የተክሌ ዝማሜ አቋቋምን የሚተካ ቃል ሲሆን አቋቋም ‹‹ቆመ›› ከሚለው የሰዋስው አንቀጽ የተገኘ ቃል ነው። የቃሉ አሰያየምም “ውስተ ዝንቱ መካን ቅዱስ ንቁም ንሰብሕ ወንዘምር ” (በዚህ በተቀደሰው ቦታ እንቁምና እናመስግን) ያለውን የሊቁን የቅዱስ ባስልዮስን ድርሰት መነሻ ያደረገ ነው ተብሎ ይታመናል። የአቋቋም አመጣጥ ብዙ ታሪክ ያለው ሲሆን ይኽ ጽሑፍ ከተክሌ ዝማሜ ጋር በተያያዘ ላይ ብቻ ያተኩራል። ዝማሜ ማለትም የሥርዓተ ማኅሌት ቁመት ሒደት ነው። ቁመቱም በሰባት ዓይነት የተከፈለ ሲሆን እነርሱም ቁም ዜማ፤ ዝማሜ፤ ቁም፤ መረግድ፤ ጽፋት፤ አመላለስና ወረብ የተሰኙት ናቸው።
በዚህ ረገድ ዝማሜ ቁም ዜማው በኅብረት ከተዘለቀ በኋላ የድጓው መጀመሪያ ክፍል መሪ እየመራ፤ ተመሪ እየተመራ ይባላል(ይመራል)። ቀጥሎም ካህናት በኅብረት ሆነው መቋሚያቸውን ወደ ቀኝና ወደ ግራ፤ ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየወዘወዙ፤ አልፎ አልፎም መሬቱን እየመቱ (እየረገጡ) ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት ጥበባዊ ስልት ነው። ወደ ቀኝና ወደ ግራ፤ ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየወዘወዙ በኅብረትና በተናጥል መዝመማቸውም ከጌታ ሥቃይ ጋር የተያያዘ የራሱ ትርጉም አለው።
በተለምዶ ተክሌ የራሳቸውን የአቋቋምና የዝ ማሜ ስልት ደረሱ ተብሎ ቢታመንም የዝማሜው የመጀመሪያው ወላጅ አባታቸው ደራሲውና ሊቁ አለቃ ገብረ ሐና ናቸው። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ግን እኒህን ሊቅ የሚያውቃቸው በተሣላቂነታቸውና በቧልተኝነታቸው (በአሽሙረኛነታቸው) ነው እንጂ በባለቅኔነታቸውና በዜማ ሊቅነታቸው አይደለም። እስቲ ከቅኔያቸው አንዷን ጉባኤ ቃና ጠቅሰንላቸው ወደ ርእሰ ጉዳያችን እንለፍ።
ኮንኖ ኃጥአን ሎሙ ኢይደልወከ ምንተ።
አፍቅሩ ጸላዕተክሙ እንዘ ትብል አንተ።
ትርጉም፡ ፈጣሪ ሆይ ! ራስህ ጠላቶቻችሁን ውደዱ እያልክ ኃጥአንን ወይም ኃጢአተኞችን መኮነን፣ መቅጣት አይገባህም።
ምሥጢር፡ ፈጣሪየ በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 6. ቁጥር 27፣35፤ እንዲሁም በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 5፤ ቁጥር 44 ላይ ጠላታችሁን ፈጽማችሁ ውደዱ እያልክ ቃልህን በመሻር የሰውን ልጅ ወደ ሲኦል አታግባ ማለት ነው። ቅኔው ጽድቅ ቅኔ ይባላል። (ማር የ2006 ዓ ም.91).
