ከ 1897 ዓ.ም ጀምሮ በበርሊን ዩኒቨርሲቲ አማርኛና ግዕዝን ያስተማሩት ፤ በርካታ መጽሐፍትን የደረሱትንና አገራቸው ከኋላ ቀርነት ተላቅቃ እንደ አውሮፓ እንድትሰለጥን ምሁራዊ ምክረ ሀሳብ በማቅረብ ብዙ ጥረት ያደረጉት አለቃ ታዬ ገብረማርያም የተወለዱት ከ 159 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 21 ቀን 1853 ዓ.ም ነበር።
“ደማቆቹ” በሚል ርዕስ በ2000 ዓ.ም ለህት መት በበቃው መጽሐፍ የሰፈረው ታሪካቸው እንደ ሚያስረዳው ፣ አለቃ ታዬ ወልደማርያም ከጣና ሐይቅ በስተምስራቅ በምትገኘው ይፋግ በተባለች የገበያ ማዕከል አጼ ቴዎድሮስ በነገሡ በሰባተኛው ዓመት ኅዳር 21 ቀን 1853 ዓ.ም ተወለዱ። ዕድሜያቸው 10 ዓመት ሲሞላ ዳዴ ያሉበት መንደር በወረርሽኝ መቅሰፍት ተመታ። አስቀድሞ መንደሩን ለቅቀው ከሄዱት ወላጅ አባታቸው በስተቀር እናታቸውን ጨምሮ ዘመዶቻቸው ሁሉ በበሽታው ረገፉ።
ብቸኛው ታዬ አባታቸውን ፍለጋ ወደሚገኙበት ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ለመሄድ ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀረ። የእናታቸው ወንድም ከሆኑት አጎታቸው ዘንድ ትግራይ ቢሄዱም አጎታቸውን ሳያገኟቸው ስለቀሩ እምኩሉ የተባለ የስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ገብተው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ።
እምኩሉ በተባለው ሚሲዮን ትምህርት ቤት ለዓመታት የወንጌልን ቃል ሲመራመሩ ቆይተው እንደገና ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው የግዕዝ ቅኔ ትምህርት ቤት ገቡ። በዚያም የግዕዝን ቋንቋ ጠንቅቀው ካወቁና ምርምራቸውንም እውቅና ባላቸው በተለያዩ አድባራትና ገዳማት ካጠናቀቁ በኋላ “አለቃ” የተሰኘውን ከፍተኛ ማዕረግ አገኙ። ከዚያም በ1883 ዓ.ም ወደ እምኩሉ ተመልሰው በመምህርነት ፣ በአስተርጓሚነትና በወንጌል ሰባኪነት አገልግለዋል። የድርሰት ሥራቸውን ጀምረው መጽሐፈ ሰዋሰው የተባለውን መጽሐፋቸውን ጽፈዋል።
አለቃ ታዬ የበርካታ መጽሐፍት ባለቤት ቢሆኑም አብዛኛዎቹ ሥራዎቻቸው ወደ ህዝብ እጅ አልደረሱም። ከሥራዎቻቸው መካከል “መጽሐፈ ሰዋሰው” ፣ እስከ አሁን በስዊዲንኛ ቋንቋ ብቻ የሚገኘውና በወጣትነት ዘመናቸው እንደጻፉት የሚገመተው “ነገረ መለኮታዊ ክርክር በራስ መንገሻ ችሎት” ፣ በዕድሜ ዘመናቸው ማብቂያ ላይ ሳይደርሱት እንዳልቀረ የሚገመተው “የአማርኛ መዝገበ ቃላት (የጽንሰ ሐሳብ መዝገብ)” እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው። “የአማርኛ መዝገበ ቃላት” በእጅ ጽሑፋቸው ያዘጋጁትና አብዛኛው ማጣቀሻው በግዕዝ ቋንቋ ሆኖ 450 ገጾችን የያዘ ነው።
