ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከ46 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ህዳር 24 ቀን 1966 ዓ.ም ነበር።
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግንባታው ተጠናቆ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የተመረቀው ጥቅምት 24 ቀን 1966 ዓ.ም ነው። አገልግሎት መስጠት የጀመረው ግን በተመረቀ በወሩ ህዳር 24 ቀን 1966 ዓ.ም ነበር። በ 1950ዎቹ መጨረሻ ግንባታው እንደተጀመረ የሚነገረው ሆስፒታል 21 ሚሊዮን 605 ሺህ 399 ብር ወጥቶበታል።
ሆስፒታሉ መጀመሪያ “የልዑል መኮንን መታሰቢያ ሆስፒታል” እየተባለ ነበር የሚጠራው። ልዑል መኮንን ወደ አዳማ ሲጓዙ መንገድ ላይ ባጋጠማቸው የትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ልጅ ናቸው። በኋላ በደርግ ዘመን የቀደመ ስሙ ተሽሮ ከ1968 ዓ.ም አንስቶ “ጥቁር አንበሳ” ተብሎ መጠራት ጀመረ።
“ጥቁር አንበሳ” በጣሊያን ወረራ ወቅት ከፍተኛ መስዋትነት የከፈሉት በ1928 ዓ.ም የተመሰረተው የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት የመጀመሪያዎቹ ምሩቆች የነበሩ ወጣት አርበኞች የትግል ስም ነው። ሆስፒታሉ በዚህ ስም እንዲጠራ የተደረገው የእነዚህ ለጋ ወጣቶች ጀግንነትንና የአገር ፍቅር ስሜትን ለትውልዶች እንዲያጋባ ታስቦ እንደሆነ ይነገራል።
ሐሙስ ህዳር 27 ቀን 1966 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ “የልዑል መኮንን መታሰቢያ ሆስፒታል ስራ ጀመረ” በሚል ርእስ ይዞት በወጣው ዘገባ “በኢትዮጵያና በመላው ምስራቅ አፍሪካ በትልቅነትና በዘመናዊነት ተወዳዳሪ የሌለው የልዑል መኮንን ኃይለስላሴ ሆስፒታል ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ለበሽተኞች በሩን በመክፈት አገልግሎት መስጠቱን ቀጥሏል።” ሲል አስነብቦ ነበር።
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የተገነባው 500 አልጋዎች እንዲኖሩት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ስራ የሚጀምረው በ 150 አልጋዎች ብቻ ነበር። ዛሬ 67 በመቶ ነጻ ህክምና የሚሰጠው ሆስፒታል ሲመሰረት 25 አልጋዎች ነጻ ህክምና ለሚሰጣቸው ችግረኞች መድቦ ነበር።
ሆስፒታሉ ስራ የጀመረው በኢትዮጵያና ስዊዘርላንድ መንግስታት መካከል በተደረገ ስምምነት በሁለቱ አገራት የህክምና ባለሙያዎች ጥምረት በ 18 ሐኪሞች ሲሆን፤ ከእነዚህ ሀኪሞች መካከል ስድስቱ ኢትዮጵያውያን ከ25ቱ ነርሶች 12ቱ ኢትዮጵያውያን 13ቱ ደግሞ የስዊዝ ነርሶች ነበሩ። በተጨማሪም 22 ኢትዮጵያውያን ድሬሰሮች ነበሩት።
የሆስፒታሉ አልጋዎች ሶስት ደረጃዎች ነበሯቸው። አንደጃ ደረጃ አልጋ እንደ ክፍሉ ይዞታ ከ30 እስከ 50 ብር ይከፈልበታል። ለሁለተኛ ደረጃ አልጋ ደግሞ 12 ብር ይከፈል ነበር። በእነዚህ ሁለት የአልጋ ክፍሎች የሚታከሙ ታካሚዎች ለሚያገኙት የህክምና አገልግሎት ተጨማሪ ክፍያ ይፈጽማሉ። ሶስተኛ ደረጃ አልጋ ክፍል ግን ለየትኛውም አይነት የህክምና አገልግሎትና ለአልጋው በድምሩ በቀን የሚከፈለው 10 ብር ነበር። ተመላላሽ ታካሚዎች ለምዝገባ የሚከፍሉት የሶስት ብር ክፍያ ሁሉንም አይነት የላብራቶሪ ምርመራ ጭምር የሚያካትት ነበር።
በሁሉም ደረጃ የመኝታ ክፍሎች ውስጥ በእያንዳንዱ አልጋ አጠገብ የሬዲዮ ዜናዎችና ሙዚቃ ለመስማት ለሚፈልጉ ታካሚዎች ሁሉ ቴፖች ተዘጋጅተውላቸው ነበር። ታዲያ የአንደኛው ፍላጎት የሌላውን ጸጥታ እንዳያውክ የተዘጋጁላቸው የማዳመጫ መሳሪያዎች በጆሮ ላይ የሚደረጉ ነበሩ።
