው ወደ አመፅ እንዲያመራ ያደረጉት።እነዚህ ነገሮች ደግሞ ኢህአዴግ ውስጥም የሃሳብ ልዩነት ፈጥረዋል።የሃሳብ ልዩነት በመፈጠሩ ራሳቸውን ወደ መገምገም ነው የሄዱት፡፡በወቅት ሚዲያውን እንዴት እንዳፈኑት፤ የፖለቲካ ምህዳሩን እንዴት እንዳጠበቡት፤ ሙስናን መከላከል እንዳቃታቸው ራሳቸው ናቸው ያመኑት።ለእኔ ያንን ማመናቸው በራሱ አንድ እርምጃ ነው።ይህንን በተመከተልም እስረኞችን መፍታት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት፣ ሚዲያው በተወሰነ ደረጃ የራሱን እንቅስቃሴ እንዲያደርግ መፍቀድ፣ በውጭ ስደት ላይ የነበሩ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረግና የመሳሰሉት ነገሮች ለእኔ ኢህአዴግ የዘጋውን መንገድ እንደከፈተ ነው የሚቆጥረው።ይህንን እንደ አንድ መልካም ነገር ልንወስደው እንችላለን እንጂ ለውጡ ይሄ አይደለም።እነዚህ ነገሮች የለውጡ መግቢያ በር ናቸው።በቀላል አነጋገር አንድ ቦታ ስትሄጂ በር ተከፈተ ማለት ገባሽ ማለት አይደለም።ከተከፈተ በኋላ መግባት መቻል አለብሽ።እናም ከገባሽ በኋላ ነው ለውጡን የምታይው።
ከዚያ በኋላ አስደናቂ ነገር የሆነውና ኢህአዴግ አለ? የለም? የሚል ጥያቄ እስኪፈጠር ድረስ አወዛጋቢ ነገር የሆነው የዶክተር አብይ ፖለቲካዊ ተክለሰውነት በኢህአዴግ ታሪክ ውስጥ ጎልቶ መውጣት ነው።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ የሚናገሩት ነገር ሰብዓዊነትን የያዘ እንጂ የፖለቲካ እንስሳ የሚናገረው አይደለም።ያ ነገር ጎላ ብሎ ለሁላችንም ተስፋን ሰጥቶናል።ይሄ ደግሞ አስፈላጊ ነበር።በተለይም ወደፊት ለመራመድ፤ ምክንያቱም ተስፋ የሌለው ሰው አንድ እግሩን አያነሳምና ነው።ስለዚህ ያቺን ተስፋ በመያዛችን ሁላችንም ተነቃቅተናል።በዚህ ምክንያት ይኸው አዲስ ዘመን ጋዜጣም ዛሬ ድንበሩን እየጣሰ እየመጣ ነው።ይሄ መልካም ነገር ነው።አሁን ግን ኢህአዴግ ውስጥ የሄድነው ርቀት በቃ የሚል ኃይል አለ፤ የእስረኛን መፈታት የጋዜጦችን መብዛት እንደለውጥ ወስዶ በቃ ያለ ሰው አለ።አይደለም! ለውጥ የሚባለው በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ መብቶች ተመጣጥነው ሲከበሩ፣ ኢኮኖሚው ወሳኝ በሆነ ሁኔታ ወደፊት ሲራመድ፣ ሥራ አጥነትንና የኑሮ ውድነትን ማጥፋት ሲቻል፣ አስተዳደራዊ ብቃቱን ሲያገለብት ነው።
ግን አሁን በዚያ መንገድ እየሄድን ነው ወይ? ብለሽ ከጠየቅሽኝ፤ ብዙ የሚያምታታ ነገር ነው ያለው።በአንድ ወገን «በቃ ፌዴራሊዝም ሥርዓቱና ህገመንግሥቱ ሊፈርስ ነውና እንቁም» የሚል ኃይል አለ።በሌላ ወገን ደግሞ «ቀኑ ከመርፈዱ በፊት ቶሎ ክልል ልሁን» ብሎ የራሱን አጀንዳ ይዞ የወጣ አለ።እንዲሁም ከዚህ በፊት በባላንጣነት ፖለቲካ ውስጥ ተሰልፈው የነበሩ ኃይሎች የባላንጣነት አስተሳሰቡን ትተው ወደ ተቃዋሚነት የመሸጋገሪያ ድልድይ ገና የጎለበተ አይደለም፡፡ዛሬ ትልቁ መረጃ እየመጣ ያለው፤ ያኔ ሲበድለን ከነበረው አካል ውስጥ ነው።ዛሬም እሱ ላይ ተንጠልጥለን ነው ያለነው።