ወደ አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለሥራ ጉዳይ ሔጄ በነበረበት ጊዜ በደቡብ ጎንደር በደብረ ታቦር ኢየሱስ የተክሌ አቋቋም ምሥክር የሆኑት ርእሰ መምህራን መርሻ መብራቴ እንዳስረዱኝ አለቃ ገብረ ሐና የራሳቸውን አቋቋም የደረሱት ጣና ገዳም ውስጥ ሱባኤ ገብተው በነበረበት ጊዜ ነው። ይኽ የአቋቋም ጥበብ በተገለጠላቸው ጊዜ የጎንደርን ቀለም በየዱሩ እየዞሩ በመዘመር ላይ ሳሉ መልአክ ተገለጠላቸውና “ እግዚአብሔር የሚመሰገንበት ሌላ ከፍተኛ ጥበብ አለ።
ይኸውም ውዝዋዜን በዚህ ሸምበቆ እየመሰልክ ሥራው” በማለት ምልክቱን ይነግራቸዋል። ይኽም የሆነው ፎገራ ውስጥ ናበጋ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ነው። ምክንያቱም አገሩ የሸምበቆ ተክል የበዛበት ስለሆነ ነው። ሸምበቆውን ነፋስ ወደ ግራና ወደ ቀኝ እያላተመ ሲያወዛውዘው የሚታየው ትርኢት አፍዝዞ የሚያስቀር በመሆኑና አለቃ ገብረሐናም በትርኢቱ ተመስጠው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እየተመሩ የቤተክርስቲያን መገልገያ የሆነውን የዝማሜ ስልት በሸምበቆ ተምሳሌት ለማፍለቅ ችለዋል።
ዝማሜ ማለትም ልክ ነፋስ ሸምበቆን እያስጎነበሰና እያሥነሳ፣ እየዘለሰ እንደሚያስደንሰው በዚያው ስልት መቋሚያን ወይንም ዘንግን ወደ ግራና ወደ ቀኝ እያዟዟሩ፤ መሬቱን እየረገጡ ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት የዜማ ስልት ነው።
አለቃ ገብረ ሐና የዝማሜን ጥበብ ከሸምበቆ መንጋ (ሠራዊት) ቀስመው ከሠለጠኑበት በኋላ ቤት ዘግተው፤ ማንም ሰው ሳይሰማቸው ለልጃቸው ለአለቃ ተክሌ በኅቡዕ ወይም በምሥጢር አስተምረዋቸዋል። አለቃ ተክሌም ከወላጅ አባታቸው የተማሩትን የአቋቋም ስልት እያራቀቁትና፤ እየተካኑበት ስለሔዱና በደብረ ታቦር ኢየሱስ ደብር ወንበር ዘርግተው በስፋት ስለአስተማሩት በዘርፉ ብዙ ሊቃውንትን አፍርተዋል። ከዚህም የተነሣ ተክሌ ራሱን የቻለ የአቋቋም ስልት ሆኖና በራሳቸው ስም ተሰይሞ ለመታወቅ ችሏል ።
በሌላ በኩል ያገኘሁት ምንጭ እንደሚያትተው (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ.ም ገጽ 123) ይኽ አቋቋም (የተክሌ ማለት ነው) ከአለቃ ገብረ ሐና በፊት የጎንደሮች ጊዮርጊስ የቤት ባህል ነበር። በተለይም በዝማሜነቱ በጣም ተወዳጅና መሳጭ ስለነበር አለቃ ገብረ ሐና በደብሩ ውስጥ በመገኘት ብዙ ጊዜ ካዳመጡ በኋላ የራሳቸውን ማስተካከያ አክለውበት በተለይም ዝማሜውን ልዩ ጣዕም፣ እንቅስቃሴ፣ ማራኪነትና ሳቢነት ያለው ልዩ የዘንግ ውዝዋዜ እንዲኖረው በማድረግ አሳምረው አዘጋጅተውታል።
ይኽንን አቋቋም ያዘጋጁበት ቦታም በጎንደር ከተማ ደብረ ኃይል ወደብረ ጥበብ በዓታ ለማርያም አካበቢ ከቤተልሔም በስተሰሜን ምሥራቅ አጠገብ በነበረው ቤታቸው ሆነው ነው። በዚህ ቤታቸው አጠገብ የሸምበቆ ተክል በብዛት ስለነበረ ነፋስ ሸምበቆውን ሲወዘውዘው እያዩ ከዘንጋቸው ጋር አዋሕደው ውዝዋዜውን አዘጋጅተውታል። በኋላም የደከሙበትን ሙያ በሥውር ለልጃቸው ለአለቃ ተክሌ አስተምረዋቸዋል።
