የሀገራችን ግብርና በተስፋና በስጋት ውስጥ ይገኛል። በአንድ በኩል ለግብርና ሥራው ትኩረት በመሰጠቱና ለዘንድሮው የ2011/2012 ምርት ዘመን የተሳካ ቅድመ ዝግጅት በመደረጉ እንዲሁም ለእርሻ ሥራ አመቺ የሆነ የዝናብ ስርጭት መኖሩ የዘንድሮውን የምርት ዘመን የተሻለ እንዲጠበቅ አድርጎታል። ከዚሁ በተጻራሪ ደግሞ አየር ጠባዩ ለግብርና ሥራው አመቺ የሆነውን ያህል ለአንበጣ መንጋ፣ለግሪሳ ወፍና ልዩ ልዩ ሰብል አጥፊ ተባዮች መራባት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
ስለዚህም እነዚህ ሁለት የግብርናው ገጽታዎች በዘንድሮ የምርት መጠን ላይ የሚኖራቸው አወንታዊና አሉታዊ ገጽታዎች ምንድን ነው? ፣ የአንበጣ መንጋ ፣ግሪሳ ወፍና ሌሎች ሰብል አውዳሚ ተባዮችን ለመከላከል ምን ተሰራ ?ምንስ ውጤት ተገኘ ?ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ምርት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ምን እየተሰራ ነው? ለሚሉትና መሰል ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ከግብርና ሚኒስቴር የግብርና ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ከአቶ ሳኒ ረዲ ጋር ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡ – ለ2011/2012 የምርት ዘመን የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች ምን መልክ ነበራቸው?
አቶ ሳኒ ረዲ፡- የዘንድሮ የሰብል ዘመን የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የመጨረሻው ዓመት ነው።ከዚህ አኳያ ባለፉት ዓመታት ያንጠባጠብናቸውን ሥራዎች ታሳቢ ያደረጉ ተግባራትን ለመፈጸም ርብርብ የተደረገበት ዓመት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት እስከወረዳ ድረስ ያለው አመራር የዓላማ አንድነት እንዲጨብጥ በማድረግ ወደ ተግባራዊ ሥራዎች ገብተናል።በተለይም ግብርናውን ለማዘመን እንቅፋት የሆኑትን በቅድሚያ በመለየት ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉ እቅዶችን ነድፈን ወደ ተግባር ገብተናል።
በተለይም የአርሶ አደሩ መሬት የተበጣጠሰ በመሆኑ የእርሻ መሳሪያዎችንና ማሽኖችን ለመጠቀም አዳጋች መሆኑ በጥናት ስለተለየ የኩታ ገጠም እርሻ ዘዴን ተግባራዊ ወደ ማድረግ ገብተናል።አብዛኛው አርሶ አደር አነስተኛ መሬት ያለውና የተበጣጠሰ ነው።ይህ ደግሞ ለዘመናዊ እርሻ ልማት እንቅፋት በመሆኑ ለአርሶ አደሩ ስልጠና በመስጠትና መግባባት ላይ በመድረስ በኩታ ገጠም እንዲያርስ ተደርጓል።በኩታ ገጠም መሬቶች በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን እንዲያመርቱ ግብዓት በማቅረብ፣ስልጠና በመስጠት ፤የብድር አቅርቦት በማመቻቸት፣ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ እንዲያገኙ በማድረግ የአመራር ክትትል እየተደረገበት በበቂ ቅድመ ዝግጅት ወደ ሥራ ተገብቷል።
በዚሁ መሰረትም በሀገሪቱ ካሉ 830 ወረዳዎች ውስጥ በ422ቱ ኩታ ገጠም ገበያ መር የእርሻ ልማት ተግባራዊ ተደርጓል።በመስክ ጉብኝት እንዳረጋገጥነውም በዚህ ዘዴ ከየትኛውም ዓመት የተሻለ ምርት ማግኘት እንደምንችል ለማረጋገጥ ችለናል።
አዲስ ዘመን ፡- በዝግጅት ወቅት ያጋጠሟችሁ ችግሮች ነበሩ?