አለቃ ታዬ በ1890 ዓ.ም እንደገና ወደ ትውልድ መንደራቸው ተመለሱ። በዚያም ትዳር መስርተው የወንጌል ስብከታቸውን ቀጠሉ። በሙያቸው ተወዳጅነትን በማትረፋቸው በዘመኑ በጌምድርን በከፊል ይገዙ በነበሩት ራስ መንገሻ አቲክም ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አገኙ። ከጥቂት ጊዜ በኋላም ራስ መንገሻ የታዬን ሊቅነት ተገንዝበው አሽከራቸውን ባልደረባ ሰጥተው በ1891 ዓ.ም ወደ አጼ ምኒልክ ሰደዱዋቸው።
ከቀናት በኋላ አለቃ ታዬ ከንጉሡ ፊት ቀርበው ተዋወቁ። እምኩሉ እያሉ ያሳተሙትን “መጽሐፈ ሰዋሰው” የተሰኘ መጽሐፋቸውንም ለንጉሡ አበረከቱ። ንጉሡም ሥራውን አይተው በመደሰት ሊቁን ካበረታቷቸው በኋላ ወደ ትውልድ ቦታቸው ሄደው በዚያው እንዲቆዩ አዘዟቸው።
ከዚያም ወደ ቤግምድር ተመልሰው ሥራቸውን ቀጠሉ። አለቃ ታዬ ከፊል ትምህርታቸውን ከውጭ አገር ዜጎች በመቅሰማቸው ምክንያት አንዳንድ የቤተ ክህነት ሰዎች ተቃውሞ ያስነሱባቸው ነበር። ቆይቶም ወደ አዲስ አበባ ሄደው ከንጉሱ ጋር በመገናኘት የፀሐፌ ትእዛዝ ገብረስላሴ ባልደረባ ሆነው ንጉሱን ማገልገል ጀመሩ። በጊዜው አንዳንድ ሰዎች የታዬ ሃይማኖት የፈረንጅ ነው ፤ ንጉሡ ይሄን ሳያውቁ ነው ማህተም የሰጡት እያሉ ያስወሩ ነበር።
ግብጻዊው አቡነ ማቲዮስ አለቃ ታዬን አስጠርተው “አንተ አህያ ሃይማኖትህ ምንድን ነው?” በማለት ለጠየቋቸው ጥያቄ ፣ አለቃ “እኛን አህያ የሚያሰኘን እናንተን መሾማችን ነው” ብለው እንደመለሱላቸው ይነገራል። በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ አለቃ ታዬ ወንጌልን ከማስተማር ጎን ለጎን የጽሑፍ ሥራቸውን ቀጠሉ።
መጋቢት 19 ቀን 1897 ዓ.ም ከዳግማዊ ምኒልክ የትዕዛዝ ደብዳቤ ደረሳቸው። ጀርመን በበርሊን የኦሬንታል (ምስራቃዊ) ጥናት ተቋም ውስጥ ግእዝን የሚያስተምር ኢትዮጵያዊ ባለሙያ እንዲላክላት ላቀረበችው ጥያቄ ከአለቃ ታዬ የሚልቅ ስመ ጥር ምሁር በአጼ ምንሊክ አእምሮ ውስጥ አልነበረም።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ “የህይወት ታሪክ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ይህንኑ ሁኔታ እንደሚከተለው ገልጸውታል። “የጀርመን መንግስት የግዕዝ ቋንቋ የሚያስተምር አንድ ሊቅ ይሰጠኝ ብሎ አጼ ምኒልክን በለመነ ጊዜ ፣ አለቃ ታዬን መርጠው ሰደዱዋቸው። በጀርመን መንግስት ሶስት ዓመት ሙሉ የግዕዝ ቋንቋ አስተምረው ኒሻን ተሸልመው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ፤ አጼ ምኒልክም ኒሻን ሸልመው የአባታቸውን አገር ሰጥተው ወደ በጌምድር ሰደዱዋቸው።”