ርእሰ መምህራን መርሻ እንደሚሉት በደብረ ታቦር በስፋት የሚታወቀው የተክሌ ዝማሜ ነው። ይኸውም ልክ እንደሸምበቆ ነው። ውዝዋዜው ውበት አለው። ድጓው ሁሉም ሊቃውንት እንደሚያውቁት በይዘቱ አንድ ሲሆን የሚለየው በጣዕመ ድምጹ ነው። በውዝዋዜው፤ በውስጠ ጉሮሮውና በርዝመቱ ከሌላው የቤተልሔም (ላይ ቤትና ታች ቤት )፤ የቆማ ፋሲለደስ፤ የጎጃም አጫብር ፤ ከትግራይ አክሱሜ፤ በሸዋ ከነበሩት ወንጨሬና ተጉለት፤ በሰሜን ወሎ ዋድላ ዋድሌ ተብለው ከሚታወቁት(ዛሬ የጥንቱን ዜማቸውን ትተው የቤተልሔም ዜማ ከሚጠቀሙት) የዜማ ስልቶች የተለየ ነው። ቀለሙ በትክክል እንደወረደ ነው። ዓይነቱም እንዳለ ሌላ ድምጽ በአልሰሙ መምህራን ሲቃኝ በእጅጉ ያማልላል።
እርሳቸው እንደሚሉት ተክሌዎች ከቤተልሔም የዜማ ስልት ጋር በድጓ ሲገናኙ በዘንግ ግን ይለያያሉ። ቤተልሔም የሚባለው የድጓ ዜማ ሲሆን የተክሌ ዝማሜ የዘንግ ዝማሜ ይባላል። ግን ከበሮ ምቱን፤ ጸናጽሉን ብዙ ሰው አይወድደውም። ዘንጉ ግን በእጅጉ ሳቢና በመላ ኢትዮጵያ ተወዳጅ ነው። በከበሮ ምትና በጸናጽል ስልት ጎንደር በዓታ ይልቃል። የጸናጽል ዋነኛ ተጠሪዋም ጎንደር በዓታ ናት ይላሉ የተክሌ ዝማሜ ሊቁ ርእሰ መምህራን መርሻ። እርሳቸው እንዳወሱት አዲስ አበባ በሚደረግ አጠቃላይ የሲኖዶስ ስብሰባ ላይ እንዲዘምም ዘንግ የሚሰጠው ለደብረ ታቦር ተክሌ ነው። ጸናጽል ለጎንደር በዓታ፤ ቅኔ ደግሞ ለጎጃም ይሰጣል። በዚህ ረገድ እርሳቸውም ለሁለት ጊዜያት ያህል በሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ተሳታፊ በነበሩበት ሰዓት ዘንግ እየተሰጣቸው ዘምመዋል። ምክንያቱም ተክሌ ምሥክር እያለ ዘንግ ለሌላ ስለማይሰጥ ነው።
ርእሰ መምህራን መርሻ መብራቴ በተክሌ አቋቋም የመምህራን ሐረግ (ተዋረድ) ስድስተኛ ሰው ናቸው። ይኸውም የመጀመሪያው አለቃ ገብረሐና ሲሆኑ እርሳቸው በሥጋም ፤ በአቋቋም ጥበብም አለቃ ተክሌን ወለዱ። አለቃ ተክሌ አለቃ መኮንንንና ሌሎችን ተክተዋል። አለቃ መኮንን፣ አለቃ ቀለመ ወርቅንና ሌሎችን፤ አለቃ ቀለመ ወርቅ አለቃ ማኅተምን፤ አለቃ ማኅተም፣ ርእሰ መምህራን መርሻ መብራቴን የቀለም አባት ሆነው ወልደዋል።
ርእሰ መምህራን መርሻ እንዳወጉኝ በመጀመሪያው ላይ አለቃ ተክሌ ገብረሐናን ፈተና ገጥሟቸው ነበር። ይኸውም አለቃ ተክሌ በክብረ በዓል ቀን ወደ ጎንደር ሔደው ፎገራ ወረዳ ናበጋ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በዝማሜ ጊዜ በበርካታ ሊቃውንቱ መኻል ዚዘምሙ ሊቃውንቱ በመገረም “ይትበሀላችን ያልሆነውን እንግዳ ነገር ከወዴት አመጣኸው” ብለው ከማኅሌት ገብተው እንዳይቆሙ ይከለክሏቸዋል። ከዚህም የተነሣ ወደ ወሎ ተንታ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሄደው ሲያስተምሩ ኖረዋል።