አቶ ሳኒ፡- ከላይ እንደነገርኩህ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ እስከ ወረዳ አመራር ድረስ በቂ መግባባት ተደርሶበት ወደ ተግባር በመገባቱ ይህ ነው የሚባል
ችግር አላጋጠመንም።አጋጠመን የምንለው ችግር ካለም የበቆሎ ዘር ላይ ያጋጠመን የምርጥ ዘር እጥረት ነው።አምና ምዕራብ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ በጸጥታ ችግር ምክንያት የተመረተውን የበቆሎ ምርት መሰብሰብ ባለመቻሉ የዘር እጥረት አጋጥሞናል።እጥረቱን ለማካካስ ከኬኒያ 6ሺ ቶን በማስገባት ለአርሶ አደሩ በወቅቱ አከፋፍለናል።ከዚህ በተለየ የገጠመን ችግር የለም።
አዲስ ዘመን፡- የዝናቡ ስርጭት ለግብርናው ሥራ አመቺ እንደሆነ ሜትሮሎጂ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር። እናንተ ምንያህል ተጠቅማችሁበታል?
አቶ ሳኒ፡- የዝናቡ ስርጭት እንደተባለው ለግብርና ሥራችን በጣም አመቺ ነበር። ከኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ባለስልጣን ጋር በጋራ በመሆን የተለያዩ ክልሎችና አካባቢዎች ያላቸውን የዝናብ ስርጭት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ በወቅቱ የእርሻ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ አድርገናል።ዝናቡን በአግባቡ ተጠቅመንበታል።
አዲስ ዘመን፡- የእናንተም ቅድመ ዝግጅት የተሳካ በመሆኑና ዝናቡም የሰጠ ስለሆነ ከዘንድሮ የሰብል ምርት ምን እንጠብቅ?
አቶ ሳኒ፡- በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የመጨረሻው ዓመት የምርት መጠኑን 406 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ እቅድ ተይዟል። ይህ የተለጠጠ ነው የሚል ከብዙዎች ቢሰማም እኛ ግን ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት ዘንድሮ ከ382 ሚሊዮን እስከ 406 ሚሊዮን ምርት ለማግኘት ዕቅድ ይዘን ሰርተናል። 13. 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ዕቅድ ይዘን ይህንኑ የሚጠጋ ተግባራዊ አድርገናል።ስለዚህም በዝቅተኛው 382 ሚሊዮን ከፍ ካለ ደግሞ 406 ሚሊዮን እናገኛለን ብለን እንገምታለን። ከመስክ ምልከታም ያረጋገጥነው ይህንኑ ነው። ከወትሮ በተለየ መልኩ ምርትን ለመሰብሰብ አጋዥ የሆኑና ምርት እንዳይባክን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የግብርና መሳሪያዎችና ማሽነሪዎችን ከግል ባለሃብቱና ከህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በመተባበር ወደ ሥራ በማስገባታችን የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ ያስችለናል ብለን እናምናለን።
አዲስ ዘመን፡- የታቀደውን ያህል ሰብል እንዳይሰበሰብ የበረሃ አንበጣ፤የግሪሳ ወፍና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ስጋት አይሆኑም ወይ?
አቶ ሳኒ፡- የዝናቡ ስርጭትና የሙቀቱ ሁኔታ ለእርሻ ሥራው አመቺ የሆነውን ያህል በዛኑ መጠን ለልዩ ልዩ ተባዮችና የሰብል በሽታዎች መፈልፈልና መራባት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።በተለይም ለበረሃ አንበጣ፣ ለግሪሳ ወፍ፣ ለስንዴ ዋግ፣ለመጤ የበቆሎ በሽታና ለሌሎች ተባዮች የተመቸ ሁኔታ ተፈጥሯል።ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ በሀገራችን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ባልተቋረጠ ሁኔታ በየመንና በሶማሊ ላንድ በኩል የአንበጣ መንጋ ወደ ሀገራችን ገብቷል።የበረሃ አንበጣው በትግራይ፣ በአፋር፣ በሶማሊ፣በአማራ ክልሎችና በድሬዳዋ ተከስቷል። የግሪሳ ወፍ ደግሞ በአፋርና ሸዋሮቢት ተከስቷል።
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ ችግሮች እንደሚከሰቱ ቀድማችሁ አውቃችኋል?