አለቃ ታዬ በጀርመን ቆይታቸው አማርኛና ግዕዝን በበርሊን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከማስተማር በተጨማሪ ከኢትዮጵያ የሄዱ በግእዝ የተጻፉ መጽሀፍት በመሰብሰብ መርምረዋል። ከአጼ ምኒልክ ጋርም በየጊዜው ይጻጻፉ ነበር። በጀርመን ቆይታቸው የአገሩን ስርዓት በየአቅጣጫው ከቃኙና ካስተዋሉ በኋላ ጳጉሜን ሶስት ቀን 1998 ዓ.ም ለአጼ ምኒልክ የሚከተለውን ደብዳቤ ጽፈዋል።
“ … በየእለቱ አዲስ ነገር አያለሁ ፤ አዲስ ነገር እሰማለሁ። ጃንሆይ ከአገርዎ ልጆች ወደ አውሮፓ ሰደው ብልሀት ቢያስተምሩ መልካም በሆነ ፤ የያጃንና የሞሮኮ መንግሥት ሰው እየሰደዱ አስተማሩ። ይህን አይቼ ለአገሬ መንግሥት ቅንዓት እንደ እሳት በላኝ . . ምን አደርጋለሁ ? አዝኜ ወደ መቃብር እወርዳለሁ።”
በማስከተልም ግንቦት 1899 ዓ.ም የውስጣቸውን ብሶትና የአገራቸውን ኋላ ቀርነት የሚጠቁምና መንስ ኤውን የሚዘረዝር አንድ ደብዳቤ ለአጼ ምኒልክ ሰደዱ።
“…እኛ ሀበሾች በመንፈሳዊና በስጋዊ ጥበብ ወደፊት የማንገፋበት ምክንያት ምን ይሆን ብሎ ለሚጠይቅ ፣ ህዝቡ ሁሉ ባይማርና የወንጌልን ስብከት በብዙ ባይሰማ እንዲሁም እውነተኛ እውቀትና አፍቅሮ ቢጽ ትህትና ቢጠፋ ነው። በአገራችን ጥቂት እውቀት ያላቸው ሰዎች በመከበር ፈንታ ስለሚሰደቡ ፤ ስለሚዋረዱና ስለሚጠቁም የጥበብ ሥራ ትተው በመቦዘን መኖርን መረጡ። የአዳምን ልጆች ዓለሙን ሁሉ የፈጠረ አድልዎ የሌለበት አንድ ልዑል እግዚአብሔር ነው። ላንዱ ወገን ህዝብ ሙሉ ፣ ላንዱ ወገን ጎዶሎ ልብ አልፈጠረም።
በፍጥረቱ የአዳምን ልጅ ሁሉ አስተካክሎ እንደፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። እንዲህ ከሆነ ስለምን ያውሮፓና የእስያ ሰዎች ከአፍሪካ ክፍልም ጥቂቶቹ ብልሃተኞች ሲሆኑ በእኛ በአበሾች ዘንድ መጽሐፍ ቢማሩ ‘ኮቾሮ ለቃሚ’ ፣ ብርና ወርቅ ቢሰሩ ቀጥቃጭ ቡዳ ፣ እንጨት ቢሠራ አናጢ እንጨት ቆርቋሪ ፣ ቆዳ ቢፍቅ ጥንበ በላ ፋቂ እያልን ለየሥራው ሁሉ ስም እየተሰጠ ስለሚሰድብ የጥበብ ሥራ ከጊዜ ወደጊዜ እየቀዘቀዘ ጠፋ። ስለዚህ ጉዳይ ጃንሆይ አስበው እንዲህ ያለው ስድብ ሁሉ በአዋጅ እንዲከለከል ፤ ሰዎቹ እንዲከበሩ ቢያደርጉ በሌላው መንግሥት ስምና መልክ የተቀረጸ ገንዘብ እንዲወጣ ቢያደርጉ ነጻ መንግሥትዎም ራሱን የቻለና የተ ሟላ ይሆናል።“
ክሪስ የተባሉ ታሪክ ጸሐፊ እንደሚሉት ይህ የአለቃ ታዬ ደብዳቤ ከተጻፈ ከአራት ወር በኋላ አጼ ምኒልክ የትምህርትን አስፈላጊነትና የሥራን ክቡርነት የሚገልጸውን አዋጅ አሳወጁ።