ለዚህ ነው የምንጨነቀው፤ ኢህአዴግ ተዋሃደ አልተዋሃደ በጣም እንጨነቃለን።የኢትዮጵያ ህዝብ ቅንጅት ተዋሃደ አልተዋሃደ ብሎ እኮ አልተጨነቀም።ግን ዛሬ ለምንድን ነው የኢህአዴግ መዋሃድና አለመዋሃድ የሚያስጨንቀን? ምክንያቱም ህይወታችን ዛሬም በኢህአዴግ ትከሻ ላይ ነው ያለው።ይሄ ነው ትልቁ ስህተት!።ህዝብ በራሱ እንዲያምን አልተደረገም።ምሁራኖቻችን በየጥጋጥጉ ላይ ቆመው ነው ሃሳብ እየሰጡ ያሉት።ያላቸውን እውቀትም ቢሆን በአግባቡ ሥራ ላይ እያዋሉት አይደለም። ሁላችንም ብንሆን ያለንን እውቀት ትንሽ ትንሽ መወርወር እንጂ የተያያዝነው እንደምሁር ተሰባስበን አገራችንን አንገብግበው የያዟት ጥያቄዎች ለመፍታት በጋራ አልሰራንም።
አሁንም ብዙ ሰዎች ያለፈውን 27 ዓመት ነው የሚወቅሱት፤ ግን ለእኔ ከ40 ዓመታት በላይ ነው ችግሩ የተፈጠረው ብዬ ነው የማምነው።ደርግም ቢሆን የራሱን ሊሂቃንን ፈጥሮ በራሱ ሊሃቃን ነበር ሲያጨበጭብ የነበረው።በዚህ ሂደት ውስጥ ነፃ የሆነ ሃሳብ የሚያመነጭ ፣ የሃሳብን ልዕልና የሚረዳና እንዲረጋገጥ የሚያደርግ ማህበራዊ ኃይል አልተፈጠረም።ዛሬ ኢትዮጵያ መንታ መንገድ ላይ ነው ያለችው።ችግራችንን በንግግር እንፍታ የሚል ኃይል አለ።በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን ነገሮች ህጋዊ በሆነ ማዕቀፍ ውስጥ መምራት የሚያስችል አቅም የለም።እኛ በሴናሪዮዎችን ( ቢሆኖች) ሰባራ ወንበር ያልነው ይህንን ሁኔታ ነው።ወይ አትቆሚበት፤ ወይ አትቀመጭበት፤ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ነው አገራችን ያለችው።እናም ይሄ ሁኔታ አደገኛ እና የሚያሳስብ ጉዳይ ነው።በእርግጥ ተስፋው ተሟጦ አላለቀም።ጥርጣሬውና ፍርሃቱም ጨርሶ አልጠፋም። የእኛን የኢትዮጵያንን ህይወት ለረጅም ዘመናት ውጦ የኖረው እሴት ፍርሃትና ተስፋ መቁረጥ ነው።ከዚህ ውስጥ ነው የሆነ የብርሃን ጭላንጭል እየፈለግን ያለነው።አሁን ደግሞ ከዚህ ቦታ ውጣ እያለ የሚጨቃጨቅ አለ።ዛሬ ይሄ ህገመንግሥት ለዘላለም ይኑር የሚል አለ፤ ይሄ ህገመንግሥት ወደ ገደል ይጣል የሚልም አለ።አሁን እኮ እስኪ ይህንን ህገ መንግሥት የትኛው ጋር ነው ስህተቱ ብለን ለመነጋገር ጊዜ መውሰድ የማንፈልግበት ሁኔታ ውስጥ የገባን ይመስለኛል።ስለዚህ እንደዚህ አይነት ዝብርቅርቅ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ለእኔ ግን እውነቱን ልንገርሽ በደንብ ተሰምሮበት እንዲቀመጥ የምፈልገው ነገር ዛሬ እየሆነ ያለው ሁሉም ነገር መሆን የነበረበትና የሚጠበቅ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ዶክተር አለማየሁ፡- ይሄ እንደዚህ አይነት ዝብርቅርቅ ያለ ሁኔታ ውስጥ መግባት ልክ በረት ውስጥ አፍነሽ እንደያዝሻቸው ፈረሶች በሩን ስትከፍችው ሁሉም ወደየአቅጣጫው እንደሚበተኑ ሁሉ እኛም እንደዚያ አይነት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሲሉ የዴሞክራሲ ያለገደብ መለቀቅ የፈጠረው ነው እያሉኝ ነው?