አቶ ሳኒ፡- ችግሮቹ ከመከሰታቸው በፊት በአግባቡ ትንበያዎችን ሰርተናል።የበረሃ አንበጣም ሆነ የግሪሳ ወፍ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ቀድመን በመገመታችን ይከሰቱባቸዋል ብለን ወደ ገመትናቸው የአፋርና የሶማሌ አካባቢዎች ባለሙያዎችን ልከን አሰሳ አድርገናል።ከ96ሺ ሊትር በላይ ኬሚካል ግዢም አከናውነናል። ችግሩ ይከሰትባቸዋል ብለን የገመትናቸው ክልሎችም ዝግጅት እንዲያደርጉ ድጋፍ አድርገናል።ከምስራቅ አፍሪካ የአንበጣ መከላከያ ጋር በመሆንም ችግሩን ለመከላከል ቅድመ ዝግጅት አድርገናል። በሀገር አቀፍ ደረጃም ችግሩን የሚቆጣጠር ግብረ ኃይል አቋቁመናል።ችግሩ ከመከሰቱም በፊት ከፌዴራል 26፣ ከክልሎች ደግሞ ወደ 200 ባለሙያዎችን አሰልጥነን አሰማርተናል።የፌዴራል መንግሥትንም በማስፈቀድ መጠባበቂያ በጀት ይዘናል።
አዲስ ዘመን፡ -ታዲያ ይህ ሁሉ ቅድመ ዝግጅት ከተደረገ ችግሩን እንዴት በፍጥነት መቆጣጠር አልተቻለም ?
አቶ ሳኒ፡- ለአንበጣ እና ለግሪሳ ወፍ ክስተት አመቺ አየር ጠባይ እንደሚኖር ብናውቅም በተለይ የአንበጣ መንጋ በሚያሳየው ባህሪ የተነሳ ቶሎ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ነው።የአንበጣው መንጋ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ዕድገቱን ጨርሶ ዝርያውን ማስቀጠል በሚችልበት ወቅት ላይ ነው።ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ለመመገብ ሳይሆን ዕንቁላሉን ለመጣልና ዘሩን ለማስቀጠል ምቹ አካባቢን በመምረጥ ነው።ቦታዎችንም ሲመርጥ ከሰዎችም ሆነ ከእንስሳት ጥቃት ነጻ የሚሆንበትን ድብቅ ቦታ በመምረጥ ነው።አሸዋማ፣ ቁጥቋጦ፣ ሸለቆና ጫካን በመምረጥ ተደብቆ ያርፋል። አንድ መንጋ ከ40 እስከ 80 ሚሊዮን አንበጣ ይይዛል።
ወደ ኢትዮጵያ ደግሞ ከሁለት እስከ ሶስት መንጋ በየቀኑ እየገባ ነው ያለው። አንዷ አንበጣ በየሳምንቱ ከ80 እስከ 120 ዕንቁላል ትጥላለች። ለሶስት ተከታታይ ሳምንታትም እስከ 360 ዕንቁላሎችን በመጣል ትራባለች። ዕንቁላሎችም ማንኛውም ኬሚካል ቢረጭባቸው መፈልፈላቸው አይቀርም። በዚህ ላይ ሴቷ ከታች ወንዱ ከላይ ተደራርበው ስለሚያርፉ የኬሚካል ርጭት ሲደረግ የመሞት ዕድል ያለው ወንዱ ነው። ሴቷ እንቁላሏን በመጣል ዘሯን ታስቀጥላለች። ይህ መከላከሉን ቶሎ ውጤታማ እንዳይሆን ያደርገዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ መጀመሪያ የገባው የአንበጣ መንጋ ያረፈው በአፋርና ሶማሊ በረሃዎች ነው። በነዚህ አካባቢዎች ደግሞ ሰው በብዛት ስለሌለ በሰው ኃይል አባሮና በትኖ በኬሚካል ለማጥፋት አዳጋች ሆኗል። ሌላው ደግሞ ለአንበጣ ተብሎ የሚረጨው ኬሚካል በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ ርጭቱ ከመካሄዱ በፊት አንበጣው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችን ማሳመንና ከቦታው ለጊዜውም ቢሆን እንዲለቁ ማድረግ ያስፈልጋል።እነዚህ ችግሮች የራሳቸውን ጊዜ የሚወስዱ በመሆናቸውና እስከ አሁንም ድረስ በየቀኑ ከ160 ሚሊዮን በላይ አንበጣ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ መሆኑ የመከላከሉን ሥራ አድካሚ አድርጎታል። ቶሎ ውጤቱም እንዳይታይ ሊያደርገው ችሏል።
አዲስ ዘመን፡- ችግሩ ከተከሰተ በኋላ የወሰዳችኋቸው ተግባራዊ እርምጃዎች ምንድን ናቸው?