አለቃ ታዬ ከጀርመን መልስ ወደ በጌምድር ተመልሰው ሥራቸውን ቀጠሉ። ብዙም ሳይቆዩ ደጃዝማች መሸሻ ወርቄ ባለጋራ ሆነው ተነስተውባቸው የበጌምድር ገዥ ለነበሩት ንጉሥ ወልደጊዮርጊስ “አለቃ ታዬ ሃይማኖቱ የንስጥሮስ ነው። ይህንንም ሃይማኖት ለህዝቡ ያስተምራል።” ብለው ደብዳቤ ጻፉ። አለቃ ታዬም ጉዳዩ በፍርድ ሂደት እንዲታይ ሲደረግ መንገላታት ቢደርስባቸውም በመጨረሻ ለወደፊቱ እንዲህ ያለ ትምህርት እንዳያስተምሩ ተመክረው ተሰናበቱ።
በአለቃ ታዬ መለቀቅ የተበሳጩት ካህናት በጊዜው የአጼ ምኒልክ ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴ ለነበሩት ለራስ ተሰማ በማመልከት ያለ ሕግ ከታላቁ ወህኒ ቤት እንዲገቡ አደረጉ። አለቃ ታዬ ወህኒ ቤት ታስረው ከከረሙ በኋላ ተፈተው በቁም እስር እንዲቆዩ ተደረገ። በመጨረሻም በ1912 ዓ.ም ለመንግሥት አማካሪነት ተመርጠው መስራት ጀመሩ።
ምሁሩ ታዬ የህይወት ዘመናቸውን ለአገራቸው ብዙ በማበርከት ከእንግልት ጋር ካሳለፉ በኋላ ነሐሴ 15 ቀን 1916 ዓ.ም ከቶም ሊቀር ወደማይቻልበት ዓለም አመሩ። እህታቸው ወይዘሮ ላቀች በቀብራቸው ወቅት ያሰሙት የሐዘን እንጉርጉሮ (ሙሾ) አለቃ ታዬ ዘመናቸውን ሁሉ ከኢፍትሀዊነትና ካለማወቅ ጋር ያደረጉትን እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ደምሮ የሚያሳይ ይመስላል።
ዕውቀትና ምግባር ጉድጓድ ተከተተ ፤
አራት ነው እንጂ መቼ አንድ ሰው ሞተ።
ወዝውዘው ነዝንዘው ጣሉት እንደ ዝሆን ፤
ያው ወደቀላቸው ይበሉት እንደሆን።
ከጨለማ መሃል ቢወጣ ብርሃን ፣
አጥፉት አጥፉት አሉ እንዳይታየን።
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ስለ አለቃ ታዬ ሲመሰክሩ እንዲህ ብለዋል ፡- “እስከዛሬ ድረስ ወደ ሩቅ አገር ተሰደው ወይም ወደ አበሻችን ከመጡት ፈረንጆች ጥቂት ጥበብ ተምረው ያገራቸውን መንግሥት ሊጠቅሙ የሚፈልጉ ወንድሞቻችንን መናፍቃን ፣ የሌላም መንግስት ሰላዮች እየተባሉ ሲራቡ ፣ ሲከሰሱም እናይ የለምን ? የሚከተሉት ሁለት ሰዎች ስም መወሳት የግድ ነው።
እነርሱም ከንቲባ ገብሩና አለቃ ታዬ ናቸው። ሶስት ዓመት ሙሉ አዲስ አበባ ላይ ስቀመጥ እንደነዚህ ሁለት ሰዎች አድርጎ መንግሥቱን የሚወድ ሰው አላየሁም። ይህ ደግነታቸው ግን እስከዛሬ ድረስ አልታወቀላቸውም። እጅግ ያሳዝናል። የእነርሱን ዕድል ያየ ሰው የኢትዮጵያ መንግሥት ለወዳጅ አይጠቅምም ብሎ ተስፋ ይቆርጣል።”
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/2012
የትናየት ፈሩ