ዶክተር አለማየሁ፡- አዎ! ዴሞክራሲ ማለት ህገወጥነት ማለት አይደለም። ዴሞክራሲ ማለት መብትን በኃላፊነት ውስጥ የምትተገብሪው ስርዓት ነው።መብት ያለኃላፊነት፣ ነፃነት ያለኃላፊነት እውን መሆን አይችልም።ለመሆኑ የዴሞክራሲ ትርጓሜ ምንድን ነው? ዴሞክራሲ ማለት እኮ ነፃነትን ተቋዋሚ ማድረግ ነው።ምክንያቱም እኔ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር የሚያስፈልገኝ አንቺ እዚህ ጋር ስትኖሪ ነው።እኔ ብቻዬን ስሆን ለምን ዴሞክራሲ ያስፈልገኛል?።ለምንድን ነው ከአንቺ ጋር ዴሞክራሲን የሚያስፈልገኝ?።እኔም አንቺም ፍላጎት ስላለን ነው።ዴሞክራሲ የእኔና የአንቺ ፍላጎት ተጣጥሞና ተቻችሎ የሚመጣበት ስርዓት ነው፡ ፡እኔ የምፈልገውን ነገር መቶ በመቶ አላገኘውም። አንቺም እንደዛው።ሁላችንም ግን እኩል ካገኘን በጣም ጥሩ ነው።ለዚያም 51 በመቶ አብላጫ ድምፅ ተብሎ የሚወሰደው።ለዚህ ነው የህግ የበላይነት በዴሞክራሲ ውስጥ አንኳር የሆነ ቦታ ያለው።ህግ የሚያስከብሩ ሰዎች የመጀመሪያ ተግባራቸው መሆን የሚገባው ጥይት መዞ መተኮስ ሳይሆን በገለልተኝነት መዳኘት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው ሁኔታ ወደዚያ የህግ የማስከበር መንገድ እየሄድን አይደለም?
ዶክተር አለማየሁ፡- ወደእዛ ለመሄድ እየተመኘን ግን አቅሙን መገንባት አልቻልንም።እርግጥ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ።ግን ፋታ የለንም።ልክ የተራበ ሰው አይነት ነው እየሆንን ያለነው።የተራበ ሰው የባቄላ ማሳ ጋር ሲደርስ ሳይፈለፍል ነው የሚበላው።ትንሽ ጠገብ ሲል ይፈለፍላል፤ በጣም ሲጠግብ ይጠረጥራል።ልክ እንደዛ ነው የሆነው።ለነገሩ የሚጠበቅ ነገር ነው!።ለዚህ ነው ትዕግስት የሚያስፈልገን።ሰዎችም እየሞቱብን፤ እየተፈናቀሉብን፤ ችግርም እያለ፤ ለረጅም ዘመናት ትከሻችን ላይ የተቆለለ አገሪቱን እያስጨነቀ ያለ ተግዳሮት በመሆኑ ትንሽ ትዕግስት ሊኖረን ያስፈልጋል።ትዕግስት ማለት ደግሞ እነዚህ ነገሮች እየተባባሱ እንዲሄዱ ማድረግ ማለት አይደለም።ደረጃ በደረጃ መቀነስ ማለት ነው።ከዚህ በፊት ህግ አልተከበረም፤ ሰዎች ያለህግ ታስረዋል እያልን ዛሬ ያንን ከደገምን ለውጥ አላመጣንም ማለት ነው።ግን ደግሞ ህግን ተጠቅመን ችግር የሚፈጥሩ ሰዎችን በህግ ቁጥጥር ውስጥ ማድረግ አለብን።ይህም ቢሆን ግን ህብረተሰቡን የማስተማር ሥራ መቅደም እንዳለበት አምናለሁ።
አሁን ትልቁ ችግራችን ምሁሩም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ዶክተር አብይ ነው፤ እሱ ካልተናገረ ሌላው ቢናገር የሚሰማው የለም።አንዳንድ ሰዎች «ይሄ ሰውዬ እንደዚያ ነግሮን ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ጉድ ሰራን» ይላሉ፤ በእኔ እምነት ዶክተር አብይ ሥራውን ጨርሷል፤ ልንሄድበት የሚገባን መንገድ በምክር ቤት ውስጥ ነግሮናል፤ ከዚያ በኋላ እኮ እኛ አህዮች አይደለንም። ሁሉን ነገር አብይ እየተናገረን መሄድ አለብን እንዴ? ልክ ድሮ የእናንተም ጋዜጣ እንደሚያደርገው ከላይ ያሉ ሰዎች «ስንዴ ዳቦ መሆን ይችላል እንዴ?» ተብሎ ሲጠየቁ «አዎ ገብስም ቢሆን ዳቦ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ነው ያለው» ብለው ምላሽ ይሰጣሉ።እናም ልክ እንደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሁሉ ታች ቀበሌ ድረስ ወርዶ ይኸው ምላሽ ይነገራል።በእኔ እምነት ይሄ አሰራር ነው መጥፋት ያለበት።አብይ በራሱ መንገድ በራሱ ችሎታ የተናገረውን ነገር አለማየሁ ደግሞ በራሱ ግንዛቤ በራሱ አስተሳሰብ የማየት ችግር ሳይፈጥር ማስረዳት መቻል አለበት።