አቶ ሳኒ፡- ችግሩ በተከሰተባቸው መጀመሪያዎቹ ወቅቶች በርካታ መኪናዎችን በማሰማራት የኬሚካል ርጭት ስናደርግ ቆይተናል።ሆኖም ግን የአንበጣው መንጋ በብዙ ሚሊዮኖች በየቀኑ ወደ ሀገራችን ስለሚገባ በመኪና ርጭት ብቻ ችግሩን መመከት እንደማንችል ስለተረዳን የእራሳችንን ሁለት አይሮፕላኖችና ከምስራቅ አፍሪካ አንበጣ መከላከያ ደግሞ ሁለት አይሮፕላኖችን በመከራየት ርጭት በማካሄድ ላይ እንገኛለን።በዋነኝነት ትኩረታችን አንበጣው ላይ ቢሆንም የግሪሳ ወፍንና ሌሎችንም ተባዮች የማጥፋት ሥራዎችን አከናውነናል።በአጠቃላይ የአንበጣ መንጋና ግሪሳ ወፍን ለመከላከል ከፌዴራል መንግሥት ብቻ ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ የመከላከል ሥራው እየተከናወነ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ምን ውጤት ተገኘ ታዲያ?
አቶ ሳኒ፡- አሁን የአንበጣ መንጋን፣ የግሪሳ ወፍን፣ የስንዴ ዋግንም ሆነ የበቆሎ አምጪ ተባይን በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት ሳያስከትሉ ለመቆጣጠር ችለናል።አሁን ባለንበት ሁኔታ የአንበጣውን መንጋ ከአፋር፣ከምስራቅ አማራ፣ከደቡብ ምስራቅ ትግራይ ማባረር ችለናል።ነጻ ወጥተዋል።በተቻለም መጠን ሰብል አምራች በሆኑ አካባቢዎች እንዳይከሰት የመከላከል ሥራዎችን ሰርተናል።ሆኖም ግን በሶማሊ ላንድ በኩል በየቀኑ በሚሊዮኖች የሚገባው የአንበጣ መንጋ እስካሁንም አልተቋረጠም። ይህም ቢሆን በቁጥጥራችን ስር ነው። ማሽላ አምራች ከሆኑት ጥቂት የአፋር፣ሰሜን አማራና ደቡብ ትግራይ ወረዳዎች በስተቀር ሰብል አምራች ወደ ሆኑ አካባቢዎች የመሄድ ዕድሉን ዘግተንበታል።እስከ አሁን 39 ሺህ 574 ሄክታር መሬት ላይ ነው አንበጣው ያረፈው፤ ከዚህ ውስጥ 34 ሺህ 500 ሄክታር የሚሆነውን መከላከል ችለናል።
ይህም ማለት መከላከል ያልቻልነው ወደ 5ሺህ ሄክታር ነው ማለት ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ በሰብል ምን ያህል ሄክታር መሬት ተሸፍኗል? ምን ያህሉ ላይስ አንበጣው ጉዳት አድርሷል ? የሚለው በቀጣይ በዝርዝር ጥናት የሚመለስ ይሆናል ።የሆኖ ሆኖ ግን አንበጣውም ሆነ የግሪሳ ወፍ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር ተችሏል። ወደ ኦሮሚያና ደቡብ አካባቢዎች ይሰራጫል የሚሉ ስጋቶችንም ከወዲሁ ማምከን ተችሏል። አንበጣ በባህሪው እርጥበታማ አየር ጠባይ ስለሚመርጥ በቀጣይ እርጥበታማ የአየር ጠባይ ወደ ሚኖራቸው ወደ ኬኒያና ታችኛው ሶማሌ ክፍል እንዲሁም ወደ ቦረና አካባቢ እንደሚሄድ ይጠበቃል። ስለዚህም የአንበጣውን እንቅስቃሴ መሰረት በማድረግ የማዳከም ሥራዎችን ለመስራት ከወዲሁ 2 አውሮፕላኖችን ዝግጁ አድርገናል።
ወደ ትግራይም ገብቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ ወደ ኤርትራ መሻገሩን ለማወቅ ችለናል።በሚኖረው የአየር ጸባይ ምክንያትም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቆይበት ጊዜ ውስን ነው ። አፋርና ሸዋ ሮቢት አካባቢ ተከስቶ የነበረውን የግሪሳ ወፍም ተደጋጋሚ እርምጃ በመውሰድ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል በቁጥጥር ስር ለማዋል ተችሏል።በዚህ ረገድ ምንም ስጋት የለብንም።