አለቃ ተክሌ ተንታ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በነበሩበት ወቅት የደብረ ታቦር ገዥ የነበሩት ራስ ጉግሳ ወሌ የተማረ ሰው ይወድዳሉ መባልን ስለሰሙ ወደ ደብረ ታቦር ይመለሳሉ። በጊዜው የደብረ ታቦር ኢየሱስ፤ የመንበረ ብርሃን እናቲቱ ማርያምና አፄ ዮሐንስ ያሠሩት የኅሩይ ቅዱስ ጊዮርጊስ አድባራት አስተዳዳሪ የነበሩት አለቃ ወርቅነህ አለቃ ተክሌን ተቀብለው ወደ ራስ ጉግሳ ያቀርቧቸዋል።
ራስ ጉግሳም ጣዕም፤ ለዛና ስልት ያለውን ድምጽ ሲሰሙ በእጅጉ ስለተመሰጡ“ ተክሌ መልአክ ነው እንጂ ሰው አይደለም ” ብለው፤ ቀለብ ሰፍረው፤ ደመወዝ ቆርጠው፤ ልብስ አልብሰው ደብረ ታቦር ኢየሱስ ተመድበው እንዲያስተምሩ አደረጉዋቸው። በዚያም አለቃ ተክሌ ወንበር ዘርግተውና ደቀ መዛሙርትን አብዝተው ትምህርቱን ሲያስተምሩ ኖረዋል። በርካታ ሊቃውንትንም በየቦታው አውጥተዋል። የደብረ ታቦር ኢየሱስ መምህርና አስተዳዳሪ ሆነው የሠሩት አለቃ ተክሌ ከቀለም ልጆቻቸው በስተቀር ከአብራካቸው የተከፈለ ዘር አልነበራቸውም። በመጨረሻም አለቃ ተክሌ ርእሰ መምህራን መርሻ መብራቴ በተወለዱባትና መንበረ ማርያም ተብላ በምትጠራው ደብር ውስጥ ስለ ዐረፉ መካነ መቃብራቸው በዚያው ይገኛል።
ርእሰ መምህራን መርሻ በ1952 ዓ.ም የተወለዱት እዚያው ደብረ ታቦር መንበረ ማርያም (እናቲቱ ማርያም) በተባለው ቦታ ነው። ከንባብ እስከ ዳዊት፤ ከጾመ ድጓ እስከ ድጓ ያለውን ትምህርት እዚያው ደብረ ታቦር እናቲቱ ማርያም ከአለቃ ማኅተም ዘንድ ተምረዋል። ቅኔንም በዚያው በደብረ ታቦር ዙሪያ በአቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን ከየኔታ ኪዳነ ማርያም፤ እንደገናም ከጉራምባ ኪዳነ ምሕረት ቅኔ ቤት ገብተው ተቀኝተዋል ።
ትምህርታቸውን በማስፋፋትም ድጓ እዚያው ደቡብ ጎንደር በክምር ደንጋይ እንዝና ማርያም ከየኔታ ሲራክ ወረቴ ዘንድ ተምረዋል። ከዚያ መልስ የተክሌን አቋቋም ለ25 ዓመታት ከአለቃ ማኅተም ለመማር ችለዋል። በእርሳቸው ገለጻ መሠረት የተክሌ አቋቋም ጸናጽሉ፤ ቀለሙ አይያዝም። በቶሎም አይገባም። ጩኸቱ፤ የቀለም ወዙ እስከሚገባ በጣም ያደክማል፤ ለሚማረውም፤ ለሚያስተምረውም ብዙ ሰዓት ይፈጅበታል። የተክሌ አቋቋም ምሥክሩ አለቃ ማኅተም ጥር 10 ቀን 1991 ዓ ም ሲሞቱ ወንበሩ እስከ ሚያዚያ 10 ቀን 1991 ዓ ም ድረስ ክፍት ሆኖ ቆይቷል።
ይኽንን የተረዳው ሀገረ ስብከቱም ማንን እንተካበት ብሎ ከአሰበና አለቃ ማኅተምም ቀለሙን አስፋፍቶ የያዘው መርሻ ነውና እኔን እንዲተካኝ ብለው ተናዝዘው ስለነበር ከሚያዚያ 20 ቀን 1991 ዓ.ም ጀምሮ የተክሌ አቋቋም ምሥክር ሆነው ተሾመዋል። ከዚያ ወቅት ይዞም 600 መምህራንን አስተምረው፤ ተናገር በከንፈሬ፣ ተቀመጥ በወንበሬ ብለው የመረቋቸው የተክሌ ዝማሜ (የአቋቋም) መምህራን በጎንደር፤ በጎጃም፤ በሸዋ፤ በወሎ በደሴና በመርሳ ወንበር ዘርግተው፣ ተማሪ አፍርተው በማስተማር ላይ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2012
ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)