የሆስፒታሉ ክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ዶክተር ይርጉ ገብረህይወት ከወራት በፊት ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲመሠረት አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 25 ሚሊዮን አካባቢ ነበር የሚገመተው። በዚያ ዘመን ዘመናዊ ሕክምናን የመጨረሻው አማራጭ ተደርጎ ነበር የሚታሰበው። ያኔ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ የሕክምና ዘዴዎችን ነበር የሚያዘወትሩት። ስለዚህም ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ተገልጋዮች ቁጥር በጣም ውስን ነበር። በወቅቱ ሆስፒታሉ ስምንት ፎቅ ቢኖረውም አልጋ የነበረው እስከ አምስተኛ ፎቅ ድረስ ብቻ ነበር። ያኔ ሕንፃው ከበቂ በላይ በመሆኑ ከስድስተኛ እስከ ስምንተኛው ፎቅ ድረስ ያሉት ክፍሎች ባዶ ነበሩ።
አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስር የሚገኘው ሆስፒታሉ በየጊዜው የአልጋዎቹን ቁጥር እያሳደገ መጥቶ አቅሙን አሟጥጦ በመጠቀሙ ትርፍ የሚባል ክፍል የለውም። ከምድር ወለሉ ጀምሮ እስከ ስምንተኛው ፎቅ ድረስ በአልጋ ተሞልቷል። በዋነኝነት አገልግሎት የሚሰጠው የደሃ ደሃ ለሆኑ ዜጎች ነው ማለት ይቻላል። 67 ከመቶ የሚደርሱት ታካሚዎች ከሚኖሩበት አካባቢ የደሃ ደሃ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ማስረጃ ይዘው የሚቀርቡ ናቸው።
ዛሬ ጥቁር አንበሳ አንድ ሺ 100 ገደማ ከጀማሪ እስከ ሰብ ስፔሻሊስት ደረጃ ያሉ ሀኪሞችንና 930 ነርሶችን ጨምሮ በአጠቃላይ ሦስት ሺ 400 ሠራተኞች ያሉት በበርካታ ዘርፎች ህክምና የሚሰጥ ግዙፍ ሆስፒታል ሆኗል። በሌሎች የህክምና ተቋማት የማይሰጡ የካንሰር ሕክምናዎች በአብዛኛው ተሟልተው የሚገኝበት ብቸኛ ሆስፒታል ነው። ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ የካንሰር ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በሁሉም የሕክምና ዘርፎች በውስጥ ደዌ፣ በሕፃናት፣ በማሕፀንና ፅንስ ፣ በቀዶ ሕክምና እንዲሁም በሌሎች የሕክምና መስኮች ልዩ ልዩ የካንሰር ሕክምናዎች ይሰጣል። በድንገተኛ አገልግሎትም በዓመት እስከ 40 ሺ ሰዎች ይታከማሉ። የአጥንት ሕክምና አገልግሎትም እየሰጠ ይገኛል። በአጥንት ሕክምና ረገድ ሰው ሠራሽ መገጣጠሚያዎችን የመትከል አገልግሎት የሚሰጥበት ተቋም ነው።
የዩኒቨርሲቲ ተቋም ስለሆነ በተጓዳኝ የሚሠራቸው ሥራዎችም አሉት። ለራሱና ለአገሪቱ የጤና ተቋማት በመስኩ የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት መልስ በመስጠት ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ነው። በቅድመ ምረቃና ድህረ ምረቃ ስድስት ሺ 500 የሚደርሱ ተማሪዎችን ያስተምራል። በድህረ ምረቃ የስፔሻሊቲና ሰብ ስፔሻሊቲ ትምህርትም ሀኪሞችን በማፍራት ላይ ይገኛል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ከሚገኙ ተቋማት ምርምር በመሥራትና በማሳተም ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ የአንደኛነት ደረጃን ተቆናጧል።
ሆስፒታሉ አሰራሩን ከጊዜ ወደጊዜ እያዘመነ በመምጣት ተገልጋዮቹ ዘመኑን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት በሚያደርገው ጥረት ብዙ መሻሻሎችን ያሳየ ቢሆንም የአንዳንድ የህክምና መሳሪያዎች አለመሟላትና የመድሃኒት እጥረት ያልተቀረፉ ችግሮቹ ሆነው ዘልቀዋል። በሆስፒታሉ ውስጥ መሠራት ካለበት የላቦራቶሪ ቴስት ሜኑ 16 በመቶ እየተሰራ አይደለም። የመድኃኒት አቅርቦቱም ከ65 እስከ 70 በመቶ ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ህዳር 24/2012
የትናየት ፈሩ