አዲስ ዘመን፡- ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብም ሌላው ስጋት ሆኗል?
አቶ ሳኒ፡- በሀገራችን በተለምዶ እንደሚታወቀው ከጥቅምት እስከ ጥር ድረስ የበጋ ወር ሲሆን በዚህ ወቅት በአብዛኞቹ የሀገሪቱ ክፍሎች ልዩ ልዩ ሰብሎች ለአጨዳ የሚደርሱበት ወቅት ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ወሳኝ ወቅት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ተከስቷል። የብሄራዊ ሜትሮሎጂ የአየር ሁኔታ ትንበያ እንደሚያመላክተውም ለዝናብ መፈጠር ምክንያት የሚሆኑ የሜትሮሎጂ ክስተቶች ከሰሜን ህንድ ውቅያኖስ እርጥበት አዘል ንፋስ ያለማቋረጥ እየገባ በመሆኑ መላው ሀገሪቱን የሚሸፍን ከቀላል እስከ ከባድ ወቅቱን ያልጠበቀው ዝናብ እንደሚቀጥል ይታመናል። በአንዳንድ አካባቢዎች የመደበኛ ያህል በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ከመደበኛውም ከፍ ያለ ዝናብም እንደሚኖር ይጠበቃል ።
ይህ ሁኔታ ከባድ ስጋት እና አደጋ የሚፈጥር ነው። በተለይም የደጋና የቆላ ጥራጥሬዎችና ሰብሎች ለአጨዳ የደረሱ ከመሆናቸው አንጻር ዝናቡን ቀድመን ሰብሎችን መሰብሰብ ካልቻልን በጥራትም ሆነ በመጠን የከፋ ጉዳት ይደርሳል። እስካሁንም ከ12.5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ መሰብሰብ የቻልነው 5.9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተዘራውን ሰብል ነው። ይህም በመቶኛ ሲሰላ 48 በመቶ ብቻ ነው። ይህም ማለት ከግማሽ የዘለለው የሰብል ምርት ገና አልተሰበሰበም።ስለዚህም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ እንዲኖረው በማድረግ ሰብሎችን የማሰባሰብ ሥራ መከናወን አለበት። በፌዴራል ደረጃ ይህንን የሚያስተባብር ግብረ ኃይል የተቋቋመ ሲሆን በተመሳሳይ በክልሎች በተዋረድ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም አቅጣጫ ተቀምጦ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው።
በተለይም ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ትምህርት ቤቶችን ለተወሰኑ ቀናት በመዝጋት ተማሪዎችና መምህራን በአጨዳው እንዲሳተፉ የማድረግ የንቅናቄ ሥራዎች ተጀምረዋል። በተመሳሳይም የመንግሥት ሠራተኞችን፣የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣የኒቨርሲቲዎችና ወጣቶች እንዲሁም ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል በሰብል መሰብሰቡ ተግባር ላይ በስፋት የማሳተፍ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።ንቅናቄው ከተጀመረ በኋላም የተሻለ ምርት የመሰብሰብ ጅማሮ ታይቷል። ይህ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