ዛሬ ላይ ለማ አብይን ከዳው ተብሎ ይጮሃል።ለመሆኑ ለማ ማነው? አንድ ሰው እኮ ነው!። በእርግጥ የሚከተሉት ብዙ ሰዎች አሉ።ለማ የፈለገውን አቋም ቢይዝ መብቱ ነው።ለምንድን ነው መብቱ ነው ብለን የማንቀበለው?። እሱ የያዘውን አቋም በትክክል ተረድተን ከሆነ የያዝከው አቋም ለኢትዮጵያ በዚህ መንገድ ይጎዳል፣ በዚህ መንገድ ደግሞ ይጠቅማል ብለን መተንተን ነው የሚገባን።በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ እውቀትን የመፈተን ልም ዱ ሳይኖር ዝም ብሎ ስለተወራ ለውጥ ይመጣል ማለት አይቻልም።ስለዚህ ዛሬ በዓለም ያሉ አገሮች ሁሉ ከእኛ በባሰ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለፉት።እኛም እየዘነጋነው እንጂ የባሰ ችግር ነበር።የእኔ ትውልድ ወጣት እኮ በቀይ ሽብር ነው ያለቀው።አንደኛውን ልጁን ለማዳን ሌላውን ልጁ አሳልፎ የሰጠ ቤተሰብም ነበር እኮ!።ቀይሽብር ይፋፋምብኝ ብሎ ደረቱ ላይ ለጥፎ የሞተ በብዙ ሺ የሚቆጠር ወጣት ነበር።በብዙ ሺ የሚቆጠር ሰራዊት እኮ ነው ሰሜን ውስጥ የጨረስነው!።ያንን እንኳ አስታውሰን ዛሬ የለውን ሁኔታ ትንሽ በረድ አድርገን በትዕግስት ወደሚያዋጣን መንገድ መሄድ ያለብን ይመስለኛል፡፡አሁን የእኔ ስጋት አሁን ያለውን ሁኔታ አብዝትን እንዳናማርር ነው፤ ይሄ ሁኔታ ከነበሩት የተሻለ ነው ብለን ተቀብለን መሄድ አለብን።
አዲስ ዘመን፡- አሁን እስቲ ወደ ሰሞነኛው ጉዳይ ከመግባታችን በፊት ሴናርዮ (ቢሆን) የምንለው ነገር ምንድን እንደሆነ ያብራሩልኝ?
ዶክተር አለማየሁ፡- ሴናርዮ ማለት በአንድ አገር ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተነስቶ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው ብሎ መተንተን ማለት ነው።አንዱ ትልቁ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር ቅድም እንዳልኩሽ አገሪቱን አንገብግበው በያዟት በተለይ ስርዓታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አጀንዳ ያለመኖር ነው።ለምሳሌ ስለፌዴራሊዝም አንቺም የመሰለሽን ነው የምታወሪው፤ እኔም የመሰለኝን ነው የማወራው።ችግሮችን የምንፈታበትን መንገድ የጋራ የሆነ እይታ፣ የጋራ የሆነ የስምምነት ድባብ መግባቢያ ነጥብ የለንም።ደቡብ አፍሪካም ከአፓርታይድ ልትወጣ ስትዘጋጅ ልክ እንደዚያ አይነት ችግር ውስጥ ነበረች።ለምሳሌ አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ውስጥ የነበሩት በማንዴላ ወገን የነበሩት ከአሁን በኋላ ነጮች አስቀርተን ስልጣኑን ተረክበን መሬቱንም እንወስዳለን በሚል እሳቤ ነበር የሚሄዱት።