በግል ፣በህብረት ሥራ ማህበራትና በመንግሥት መ/ቤቶች እጅ ያሉ የምርት መሰብሰቢያ መሳሪያዎችንና ማሽነሪዎችን በመለየት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረጉ ነው። የግብርና ባለሙያዎችም ከመቼውም ጊዜ በላይ በመንቀሳቀስ ለመሰብሰብ የደረሱ ሰብሎችን ለይቶ ለአርሶ አደሩ ምክር በመስጠት ቶሎ እንዲሰበሰብ እየተደረገ ይገኛል። የተቋቋመው ግብረ ኃይልም በየሶስት ቀናቱ ከቀበሌ ጀምሮ ያሉ ክንውኖችንና ስጋቶችን እየገመገመ መስተካከል ያለባቸውን በፍጥነት እንዲስተካከሉ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል። ከኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ጋርም በቅርበት በመስራት በሚሰጡን ትንበያ መሰረት ከፍተኛ ዝናብ ሊጥል የሚችልባቸውን ቦታዎች በመለየት ሰብሎችን በፍጥነት የመሰብሰብ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንገኛለን።
እነዚህን ተግባራት በማጠናከርና በተለይም ሁሉም ህብረተሰብ የደረሱ ሰብሎች በደቦ ወጥቶ እንዲሰበስብ በማነቃቃት ወቅቱን ያልጠበቀው ዝናብ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት የደረሱ ሰብሎች ሰብስበን እንጨርሳለን የሚል እምነት አለን።
አዲስ ዘመን፡- ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብም ይሁን በአንበጣ መንጋ ምን ያህል ሰብል ልናጣ እንችላለን?
አቶ ሳኒ፡- እስከ አሁን ከደረሰው ሰብል ውስጥ 48 በመቶ ያህል በዚህ ሰዓት መሰብሰብ መቻሉ ከሌሎች ዓመታት አንጻር ሲታይ በጣም ጥሩ ነው።አርሶ አደሩ የሚሰጠውን ምክር በመቀበል ከዝናቡ ጋር በመሻማት ሰብሎችን በፍጥነት እየሰበሰበ መሆኑን ያሳያል። ይሁን እንጂ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሰብል ገና ያልተሰበሰበ በመሆኑ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ከወዲሁ መተንበይ አይቻልም። ሆኖም ግን በቀጣይ ባለሙያዎችን በማሰማራት የደረሰውን ጉዳት አጥንተን መረጃውን ይፋ እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን፡- ከወቅታዊ የግብርና እንቅስቃሴ ወጣ እንበልና፣ ባለፉት 28 ዓመታት ግብርናው በሚፈለገው መልኩ መዋቅራዊ ሽግግር ያላደረገባቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ሳኒ፡- አጠቃላይ ሀገራዊ ኢኮኖሚያችን የተመሰረተው በግብርና ላይ ነው።ግብርና ባደገበት መጠን ሌላውም ኢኮኖሚ አብሮ ያድጋል።የግብርናው ዕድገት ዝቅ ሲል የሌላውም ዕድገት ዝቅ ይላል። ግብርና ለኢንዱስትሪው በተመጣጣኝ ዋጋና በአይነት ምርቶችን ካላቀረበ ኢንዱስትሪው ሊያድግ አይችልም። 80 በመቶ የውጭ ምንዛሪያችን የተመሰረተው በግብርና ላይ ነው።ባለፉት ዓመታት ሀገራችን ላስመዘገበችው ዕድገት ግብርና ዋነኛውን አስተዋጽኦ ሲያበረክት ቆይቷል።