ፓን አፍሪካ ኮንግረስ የሚባለውደግሞ ለእያንዳንዱ ነጭ አንዳንድ ጥይት ነበር ያዘጋጁት፡፡የዴክለርክ ቡድን ደግሞ ጥቁሮች የሚተናኮሉን ከሆነ ራሳችንን የምንከላከልበት ሁኔታ ማዘጋጀት አለብን የሚልእምነት ነበረው።እነሱ ታዲያ በወቅቱ የነበሩትን የተለያዩ ሃሳቦች ወደ አንድ በማምጣት ሊሆኑ የሚችሉትን እውነታዎች በዝርዝር ተንትነው አስቀምጠዋል።የሆነውም ይኸው ነው።በነገራችን ላይ ሴናርዮ የሚባለው ነገር ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ነው የተጀመረው።ይኸው ሂደት ኮሎምቢያ ላይ ሜክሲኮ ላይ ታይላንድ ላይ ተጠቅመውበታል።በአጠቃላይ የሴናሪዮ (ቢሆኖች) ፕላኒንግ ዋነኛ አላማ የጋራ የትኩረት አቅጣጫ፤ የጋራ እይታ መፍጠር ነው።ከዚያ በኋላ እያንዳንዳችን የምንሰራውን ሥራ ከጋራ እይታችን ጋር ማገናዘብ ነው የሚገባን።አሁን ማገናዘቢያ የለንም።ለምሳሌ አንቺም የፈለግሽውን ትናገሪያለሽ፤ እኔም እንደዛው።የጋራ እይታና የጋራ ትኩረት እስከሌለን ድረስ የጋራ ነገር የለንም።ስለዚህ እኛ ሴናርዮን በምንጀምርበት ጊዜ ይህንን ፍለጋ ነበር ጥረት ስናደርግ ነበር።የኮር ቲሙ አባላት በተቻለ መጠን የፖለቲካም፤ ከምሁራን የተለያየ አመለካከት የያዙ ሰዎችን በማሰባሰብ ከድርድር ውጭ የሆነውን ነገር አስቀምጠው ነው የሚገቡት።ለምሳሌ አገርን ከድርድር ውጭ ነው የምናደርጋት።
አዲስ ዘመን፡- ከድርድር ውጭ ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ዶክተር አለማየሁ፡- ለምሳሌ እኔና አንቺ ስንነጋገር «ኢትዮጵያ ትኑር ፤አትኑር» ተባብለን አንጠያየቅም፡፡ሲጀምርም ኢትዮጵያ ከሌለች ውይይትም አያስፈልገንም።የጋራም አጀንዳም አያስፈልገንም።ግን ኢትዮጵያ ትኖር ዘንድ ለአንቺም ስኬት ለእኔም ስኬት ወደሚሆን ነገር መምጣት አለብን ማለት ነው።ይህም የሚሆነው ግን እኔ አንቺን ለምኜ ወይም አንቺ እኔን ለምነሽ አይደለም፤ ምክንያቱም የእርቅ ጉዳይ አይደለም።የጋራ ጉዳይ ካለን ሁላችንም የምንፈልገው ነገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተሳክቶልን እንዴት ነው አብረን ልንኖር የምንችለው የሚለውን ነገር መለየት ማለት ነው።ያንን የጋራ ጉዳይ ለመፈለግ ነበር የእኛም ቡድን የተሰባሰበው።
አዲስ ዘመን፡- የተመረጣችሁበት መስፈርት ምን ነበር?
ዶክተር አለማየሁ፡- እያንዳንዳችን በነበረን አስተዋፅኦ፣ ባለን ተሳትፎ በልዩ ልዩ ሁኔታ ነው የተመረጥነው፡፡ለምሳሌ እኔ የነበረው አቋሜ በምፅፋቸው ፅሁፎች በምናገረው ነገር ይታወቃል፤ ኢትዮጵያን እኔ ከብዙ ችግሮቿ ጋር ተቀብዬ ችግሯ ሊቃለል የሚችልበትን ሁኔታ በየቦታው እናገራለሁ።ከዚህ በፊት በፃፍኳቸው «ምሁሩ»ና «የሰጎን ፖለቲካ የተባሉ ማፃጽፎቼ ላይ ያለኝን ምልከታ አቅርቢያለሁ።በዚያም የነበረኝን ሁኔታ በመረዳት አለማየሁ ለአገር የሚጠቅም ሃሳብ አለው በሚል ነው የመረጡኝ።የፖለቲካ ተሳትፎ ነበረኝ።የግሉ ዘርፍ ውስጥ እንቀሳቀስ ነበር።የመንግሥት ድርጅት ውስጥም ሰርቻለው በዚህ ሁኔታ ተመርጬአለሁ የሚል እምነት አለኝ።ሌሎችም እንደዚሁ ለምሳሌ ፖለቲከኞቹ በፖለቲካ አቋማቸው ነው የተመረጡት።ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች የኢትዮጵያን እጣ ፈንታ የሚወስኑ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ውይይታችሁ ምን ይመስል እንደነበር እስቲ በጥቂቱ ያስታውሱን?
ዶክተር አለማየሁ፡- የመጀመሪያ ስብሰባችንን ያደረግነው ሂልተን ሆቴል ነበር።በወቅቱ ገና ስንተዋወቅ በእውነት ነው የምልሽ ማንም ይምጣ ማንም ለእኔ ብዙ ችግር የለውም ነበር።ለሌሎች ሰዎች ግን ከባድ ነበር።ለምሳሌ የአብን መሪና የኦነግ መሪ ፊት ለፊት ሲተያዩ የሚጣሉበት አጀንዳ ያላቸው ይመስል ነበር።በእኔ እምነት ይህም የሆነው ከመጀመሪያውኑ «የኔ ተቃዋሚ እሱ ነው» ብለው የማመን ነገር በአእምሯቸው ውስጥ ስለነበረ ነው፡ ፡አንዳንዶች ይህንን ውጥረት በማየት «ይህች ነገር የት ነው የምትደርስው?» የሚል ጥርጣሬ ነበራቸው። በኋላ ግን በስልጠናው ባገኘነው ግንዛቤ መሰረት ጥርጣሬው እየተፈታ መጣ።አሰልጣኞቻችን የሚሰጡትን ቴክኒኩን ብቻ ነበር፤ የውይይቱ አጀንዳ የምንናገርበት ርዕሰ ጉዳይ በእኛ ነው።በተለይም በደቡብ አፍሪካ ሴናሪዬ ላይ የሰራው ካናዳዊው አሰልጣኛችን ልዩነቶቻችንን የምንፈታበትን መንገድ በጥልቀት ነበር ያሳየን፡፡ማንም ሰው ያነሳው ሃሳብ በሂደት የሆነ ቦታ ላይ ደርሶ ይወድቃል እንጂ እኔ ስለጠላሁት ብቻ አይወድቅም።ማንም በማንም ሃሳብ ላይ ውሳኔ ማሳለፍ አይችልም ነበር።ግን በጋራ ነበር የምንሄደው፡፡ሃሳቦች የሚወድቁት በጋራ ውይይት ነበር።በዚህ ምክንያት የማንግባባት ምክንያት አልነበረም።
አዲስ ዘመን፡- ልዩነቶቻችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በሰፋበት ሁኔታ ወደአንድነት የሚያመጡንን ሃሳቦች ማግኘት አዳጋች አልነበረም?
ዶክተር አለማየሁ፡- ለምሳሌ እኛ ልዩነትን ለብቻ ፤አንድንትን ደግሞ ለብቻ ደሴት ውስጥ አስቀምጠን ነው የምናወራው፤ የምንነጋገረው።ስንፅፍ እንደዛ ነው።አንድነት የሚለው አካል ልዩነትን ሰብሮ ነው።ልዩነት የሚለው አንድነትን ሰብሮ ነው።ግን አንድነት የሚለው ሃሳብ የሚመጣው ልዩነት ሲኖር ነው።ልዩነት ከሌለ አንድነት የለም።ለምን ስለአንድነት ታወሪያለሽ? እኔና አንቺ አንድ ነን የምንለው እኔ አለማየሁ፤ አንቺም ማህሌት ስለሆንሽ ነው።ስለዚህ ልዩነት የአንድነት መነሻ ነው፡፡አንድነት ደግሞ በልዩነት ውስጥ ነው የሚመጣው።ለምሳሌ ለምንድንነው ጨንበላላ ወይም ገዳ ስርዓት የኢትዮጵያ ባህል የማይሆነው? ለእኔ ጨንበላላም ሆነ ገዳ የኢትዮጵያ ባህል ነው።ብዙዎቻችን ግን አንድን ባህል ለአንድ ብሄር ብቻ ነው የምንሰጠው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግን ይህንን አስተሳሰብ የወለደው ምንድን ነው ይላሉ?