ሆኖም ግን ግብርና ባለው ዕድል ልክ ለምን አላደገም? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው።ግብርና ሰፊ ዕድል አለው፤ግብርና ሰፊ መሬትና ጉልበት አለው፤ግብርና ምቹ የአየር ንብረት አለው፤ግብርና ሰፊ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ሀብት አለው።ግብርና ሰፊ የሀገር ውስጥና የውጭ ገበያ አለው። እነዚህን ሁሉ ዕድሎች ተጠቅመን ለምንድነው ዘርፉን በሚፈለገው መጠን አሳድገን ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ሽግግር ማድረግ ያልቻልነው የሚለውን ጥያቄ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲው(HOME GROWN ECONOMIC POLICY) በአግባቡ ይመልሰዋል።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲው ለግብርና ዘርፍ ልዩ ትኩረት ይሰጣል።ግብርና ዘመናዊ እንዲሆን በርካታ ስልቶችን ይጠቀማል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ኩታ ገጠም ገበያ መር የእርሻ ልማት ዘዴን አንዱ ነው። ኩታ ገጠም ገበያ መር የአስተራረስ ዘዴ የተበጣጠሱ መሬቶችን ገጣጥሞ በዘመናዊ ትራክተሮች ለማረስ ያስችላል። ምርትም ሲሰበሰብ በኮምባይነር በአንድ አፍታ ለመሰብሰብ ያስችላል።ስለዚህ ግብርናው ከኋላ ቀር አስተራረስና አሰባሰብ ለማላቀቅ የሚያስችል ዘዴ ነው።
በዚህ ዓመት ካሉት 830 ወረዳዎች በ422 ቱ ኩታ ገጠም ገበያ መር የአስተራረስ ዘዴን ተጠቅመን አምርተናል። ከወዲሁም በርካታ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን አግኝተናል።አርሶ አደሩ በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን ለማምረት ከመቻሉም በላይ በዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች በመጠቀም መሬት ከመከስከስ ጀምሮ መስመር ማውጣትና ዘር መዝራት ተችሏል። እነዚህ ተግባር ላይ የግል ባለሃብቶች፤ የህብረት ሥራ ማህበራትና የመንግሥት ተቋማት ተሳትፈውበታል። ግብርና ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ፤ ዘመናዊ ግብዓቶችን ካልተጠቀመ ሊያድግ አይችልም። ግብርናችን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂና መሳሪያዎች የራቀ ነበር። ሁሉም ነገር በተለመደው የአርሶ አደሩ ጥረትና በበሬ ጉልበት ብቻ ሲከናው ነበር የቆየው።
ግብርና ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችና ማሽነሪዎችን እንዳይጠቀም ያደረጉት ደግሞ ሶስት ዋነኛ ምክንያቶች ነበሩ።ግብርና የብድርና ኢንሹራንስ አገልግሎት የሌለው መሆኑ አንዱ ነው።የግብርናውን ዘርፍ ካለው አስተዋጽኦ አንጻር ሊደግፈው የሚገባ የብድር ሥርዓት ያስፈልገዋል።ባሉት ባንኮችም ይሁን እራሱን የቻለ የግብርና ባንክ በማቋቋም አርሶ አደሩ ምርቱን ሊያሳድግ የሚችልበት የብድር አቅርቦት ሊመቻችለት ይገባል።ይህ አለመሆኑ ግብርናውን ጎድቶታል። በብድር እጦት ምክንያት አርሶ አደሩ ግብርናውን ለማዘመን የሚያስችሉ መሳሪያዎችንና ማሽነሪዎችን ገዝቶ እንዳይጠቀም እንቅፋት ሆኖበታል። ሌላው ከዚሁ ጋር የተያያዘው ደግሞ ግብርናውን የሚደግፍ የኢንሹራንስ አገልግሎት አለመኖሩ ነው።አርሶ አደሩ ለሚዘራው ዘር ኢንሹራንስ የሌለው በመሆኑ በልበ ሙሉነት ምርት እንዳያመርት እንቅፋት ሆኗል።