ዶክተር አለማየሁ፡- በእኔ እምነት ፖለቲካችን ሳይከፋፈል ሊገዛ ስለማይችል በከፋፍለህ ግዛው ዘዴ በየዴስካችን አስቀምጦ ጥግ ጥጋችን እንድንይዝ አድርጎናል።በ1983ዓ.ም የተሰራው ትልቁ ግፍ ብዬ የማስበው የኢትዮጵያን ምሁራን በልዩ ልዩ ጥጋቸው እንዲቀመጡ መደረጉ ነው።እስከዚያ ድረስ ግን አገራዊ ብሄርተኝነት ነበር በጉልበት የሚሰጠን።«ኢትዮጵያ ትቅደም፤ አቆርቋዥዋ ይውደም» ይባላል፤ ስለዚህ ከገዢው የተለየ ሃሳብ ሲነሳ አቆርቋዥ ነው።ግን ከተቃዋሚው አካል ኢትዮጵያን ሊያግዝ የሚችል ሃሳብ ሊወጣ የሚችልበት እድል ሊኖር ይችላል ብለን እንኳ አንነጋገርም።ይህ ዓለም ሁሉ የሄደበት ሁኔታ ነው።አሜሪካ እስከቅርብ ጊዜ ውስጥ ይህ ችግር ነበር።ብዙዎቻችን ግን አሜሪካ ስትፈጠር ዴሞክራሲያዊ አገር እንደሆነች ነው የምናስበው።እውነታው ግን ሁሉም አገር በጎራዴ ነው ታሪክ የተሰራው። አሁን ደግሞ ዘመናዊነት ማለት ጎራዴን ማስቀረትና ልዩነትን ለአንድነት መሳሪያ ማድረግ ነው።
ስለዚህ አሁን በሄድንበት ሂደት አብንም ሆነ ኦነግ አንድንት የሚያስፈልገው ልዩነት ስላለ ነው ብለው ሊገነዘቡ ይገባል ማለት ነው።ለምሳሌ የማንነት ጥያቄ ሲነሳ ምንም ሊያስፈራን አይገባም።እኔ የአንድ ኦሮሞ መብት ይከበር ለማለት የግድ ኦሮሞ መሆን አይገባኝም!።የአማራውም ፤የሌላውም እንዲሁ ፡፡ እኔ የሌላው ሰው መብት ይከበር ብዬ የምጠይቀው እኔ በሰላም እንድኖር ነው።ለእሱ ብዬ አይደለም።ቅዱስ ጽሐፍም «በአንተ ላይ ሊደረግብህ የማትሻውን በሌላው አታድርግ አይደል» አይደል የሚለው!። በስልጠናችን በዚያ መድረክ ከልዩነት ውስጥ አንድነት እንደሚወጣ በደንብ ተነጋግረናል። በእርግጥ አስቀድሜ እንዳልኩሽ መጀመሪያ አርባ ምንጭ ያሳለፍናቸው አራት ቀናት ውጥረት የተሞላበት ነበር።ሁሉም ሰው በራሱ ችካል ውስጥ ሆኖ ነበር የሚሄደው። ግን በትዕግስትና በስርዓት በሚመራ ሂደት ውስጥ ግን ሁላችንም ቀስ በቀስ አንድ ጀልባ ውስጥ ነው የተሳፈርነው፡፡ይህም ሲባል አንዳችንም ማንነታችንን መስዋዕት ሳናደርግ ማለት ነው።እኔ የፖለቲካ አቋሜን መስዋዕት ሳላደርግ፤ ሌላውም እንዲሁ፡፡በዚህ አግባብ ነው አንድ ጀልባ ላይ እንደምንሄድ አረጋግጠን የወጣነው።ስለዚህ አብና ኦነግ ዛሬ ቁጭ ብለው በጋራ ጉዳይ ላይ መነጋገር የሚችሉበት እድል ተፈጥሯል።
አዲስ ዘመን፡- ቡድኑ የለያያቸውን አራት ሴናሪዮዎች (ቢሆኖች) ምንነት ያብራሩልን እስቲ?
ዶክተር አለማየሁ፡- አራቱ ሴናሪዮዎች (ቢሆኖች) ሰባራ ወንበር፣ አፄ በጉልበቱ፤ የፉክክር ቤትና ንጋት ናቸው።ሰባራ ወንበር ያልነው አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ አሁን ያለው ሁኔታን ነው፡፡ይህም ማለት ፍላጎቱ አለ፤ ተስፋ እንዲጎለብትም ምኞቱ አለ።ይህም መልሰው የሚደፍቁት ቢኖሩም በንግግርም ይገለፃል።የእኔ ጥያቄ ይቅደም ተብሎ የሚደረግ ሩጫ አለ፤ በዚህ ሁኔታ ለውጡን ለማስቀጠልና ህግ ለማስከበር ረገድ አቅም ያንሰዋል።ሰባራ ወንበር ያልነው ለዚህ ነው።ወንበሩ አለ ግን ብትቀመጭበት ሊወድቅም ይችላል።ስለዚህ መጎልበት፣ መጠገን ወይም መለወጥ አለበት ማለት ነው።በዚህ ሁኔታ ከቆየ የሚከሰተው አፄ በጉልበቱ ሊመጣ ይችላል።ይህም ማለት ያለፈው የአምባገነን ስርዓት ማለት ነው።ለሁሉም ነገር ጥይት መጠቀም፣ የይስሙላ ምርጫ ማካሄድ ይህ ሁኔታ ሊመጣ ይችላል።
ሌላው የፉክክር ቤት ነው።ይህም ዛሬ እያየነው ያለው ነገር ነው።ይህም ሲባል በፌዴራሉ መንግሥትና በክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት ስንመለከት አንዳንድ ክልሎች ኮንፌዴሬሽን እየጠየቁ ነው ያሉት።በአንድ ወገን ፌዴራሊስቶች በሌላ በኩል ብልፅግና ተቀምጠዋል።ደቡብ ክልል ደግሞ ሁሉም ክልል እንሁን ብሎ ጠይቋል።አቅም የጎደለብትን ሁኔታ ተጠቅሞ የፉክክር ቤቱ ያይልና ደካማ ፌዴራል አስተዳደር፤ ጠንካራ የክልል አስተዳደር ይፈጠርና እነዚህ ቅራኔዎች የበለጠ እየተባባሱ የሚሄዱበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚለው ሶስተኛው ቢሆን ነው። አራተኛውና ሁላችንም የምንፈልገው ንጋት ነው።አሁን የጨበጥነውን ተስፋ አንዳንድ ለውጦች ይዘን እነሱ ላይ እየገነባን ቀስ በቀስ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተገነባበት አገር እንድትሆን መስራት ነው።ምክንያቱም ዴሞክራሲ በአንድ ጀምበር አይመጣም።ድህነታችንም በአንድ ጊዜ አይወገድም።ስለዚህ እነዚህን ጉዳዮች በ20 ዓመታት ውስጥ ቀስ በቀስ በማምጣት አገሪቱ የተረጋጋችና የተሟላ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያላት ሀገር ትሆናለች የሚል እምነት ነው የያዝነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከጠቀሱልኝ አራት ቢሆኖች ውስጥ አሁን ባለው ሁኔታ የትኛው ነው የመሳካት እድል ያለው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር አለማየሁ፡- እኔማ እሰራለሁ ብዬ ያሰብኩት ፤ እንዲሳካም የምፈልገው ንጋትን ነው። ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እውን መሆን ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ለመስራት ነው ቃል የገባሁት።በእርግጥ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ለሁሉም የተጋለጠ ነው።ለዚህም ነው ሁሉም የራሱን ኃላፊነት መወጣት አለበት ብለን የምናምነው።አንቺ የምትሰሪው ሥራ ወዴት ነው የሚያመራው የሚለውን መለየት አለብሽ፡፡ንጋት ሊመጣ የሚችለው ለፍተሽ በመሆኑ ነው።ስለዚህ እኛ ሥራችንን ጀምረናል፤ ይህንን ስልሽ ደግሞ በተስፋ ብቻ አይደለም።አሁን ያለውን የመለወጥ ጉጉት ይዘንነው፤ ጅምር የሆኑ ለውጦች አሉ።በተለይም ሚዲያው እነዚህን ሴናሪዎች ለህዝቡ ግንዛቤ በማስጨበት መሪና ሀሳብ አመንጪ መሆን ይገባዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ንጋት እውን እንዲሆን ከምሁሩ ምን ይጠበቃል?
ዶክተር አለማየሁ፡- እኛ አገር ብዙ የተማረ ቢኖርም ሊሂቅ የሚባለው ግን ጥቂት ነው።አብዛኛው የተማረ ኃይል በእሽግ ውስጥ ሆኖ የሚያበራ ሻማ ነው።አዲስ ሃሳብ የሚያመነጭ አካል የለም።ከዚህ አንፃር እንግዲህ አስቀድሜ እንዳልኩሽ የእኛ ቡድን ምሁሮች፣ አክቲቪስቶች ፖለቲከኞች አሉ።እነዚህ አካላት በየመጡበት ተቋም ሲመለሱ ይህንን አስተሳሰብ ለሌላው ያሰርጻሉ ተብሎ ይተመናል። እኛም በግሉና በሲቪል ሶሳይቲ ዘርፍ ለመነቃነቅ ዝግጁ ነን።ይህም ማለት በግድ እንዲቀበል ማድረግ ሳይሆን ኢትዮጵያ ከፊቷ የተጋረጠውን አደጋዎች ተመልክተው የሚበጃትን ነገር በፈቃዱ ሁሉም መርጦ እንዲሰራ ማድረግ ነው። ዋናው ሥራ በድምስሱ አፍራሽ ሃሳቦችን የማጥፋት ሳይሆን የመቀነስ ነው።እነዚህ አፍራሽ ሃሳቦች ምንም ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ መድረስ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር አለማየሁ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/12
ማህሌት አብዱል