የመንግሥት የታክስ ፖሊሲ ደግሞ ሁለተኛው እንቅፋት ነው።ጥቂት ባለሃብቶችን ከመንግሥት ታክስ ነጻ አድርጎ የፈለጉትን የግብርና መሳሪያዎችን እንዲያስገቡ ፖሊሲው ይፈቅዳል።95 በመቶ አርሶ አደሩ ግን ታክስ እንዲከፍል ይገደዳል።ስለዚህ ግብርናው የተመቸው ለጥቂት ባለሃብቶች ነው ማለት ነው። አርሶ አደሩ ግብርናውን ሊያዘምን ፍላጎት እንኳን ቢኖረው በመንግሥት የተጣለበትን ታክስ አንቆ ይይዘዋል።
ሶስተኛው ጉዳይ ደግሞ የሀገራችን አርሶ አደር የይዞታ መጠን አናሳ መሆንና በዚያው ላይ ደግሞ የተበጣጠሰ መሆኑ ለግብርናው አለመዘመን እንቅፋት ሆኗል። የተበጣጠሱት መሬቶችን በዘመናዊ ማሽነሪዎች ለማረስ ደግሞ አዳጋች ስለሚሆን አርሶ አደሩ ኩታ ገጠም አድርጎ እንዲያርስ ማድረግ ነበረብን ። ይህንን ችግር ለአርሶ አደሩ በአግባቡ ከአስረዳነው በኋላ መተማመን ላይ በመድረሳችን ዘንድሮ ወደ ሥራው ገብተናል። ሆኖም ግን ቀደም ብዬ በጠቀስኳቸው የፋይናንስ ችግሮች ምክንያት አርሶ አደሩ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች የሌሉት በመሆኑ መሳሪያዎችን የሚያከራዩ የህብረት ሥራ ማህበራትና ግለሰቦችን ወደ ሥራው እንዲገቡ የማበረታታት ሥራዎች ተከናውነው ጥሩ ውጤቶች ተገኝተዋል። እነዚህን የግብርናው ማነቆዎች የመቅረፍ ሥራዎች በሀገር በቀል የኢኮኖሚው ፖሊሲ መልስ ማግኘት ጀምረዋል።
በሌላ በኩል ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ የመስኖ ስራዎች በስፋት ለመስራት በእቅድ ተይዟል። በመንግሥት ብቻ ሲከናወኑ የነበሩ የመስኖ ልማት ግንባታዎች በግል ባለሀብቱም ተሳትፎ እንዲታገዝ የማድረግ ሥራዎች በቀጣይ በስፋት የሚከናወኑ ይሆናሉ።አርሶ አደሩም በማህበርም በግልም ተበድሮም ቢሆን መስኖ እንዲገነባ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራዎች በቀጣይ ይከናወናሉ።
አርሶ አደሩ በአመረተው ልክ ተጠቃሚ የሚሆንበት የገበያ ስርዓት የመዘርጋትና የመጨረሻ ተጠቃሚው ህብረተሰብም በዋጋ ውድነት ሳይጎዳ ምርቶቹን ከአርሶ አደሩ እንዲያገኝ ሰፋፊ ሥራዎች ይሰራሉ።እነዚህ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች በአግባቡ ከተከናወኑ ግብርናው ሽግግር የማያደርግበት ምክንያት የለም። ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲውም በግብርና ዘርፉ ውስጥ ያሉ ማነቆዎች በአግባቡ በመለየት የሚፈቱበትንም ስልት አመላክቷል።
አዲስ ዘመን ፡- ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲው ከወዲሁ እየመለሳቸው ያሉ ጥያቄዎች ካሉ ቢጠቅሱልን?
አቶ ሳኒ፡- ለአብነት ማንኛውም የግብርና ግብዓት ከውጭ ሲገባ፣ምርጥ ዘር ይሁን ኬሚካል ፣ መሳሪያዎችና ማሻነሪዎች ይሁኑ ከማንኛውም ቀረጥ ነጻ ሆኖ እንዲገባ ተወስኗል።የግል ባለሃብቶችንም በአጨዳ፤ በመሬት መደልደል እና መስመር በማውጣት እንዲሰማሩ እየተደረገ ነው። በቀጣይም ሌሎች ግብርናውን ሊደግፉ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ እርምጃዎች በሙሉ ጊዜ ሳይሰጣቸው ተግባራዊ እየተደረጉ ይሄዳሉ።
አዲስ ዘመን ፡- ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
አቶ ሳኒ ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2012
እስማኤል አረቦ